ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት፣ ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ በሮሜ.7:9-14 ላይ እንደተገለጸው፦
‘’እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር።ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ።’’
ነገር ግን ምንም ሕጉ ቅዱስ ቢሆን ሰው በህጉ ፊት ሊቀደስ አልቻለም፤ ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅ በጎም ብትሆን ሃጢያት የሰውን ልጅ ስለወረሰ በተዛዚቱ ኖሮ ቅዱስና ጻድቅ መሆን አልቻለም፤ እግዚአብሄር ለሰው መኖሪያ በጎ የሆነውን መመሪያ በሰው ዘንድ ቢያኖርም ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝና ምንም መሆን አልቻልኩም።ነገር ግን እግዚአብሄር በአብረሃም ተስፋ በኡል እኔን ሊያድነኝ ወድዶ በእምነት ሊያድነኝ ጸጋውን ገለጠ።
‘’ሕጉ መቅሠፍትን ያደርጋልና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም። ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።’’ (ሮሜ.4:15-17)
ለሕጉ ተሟጋቾች ቃሉ ሕጉ ሰውን ለመቅሠፍት አሳልፎ እንደሚሰጥ፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጸጋ ግን ባለበት መተላለፍ የለምና መዳን እንደሚሆን ያበስራል። ነገር ግን ሕግም ሆነ ጸጋ ሁለቱም ድንቅ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። ሕጉ ስር የሰደደውን አመጻችንንና ክፉ ኃጢአታችንን ከተሰወረበት ማንነታችን ውስጥ ፈልፍሎ አውጥቶና ግልጥ አድርጎ በማሳየት በእኛ ላይ አስከፊ መሆኑን በእግዚአብሄር ዘንድም ቁጣ እንደሆነ አስቀድሞ ለአይሁድ ብሎም ለቀረው ፍጥረት አሳየ፤ እንዲሁም ይህ በማንም ስልጣን ወይም በምንም መንገድ ሊወገድ የማይችል ፍርድ፣ በህጉ ሃይል የተገለጠና ሰው እንዲያውቀው ያደረገ ሲሆን ሊወገድ የማይቻለውን የሃጢያት እዳ በእግዚአብሔር ጸጋ አሰራር በንስሐና የሃጢያት ስርየት በኩል እንደሚሻር አመልካች ሆነ። ህጉ ሃጢያታችንን እያሳየ በራሳችን ስራ እንድናዝን ሲያደርግ ጸጋ ከዚያ የሞት ሃዘን ወጥተን በእግዚአብሄር ምህረት ውስጥ እንድንገባ፣ በደስታና በተስፋም አዲስ ህይወት እንድንኖር የሚያደርግ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕግና ጸጋ ምን ይላል? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ቃሉን ማስተዋል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን የሕግና የጸጋ ጽንሰ-ሐሳቦች መረዳት በተለይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ለሚፈልጉ አማኞች ያስፈልጋል። በሕግና በጸጋ መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው ተገልጾአል፤ በአዲስ ኪዳን በተለይ ሃዋርያው ጳውሎስ ስለሕግና የጸጋ ምንጭ፣ ተግባርና ውጤቱንም ጭምር ያስተማረውን እናገኛለን፤ ትርጉማቸውን እንዲሁም ሕይወታችንን እንዴት እንደሚቀርጹም አብራርቶ ገልጾአል። ቃሉም ሲናገር፦
‘’አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።’’ (ሮሜ.3:19-24)
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብሉይ ኪዳን መጽሃፍት ውስጥ የተቀመጠው ሕግ በተለይ ለእስራኤል ሕዝብ ብቻ የተሰጠ ሲሆን አላማውም ከግብጽ ያወጣው ህዝብ ከአምላኩ ጋር በጽድቅና በቅድስና ሕይወት ይኖር ዘንድ ነበር። እግዚአብሔር የሰጠው መለኮታዊ ትእዛዝና መመሪያ መጠበቅ ስለነበረበት ህጉ እጅግ ጥብቅ ነበር። በዚህ ምክኒያት ብሉይ ኪዳን በሙሴ እጅ የተሰጠውን አስርቱን ትእዛዛትና ሌሎች በርካታ መመሪያዎች እንዲያካትት ተደርጎ ለህዝቡ ተዘጋጅቶአል። ትእዛዛቱ የሞራል ስነምግባርን፣ ማህበራዊ ፍትህንና ሃይማኖታዊ ተግባራትን ጨምሮ የተለያዩ የህይወት ዘርፎችን ለመምራት ከእግዚአብሄር ዘንድ ምሪት ሆነው የተሰጡ ነበሩ። ሕጉ ህዝቡን በጽድቅ መመዘኛ እና እንደማህበረሰብ ሥርዓትን በመሃከላቸው ለማስፈን ትልቅ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሙሴ በዘዳ.5:22 ላይ ለህዝቡ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦
‘’እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳትና በደመናው በጨለማውም ውስጥ ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤአችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጣቸው።’’
ሙሴ የተቀበለው ህግ በአጠቃላይ ህዝቡን ወደ ከነአን ምድር የሚመራና በተቀመጡበት ምድር የሚያኖር ብቻ ሳይሆን አልፎ ለአዲስ ኪዳንም የሚያዘጋጅ ሆኖ የተሰጠ መንፈሳዊ መመሪያ ነበር፤ በጊዜው በእግዚአብሄር ትእዛዝ ህዝቡ ከግብጽ ይውጣ እንጂ ከልማዱ ጋር ስለነበረ የእግዚአብሔርን ቅድስናና በእግዚአብሄር ፈቃድ እንዴት መኖር እንደሚገባው የሚያሳይ ብርቱ መመሪያ ሊያግዘው አቅጣጫውንም ሊያቀና እጅግ ያስፈልግ ነበር። በህጉ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ህጉን የመታዘዝ አስፈላጊነት በዚያም ያለውን የእግዚአብሄር ምህረትና በረከት ከማሳየቱም ሌላ በህዝቡ ዘንድ በሚፈጠረው አለመታዘዝ የሚከተለው ታላቅ ጥፋት እና መዘዝ ምን እንደሆነ አጉልቶ አሳይቶአቸዋል፤ እነርሱም ከተቀበሉት ስርአትና ትእዛዝ ጋር ሲታገሉ በብዙ እንደደከሙ እንደወደቁም እናያለን።
‘’በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ። ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም፥ ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም። በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።’’ (ዘዳ.30:16-20)
በሌላ በኩል ሕጉ የሰው ልጅ ከአምላኩ ዘንድ የሚጠበቅበትን ፍጹም ህይወት በማሳየት ይህን ህይወት የሰው ልጅ አጠቃላይ በሆነ መልኩ ማሟላት አለመቻሉን በማሳየት ከእግዚአብሄር ዘንድ አንዳች መፍትሄ (ያም የሃጢያት ስርየትና የበደል ይቅርታ የሆነ) እንደሚያስፈልግ አጉልቶ አሳይቶአል። ሕጉ ለጽድቅ ከፍተኛ መሥፈርት እንደሚያስፈልግ አጉልቶ በማሳየት የሰው ልጆች ኃጢአተኛ መሆናቸውንና መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል።
ገላ.2:16 ‘’ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።’’
በአዲስ ኪዳን መጽሃፍት በብዙ ስፍራ የሙሴ ሕግ ሁኔታ ምንነቱን በሚያሳይ መልኩ ተነስቶአል፤ በተለይ በሐዋርያው ጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ የበለጠ ተብራርቷል። ሃዋርያው ወገኖቹ የሆኑ አይሁድን በሚሞግት መንገድ ሕግ ብቻውን ድነትን ወይም መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንደማይችል አጽንኦት በመስጠትና በማሳየት በሕግና በኃጢአት መካከል ያለውን ግንኙነት ሲያብራራላቸው እንመለከታለን። ከዚያ አልፎም ሕጉ የኃጢአትን እውቀት እና የጸጋን አስፈላጊነት ለመግለጥ እንደሚያገለግል ሃዋርያው ጳውሎስ ሲያብራራ እንመለከታለን። በተለይ ግን ሕግ የኃጢአት ገላጭ (ሃጢያትን ግልጥልጥ የሚያደርግ መሳርያ) እንደሆነ መረዳትና ወደ ጸጋ መመልከቻ (የፍለጋ መነጽር) ሆኖ እንደሚያገልገል መረዳት እንዲሁም በክርስትና እምነት ውስጥ ያለውን ሚና ማመን ወሳኝ ነገር ነው። ሰዎች የህግን ጠንካራ ግድግዳነት ካላወቁ ወደ እግዚአብሄር የሚያደርሰውን የጸጋ አሰራር አይመለከቱም፣ አይናፍቁምም።
ሮሜ.7:5-9 ‘’በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤ አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ፦ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ’’
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የሕግ ጽንሰ-ሐሳብ ዘርፈ ብዙ ነው፣ በተለይ እስራኤል እንደ እግዚአብሄር ህዝብ ለአምላኩ ተለይቶ ይኖር ዘንድ ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት አስይቶአል፣ በዚያ ውስጥ መገዛትና መታዘዝን ይለማመድ ዘንድ ለህዝቡ ትእዛዝ ተሰጥቶአል፤ ህዝቡ በእግዚአብሄር ቅድስና አንጻር እንዴት መጓዝ እንደሚገባው መንገዱን ተጠቁሞአል፣ በዚያ ውስጥ ለአብረሃም አምላክ መለየትንና የግብጽን ልማድ መጣልን ይለማመድ ዘንድ ታዝዞአል፤ እንዲሁም ህዝቡ እርስ በርስና አንድ ወገን ከሌላው ከሚኖረው ግንኙነት አንጻር እንዴት መመላለስና አብሮ መኖር እንደሚገባው መንገዱን አሳይቶአል፣ በህብረት አምልኮና ስግደት፣ በህብረት ለአምላኩ ተእይቶ መኖር፣ በአንድነት ወደ እግዚአብሄር መቅረብንና ባእድ ልማድን ከመሃሉ ማራቅን ታዝዞአል፤ በአስተዳደራዊ መልኩ ህዝቡ ሊከተል የሚገባውን ትእዛዝ አስቀምጦለታል፣ በዚያም አምላኩ እንዲመራው ለሾመው እንዲታዘዝ፣ ከአምላኩ ጋር ላለው ግንኙነት መሪዎቹን ሙሴንና ኢያሱን እንዲሁም በመቅደሱ ስርአት አሮንና ልጆቹን እንዲሰማ ታዝዞአል። የእስራኤል ህዝብ ትግል ራሱን ለዚህና ለመሳሰሉት የህጉ ትእዛዛት ራሱን ማስገዛት ይችል ዘንድ ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ገብቶአል፤ ራስን ለቃሉ ማስገዛት ላይ የነበረው ትንቅንቅ ብዙ መንገድ አስኪዶታል።
ተገዙ፣ ስገዱ፣ ስሙ
ዘኊ.12:6-7 ‘’እርሱም፦ ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።’’
ዘዳ.5:1 ‘’ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ አላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ።’’
ዘዳ.12:5-6 ‘’ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ።’’
ኢያ.23:7-9 ‘’በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ እንጂ። እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አስወጥቶአል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።’’
ዘጸ.34:14 ‘’ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ።’’
በአጽኖት ቃሉ ላይ ብንመሰረት ሲበራ የምናየው እውነት ቢኖር ይህ ነው፦ እግዚአብሄር ከእምነታችን በላይ መሆኑ፣ ከፍላጎታችን በላይ መሆኑ፣ አምላክ ብለን በአእምሮአችን ከምንስለው በላይም መሆኑ። ስለዚህ ለማለም፣ ለመሳል፣ በልቦናችን ለመቅረጽ ከምናጠናው፣ ከምንመራመረውና ከምንፈልገው በላይ ማመን ብቻ መልካም እንዲሆንልን እናስተውላለን፣ ቃሉን ከምንመረምረው በላይ አሜን እንዲያጸድቅ እናውቃለን፣ ለቃሉ ከምናወጣው የትርጉም ትንታኔ በላይ በተናገረው ቃል ላይ በመቆም ከርሱ ጋር እንገናኛለን። እንደ መጥፎ ገጠመኝ ሆኖ ግን በተለይ ለአህዛብ የቃሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰራ አይታይም፤ በዚህ ትውልድ ከጣኦት አምልኮ የተዋረሰ እምነት በስመ ክርስትና ዘመኑን ተቆጣጥሮታልና።
ከህጉ ወደ ጸጋ የሚወስድ ጌታ ብቻ
በሌላ በኩል ህጉ ለጽድቅ ሕይወት መመሪያ፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ ነጸብራቅና የሰው ልጅ የመቤዠትን ፍላጎት ለመቅረጽ አገልግሎአል። ስለዚህ ህጉ የተጻፈበትን አጠቃላይ አላማ ማወቅ እንድንችል (በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐውደ-ጽሑፍ የሕጉን ልዩነት መረዳት እንዲመጣ) ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጠውን የጸጋ አሰራር ለማሳየት እንዲሁም በአማኞች ሕይወት ውስጥ ጸጋውን የመሻት ፍላጎት እንዲፈጠር ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በአጠቃላይ ሲታይ ህጉ የተሰጠበት አላማ ካልገባን የጸጋውን ታላቅነት ለእኛ የተሰጠበትም አላማ ምን እንደሆነ አይገባንም ማለት ነው። ስለዚህ እግዚአብሄር ህጉን ሰጥቶአልና በራሱ መንገድ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነው፦
ማቴ. 5:17-19 ‘’እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።’’
ጸጋን የተሞላ ጌታ በሙሴ በኩል እስራኤላውያን የተቀበሉትን ሕግ በራሱ ፈጽሞ ጸጋ እንድንቀበል አስችሎአል፦
ዮሐ.1:16-17 ‘’እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።’’
ስለዚህ መዳን ሆነ፣ ከአምላክ ጋር እርቅ ሆነ፣ የሃጥያት ስርየት ሆነ፣ መዳን ሆነ፣ የትንሳኤም ተስፋ ሆነ!