ሀጢያት ስንሰራ ከጻድቁ አምላክ ፊት እንሸሻለን፡፡ ሀጢያት ያሳድዳል፣ ሂድ ሂድ ጥፋ ተሰወር ይላል፡፡ የምህረት በር እንዳናይ አድርጎ የሽሽት ቁለቁለት ላይ ያኖረናል፡፡ ከእግዚአብሄር ፊት የሚሸሹ ሁሉ ስብራት ላይ ይወድቃሉ፡፡ መሸሽ ከእግዚአብሄር ክልል ያስወጣል፡፡ አዳም ከእግዚአብር ፊት በሸሸበት ቀን ከኤደን ገነት እስከወዲያኛው ተባረረ፡፡ከመልካም ነገር በራቅን ቁጥር እየለቀቀን የሚሄድ የእግዚአብሄር መልካም ነገር ብዙ ነው፡፡
ዘፍ.4:9-16 ”እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፡- ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፡- አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? አለውም፡- ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፡- ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።እግዚአብሔርም እርሱን አለው፡- እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።”
ከእግዚአብሄር የሚሸሽ ሁሉ ሀይል አልባ እንደሚሆን ከላይ እናያለን፡፡ እንደ ቃየን ያለ ሁሉ መንፈሳዊ ህይወቱ የተማረከና የተሸነፈ ነው፡፡ በምድርም ላይ ኑሮው አይቃናለትም፤ ስለዚህ መንፈሱ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ይሆናል። ኃጢአት የሚፈጥረው ክብደትና ስቃይ ሰውን ሁሌ እንዳሳደደው ነው፡፡ እግዚአብሄር ከተወን ማን ይቀበለናል፣ ከጠላት ውጪ?! ሞገስ የለ፣ ክብር የለ፣ እና የሚያስመካ ስለማይኖርም ቀና ማለት የለ፡፡
አዳምና ልጆቹ ከእግዚአብሄር ፊት ወጥተው እንዲሸሹ ያደረጋቸው ቀድሞ የተማረከው አእምሮአቸው ነበር፡፡ ይህ አእምሮአቸው ከእግዚአብሄር የሚያሸሽ ሃሳብ የሚያመነጭና የቀናውን አሳብ የሚያሳጣ ነበር፡፡
ሆኖም ሰው ከመውደቁ በፊት እንዲጠነቀቅ በሀጢያቱ ቢወድቅም በንስሀ እንዲመለስ የእግዚአብሄር ፍላጎት ነው፡፡ሀጢያት ሲያሳድድ ግን ማሸፈትና መሰወር እንጂ መቅረብን አይፈጥርም፡፡ የመሸሽ ገጽታዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ብናያቸው ሊጠቅሙ የሚችሉ የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፡-
• ከጽድቅ መንገድ መሸሽ- ከእግዚአብሄር ቃል ምክር መሸሽ፣ ከተግሳጹ መሸሽ፣
ዘዳ.28:15-25 ”ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።… እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል። እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል። …”
• ወደ እግዚአብሄር መሸሽ- ከጥፋት መሸሽ ፣ ከጠላት ወጥመድ መሸሽ፣ ወደ አርሱ መጠጋት
ስንሸሽ የሚራራ ካገኘን ያስጥለናል፣ ያልያም ጨካኝ እጅ ከወደቅን መዋጥ ሊገጥመን ይችላል። እግዚአብሄር ግን መሃሪ ነውና ወደርሱ የሸሹትን እጁ ትቀበላቸዋለች።
ዕብ.6:17-18 ”ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤” ስላለ ማንኛውም ሰው የሚመካበትን ጥሎ ትምክህቱ እግዚአብሄር ቢሆን አስተማማኝ መጠጊያ ያገኛል፡፡
መተማመን ይሆነን ዘንድ “እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ “አለ እግዚአብሄር። አላውቅም አላርፍም ብለን ከሸሸን በእርግጠኝነት አጥፊ እጅ መውደቂያችን ይሆናል። እግዚአብሄር በባህሪው በፍቅር መቅረብ የሚወድ አምላክ ነው። ስለዚህ ሊጠቅመን ወዶ በፍቅር ይቀርባል፣ በፍቅር ይመክራል፣ በፍቅር ሁሉን ያደርጋል። ወደ እኛ ሲመጣ በደጅ ቆሞ ያንኩዋኩዋል።መጥቶም ሊያስተምረን በህሊናችን በኩል ሲናገረን ግን ድምጹን ላለመቀበል የምንታገል ከሆነ የማንመለስበት ሽሽት ውስጥ እንገባለን።
• ሽሽ ይላል እግዚአብሄር
ከጠላት የሚያስጥል አምላክ ለሰላምህ ይበጅ ዘንድ ከጠላትህ አካባቢ ሽሽ ይላል። ከጠላት ሰፈር ርቀህ እግዚአብሄር ወደ ሚገለጥበት ቤቴል (የአግዚአብሄር ቤት) ድረስና በዚያ ኑር፣ በዚያ እርሱ ይመግብሀል፣ ይንከባከብሀል፡፡
ዘፍ.35:1 ”እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው፦ ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።”
እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሆነ ሽሽት እግዚአብሄር እንዲቀበለን ያደርጋል። እግዚአብሄር በሚመክረው አንጻር መቆምም ሁሌ መልካምነቱን ያስወርሳል፡፡
እንዲሁም እግዚአብሄር ስፍራችንና የህይወት ይዘታችንን በማየት ውጡ፣ ሽሹ ይላል፣ ያለንበት ስፍራ የሞት ሰፍራ ሊሆን ይችላልና። ባንረዳውም መቃብር አፍ ላይ ቆመን ሊሆን ስለሚችል እግዚአብሄር ሊያድነን ሲፈቅድ ውጡ ተለዩ ይላል፡፡ያኔ ለማስጠንቀቂያው ፈጣን መልስ ከሰጠን እንተርፋለን።ካልተቀበልነውና ስሜታችንን አዳምጠን ከወሰንን ግን እንጎዳለን፡፡
ዘፍ.19:12-14፣26 ”ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት፡- ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤ እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል። ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም። ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።…የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች”
• መሸሽ አማራጭ የማይሆንበት አጋጣሚ አለ ወይ?
ያለንበት ሁኔታ ሲያውከንና ሲሰለቸን ከምንኖርበት የህይወት ስርአት ለመውጣት መቡዋጠጣችን ያለ ነው። ስለዚህ ፍላጎታችንን ሁሌም አበጀ ልንለው ባንችልም (መልካም ሁኔታ ውስጥ እያለንም ስጋችን ሊሰለች ይችላልና) ለበጎ ንቅናቄ ስፍራ መስጠታችን ወደ ሌላ መልካም ስፍራ ሊያደርሰን ይችላል። ሆኖም ካሉበት የተሻለ ስፍራ ወጥተው የከፋ ሁኔታ ላይ የሚወድቁ ሰዎች በአብዛኛው የሚኖሩበትን ሁኔታ አክብረው መያዝ ሲሳናቸውና ያለምንም አጥጋቢ ምክኒያት ወደ ሌላ አይናቸውን መጣል ሲጀምሩ ነው። ከራስ መሸሽ (ከራስ ነገር መሸሽ) የራስን አክብሮ ባለመያዝ ሊፈጠር ይችላልና እንዲህ ሲገጥመን መሸሽ አማራጭ አይሆንም። እዚህ ላይ የእስራኤልን ታሪክ ማየት እንችላለን፦
እስራኤል ከግብጽ የወጡት በፈጣሪቸው እቅድ እንደነበር እናስታውሳለን፡- እግዚአብሄር እነርሱ ወዳሉበት ስፍራ ድረስ ሄደና መቸገራቸውን አየ፤ አዝኖላቸውም ለአባቶቻቸው የገባውን ቃልኪዳን አሰበ፣ ሊያወጣቸውም ወስኖ ሙሴን ላከው። እስራኤላውያን ግን የነጻነታቸው ብስራት ከታወጀ ጊዜ አንስቶ የተቃውሞ መንፈስ አደረባቸው። ከግብጽ ምድር ከወጡም በሁዋላ ይጉዋዙ በነበረበት ስፍራ ሁሉ ከተጠሩበት አላማ ውጪ የሆነ ድርጊት በመፈጸም እግዚአብሄርን ደጋግመው አሳዝኑት። ከናንተ ጋር እኔ አልወጣም ብሎ እስከሚወስን ድረስ ያን አደረጉ። የተሰጣቸውን ታላቅ ነጻነት አላከበሩትም። እግዚአብሄር የወሰነላቸውን የነጻነት ህይወት አቃለሉት፣ ደጋግመው እየሸሹት ጠላት ሰፈር ይገቡና እጅግ ያሳዝኑት ነበር። ውጤቱ ምን ነበር?- መቆረጥ! ከግብጽ ምድር ከወጡት አንዳቸውም ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገቡ እግዚአብሄር ወሰነባቸው። ሙሴ እንኩዋን በማጉረምረም ከማዶ የቀረው የተሸከመውን ሃላፊነት ለመሸሽ ሲያጉረመርም ነበር።
ወደ ራሳችን እንመለከት እስቲ? ከእግዚአብሄር የተቀበልነው ብዙ ነገር አለን ብለን ካመንን ያን አክብረን የማንይዝበት ምክኒያት ምንድነው? በእርግጠኝነት እግዚአብሄርን ተቀብለነዋል ካልን አጥብቀን እንጠጋው እንጂ አንሽሸው። በሸሸን ቁጥር እንርቃለን፣ በራቅንም ቁጥር ወደ ክፉ ወጥመድ እንቀርባለን።
መዝ.34:12-14 ”ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም።”
በአጠቃላይ ድል ያለበት ህይወት እንዲኖረን ሰላም ያለበትን ነገር እየተከታተልን ክፉን ከሁዋላ ማድረግና በፍጥነት መጉዋዝ አለብን፡፡ሆኖም በእግዚአብሄር ዳግም የተወለድን ሁላችን ከራሳችን ለመሸሽ መሞከር የለብንም። ያ ማንነት ከእግዚአብሄር ከአምላካችን የተቀበልነው የከበረ ነገር ስላለው ልንሸሸው አይገባም። ከዚያ ውስጥ በጎ ህሊና ዋነኛው ነው። የተፈጠረልን ህሊና በጎ በጎውን ያሳስበናል። ወደ በጎ ይመራናል። በጎውን ያስመርጠናል። ከበጎነት ስናፈነግጥ በሃይለኛ ድምጽ ያስደነግጠናል። ስናጠፋ ግን ጠፍተን ላለመቅረት ንሰሃ መግባት እንጂ መሸሽ አያስፈልገንም። የሸሸ አንድ ቀን ማፈንገጡ አይቀርም፣ እምቢ ህሊናን አልሰማም ያለም አንድ ቀን ከበጎ ነገሩ መነቀሉ ያልያም መሰበሩ አይቀርም። ስለዚህ ተመለስ ሲል ለውስጣችን እምቢ ሳይሆን እሺ ማለት ተገቢ ነው፣የሚያዋጣም ነው።