እግዚአብሄር ምልክት የሚያኖርባቸው ሰዎች በእግዚአብሄር የታዩ ሰዎች ናቸው፤ በእርሱ ከለላ ውስጥ ያሉ በአላማው ውስጥ የተቀመጡም ናቸው፡፡ በእግዚአብሄር እቅድ ላይ በክፋት የተነሳው ቃየን እንኩዋን ከሚያገኘው ክፋት ይጠበቅ ዘንድ በሰዎች ዘንድ የመጀመሪያ የሆነውን ምልክት ከእግዚአብሄር ተቀብሎአል፡፡ ይህ ምልክት እርሱን በሰራው ሀጢያት ከመጥፋት የሚታደገው የእግዚአብሄር ምልክት ነበር፡፡ እግዚአብሄር ለራሱ ለለየው ህዝብ ደግሞ የተለየ ጥበቃ በማድረግ ምልክት በላዩ ላይ ያኖራል፡፡
የእግዚአብሄር እርዳታ ለእስራኤላውያን ሲመጣ አመጣጡ በህግ በኩል ነበር፤ እርሱም ህዝቡን በቸልተኝነትና በመዘንጋት የሰሩትን ሀጢያትና በደል ያርቁ ዘንድና ይህ ችግራቸው ተወግዶ ዳግም ወደ ማስተዋል ይመጡ ዘንድ በልብሳቸው ጫፍ ምልክትን እንዲያደርጉ ያሳሰበበት ጊዜ ነበር፡፡
ዘኊ.15:37-41 ”እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው;- እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው፡- እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥ ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”
እግዚአብሄር በሚሰጠው ምልክት ውስጥ የሚተላለፉ መልእክቶች፣ ማስጠንቀቂያዎችና ማንቂያዎች ስላሉ በነርሱ አማካይነት ህዝቡን ከጥፋት ሲታደግ እናያለን፤ በተለይ ለእስራኤል በሰጠው ምልክት በኩል አስቀድሞ ለብዙ ዘመናት ተከትለው ያመነዘሩባቸውን የልቦናቸውንና የዓይኖቻቸውን ፈቃድ ዳግም እንዳይከተሉ በማስጠንቀቂነት ተጠቅሞበታል፡፡
ስለዚህ፡-
• እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ ታዘዙ፣
• በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድም እዘዛቸው፣
• የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ ይህን አድርጉ ሲል አሳሰበ፣
• እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ ይህን አደርጉም አለ፣
• ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ ያን አድርጉ አለ፣
• ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን አለ፣
• ይህን ያዘዝኩ አምላካችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ አለ፣
• አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ በማለትም ተናገረ።
አይሁዳውያን ለእግዚአብሄር የተለዩ ህዘቦች ስለነበሩ ከጎረቤቶቻቸው (በቅርብና በሩቅ ካሉ አህዛብ) በአለባበሳቸው፣ በአመጋገባቸውና በአስተሳሰባቸው ተለይተው እንዲታዩ ተደርገዋል፡፡ በተለይ በሚለብሱት ልብስ ላይ የተደረገው ምልክት እነርሱም ሌላውም ህዝብ ለእግዚአብሄር የተለዩ ወገኖች መሆናቸውን ለይቶ እንዲያውቅ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡
እግዚአብሄር ምልክት ሲያደርግ ከሰው ፍርድ የምንድንበት ማምለጫ አድርጎ ቆመዋል፤ ለምሳሌ ቃየን ነብሰ-ገዳይ ስለነበረ ያን የሚያውቁ በራሳቸው ፈቃድ እንዳያጠፉት ፍርድ ግን የእግዚአብሄር ነውና በተጠበቀው የእግዚአብሄር ሰአት ከሚሆነው ውጪ የሰው ልጆች ምንም እንዳያደርጉ ያሳይ ዘንድ ቃየን ላይ ምልክትን አደረገ፡-
ዘፍ.4:15 ”እግዚአብሔርም እርሱን አለው፡- እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።”
የሰው ልጅ አመጽ እየበዛና እያየለ በሄደ ጊዜ ግን የቃየንና የርሱን አመጽ የተከተሉ ሁሉ ይጠፉ ዘንድ የእግዚአብሄር ውሳኔ ሆኖ ነበር፡፡ ከእግዚአብሄር የውሀ ጥፋት ፍርድ በሁዋላ የሰውን ልጆች ዳግም ከውሀ ጥፋት የሚያስቀር ቃል ኪዳን በምልክት ሊጸና ችሎአል፡-
ዘፍ.9:12-16 ”እግዚአብሔርም አለ፡- በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።”
እግዚአብሄር በእርሱና በምድር መካከል ባደረገው የቃል ኪዳን ምልክት ምክኒያት የሰው ዘር ከተመሳሳይ ጥፋት ሊተርፍ ችሎአል፤ እኛም ሰዎች ቀስተ ደመናውን ባየን ቁጥር የእግዚአብሔርን ታማኝነት እና የተስፋ ቃሉን ሁሉ ማስታወስ ይገባናል። ከእኛ ጋር ያለው የሰላም ቃል ኪዳን ከኖህ ጀምሮ ወደ ቀጣይ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሶአል፣ ገና እስከ አለም ፍጻሜ ይደርሳል፡፡ ያም በመሆኑ እግዚአብሄር በሰጠው የምህረት ቃል ኪዳን ሰው እየኖረ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል። የቀድሞው ዓለም በእግዚአብሄር ቁጣ ቢጠፋም ታሪኩ የጽድቅ ፍርድ ምልክት በመሆን ለአሁኑ ትውልድ እንደ ሀውልት የቆመ ሲሆን ከጥፋት ውሀ በሁዋላ ላለችው ዓለም ደግሞ የምሕረት ምልክት በመሆን ዛሬም ይመሰክራል። እንዲሁም በየትኛውም ጊዜ እግዚአብሔር ቀስቱን እንደሚመለከት፣ ቃል ኪዳኑንም በዚያ እንደሚያስታውስ፣ እኛም የተናገረውን ቃል ኪዳን በእምነት እና በምስጋና እናስብ ዘንድ ይገባናል።
እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ምልክትን ከማድረጉም ሌላ የቃል ኪዳን ሰው ባገኘ ወቅት ቃል ኪዳን በራሱ ላይ አድርጎ እግዚአብሄር ያን እንዲያይ አድርጎአል፤ ይህንን ከአብረሃም ታሪክ እናገኛለን፡-
ዘፍ.17:9-12 ”እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፡- አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል።የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ።”
እግዚአብሄር ቃልኪዳን ሲያስገባ አብርሃምን ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ አለው፤ እግዚአብሔር ለአብርሃም በዚህ መንገድ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር እንዲያደርግ ሰጠው፡፡ እርሱና በቤቱ የነበሩ ወንዶች ሁሉ የእግዚአብሄርን ቃል ኪዳን በእምነት መቀበላቸውን ለማሳየት የቃል ኪዳኑን ምልክት በራሳቸው ላይ አደረጉ። አብረሃምም ለገባው ቃልኪዳን ታማኝ ስለነበረ እግዚአብሄር በቃል ኪዳን አባትነቱን ለዘሩ ብቻ ሳይሆን ለአህዛብም ጭምር እንዲሆን ባረከው፡፡ ሀዋርያው ጳውሎስ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
ሮሜ.4:9-12 ”እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገረዝ ተነገረ? ወይስ ደግሞ ስለ አለመገረዝ? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና።እንዴት ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ተገርዞስ አይደለም፥ ሳይገረዝ ነበር እንጂ።ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው።”
በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር የመገረዝን ምልክት በእምነት ለተገኘው ጽድቅ ማኅተም ይሆን ዘንድ ሲፈቅድ ከአብረሃም እምነትን ቅድሚያ ማየት ግድ ብሎት ነበር፡፡ መታተም ቅድመ- ሁኔታን የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ አብርሃም ከአገሩና ከወገኖቹ መሃል ከተጠራ በሁዋላ በእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ተጉዞአል፣ በዚህ ለዘመናት የቀጠለ ጉዞ ማረጋገጫ እንዲሆን እግዚአብሔር የማኅተም ሥርዓትን ሊሰጥ ወሰነ፣ አብርሃምም ይህን ማህተብ ተቀበለ። ምንም እንኳን መገረዝ ደም ማፍሰስን የሚጠይቅ ሥርዓት ቢመስልም፣ ልዩ የምህረትና የጽድቅ ማረጋገጫ ምልክት በመሆኑ አብርሃም ለትእዛዙ ተገዛ፣ ልዩ ሞገስንም ተቀበለበት፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በመታሰቢያ ምልክት ያጸናው ሲሆን ያደረገው ምልክትም በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የሚለይ ምልክት ሆኖ እስከ አዲስ ኪዳን ዘመን ቆይቶአል፡፡ በአዲስ ኪዳን መገረዝን ጥምቀት ስለተካው አህዛብ በሙሉ የእግዚአብሄር ቤተ- ክርስቲያን ብልት ሆኖ ከአይሁድ ጋር በአንድ አካል ወደ እግዚአብሄር መንግስት የመግባትን እድል አግኝቶአል፡፡ ስለዚህ ለአብረሃም በመገረዝ የተገለጠው ጊዜያዊና ውጫዊ የቃል ኪዳን ምልክት አሁን ዘላለማዊ በሆነው ውስጣዊ እና መንፈሳዊ የጸጋ ምልክት መቀየሩን እንመለከታለን። በአዲስ ኪዳን የግርዘት በጥምቀት መተካት ከህግ ወደ እምነት መምጣትና የጽድቅ ማኅተምን በዚያ መቀበልን አመልካች ነው።
ቆላ.2:11-12 ”የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ።በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።”
በግርዛት ወቅት ሸለፈት ብቻ ይወገድ ነበር፤ በአዲስ ኪዳን በስሙ ጥምቀት ምክኒያት ዳግም መወለድ ተቻለ፣ እንዲሁም የኃጢያት ሥጋ በመንፈስ ተገፈፈ፤ ይህ መንፈሳዊ ግርዘት ነበር፤ ሂደቱ የተከናወነው በክርስቶስ ሲሆን የተከናወነውም በውሀ ጥምቀት ውስጥ ነው፤ ያ ሂደት የክርስቶስን የግርዘት ስራ የሰራ ብቻ ሳይሆን እርሱን ራሱን ያስለበሰ ስራ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል ሲቀበል ከቃል ኪዳኑ አምላክ ጋር በመንፈስ በመገናኘት የአብረሃምን ተስፋ እውን የሚያደርግበት አሰራር እንደተቀበለ በጥምቀት አሰራር ውስጥ እናያለን፡፡
ሮሜ.2:26-29 ”እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል።
በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።”
ሰው የስጋውን ሸለፈት በተገረዘ ዘመን አይሁዳዊ መሆኑ ብቻ ታወቀ፣ በአዲስ ኪዳን ዘመን ግን በመጠመቁ ክርስቶስን ለበሰ፣ የእግዚአብሄር ልጅ መሆኑም ተረጋገጠ፡፡ የስጋ መገረዝ ስጋዊ አይሁድ ሲያደርግ፣ በመንፈስ የሆነ ግርዛት (ጥምቀት) ደግሞ መንፈሳዊ አይሁድ አደረገ፡፡
የእግዚአብሄር ምልክት በሰዎች ላይ መሆኑ ብዙ ትርጉዋሜ ያለው ነው፡-
1. ምልክቱ የተረጋገጠ ማምለጫን የሚገልጥ ነው
ሕዝ.9:4-10 ”እግዚአብሔርም፡- በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፡- እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ። እርሱም፡- ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ፤ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ። ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ፡- ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን? ብዬ ጮኽሁ። እርሱም፡- የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኃጢአት እጅግ በዝቶአል ምድሪቱም ደም፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፤ እነርሱም፡- እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል። እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ አለኝ።”
2. የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝ ምልክት
ሮሜ.4:11 ”ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው።”
3. ምልክቱ መጠበቂያ ነው
ራእ.7:2 ”የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፦የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው።የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።”
4. የእርሱ መሆናችንን ማረጋገጫ ነው
ራእ.14:9-13 ”ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ፦ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል።የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው።ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።”