የሰማይ እውቀት የሰማይ የሆነው፣ የመለኮት የሆነው፣ መንፈሳዊ የሆነው ሲሆን ከምድራዊ እውቀት፣ ምጥቀት፣ ፍልስፍናም ይባል ጥልቅ የአጋንንት እውቀት፣ ከነዚህ በላይ የሚልቅ፣ የተለየ፣ የተቀደሰ፣ ሃይል ያለውና አሸናፊ እውቀት የሆነ እርሱ የሰማይ እውቀት ስለሆነ ለእግዚአብሄር መንግስት ማብቃት የሚችልና ከእግዚአብሄር ምንጭ የሚቀዳ መሆኑ የታመነ ነው። የሰማይ እውቀት በመሰረታዊነት በቃሉ ይገለጻል፦
ዳን.10:9-11 ”የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ። እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ። እርሱም፦ እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ።”
የቃሉ ትምህርት በመንፈስ ድምጽ ሲሆን የሰዎችን አሳብ፣ ውሳኔና ባህሪ አንጣሪ መንጣሪ እንደሆነ ቅዱሱ መጽሃፍ ያሳያል፤ የተገለጠው ቃል የመነቸከ ነፍሳችንን ጌታ በደሙ እንደሚያነጻ ያመለክታል። በእርግጥ ጌታ በክቡር ደሙ አጥቦ በሞገስ ያቆማል፤ እርሱ በአሰራሩ በነፍስ እርቃናችንን እንዳንሆን የጽድቅ ልብስ አልብሶናል፤ ነፍሳችን የክብርና የጽድቅ ልብስ በስሙ ጥምቀት ተጎናጽፋለች።
ደግሞ እርሱን የሚገልጠው ቃል ሲናገር እረኛ ነው ይለኛል፣ የነፍሴ ጠባቂዬ ስለሆነ፤ በር ነው ብሎኛልም ወደ ደህንነትና ወደ ዘላለሙ ህይወት በእርሱ ስለምገባ፤ ነፍሴንም ባምላኬ ፊት ነጻ ያወጣ ደግሞ እርሱ ነው። ንጉስ ነው ያለውም በኃጢያቴ ላይ ነግሶበታልና ነው፤ ጠላቶቼን ከእግሩ በታች የጣለ ጌታ ነው፤ እኔም በዚህ የማዳኑ ባህሪ አውቄዋለሁ። ሩህሩሁ እረኛ በጎቹን ሳይታክት ይጠብቃል። እንጀራ ነውና የቆረሰውን ስጋውን ያፈሰሰውን ደሙንም ለዘላለም ህይወት ይመግባል።
1ጴጥ.2:24-25 ”ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።”
የዚህ የሰማይ እውቀት ባይበራልን ኖሮ ስለኃጢአት ምንነት ከየት አምጥተን አወቅን? በኃጢያት መሞትና ስለሃጢያት መሞት የሚባለውስ? ለጽድቅ መኖር የሚባለውን ሰማያዊ እውቀትም ቢሆን… በስጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ መሸከሙ፣ በመገረፉ ቁስል መፈወሳችን፣ እርሱ የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ መሆኑና ወደእርሱ እንደመለሰን ከላይ በመጣ እውቀት ምክኒያት ነው የተረዳነው።
የትንሳኤውን ሃይል ማወቅ
የትንሳኤውን ሃይል ማወቅ ማለት ኢየሱስን ማወቅና በእርሱ ውስጥ ያለውን የሚሰራ ሃይል ማወቅ ማለት ነው። የሚሰጠንን አዲስ ህይወት የምንለማመደው በሞታችን ሳይሆን በህይወታችን ሳለን የእርሱን የመንፈስ ጉብኝት በመለማመድ ነው ማለት ነው። ከጌታ የምንቀበለው ህይወት የሃይል ህይወት ሲሆን በአጋንንት ላይ የሚያሰለጥን ነው። ከዚህ በተጨማሪ የትንሳኤው እውቀት የሚገልጥልን ነገር ቀጥሎ እንመልከት፦
. የትንሳኤው ሃይል ተገልጦ የሚሰራ ሃይል በመሆኑ በትንሳኤው ምክኒያት በአማኝ ህይወት የሚታይ ብዙ ለውጥ አለ።
· የትንሳኤው ሃይል ጽድቅን የሚፈጥር ሃይል በመሆኑ አማኞች በእግዚአብሄር ፊት ተቀባይነትና ሞገስ አግኝተው በነጻነት
እንዲመላለሱ ትምክህት ይሆናል።
· የትንሳኤው ሃይል ህይወት የሚሰጥ ሃይል በመሆኑ አማኝን ከሞት አውጥቶ በህያውነት የሚያመላልስ ነው።
· የትንሳኤው ሃይል የመጽናትና የመጽናናት ሃይል ስለሆነ በአማኝ ህይወት በሁኔታዎች ሁሉ መጽናትን ይፈጥራል።
በሮሜ.6 ውስጥ በትንሳኤው ሃይል ከመጎብኘታችን አስቀድሞ የምናልፍበትን መንገድ እንመለከታለን፦ ያም ህይወት ከሆነው
ጌታ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመንፈስም በአካልም ህብረት ለማድረግና ከእርሱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በህያው ስሙ መጠመቃችንን የሚያሳይ ነው። ስሙን እየጠራን የተጠመቅንም ያለአንዳች ልዩነት ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን ቃሉ አስረግጦ ይናገራል።
ተጠምቀን እሱ ስለእኛ ሃጢያት መሞቱን በራሳችን ላይ ልናሳትም፣ እኛ በራሳችን ሃጥያት የሞትንበትን ፍርድ በሰራው ስራ ልናሽርና ልናስቀብር ከእርሱ ጋር ተባበርን። ተቀብረን እንዳንቀር ለመነሳትም የትንሳኤው ሃይል ተካፋይ ሆነናል፤ ይህም የተቻለው ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ስለተቀበርን ነው። የትንሳኤው ቃል ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር በመተባበር ብቻ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ ጋር መተባበር እንደሚቻል ያመለክታል።
የክርስቶስን መከራ መካፈል ኢየሱስን ከማወቅ የሚመጣ ጸጋ ነው። ክርስቶስን በእውነት በመከተልና በእርሱ በመኖር የሚመጣ መታዘዝ ውጤትም ነው። በክርስቶስ የሆነ መከራ በእግዚአብሄር ልጆች ዘንድ ያለ መሆኑን በማስተዋል ሊያምኑ የሚገባ ነው። የእግዚአብሄር ልጆች በክርስቶስ በረከት መኖር ስናስብ፣ በምህረቱ ተከልሎ ከመኖር ጎን ስለጽድቅ የሚሆን መከራን መካፈል የሚጠይቅ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
ሮሜ.8:17-18 ”ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።”
ሃዋርያው በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ በማለቱ በክርስቶስ መሆን ማለት በህይወቱ መኖር ብቻ ሳይሆን በሞቱም መምሰል እንደሚጨምር ያሳያል። በዚህም ምክኒያት ሃዋርያው በወንጌል ምክኒያት መስዋእትን እስከመቀበል ደርሶአል።
የክብሩ እውቀት ብርሀን ፥ የከበረው ወንጌል መገለጥ
2ቆሮ.4:2-6 ”ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።”
ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው ይላል፦ ምክኒያቱም ሰዎች ለዚህ ለከበረ ወንጌል ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ በላያቸው ላይ ጥፋት ማምጣታቸው /ለጥፋት ተላልፈው መሰጠታቸው ቢሆንም የዚህ ጥፋት ተጠያቂው ሰባኪው ወይም ወንጌሉ ራሱ ሳይሆን በራሳቸው ላይ ፍርድን የሳቡት እራሳቸው ባለቤቶቹ እንደሆኑ ሲያመለክት ነው። በዚህ የሚጠፉ ብቻ ወንጌሉን ሰምተው ባለመቀበል በቸልተኝነት የሚጠፉ መሆናቸውን እናያለን።
የማያምኑ ሰዎች በሚፈጠርባቸው እውርነት፣ ቸልተኝነትም ይሁን ክህደት የወንጌሉ ተቀባይነት እንደማይጓደልና እንደማይደክም ግልጽ ነው። እንዲሁም የወንጌሉ እውቀት ብሩህና የማያወላውል መሆንንም አይገድብም።
በኢየሱስ የማያምን ሁሉ ጠፍቶአል፣ ከኢየሱስ ውጪ ሞት ስለሆነ፤ የማያምነውን እግዚአብሄር አያውቀውም፣ የሚያገለግለው ልጁ ሊሆን አይችልም፣ እንደ ልጅ ምህረትን ከእግዚአብሄር አይቀበልም።
የጠፋው ልጅ ከእግዚአብሄርና ከእግዚአብሄር ማህበር አንዴ ጠፍቶአል፤ እውነት ከሆነው እግዚአብሄር ስላፈነገጠ ለእውነት መቆም አይችልም፣ መንፈሱ ስለሌለው እውነትን አያስተውልም፣ ሰማያዊ ምስጢራትን አይረዳም።
2ቆሮ.10:5-6 ”የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፤ መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።”
የሰዎች የፍልስፍና አስተሳሰብ ነጻ በሚያወጣው የእግዚአብሔር እውቀት ላይ ተነስቶ ቢቃወምም በቃሉ ስብከት ሃይል የሚሻር ነበር፤ ለሚታዘዙ ሰዎች ደግሞ የሰማይ እውቀት አእምሮን የመቆጣጠር ችሎታ ስላለው ማንንም ወደእርሱ የመጣን ሰው ለክርስቶስ እንዲታዘዝ በማድረግ ምህረቱን እንዲቀበል ያደርጋል።
ከሰማይ እውቀት መጉደል ግን ተስፋ የተገባላቸው አይሁድን ሳይቀር አጥፍቶአል። ህጉን እናውቃለን የሚሉ አስተማሪዎች የእግዚአብሄር ቃልኪዳን የሚፈጸምበትን ዘመን ማስተዋል ስላልቻሉ ዋጋ ከፍለዋል፤ ህጉን ሳይኖሩበት ማነብነብ ላይ ብቻ በማተኮራቸው የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል ኪዳን ቸል እንዲሉ ሆነዋል፡፡ በተወሰነው ዘመን ሲመጣና ተስፋው ሲፈጸም የቃሉን ክንዋኔ ልብ ስላላሉ ወደ ሁዋላ ቀሩ፣ የሚበዙትም ከፈቃዱ ጋር ተጋጩ፣ ሌሎቹም እንደተመኙት ሳያገኙ ቀሩ፡፡
በዮሐ.6 ውስጥ ያለው ታሪክ እንደሚያሳየን ከሆነ አይሁድ ጌታ ኢየሱስን በቃሉ እንዳወቁት ሆነው ሳይሆን ከርሱ እለታዊ ጥቅምን ፈልገው ይከተሉት ነበር፡፡ ዘላለማዊ ጌታ እቅዱ የሰውን መልካም ፍጻሜ ዘላለማዊ ማድረግ ሆኖ ሳለ በተከታዮቹ እውቀት ማነስና እምነት ማጣት ምክኒያት የዚያን ሰማያዊ ፈቃድ እንዳይገልጥላቸው ሆኖአል፡፡ እነዚህ አይሁዶች ለእለታዊ ፍላጎታቸው የሚሆን አንድ ነገር ከርሱ እናገኝ ይሆናል በሚል በሚሄድበት ሲከተሉት በታሪካቸው ውስጥ የምናየው ነው፡፡ በዚያ ወቅት ጌታ ኢየሱስ ተነስቶ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፣ ተከተሉትም፤ ደግሞ ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። አይሁድ መከተላቸውን አላቆሙም፣ እንዲሁ በፍለጋ ሲከታተሉት በመሀል ደክመው አየና አዘነላቸው፤ የፈለጉትን ምግብም ሊመግባቸው ደቀመዛሙርትን አዘዘ፡፡
በዮሐ.6:11-15 ላይ ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ፡- ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።
በዚህ ስፍራ እንደምንመለከተው አይሁድ ያተኮሩት የጌታ ፈቃድና ቃሉ ላይ ሳይሆን ከእጁ ያገኙት እርካታ ላይ ብቻ ነበርና ባደረገው ነገር ረክተው ድምዳሜ ላይ ደረሱ፣ በልተው ስለጠገቡ ብቻ ይመጣል የተባለው ነቢይ እርሱ ነው አሉ፡፡ በመለኮት እቅድ መሰረት ግን ከነብይ የሚበልጠው መሲህ ምድር ወርዶአል፡፡
የአይሁድ ምኞትም ደጋግሞ ይገለጥ ያዘ፣ ክትትላቸው የማያቁዋርጥ ሆኖ እጁን ፍለጋ መቅበዝበዝ አበዙ፡፡ ቀጥለው ቀጥለው በምድርም በባህሩም ላይ ተጉዋዙ፡፡ ስለዚህ፡-
”በባሕር ማዶም ሲያገኙት፡- መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” ሲል ሞግቶአቸዋል (ዮሐ.6:25-27)።
ከሰማይ እውቀት መጉደል የልብ አይንን ስለሚከልል መንፈሳዊ ነገርን እንዳናይ ይጋርዳል፡፡ መንፈሳዊ ነገርን ካላየን ደግሞ ስጋዊ ነገር ብቻ ላይ እናተኩራለን ማለት ነው፤ ስጋዊ ነገር ላይ ማትኮር፣ ለርሱ/ለስጋ ያለንን ግምት አጉልቶ መንፈሳዊ ነገርን ደግሞ ዝቅ ስለሚያደርግ በእግዚአብሄር አሳብ ላይ ተቃርኖ ይፈጥራል፡፡ ይውል ያድርናም የአምላክን ፈቃድ ፈጽሞ ይጻረራል፣ ይቃወማል፣ ሲብስ ደግሞ ይክዳል፡፡ ቀላል የማይባል የመንፈሳዊ ህይወት ጉዳት እንዲህ ባለ ሂደት ውሰጥ ይጉዋዝና በመገባደጃው ስብራት ላይ ያደርሳል፡፡ የልቦና አይናቸው አጥርቶ የማዩዩቱ አይሁድ ለእግዚአብሄር አሳብ እንቅፋት ሆነው ከክርስቶስ ጋር መተዋወቅ ተስኖአቸው ነበር፡፡ በዮሐ.6:28-29 ውስጥ የሚሉትን ሳያውቁ የተናገሩት እንዲህ ይላል፡-
”እንግዲህ፡- የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።”
በተስፋ ቃልና በህጉ መሃል በነበረው የትርጉዋሜ ክፍተት ህዝቡ ከፍ ያለ ስህተት ውስጥ ወድቆ ነበር፤ ህጉ የተስፋው ቃል ፍጻሜ እስኪያገኝ ሞግዚት መሆኑ ለብዙዎች ስለተሰወረ የጌታን እውቀት በማስተዋል ሊቀበሉት እንዴት እንዳዳገታቸው የሚታይ ነው። ከጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እርገት በሁዋላ የዚህ እውቀት ክፍተት ጎልቶ መታየቱ ቀጥሎ ነበር፤ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የሚያብራራው እውቀቱ በአማኞች ህይወት መገለጡ እንዲቀጥል እየጣረ እንደነበር አመልካች ነው፦
ገላ.3:15-20 ”ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።”
በማህበረሰብ ውስጥ ያለው ልምድ እንኩዋን ስለቃል ኪዳን ጽናት ትልቅ ምስክር አለው፤ እናም ይህ ምድራዊ እውቀት ጥብቅ መሆኑን እያመለከተን ካለ የሰማዩ እውቀት እንዴት የሚልቅ ነገር አይሰጥ? የሚበልጠው ነገር ከእግዚአብሄር የሚሰጠን ስጦታ እንደመሆኑ መጠን እግዚአብሄር ሊጠበቅና ሊጠየቅ ተገቢ ነው።
ያ የተስፋ ቃል ለአብረሃም ለአባታቸው እንደተነገረ አይሁድ ቢያውቁም እግዚአብሄር ለዘርህ ሲል ምን ማለቱ እንደነበር ሊያስተውሉ አይችሉም ነበር፣ እውቀቱ እስኪመጣ ድረስ በህግ የማይገለጥ እስከሆነ ድረስም ሊጠበቅ የግድ ነበረ።
ህዝቡ ግራ የገባው ስለነበረ የጠይቃል፦
ዮሐ.6:30-36 ”እንግዲህ፦ እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት። ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። ስለዚህ፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።”
ከሰማይ እንጀራ ጋር የሚያገናኝ የሰማይ እውቀት በምድር ላይ ይገለጥ፣ ይስፋ፣ ይውረድ። ያለበለዚያ ጥያቄያችን በሙሉ ከምድራዊ ጥያቄ ጋር ይያያዝና እንደ እስራኤል አስቸጋሪ ነገር ይሆናል፤ የሰማይ እውቀትም ሳያገኘን ያልፈናል።