የህይወት ህያውነት

የመጨረሻ ዘመን

አዲሱ ህይወታችን በጌታ ኢየሱስ አሰራር የተፈጠረ ለዘላለም የሚኖር ዳግም የተወለደና መንፈሳዊ ነው፡፡: ይህ ህይወታችን በምድር ላይ እንደሚሆነው ሁሉ በመንፈሰዊውም አለም ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ያስፈልጋል፡፡ህይወታችን አሁንም ቀጥሎም፣ ዛሬም ነገም ህያው እንዲሆን ከጌታ ከኢያሱስ ጋር ህያው መስመር ሊኖረው ይገባል፡፡ ጌታ በመንፈሱ እለት እለት ሊያጠጣው፣ ሊያለመልመውና ህያው ሊያደርገው ከእርሱ ጋር መጣበቅ የግድ ነው፡፡ ዳግም የተወለደው ሰው በጌታ ህያው ሊሆን የተጠራ ነው፡፡ ያ ማለት ያለ አምላኩ ሙሉ ሆኖ በራሱ ሊኖር አይችልም፣ ይልቁንም እርሱ ጌታ በእርሱ የውስጥ ሰውነት ውስጥ በመኖር ህያው ሊያደርገው ይገባል ማለት ነው፡፡ ቃሉ በሮሜ.8:5-11 እንዳለ፡-
”እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።”
በእኛነታችን ውስጥ ሁለት ሰዎች አሉ፡- አንዱ የሌላው ተፎካካሪና ተቀናቃኝ ነው፣ አንዱ ሌላኛውን ሊቆጣጠርና ሊሰለጥንበት ይሞክራል፤ መፍትሄውም አንዱ መሞት ሌላው ህያው መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ ዛሬስ በየትኛው በኩል ህያው መሆን እንሻለን? በስጋ ሞተን በመንፈስ ህያው መሆን ወይስ በተቃራኒው የመንፈስን ሞት መምረጥ?
ኤፌ4:22-24”ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”
በስሙ ስንጠመቅ ጽድቃችን የሆነውን እርሱን በእምነት የመልበስ ጸጋ አግኝተናልና፣ በዚያም ጽድቃችን ክርስቶስን የለበስንበት ሰአት ላይ የእኛ የህይወት አቅጣጫ ለአንዴና ለመጨሻ ጊዜ ተለውጦአልና፡፡ ያ የህይወት ለውጥ ወደ ሁዋላ ዞረን የቀድሞ አሮጌ ሕይወታችንን እንዳናስብ ይልቅ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘውን አዲስ ህይወት እንድናጸና የሚያደርግ ታላቅ ለውጥ ነው፡፡ አሮጌው ሰዋችን እኛን በሞት ፍርድ ውስጥ ያሰጠመን የድሮ ማንነታችን ነውና እርሱን ባስወገደልን የጌታ ኢየሱስ አሰራርና ጸጋ ውስጥ በመመላለስና በመኖር አዲሱን ሰው ማሳደግ አለብን፡፡ ይሄ የክርስቲያኖች ዋነኛ ተግባር ነው፡፡
ቆላ.3:1-11 ”እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው። በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል። እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ። እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል። በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።”
ቃሉ በሮሜ.6:1-11 ውስጥ ሲጠይቅ እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? ይላል፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሄር ፈቃድ ያ አይደለም። ታዲያ ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ይህ ጥያቄ ነው ሃዋርያው ጳውሎስን የሚያሳስበው፡-
ሃዋርያው ጳውሎስ መፍትሄውን ሊያሳየን የሚሞክረው ከአሮጌው ሰውነታችን ወደ አዲሱ ሰውነታችን የተለወጥንበትን አሰራር በማስታወስ ነው፡፡ ይሄ ትምህርቱ ለዛሬው ትውልድ እጅግ ቁልፍ የሆነ ትምህርት ነው፡፥
መለወጣችን እንዴት ጀመረ? ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ጊዜ በዳግም ልደት ጀመረ፤ በመጠመቃችን ከሞቱ ጋር አንድ እንድንሆን ተደረገን፤ እንዲሁም ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፣ በዚያን ጊዜ አሮጌና ሙት ማንነታችን ተቀበረ አዲስ ህያው ህይወትም አገኘን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ስለተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር ተባብረናል፣ በዚህ ጸጋ ትንሳኤን የምንካፈል የህያው እግዘአብሄር ልጆች ሆንን፤ በአዲሱ ማንነት ያለን በእግዚአብሄር ምሪት፣ ፈቃድና አሰራር ውስጥ ጸንተን ለኃጢአት እንዳንገዛ መቁረጥ፣ የኃጢአት ሥጋችን ይሻር ዘንድ አንዴ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር ስለተሰቀለ የተሰቀለው በተሰቀለበት እንዲቀር የተቀበልነው አዲስ ህይወት ደግሞ በእኛ ዘንድ እንዲጸና መትጋት ተገቢ ነው፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋል የሚለው አዋጅ አሮጌው ሰዋችን ከእኛ ላይ መራገፉንና ነፍሳችን ነጻ መውጣትዋን የሚናገር ብስራት ነው። ይህን ሁሉ እግዚአብሄር በጸጋው ከሰራልን ምን ስራ ከእኛ ይጠበቅ? አዎ ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እርግጠኞች መሆን ፣ እንዲሁም እኛ በእርሱ አሰራር መዳንን ያገኘን ለኃጢአት እንደ ሞትን ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆነን ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆነን ራሳችንን ዘወትር መቁጠር ማስታወስም አለብን፡፡
2ቆሮ.5:17 ”ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” ይላልና፡፡
በዚህ አዋጅ መዳናችን ተረጋግጦአል፣ እንዲሁም በክርስቶስ በመሆናችን ሁለመናችን አዲስ ሆኖአል፡- አዲስ ማንነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ ነጻነት ያለው አምልኮ… ብዙ ነገር በአዲስ ተቀብለናል፡፡
አስጨናቂው አሮጌ ሰው
የአሮጌው ሰው ተጽእኖ በቀላሉ መታየት የሌለበት ጉዳይ ነው፣ እርሱ ለአዲሱ ሰው ጸር ነው፤ ለጠላት ዲያቢሎስ መንገድ ያመቻቻል፤ ከእግዚአብሄር ይለያል፡፡ ያን የሚያውቅ አምላክ ጥንቃቄ እንድናደርግ በቃሉ ያሳስባል፡-
”ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ” ይላል (ኤፌ4:22)፡፡
የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ ሲል አሮጌው ሰው በሚታወቅበት አታላይ ምኞት ተይዛችሁ የፊተኛ ኑሮአችሁን እንድታስቡ እንዳትገደዱ በማለት ነው፡፡ የአሮጌው ሰው መገለጫ በምድራዊ ብልቶች ቁጥጥር ስር ያለ ነው፤ በእርሱም ጠንቅ የእግዚአብሄር ቁጣ ይመጣል፡፡
ቆላ.3:5-9 ”እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው። በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል። እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ። እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና”
ቃሉ በተለይ ያተኮረው አሮጌውን ሰው ማስወገድ ላይ ነው፡፡ ምክኒያቱም በአሮጌው ሰው ሥራ/ባህሪ አማካይነት አዲሱ ሰው ላይ ከፍተኛ ውድቀት ሊመጣ ስለሚችል ነው፡፡
1ቆሮ.6:9-11 ”ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።”
ዛሬም ሆነ ነገ በህይወት እስካለን ማለት ነው ለራሳችን ለአለምም በቃልና በስራ መመስከር ያለብን ያዳነን አምላክና የዳንንበት አዳዳን ሊሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄ ትክክለኛው የመንፈሳዊ ውጊያ ስልት ነው፡፡ አመንኩ ስለዚህም ተናገርኩ ስለሚል ባለማመን የሚመጣን የደህንነት ሸንጋይ ጠላት የምናቆመው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ዛሬን ህያው ሆነን የቆምነው ትላንት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ በመታጠባችን፥ በእርሱ በመቀደሳችንና በመጽደቃችን ብቻ ነውና፡፡
አንዴ የዳነ ለዘላለም ዳነ
”እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።”(ዮሐ.15:1-4)
አንዴ የዳነ ለዘላለም ዳነ፡- በእግዚአብሄር ዘንድ የተረጋገጠው ለእኛ ያለው እቅድ ይሄ ነው፤ በእኛ ዘንድስ? አሳሳቢው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ እግዚአብሄር ካዳነን በሁዋላ እንደዳንን ከቀረን ተስፋው ሞላ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንዲያ እንዳይሆን የምንኖረው (ድነንም ቢሆን ወደ እርሱ እስካልተሰበሰብን ድረስ) በምድር ላይ በመናፍስት አሰራር ተከብበን ነው፤ ያለነው ለነፍሳችን ባላንጣ በሆነ በወደቀ ሰው ውስጥ ነው፤ የምንኖረው ከእግዚአብሄር ጋር ጥል ውስጥ ካለች አለም መሃል ነው፡፡ መዳናችን የሚረጋገጠው ግን ህያው ሆነን ከነዚህ ባላንጣዎች ጋር እየተጋፈጥንና እያሸነፍን በድል ስንሰበሰብ ነው፡፡
ታዲያ አስተዋይ አማኝ ማን ነው? ምክኒያቱም የተጋፈጡን ሶስት ሀይለኛ ተገዳዳሪዎች ናቸውና፡፡ ልብ ብለን እንደሆን ህያውነታችንን የነጠቁን አሮጌው ሰዋችንና ጠላት ዲያቢሎስ ለእግዚአብሄር እርግማን አሳልፈው የሰጡን በመንፈስ ብርቱ በሚባል የህይወት ደረጃ ላይ ሳለን ነበር (የመጀመሪያዎቹ ወላጆች አዳምና ሄዋን ከእግዚአብሄር ጋር የነበራቸው ግንኙነት ፍጹም እንከን የሌለው ነበርና ጥበቃው ጠንካራ ነበር)፡፡ በዚያ ብርቱ ጥበቃ ውስጥ ሳሉ ነው አሳባቸው ሾልኮ በመውጣት የጠላት ወጥመድ ውስጥ የገባው፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ከዚያን ዘመን እጅግ የወረደና አደገኛ ነው፤ ለዚህም ነው የእግዚአብሄር እርዳታና ጥበቃ የሚያስፈልገው፡፡ ይህን የሚያውቅ ጌታ አስቀድሞ ያለውን እናስብ፤ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
”እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።” (ዮሐ.15:5-7)
ፍሬያማ ህይወት ከህያውነት የሚመነጭ ውጤት ነው፤ እኛ በእግዚአብሄር መገኘት ውስጥ ሆነን የምናገኘው ውጤት ብቻ ነው፡፡ ዋስትናችንና ህይወታችን እንዳይደርቅ የሚያደርግ ከጌታ የሚፈስልን የህይወት ምንጭ በእኛ ሲኖር ብቻም ነው፡፡በዮሐ.7:37-39 ውስጥ ሲናገር፡-
”ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፡- ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።”
ይህ ቃል በአለም ባሉት ዘንድ ትርጉም ሊሰጥ የማይችል ንግግር ቢመስልም በእርሱ ለሚያምን ግን የህያውነቱ ዋስትና ነው፡፡ በትውልዳችን ያለን ተግዳሮት እያሸነፍን እንድንቀጥል የእርሱ አቅርቦት የሆነ የህይወት ውሀ ወንዝ ይፍሰስልን፡፡ቸል የተባለ አቅማችንን ያሳጣ ዋና ነገር ይሄ ነውና፤ ደግመን ደጋግመን ከእርሱ ዘንድ መጠየቅ፣ መለመን፣ ፊቱን መፈለግ እስክንቀበል ያለመታከት ተቀብለንም ቢሆን ልመና ያለማቆም ተገቢ ነው፡፡ ያለንበት ሁኔታ ዘና የሚያደርግ አይደለም፣ የቆምንበት መንፈሳዊ ሰርአት የሚያዘናጋ መሆንም የለበትም፣ መተማመኛ የእርሱ መንፈስ ብቻ ይሁን! አትኩሮታችን እንደ ሃዋርያት ወደ ጌታ ፈቃድ ይመለስልን እላለሁ፣ እርሱ ሲቀርበን የሚሰጠን የጉዋጉዋነውን ሳይሆን የሚያውቀውን የሚያስፈልገንንም ነው፡-
”እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፡- ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም፡- አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።” (ሐዋ.1:6-8)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሀይል የሚቀበል ህያው ትውልድ ለመሆን ያብቃን!