ከእምነት መንሸራተት

የእውነት እውቀት

በማቴ.8:237 ውስጥ ያሉ ደቀመዛሙርት በሁኔታዎች አስቸጋሪነት ምክኒያት ልባቸው በፍርሀት ተያዘና አብሮአቸው ያለውን ጌታ እስከመርሳት ደረሱ፡-”ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀመዛሙርቱ ተከተሉት። እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፡- ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉአስነሡት። እርሱም፡- እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ሰዎቹም፡- ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።”
ከላይ ካነበብነው ጥቅስ እንደምንማረው ከእግዚአብሄር ይልቅ ሁኔታዎችን የሚፈሩ ሰዎች ከእምነት ይንሸራተታሉ፡፡የሚያንሸራትታቸው ፍርሀት ምንጩ ጥርጥር ነው፡፡ አንዳንዴ ፍርሀት ባለጋራን ያገዝፋል፣ ውጤትን መፍራት እንዲህ እሆናለሁ ብሎ መጨነቅም ያስከትላል፡፡ደቀመዛሙርቱ አትኩሮታቸው በባለጋራቸው ላይ ነበር እንጂ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ላይ አልነበረም።ጌታም ፍርሃታቸውን ሊያስወገድ አትኩሮታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ አደረገ፣ከዚያም በማስከተል በእምነትና በመደነቅ እንዲሞሉ አደረገ።
ፍርሀት የመጨረሻው ዘመን ምልክት ነው፡፡በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ከሚሰሙትና ከሚያዩት ነገር የተነሳ በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ይዝላሉ።ፍርሀት ደግሞ በእግዚአብሄር ላይ ያለውን እምነት ይሸረሸራል፣ ማመንታት ይፈጥራል፡፡በጣም የፈራ ሰው የራሱን ህልውና እንኩዋን እስከ መርሳት ይደርሳል፡፡ጌታ ግን እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ይላል(ማር.5:35)።
ዘጸ.15:9-11 ”ጠላትም፡- አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?”
ሰይጣን ፍርሀትን በመዝራት የአማኝን ልብ ያቀልጣል፡፡ ፍርሀት ይጎዳኛል ብለው የሚፈሩትን ማጉላትና ማመን አስተማማኙን እግዚአብሄር ግን መጠርጠርና ያለመታመን ያስከትላል፡፡
እውነተኛ ፍርሀት ግን ፈጣሪን በማክበር የሚገለጽ መፍራት ነው፡፡በዚህ ፍርሃት ውስጥ ጥልቅ የአባትነት ፍቅር አለ።እግዚአብሄርን በመፍራት ትዛዙን እንሰማለን፣ለቃሉ ክብደት በመስጠት ከነገሮች በፊት ቅድሚያ እንሰጣለን።ያን የማናደርግ ሲሆን ቃሉን ተራ ንግግር እናደርግና ጥፋት ውስጥ እንገባለን።
በሁኔታዎች ውስጥ የምናገኛቸው አስደንጋጭ ነገሮች ሊያስፈራሩን ይችላሉ፣ ሰው አልቁዋቁዋመውም የሚለውን ይፈራልና፡፡ አንድ የምናጣው ነገር ቢኖር ስለ እርሱ ፍርሀት ይገባናል፡፡በስጋ ከመደንገጥ የሚያልፍ ግን የፍርሀት መንፈስ የሚባል ከክፉ መንፈስ የሚወጣና ልብን መያዝ የሚችል ሃይል አለ፡፡የፍርሀት መንፈስ ሲይዝ መላ አካልን ይቆጣጠራል፡፡የፍርሀት መንፈስ ሲቆጣጠር ልብ ይቀልጣል፣ድፍረት ይጠፋል፣ መጸለይም ይከብዳል፡፡ አይንን ወደ ፈጣሪ ማንሳት አይቻልም፡፡
ክፉ መንፈስ የሰውን መንፈስ በፍርሃት በኩል ከተቆጣጠረ ሰው ከምሪት ውጪ ይሆናል፡፡ የፍርሀት መንፈስ ከእግዚአብሄር የተሞላነውን ሀይል ያስጥላል፡፡የፍርሀት መንፈስ ሲቆጣጠረን መውጫ መንገድ መፈለግ ይሳነናል፡፡ እምነታችን ስለሚነጠቅ ሁሉ ነገራችን ታስሮ መንቀሳቀስ አንችልም፡፡መጸለይ የሚያዳግትበት ወቅት አለ፣እርሱም በፍርሀት መንፈስ ልባችን ሲዝል ነው፡፡
የእግዚአብሄር ፍርሀት
እግዚአብሄርን መፍራት ፍጹም በጎነት አለው፡፡ ስንፈራው ከእርሱ ምህረትና ሞገስ እንቀበላለን፡፡በመከራ ውስጥ እንኩዋን ቢሆን እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰው ልቡ በእምነት ሀይል ይሞላል እንጂ በድካም አይዝልም፡፡ለምሳሌ በከባድ ጭንቅና ፍርድ ውስጥ የነበረን ወንበዴ የጽድቅ ምንጭ እንመልከት፡-
ሉቃ23:39-43 ”ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ፡-አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ፡-አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለአደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም፡-ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፡-እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።”
እግዚአብሄርን መፍራት በጠላት ላይ ጉልበትን ያመጣል፣ አሸናፊን ያሸንፋል፡፡በይበልጥ ደግሞ እግዚአብሄርን የምንፈራው አባታችን ስለሆነ ክብር ስለሚገባውም ነው፡፡ ባለጌ ልጆች ግን ያን አያደርጉም፡-
ሚል.1:6 ”እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
ሌላው እግዚአብሄርን የምንፈራው እርሱ ብቻ ፈጣሪ በመሆኑ ከርሱ በቀር አዛዥም ገዢም እንደሌለ በማስተዋል ነው፡፡ጠላት የሚያስፈራራው ነጻነትን ከላያችን ሊነጥቅ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የምንፈራው ግን በጠላት ላይ ድልን ለመጨበጥ ነው፡፡ጠላት በአምላኩ ላይ ደፋር ስለሆነ እግዚአብሄርን ይጠላል፡፡ ሰው ግን ትሁት ሲሆን አምላኩን ይፈራል፣ ያከብራል፡፡ይህ ደግሞ መለኮታዊ ጥበብ ነው፡፡
ዘዳ.10:12-13 ”እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው?”
በሰይጣን መንፈስ የሚመሩ በጽድቅ ላይ ይደፍራሉ፡፡ ክፋትን ሲያደርጉ አይፈሩም፣ እግዚአብሄርንም አያከብሩም፡፡እግዚአብሄርን የሚፈሩ ግን በጽድቅና በስርአት ይኖራሉ፡፡
ዘፍ.6:5-8 ”እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደበዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፡-የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።”
ተላላፊዎች አመጸኞችና ሀጠያተኞች የሚበዙት ደፋሮች ሲበዙ ነው፡፡በነርሱም ምክኒያት ምድር በረከት ታጣለች።እሾህና አሜኬላ ይበዛል፣ሃዘንም አይጠፋም። ትህትና ግን ያን ያርቃል፣ ምህረት ከእግዚአብሄር ዘንድ ያመጣል፡፡እግዚአብሄር ያየኛል የሚል እግዚአብሄርን የሚፈራ ብቻ ነው፡፡ የማይፈራና የማያፍር አእምሮው በሰይጣን የተያዘ ሰው ነው፡፡ክፋትን ለመስራት ድፍረት ማብዛት በክፉ መንፈስ የመያዝ ምልክትም ነው፡፡ምን ጊዜም ድፍረት ተጉዞ ተጉዞ ጥልቅ ጸጸት ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡ ይህን ጸጸት የሚከተለው ንሰሃ ሳይሆን ድንጋጤ መጨረሻም መውጫም የሌለው ሰላም ማጣት ነው፡፡
በአለም ያለ እንዲህ ያለ ድፍረት መውጫ ስለሌለው ብዙ ሰው መጨረሻው አያምርም፡፡ያስተዋለ ካለ ቆም ብሎ ማሰብ ይሄኔ ነው።
ዘሌ.26:14-17 “ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።“