ወድጃችሁዋለሁ የሚል የአምላክ ድምጽ እንዴት ያለ እረፍት፣ እንዴት ያለ ደስታ፣ እንዴት ያለ ሰላም የሚፈጥር መተማመኛ ቃል ነው? እንኩዋን የአምላክ ድምጽ የምንደገፈው ሰው እንኩዋን ይህን ቃል ቢያሰማን ልባችንን ያሞቀዋል፡፡
እግዚአብሄር የጠራውን ህዝብ ሊያጸናና በጉዞው መሀል ሊያበረታው እንዲህ ያለ ቃሉን ይልካል፡፡ አብራምን ስንመለከት እርሱ ተስፋ ቆርጦ ሳለ ቃሉ በዘፍ.15:1-6 ሲመጣለት እናያለን፡-
”ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል፡- አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው። አብራምም፡- አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ። አብራምም፡- ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ። እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፡- ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል። ወደ ሜዳም አወጣውና፡- ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው። አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።”
እግዚአብሄር ይናገር እንጂ ድምጹ ልባችንን እምነት በመሙላት በህይወታችን ራእዩን የሚያመጣ፣ የህይወት አቅጣጫችንን የሚያስተካክል፣ መንገዳችንንም የሚያበራ ነው፤ ድምጹ የትኛውንም ነገራችንን ይፈጥራል፣ ያስተካክላል፣ ይመራል፡፡ ትእቢት የያዘው ልጅ ግን ይህን መለኮታዊ ድምጽ አያስተውልምና ለመጣለት ድምጽ ተገቢውን መልስ አይሰጥም፣ ከበጎ ነገር ይልቅም በስንፍና ይመልሳል፡፡
ሚል.1:2-5 ላይ ያለ የሚያጸና ቃል ሲናገር፡-
”ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን:- በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው። ኤዶምያስ፡- እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ፡-የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል። ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፡- እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ።”
የእግዚአብሄር አባቱን ባህሪ ባለማወቁ ያእቆብ እንዴት እንደደከመ፣ ለጥሪው ሲመልስም እንዴት ባለ ስንፍና እንደነበር እናያለን፤ ያኔ ሁኔታዎች አስረውት በደከመ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ስለነበር ለታላቁ የእግዚአብሄር ፍቅር መልስ ሲመልስ የሚያረካ ሆኖ አይታይም፡፡ ዛሬም እግዚአብሄር ወድጃችሁዋለሁ ሲል በአምላክነቱ ልክ እየተናገረ እንደሆነ ካላስተዋልን የታላቅነቱን ልክ ከሁኔታችን በታች እናደርገዋለን ፤ይሄ ደግሞ አደጋ አለው፡፡
በተፈጥሮ የሰው ልጅ ለእግዚአብሄር ድምጽ ያለው ግብረ-መልስ እጅግ የዘገየ ነው፡፡ ይህ ከየትኛው ድካማችን የመነጨ እንደሆነ እንረዳለን ወይ? ብዙ ምክኒያቶች ሊኖሩ ቢችሉም ዋናዎቹ ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ባለማስተዋል ምክኒያትና ዘመንን ባለመለየት ምክኒያት ነው፡፡
ዮሐ.14:15-17 ”ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።”
በጥቅሱ ላይ እንደተመለከተው ፈቃዱ ትእዛዙን እንድንጠብቅለት ነው፡፡ ከዘመን ጋር ያለን የማስተዋል እጥረት ግን እየሆነ ያለውን የእግዚአብሄር አሰራርና እግዚአብሄር አንድያ ልጁን ገልጦ የሚሰራበትን ጊዜ ያለማወቅ መሆኑ በግልጥ ይታያል፡፡ እግዚአብሄር ግን ቸር ነው፣ መንፈሱን በማውረድ ችግራችንን እንደሚፈታው ቃል ገባልን እንጂ!
አዎ፣ የእግዚአብሄር ፍቅር በውስጡ በውዴታ የምንከተለው ትእዛዝና መጠበቅ ያለበት ስርአት ስላለው እግዚአብሄር የወደዳቸው ያን ልብ እንዲሉ እንዲከተሉትም ይፈልጋል፡፡ ይሄንንም ከእስራኤል ፈልጎ ሲጠይቅ ይታያል፡፡ ምክኒያቱም ወደውት ቢሆን ትእዛዙን ሊጠብቁ አያዳግታቸውምና፡፡
የእግዚአብሄር ድምጽ ውስጥ የተገለጠው የፍቅር ስሜት እንደሰው ያለና ጊዜያዊ ሳይሆን የጸና ነው፣ በውስጡ የማይሻር የዘመን አሻራ አለበት፣ እርሱ ትላንት እንደወደደን ዛሬም እንደሚወደን እንዲሁም ነገንም ሊወደን የታመነ ስለመሆኑ የሚገልጽ ነው፣ የማይለወጥ እግዚአብሄር ፍቅሩም አይለወጥም፡፡
የጥያቄያችን መጀመርያ፡- በምን ወደድኸን? ብላችኋል ይላል፡፡ እግዚአብሄርስ ለእስራኤል ያለውን ፍቅር በምን መንገድ ገለጠው?
እግዚአብሄር ፍቅሩን ለያእቆብ የገለጠው በልጆች ተባርኮ፣ ማረፍያ ምድር ወርሶና በትውልዶች ተባዝቶ ሳለ ሳይሆን ገና በማህጸን ሆኖ ክፉና በጎውን የማያውቅ ደካማ ሳለና ከወንድሙ ጋር ሲታገል ነበር፡፡ ያእቆብ ገና ራሱን ባላወቀ ጊዜ እግዚአብሄር አውቆት ነበር፤ ገና ራሱን መርዳት ሳይማር የወደፊቱን ሲያሳካለት የነበረው የአባቱ አምላክ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ለአባቱ የገባውን የተስፋ ቃል ይፈፅም ዘንድ በቀጥኛ መንገድ መራው፡፡ ያእቆብ በልቡ ቅንነት ሲመራ በተሳሳተባቸው ስፍራዎች እግዚአብሄር ደርሶ ሲያቀናው ነበር፡፡ እንደወንድሙ በትእቢት ሳይሆን በየዋህነት የሄደውን እግዚአብሄር አይቶአል፡፡ ከእግዚአብሄር የተሰጠውን የብኩርና ጸጋ ወንድሙ ባቃለላት ጊዜ ትሁት የነበረው ያእቆብ እግዚአብሄርን ተማምኖ አብዝቶ ሽቶአት ነበርና እግዚአብሄር በፍቅሩ እንዲመራው አደረገው፡፡ እኛስ? እኛምኮ ያልጠፋነው እግዚአብሄር ስለወደደን እንጂ መልካም ስለሆንን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በፍቅሩ እያኖረን፣ እየመራንና እየጋረደን ሳለ ያን ሳናስተውል በድካምና ባለማወቅ ምክኒያት በራሳችን ብልሀት እየወጣንና እየገባን ይመስለናል፡፡
የእግዚአብሄርን ፍቅር በእግዚአብሄር አላማ አንጻር ስንመለከት እኛ ለእርሱ ፍቅር ያለን ምልከታ ከባድ ብዥታ እንዳለው እናረጋግጣለን፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር ማስተያየት፣ የእግዚአብሄርን ፍቅር ከሰው የፍቅር ትርጉዋሜ ጋር ማቀራረብ፣ የእግዚአብሄርን ፍቅር ከስሜት ሙቀትና ቅዝቃዜ ጋርም ማመሳሰል ይቀናናል፣ ይህ ትልቅ ችግር በመሆኑ እውቀታችንን በመዘባረቅ እየጎዳን ይገኛል፣ እንዲያውም መስመር አስቶናል፡፡ በተጨማሪም እርሱ የገለጠው ፍቅር መሀል የኛን ግምት ስናስገባ ግምታችን የፍቅሩን ጉልበት የሚገልጥ ሳይሆን የሚያደፈርስ፣ የሚያዛባና የሚከልል ሆኖአል፡፡ ስለእርሱ የምንናገረው ፍቅር ግን ግምት ሳይሆን ተጨባጩን ሊሆን ይገባዋል፤ ይህን የሚያሰኘው በእውነት ለእኛ የገለጠበት አገላለጥ በእኛ ዘንድ ሲኖር ነው፡፡
ዮሐ.15:12-3” እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”
እርሱ እኛን መውደዱ አንድ ነገር ነው (የእርሱ ችሎታ ብቻ ነው)፤ የሚያስደንቀው ነገር የእርሱ ፍቅር በእኛ ህይወት ውስጥ ተገልጦ ሰውን መውደድ ማስቻሉ ነው፡፡ የዚህ እውነት ብርሀን በመንፈስ ቅዱስ ለበራለት ሰው ”ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር” ለሚለው ቃል በቂ ማብራሪያ እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡
ነገር ግን በሚልክያስ ዘመን እስራኤላውያን የደረሰባቸውን ውድቀት የሚገልጠው የጠየቁት ጥያቄ ጥልቀት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
– እግዚአብሄር ወድጃችኋለሁ ሲል እነርሱ፡- በምን ወደድኸን? ብለዋል፣
– እርሱም ተናገረ፡-እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? አላቸው፣
– ግራ የገባቸው ይቀጥላሉ፡- ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ይላሉ፣
– ያረከስንህ በምንድር ነው? ይላሉ፣
– ያታከትንህ በምንድር ነው? ይላሉ፣ እርሱም ሲመልስ፡- ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ፡- የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው ሲል ያመለክታቸዋል።
-ደግሞ፡- የምንመለሰው በምንድር ነው? ይላሉ፣
-የሰረቅንህስ በምንድር ነው? ይላሉ፣
-በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ይላሉ።
ይሄ ሁሉ ትህትና የሌለውና ጥርጣሬን የሚያንጸባርቅ ጥያቄ አምላክን በመርሳታቸው/ በመራቃቸው ምክኒያት በተፈጠረ ውዥንብር የተናገሩት ነበረ፡፡ ወድጃችሁዋለሁ የሚለው ድምጽ መተማመን፣ ደስታና ሰላም የሚፈጥር ሊሆንላቸው ያልቻለውም ለዚያ ነበር፡፡ እግዚአብሄር በእያንዳንዱ ንግግራቸው መልሶላቸዋል፣ እነርሱ ግን የተመለሱበትን የንሰሀ ቃል ሲያወጡ አይታዩም፡፡
እግዚአብሄም ሰው አይደለምና በሚል.1:9-11 መውጫ መንገዱን እንዲህ ሲል ያመለክታቸዋል፡-
”አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ! ይሄ የምህረት መንገድ ነውና ያቆመናል፡፡
ዘዳ.7:6-11 ”ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። እንግዲህ ታደርጋት ዘንድ እኔ ዛሬ ለአንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድንም ጠብቅ።”
መስዋእት ያለው ፍቅር
የእግዚአብሄር የፍቅር ብርታት እውቀት ልባችንን ሲሞላ የሚያበራልን ነገር አለው፡- የእግዚአብሄር ፍቅር በአዲስ ኪዳን በመስዋእት የተገለጠ መሆኑ፤ ይህም መስዋእት እግዚአብሄር አንድያ ልጁን ለመስቀል ሞት እስኪሰጥ ድረስ የሄደ ፍቅር እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ መስዋእቱ የነገሰብንን ሞት እስከመዋጥ የደረሰ ነው፡፡ መስዋእቱ የዘላለም ጥል በዘላለም እርቅ እንዲለወጥ ያስቻለም ነው፡፡
ዮሐ.3:16 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” ሲል እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር አስተማማኝ መሆኑን ያውጃል፡፡
እግዚአብሄር የአለምን ህዝብ አንዱን ከሌላው ሳይለይና ሳያበላልጥ ሊያድን የወሰነው ውሳኔ በማዳን ብቻ ያቆመ ሳይሆን አልፎ በፍቅሩ መኖር የምንችልበትን ጸጋ አጎናጽፎናል፡፡ በዚህም በቀረልን ዘመን መስዋእትን እየከፈልን ለእግዚአብሄር ያለንን ፍቅር በሚያረጋግጥ መልኩ በእርሱ እንድንኖር ይጠብቅብናል ፡-
”በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፡- እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” (ማቴ.16:24-26)