ማቴ.4:3-20 “እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት።ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ።ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም።ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ።የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ … ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል።እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ።በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል።በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።“
በጌታ ኢየሱስ መገኛ ኣካባቢ የሚመላለሱ ሰዎች የተለያየ የህይወት ይዘት ነበራቸው።ጌታ ኢየሱስን በተለያየ ምክኒያት ሰዎች ተከትለውታል።ጌታም እነዚህን ሰዎች ቆም ኣድርጎ ያሉበትን ሁኔታ የልባቸውንም ይዘት በማሳየት ያስረዳቸው ነበር።ፍላጎታቸው የተለያየ ሰዎች በአጋጣሚ ያልያም በምክኒያት በሚመስል መንገድ ቃሉን የመስማት እድል ያገኛሉ።ጌታ በቃሉ በኩል ወደ መንግስቱ እንዲህ ሰዎችን ይጠራል። ነገር ግን የጠራበትን ቃል የመቀበል ችሎታ የሰዎቹ የልብ ይዘት ይወስነዋል።በዙሪያው ከሚሰበሰቡበት አጋጣሚ በአንደኛው ብዙ ህዝብ ከእስራኤል ከተሞች መጡና በዙሪያው ሆኑ።በዚያ ኣጋጣሚ ጌታ ኢየሱስ አንድ ትልቅ ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር።ምሳሌው ስለ ቃሉና ስለሰዎች የመቀበል ኣቅም (የልብ ሁኔታ) የሚያስረዳ ነበር፦በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች እነዚህ ናቸው፦
1. መስማት የሚችሉ ማስተዋል ግን የተሳናቸው
ቃሉ እንደሚለው “እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት።…. ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል።“
እነዚህ ሰዎች ወደ ጌታ የመቅረብ እድል አግኝተው ነበር። ልባቸው ግን መንገድ እንደተሰራበት የደደረ መሬት ጠጣር ስለሆነ የሰሙትን ቃል ወደ ውስጥ ማስገባት ተስኖታል፣ስለዚህ የተዘራባቸውን የህይወት ቃል ለጠላት አጋልጦታል።መንገድ አካባቢ የሚወድቅ ዘር ለእንስሳና ለወፎች ንጥቂያ የተጋለጠ ነው።እንዲሁ ጠላት በሚመላለስበት መንገድ አቅራቢያ መልካም ነገር ከጥፋት ተርፎ መቆየት አይችልም።
እንደ መንገድ ዳር የሆነ ልብ የህይወትን ቃል የማግኘት እድል ቢያገኝም ያፈራ ዘንድ በውስጡ መጠበቅና ከህይወቱ ጋር ማዋሃድ ስለማይችል ጠላት ዲያቢሎስ ፈጥኖ ይነጥቀዋል። የእግዚአብሄርን ቃል መስማት አስፈላጊ ቢሆንም ለፍሬያማነት ማስተዋል፣ ማመንና መጠበቅ ያስፈልጋል።
ዕብ.4:2 “ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።“
2. መስማት የሚችሉና በደስታ የሚቀበሉ መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ግን የሚሰናከሉ
“ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ… እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ።“
ጭንጫ መሬት ዘርን ማብቀል ይችላል። ግን ጥልቅ አፈር ስለማይኖረው ዘሩን በበቂ ሁኔታ መግቦና አሳድጎ ለፍሬ ማብቃት አይችልም። እንደ ጭንጫ መሬት የተመሰሉ ልቦችም ጌታ ኢየሱስን በደስታ ይሰሙታል።የተናገረውንና የሰራውን ያምናሉ። ባዩት ይደሰታሉ፣ ነገር ግን ማንነቱን ስለማያስተውሉ በእምነታቸው ስር መስደድ አይችሉም። በዚህ ምክኒያት የፈተና ነፋስ ከስር ነቅሎ ይጥላቸዋል። በእምነት ስር መስደድ ግን በጌታ ላይ እንድንጸና ያደርጋል። ላይ ላዩን የሆነ እምነት በረከትን ለመብላት ያዘጋጃል እንጂ ስለጌታ የሆነን ፈተና አይታገስም።
ፊል1:28-29 “በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም“
ዘር ተዘርቶ ፍሬያማነት ደረጃ ይደርስ ዘንድ በትግስትና በጽናት በተተከለበት ስፍራ መጠባበቅ ያስፈልገዋል። ውሃ እጥረት ሊፈጠር ይችላል። የጸሃይ ግለት ሊበረታ ይችላል። የነፋስና የጎርፍ ጉልበት ሊመታ ይችላል። በጽናት መጠባበቅ ግን በረከት የሆነ ፍሬያማ ደረጃ ላይ ያደርሳል።
3. መስማት የሚችሉና የሚያምኑ ግን በዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል በምኞትም መጽናት የማይችሉ
“ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም።…. በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል።“
እነዚህ መስማት የሚችሉ ሰዎች በእምነት ቃሉን የሚቀበሉ ናቸው። በቃሉ ለመቆምም ሙከራ ያደርጋሉ። ግን በዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል በምኞትም ይሸነፋሉ።በዚህም መጽናት የማይችሉ ሆነው ይዝላሉ ማፍራትም ይሳናቸዋል።
ፈተናዎች የትኩረት አቅጣጫን በማሳት ከቃሉ ፈቀቅ የሚያደርጉ ናቸው።ዛሬ የእግዚአብሄር ቃል እያስደሰተ የሚያንጸን ካልሆነ ሌላ ምኞት፣ አሳብና ፈቃድ በህይወታችን ውስጥ ገብቶ ከላይ የተጠቀሰውን እንቅፋት ያመጣል።
1ዮሐ.2:15-16 “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።“
4. ቃሉን የሚሰሙና የሚያምኑ ቃሉንም የሚጠብቁና በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ
“ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ።…… በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።“
ቃሉን የሚሰሙ፣ የሚያምኑና የሚጠብቁ ህይወታቸውን ለእግዚአብሄር ስራ ያዘጋጁ ናቸው። የልባቸው ዝግጅት በቃሉ ጸንተው የሚጠባበቁበትን ችሎታ በመፍጠር ፍሬ የሚያፈሩበትን ምሪት ከእግዚአብሄር እንዲቀበሉ ያደርጋል።ልባቸውን በእግዚአብሄር ላይ አድርገው በእምነት ስለሚጠባበቁ በቃሉ ላይ መጽናት የሚችሉና ፍሬያማ ናቸው።
በእግዚአብሄር መገኘት አካባቢ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች አትኩሮትንና ፍለጋን ይጠይቃሉ።ድምጹን መለየት፣ እርሱ እንዲናገር መፍቀድ፣ ለመለወጥ መፍቀድና እንደተናገረው መቀበል በረከትን ያመጣሉ።የልብ ለውጥ፣የአስተሳሰብ ለውጥ፣የፈቃድ ለውጥ እንዲሁም መጠበቅ እንደ መልካም መሬት ለቃሉ የተመቸ ልብን ይፈጥራሉ።
ከምን ጊዜም ይልቅ በቤቱ ለመኖር እንድንችል በልብ ስፋት የቃሉን ምክር አጥብቀን መረዳትና መያዝ የፍቅር ግዴታችን መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።የቆላ.3:12-17 ምክር እንዲህ ይነግረናል፦
“እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ።እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ።የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።“