በእግዚአብሄር ከፍ ላለ ህይወት ተጠርተው ያሉ ወገኖች የእግዚአብሄርን ፈቃድ ባለማስተዋልና ባለመከተላቸው ምክኒያት የሰማይ እውቀት ጎደሎ ሲሆንባቸው ኖሮአል። ወደ እግዚአብሄር የተጠጋ የእግዚአብሄርን መንገድ ግን ልብ የማይል ሁሉ ከእውቀት በመጉደሉ በብዙ ይጎዳል። አንድ የእስራኤል መምህር የሆነ ቆርኖሌዎስ የተባለ ሰው በጌታ ፊት ቀርቦ ሲነጋገር ያን ችግር አጉልቶ ሲያሳይ ነበር፡፡ ይህ ሰው በአዋቂዎች ቦታ የተቀመጠ ሌሎችንም በእግዚአብሄር ቃል የሚመራ በመሆኑ ብዙ የሚጠበቅበት ሆኖ ሳለ ከሰማያዊ እውቀት ጎድሎ ይታይ ነበር፦
ዮሐ.3:1-13 ”ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። ኒቆዲሞስ መልሶ፦ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።”
እስራኤል ከሰማይ መና ቢበላም መንፈሳዊው መና ስላልተገለጠለት በመንፈሳዊ እውቀት እጥረት ደርቆ ነበር። የሰማይ እውቀት ግን መለኮታዊ መገለጥ ያለበት የእግዚአብሄር እውቀት ነው። ቃሉን እንደፈሪሳውያን በመድገም የሚፈጠር መለኮታዊ እውቀት የለም። የሰማይ እውቀት የሚመጣው ጌታ ቃሉን ሲልክ ነው፣ እርሱም ለሃዋርያቱ እንደገለጠው ያለ እውቀት ነው፦
ማቴ.16:13-20 ”ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።”
የሰማይ እውቀት እምነት የሚሰጥ፣ በእግዚአብሄር ላይ ታምነን እንድንኖር የሚያደርግ፣ ህይወታችንን ለቅዱሱ ፈጣሪ ለይተን እንድንኖር የሚያስችል ነው። የሰማይ እውቀት ከምድራዊ እውቀት ፈጽሞ ይለያል፤ ከመነሻው እውቀቱ ሰማያዊውን አለም የሚያስተዋውቅና በሰማያዊ ስፍራ የሚሆነውን ነገር የሚገልጽ ነው። እውቀቱ ከመለኮት የሚመነጭ እውቀት ነው።
በሰማይ እውቀት ጉድለት ሰበብ የተሰጣቸውን የክብር ስፍራ አክብረው ያልጠበቁ ህዝቦች ግን ብዙ ጉዳት አስተናግደዋል፦
ነቢዩ ኢሳያስ በኢሳ.6:8-12 ላይ ሲናገር፦
”የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። እርሱም፦ ሂድ፥ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ። እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው።” ይላል።
በነቢዩ ኢሳያስ ዘመን ላይ ሆኖ እግዚአብሄር እስራኤል ሊደርስበት ያለውን መከራ አስቀድሞ ተናግሮአል። ለምን ያ ሊሆንባቸው ቻለ? በአጭሩ የሰማይ እውቀት ጎድሎአቸው ስለነበር ነው።
ህዝቡ ማየት ይገባቸው የነበረውን በተከፈተ ዓይናቸው እንዳያዩ፥ መስማት የነበረባቸውን መለኮታዊ ድምጽ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ አይተውና ሰምተውም በልባቸው እንዳያስተውሉ፥ በማስተዋላቸው ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የተዘጋው ልባቸው ዝግ ሆኖና ባለማስተዋል ደንድኖ ጆሮአቸውም ደንቁሮና ዓይናቸው ተጨፍኖ ነበር። ነቢዩ ይህ ውድቀት እስከምን ድረስ እንደሚያዋርዳቸው እግዚአብሄርን ሲጠይቅ፦ የነርሱ ድንቁርናና እውርነት በሚፈጥረው ቸልተኝነት የእስራኤል ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው በእግዚአብሄር ቁጣ እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም የሚኖርባቸው ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ነዋሪ ሳይኖርባት በብቸኝነት ፈጽሞ ባድማ ሆናና የተፈታች ሆና እስክትቀር ድረስ እንደሆነ ነገረው፤ ያም ቃል በጊዜው ደርሶ እግዚአብሄር ልክ እንዳለው በነቢዩ ኤርሚያስ ዘመን ተፈጸመ።
ንጉስ ሰሎሞን በምሳ.2:10-15 ላይ አንድ ምክር ይሰጣል፦
”ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤ እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተው፥ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው”ይላል።
ንጉሱ ጥፋት እንዳያገኝህ እውቀት ይኑርህ፣ እርሱም ጥንቃቄና ማስተዋል ይሰጥሃል፤ ከክፉ መንገድ አንተን እንዲያድን፣ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎች እንዲሰውርህ፣ በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና ከሚተው ይጋርድህ ዘንድ ያደርጋል። ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥ መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ሰዎች አግኝተው እንዳይጥሉህ ያደርግሃል ይላል።
በመጨረሻው ዘመን የተገለጠ ዘላለማዊ እውቀት
ስለዘላለማዊነት ከእግዚአብሄር ቃል ብዙ እንማራለን፡፡ ዘላለማዊነት በዘለአለም አምላክ የሚፈጠር ምድራዊነት የሌለበት መንፈሳዊ ጊዜ ነው፡፡ ጊዜያዊው የዚህ አለም ኑሮ በዘላለማዊነት ውስጥ አይካተተም፤ እንዲሁም አለም ላይ ባለው በጊዜ በተገደበ ሁኔታ ዘላለም አይገለጥም። ዘላለማዊ እውቀት ከዘላለም አምላክ የሚመነጭ ስልሆነ ሰዎች የጊዜውን ሁኔታ ከዘላለማዊው የእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር እንዳያቀላቅሉት መጠንቀቅ ይገባቸዋል።
ዕብ.1:1-2 ”ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።”
እግዚአብሄር ያሰበውን ዘላለማዊ አሳብ ካስተዋልንና ካወቅን እግዚአብሄር በነቢያቱ የተናገራቸውን ትንቢቶች ልብ እንላለን፣ በሆኑም ጊዜ ምስክር ሆነን ለመቆም እንበቃለን።
ሃዋርያው ጳውሎስ ስለ አንድ ታላቅ እውቀት በፊል3:7-11 ላይ ሲናገር ነበር፦
”ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ።” ይላል።
ካወቅኩ አይቀር ትልቅ እውቀት የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን እንዳውቀው እሻለሁ አለ፤ ይህ ቀላል ያልሆነ የጳውሎስ የልብ ልመና ለእርሱ መዳንና መጽናት እጅግ አስፈላጊ ነበር። ከአምላኩ ጋር አንድ የአብሮነት ሰላም ለመፍጠር የግድ ራሱን በዚህ እውቀት መቃኘትና ማስተካከል አለበት። ኢየሱስን ማወቅ ታሪካዊ ክስተትን ከማወቅ ጋር አንድ አይደለም፣ ወይም የሰዎችን ነገር እንደማውቅ የቀለለ አይደለም። ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ትምህርቶች ከማወቅ ጋር የሚያያዝ ነው፤ የህይወት ምሳሌነቱን ከማወቅ ጋር የሚገናኝ ነው፤ ከምንም በላይ ማን መሆኑን ከማወቅ ጋር የሚያያዝ ነው።
በእውቀት ደረጃ ለራሳችን አወቅን ልንል የሚያስደፍረን ነገር መኖር አለበት፣ ሌላውንም ነገር በዚያ ልክ ስለምናይ፣ ለምሳሌ፦
– በአለም ሁኔታና በሰው ደረጃ ሰዎችን እናውቃቸዋለን የምንለው ማንነታቸውን ስለለየን ነው፤ ሁኔታቸውን ስላወቅን ነው፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲስተያዩ የራሳቸው መለያ ስላላቸውና ያን ስለምናውቅ ነው፤ እነርሱን ከሌላው ሰው ጋር አወዳድረን የነርሱነታቸውን/የራሳቸውን መገለጫ ስለሚላበሱና መለኪያውን ስለሚሞሉ ነው።
እንግዲህ ይህን እውቀት ወደ ጌታ እውቀት ስናመጣው እርሱን በመንፈሳዊው አለም አንጻር መመልከት ስለሚገባን እውቀታችን እርሱ ማን መሆኑ ላይ ማተኮር እንዳለበት መረዳት ይገባናል፤ እርሱ ራሱ ለሳምራዊቷ ሴት ሲናገር ”ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት።” (ዮሐ.4:10)
በተለይ ደግሞ በሰው ደረጃ ሲታይ (በመሃከላቸው ከተገኘው አይሁድ አንጻርም ሲታይ) የሰው መልክ ይኑረው እንጂ ከአዳም የተለይ የእግዚአብሄር ልጅ የሆነ ነው። ከማርያም ቢወለድም የአዳም ልጅ ሳይሆን የእግዚአብሄር ልጅ በመሆኑ የተለየ ነው። መወለዱ አማኑእል (እግዚአብሄር በሰዎች መካከል መገኘቱን) እና ትንቢቱ መፈጸሙን እንደሚያመለክት ሊታመን የተገባው ነው።
– እንዲሁም የሆነ ሰው እናውቃለን የምንለው የርሱን የተለመደ ድርጊት ጠንቅቀን ስላወቅን ነው፤ የሚሰራ ባለሙያ ከስራው የሚለይበት የራሱ ነገር አለውና።
የጌታ ኢየሱስም ነገር እንዲሁ ነው፤ የእርሱ ስራ በእስራኤል ምድር በተገለጠ ጊዜ ያዩትን አምነው ወደ እርሱ የመጡ ክርስቶስ መሆኑን አስተውለው ነበር። ከነርሱ መሃል ይገኝ የነበረ አንድ የመቶ አለቃ በእምነቱ የተመሰከረለት ነበርና እንዲህ ሲል ተናገረ፦
”ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። ኢየሱስም፡- እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ፡- ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፡- ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፡- ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፡- ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፡- እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም ለመቶ አለቃ፡- ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ።” (ማቴ.8:5-13)
ይህ ቃል ኪዳን ቀላል ነገር አይደለም፦ ከእምነት አባቶች ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር የሚያስቀምጥ እውቀት የነበረው መቶ አለቃ በጌታ ላይ ጥብቅ እምነትን ፈጥሮለታልና።
– አንድን ሰው እናውቀዋለን የምንለው ከዚህ ቀደም ከርሱ ጋር ተገናኝተንና ተነጋግረን ስለምናውቅ ነው፣ በዚህ አሳቡን ስለምናውቅ፣ አመለካከቱን ስለምንረዳና የውስጥ ምኞቱን ስላካፈለን ነው። ከዚህ ባለፈ ከግለሰቡ ጋር የተነጋገርንበት የጋራ ጉዳይ ስላለን ነው ።
ሃዋርያት ከጌታ ጋር በየስፍራው ተጉዘዋል፣ ከርሱ ጋር ወጥተዋል ገብተዋልም። ከእርሱ ጋር ተነጋግረዋል፣ ስራውን አይተዋል፣ ቃሉን አድምጠዋል፤ አሳቡን፣ ፈቃዱንና ስራውን አስተውለዋል። ስለዚህ ስለእርሱ የሚናገሩት ብዙ ነገር አላቸው ማለት ነው፦
”ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉእርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ።እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን።በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” (ሐዋ.10:34-43)
– አንድን ሰው የምናውቀው በቤቱ ተገኝተን ስለነበረ ወይም ከቤተሰቡ ጋር ጊዜ ስለምናሳልፍ ሊሆን ይችላል ። ከጌታ ኢየሱስ ጋር ያሳለፉ ከእርሱ መለየት አልቻሉም። ማንነቱን አውቀው ነበርና። ጌታ ኢየሱስ በተጠጉት ቁጥር ያውቁታል፣ ይወዱታል፣ ከዚያ በሁዋላ ከእርሱ ይርቁ ዘንድ አይችሉም፦ በመንፈሱ ተጥለቅልቀዋልና፣ በቃሉ ፍቅር ተይዘዋልና፣ በምህረቱ ታቅፈዋልና።
”… ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።ደግሞ፦ ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፦ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።ስምዖን ጴጥሮስ፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።” (ዮሐ.6:63-69)
– አንድን ሰው እናውቀዋለን ያልነው በሕይወታችን ውስጥ ተጽእኖ ስላለው ከእነርሱም ጋር በየእለቱ ስለምንኖር ነው፤ አብረን ስንኖር በተለያየ ማህበራዊ ግንኙነት በህብረት ስለምንኖር ነው።
የእግዚአብሄር ልጆች እድል ፈንታቸው አምላካቸው ስለሆነ በማንኛውም ጊዜ አብሮነቱ ከነርሱ ሊለይ አይገባም። በማጣትም በማግኘትም እርሱ ሲኖር፣ በደስታም ሆነ በሃዘን የእርሱ አብሮነት ካልተለየ ነገሮች እንደአመጣጣቸው አይሆኑም። ምህረቱ የጋሉ ተወርዋሪ ፍላጻዎችን ያበርዳል፣ ስለቶችን ያዶሎድማል፣ ቀስቶችን ይሰብራል፣ በአውሎውና በወጀቡ በእሳቱም ውስጥ በአብሮነት ያልፋል።
”ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ። ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም ለዘላለም ታጠናኛለች፥ ተግሣጽህም ታስተምረኛለች።” (መዝ.18:31-35)