ወንጌልን መቀበል

የእውነት እውቀት

በወንጌል ጉዳይ ዋነኛ ናቸው ከሚባሉት ነገሮች መሀል በወንጌል መልዕክት ውስጥ የሚገኘውን የጌታ ደህንነት ሰው እንዴት አድርጎ እየተቀበለውና እየኖረው ነው? የሚለው ነው፡፡ታላቅና ዘላለማዊ የሆነ የአምላክ እቅድ ወደ ሰዎች ሲላክ ሰዎች አቀባበላችን እንዴት ነበር? መላእክት የጌታን መወለድ በአድናቆትና በሙገሳ ሊያጅቡ ከሰማያት ወርደዋል።ነብያት ስለዚህ መዳን በትልቁ አጉልተው ተናግረዋል።ቅዱሳን በመንፈስ ሆነው ስለእርሱ አመስግነዋል።
ሉቃ1:67-75 “አባቱ ዘካርያስም(የመጥምቁ ዮሃንስ አባት) መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤
ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ሉቃ1 ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤
እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።“
እግዚአብሄር ከዘላለም ዘመናት በፊት አቅዶ የነበረውን ደህንነት እጅግ ደካሞች ለሆንን ሰዎች ሲሰጠን እኛስ እንዴት ተቀበል ነው? ተመልከቱ የእኛ ደካማነትና የእሱ የጥበብ ስራ እንደምን የተራራቀ ነው?!
በዮሐ.1:9-13 ሲናገር “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።“ አለ።

የሰው ልጅ በተለይ ወገኖች የተባሉ አይሁድ የከበረውን መዳን እንደክብሩ መጠን ሊያከብሩና ሊቀበሉት እንዳልቻሉ እንመለከታለን።
ወንጌል የሰው ልጆች ከእግዚአብሄር የሚወለዱበትንና ከምድራዊ ዘር ወደ ሰማያዊ ዘር የሚለወጡበትን ታላቅ የምስራች የያዘ ነው። እንዲሁም የሰው ልጆችን ካሸነፈው ሀጢያት፣ መተላለፍ፣ እርግማን፣ በደል፣ አመጽ፣ ችግር፣መከራ፣አበሳ፣ለቅሶ፣ዋይታ፣ጭንቀት፣ጨለማ፣ድህነትና የዘላለም ሞት ማምለጫና ሰይጣን የሚሻርበትን የእግዚአብሄር አሰራር የያዘ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ይህ ምስጢር ተገልጦ ሰው ካልተቀበለ የጥፋት እድሉ ሰፊ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሰው ልጅ ጠላቶች ሁሉ ላይ የእግዚአብሄር ድል የሚታወጅበት፣ የክርስቶስ ክብር አንድ ቀን በምድር ላይ የሚታይበት፣ አንድ ሺ አመት ንግስና በክርስቶስም መንገስ ጠላት አንድ ሺህ አመት የሚታሰርበት አስደናቂ ተስፋና ድል በወንጌል ተበስሮአል፡፡ይሁን እንጂ አሁንም አሳሳቢው ነገር ሰዎች ይህን የክብር ተስፋ ያለው ወንጌል እንዴት ነው የምንቀበለው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ከዚህም ባሻገር ክርስቶስን በማመን የተቀበልነውን የዘላለም ተስፋ በተጨባጭ እንድናገኝ በተገለጠልን ወንጌል በርትተን ለመኖር እንጸናለን ወይ? የሚለው ጥያቄም መመለስ ያለበት ነው፡፡

ሐዋ.11:21-23 “የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤“
በርናባስ የጌታ እጅ ሰርቶ ቍጥራቸው እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር ማለታቸው ታላቅ ደስታ ቢሰጠውም ሁሉም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መምከርን ግን አልተወም።ዋናው ቁምነገር መቀበሉ ላይ ብቻ ያረፈ አይደለም፣እንደተቀበሉት እስከ መጨርሻ መጠበቅም ላይ ነው።
ጳውሎስ የእምነት አባት ስለሆነው አብረሀም በገላ.3፡6-9 ውስጥ ሲናገር፡-
”እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደሆኑ እወቁ፡፡መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ፡፡እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ይላል፡፡
ከአመነው ከአብርሃም ጋር ለእኛ የተሰጠው ደህንነት በእኛ ጥንካሬ ወይም እግዚአብሄር የሰጠውን ህግ በመጠበቃችንና ልዩ ችሎታ በማሳየታችን የሆነ አይደለም፡፡
እንዲያውም የርሱ በረከት ወደ እኛ ከመድረሱ አስቀድሞ አብረሃም የሰማውንና ያመነውን ቃል ያገኝ ዘንድ በብዙ ትግስት ጠብቆአል።ያን በትግስት ጠብቆ ያገኘውን የተስፋ አምላክ እኛ በማመናችን ብቻ እርሱን ከአብረሃም እኩል እንድንቀበል ሆነ።አብረሃም ተስፋ ከተነገረው ጊዜ አንስቶ በትግስት የህይወት ጉዞውን ተራምዶአል።እኛም ብንሆን ለአብረሃም የተገባውን ተስፋ እንጭብጥ ዘንድ በእርሱ ምሳሌነት ጸንተን ከጌታ ጋር እስከመጨረሻው መጉዋዝ ይገባናል።
ማር.13:13 “በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።“ ስለሚል።