ከሰማይ እውቀት መጉደል[1…]

የእውነት እውቀት

ከሰማያዊ እውቀት መጉደል የሚያመጣውን መምታታት፣ የሚፈጥረውን የማስተዋል እጦት፣ የሚጥለውን የጉዳት ጠባሳ፣ የሚያስቀረውን መለኮታዊ ጸጋ፣ ተመትቶ ማንከስ ወይም ተቆርጦ መንገድ ላይ መቅረትን ለመገንዘብ በግልጽ ከአይሁድ የህይወት ተሞክሮ በማየት መማር እንችላለን፡፡ ሰማያዊ እውቀት ምንድነው? የእውቀቱ መታጣት እንዴት አስከፊ ቢሆን ነው የዚህን ያህል ጉድለትና ጥፋት ያሚያስከትለው? የምንል ልንኖር እንችላለን፡፡ ቅድሚያ በዘኊ.24:15-16 ላይ የሚገኘው በለአም የተባለ ሰው ስለ መለኮታዊ እውቀት ያስተዋለውን ነገር እንመለከታለን፡-
”የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።…”
ከላይ ባለው ጥቅስ መሰረት ሰማያዊ እውቀት መለኮታዊ እውቀት/የልዑል እውቀት እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ እውቀት የሚባል የሰው ልጅ ነፍስ ልታስተውለው የተገባ ይህ መለኮታዊ እውቀት አስፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ነፍሳችን አምላኩዋን ታውቅ ዘንድ ከፈጠራት ከርሱ የተላለፈ ትእዛዝ በመሆኑ እርሱን ባለማወቅዋ የሚከተላት ጥፋትና እጦት እስከ ሞት የሚያደርሳት ነው፡፡ በለአም ግን የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማ የልዑልን እውቀት እንዳወቀ ዓይኖቹም ሲከፈቱለት ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ እንዳየ ይመሰክራል፡፡ ነቢዩም በኢሳ.43:10 የእግዚአብሄርን ድምጽ እንዲህ ያስተላልፋል፡-
”ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።”
ሰው ላለመፍራት ዋስትናው ምንድነው? ቃሉ በግልጽ እንደሚለን እርሱን ማወቅ ነው፤ እውቀቱም ምድራዊ ሳይሆን መለኮታዊ ነው፡፡ ነፍስን ከዘላለም ህይወት ያጎደላት ያለማስተዋልዋና ከአምላክዋ የመለየትዋ ችግር ከሆነ እርሱን በማወቅ መንቃትና ከእርሱ ጋር ዳግም መገናኘት በሆነላት ወቅት መዳንን ትጎናጸፋለች ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄር ለእስራኤላውያን አትፍሩ እኔ አምላካችሁ ነኝ ሲል ያጽናናቸዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በእግዚአብሄር ተመርጠው ሳለ በሆነ ወቅት ከእርሱ ኮብልለው በባእድ አማልክት ስር ሲወድቁና ለጠላቶቻቸው ተላልፈው ሲሰጡ እጅግ ተስፋ ያጡና የተጠቁ ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ እግዚአብሄርም ይሄን አይቶ እኔን እወቁና ወደ እኔ ተመለሱ እንጂ የሚያስፈራችሁ አንዳች ጠላት ሊኖር አይችልም የሚል ዋስትና ሲሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ እኛም ብንሆን ከሰማይ እውቀት ጎድለን ያለተስፋና ያለአምላክ ሆነን በባእድ አምላክ የጨለማ ጥላ ድንጉጥ ከመሆን እርሱን በማወቅና በማመን ዋስትናውን ማግኘት አለብን፡፡
የእስራእል መዳን የተቁዋጠረበት እውቀት
እግዚአብሄር ድምጹን ልኮ ህዝቡን ባስተማራቸው ዘመን ሁሉ እርሱን የሚያውቁበትን መንገድ ገልጦላቸው ነበር፡፡ በየዘመናቱ በተነሱት ትውልዶች ውስጥ ግን መለኮታዊውን ትምህርት የሚበርዙ አሳሳቾች መነሳታቸው ስላልቀረ እግዚአብሄር ከነዚያ አሳቾች ህዝቡን ነጻ ያወጣ ዘንድ ነቢያትን አስነስቶ ሰማያዊውን እውቀት ደጋግሞ ልኮአል፡፡ በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ተነስቶ መለኮታዊውን እውቀት ለህዝቡ ያውጅ ነበር። እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ… ሲልም ተናግሮአል፡፡(ኢሳ.1:1) ህዝቡም የእግዚአብሄርን ነገር ያስተውል ዘንድ መመልከት የነበረበት፣ እንዲሁም ማወቅና ማመን ያለበት የእግዚአብሄር ነገር ምን እንደነበር ሲያሳይ እንዲህ ይል ነበር፡-
• የእግዚአብሄር ምክርና ብርቱ እጅ ከጠላትና ከፈተና ያድናቸው ዘንድ እንዳለው ሊያውቁና ሊያምኑ ይገባል
ኢሳ.43:1-3 ”አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ።”
ህዝቡ በዚህ እወቀት ሲገነቡ እርሱ የአባታቸው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር መድኃኒታቸው መሆኑን ስለሚያምኑ አባቶቻቸውን በረዳበት ክንድ እነርሱም መረዳት እንደሚችሉ ያስተውላሉ፡፡
• እግዚአብሄር ህዝቡን እንደሚወድ ሊያውቁ የተገባ ነው
ኢሳ.43:4 ”በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ።”
እግዚአብሄር እንደሚወዳቸው እንዲያውቁ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡዋቸው ነገስታቶችን ማርኮ ከእግራቸው በታች ሊያደርግ እንዳለው በማመልከት ተናግሮአቸዋል፡፡
• እግዚአብሄር ከህዝቡ ጋር እንደሆነና ለህዝቡ ምርኮን ሁሉ እንደሚመልስ ሊያውቁ ይገባል
ኢሳ.43:5-7 ”እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፡- መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም፡- አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።”
• አምላካቸው በዙሪያቸው ያሉ አህዛብ እንደሚያመልኩዋቸው አማልክት አይነት እንዳልሆነ ሊያውቁና ሊያምኑ ይገባል
ኢሳ.43:11-13 ”እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?”
እግዚአብሄር ያስተዋለውን ህዝብ ምስክሮቼ ናችሁ ማለቱ የህዝቡ እምነት ካደገ እግዚአብሄርን በታላቅነቱ መመልከት እንደሚችል ሲያሳይ ነው፡፡ እንዲሁም እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር አንስቶ በመራቸው አርባ አመታት ውስጥ የሰራውን ማዳን ካስተዋሉ አብዝተው ሊመሰክሩ እንደሚነሱ ይናገራል፡፡ ጣኦትን ያመለኩ አህዛብ ግን ህያውን አምላክን ስላላወቁ ስለእርሱ ሊመሰክሩ አልቻሉም፡፡ እርሱ እንደ አህዛብ አማልክት በቁጥር ሊባዛ የማይችል አንድ ብቸኛ የሆነ አምላክ መሆኑን ደግመው ደጋግመው በአእምሮአቸው እንዲያመላልሱ፣ እንዲያምኑትና ለልጆቻቸው ይህን እውቀት እንዲያሳልፉ፣ ከትውልዳቸውም ይህ እውቀት ጠፍቶ ማንም እንዳይስት ሲል ከህጋቸው መሀል በመጀመሪያው ረድፍ ስማ እስራኤል! በማለት በሃይለ ቃል ያስጠነቅቃል፡-
ዘዳ.6:4-9 ”እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።”
ይህ እውቀት እስራኤልን ከአህዛብ አማልክትና ወገን ለይቶ ወደ ህያው አምላክ ጥላ ያስገባ ነው፡፡ እውቀቱ የእስራኤልን ልብ በሙሉ ጠይቆአል፣ በዚህ እውቀት ምክኒያት ነፍሱ ያለ አንዳች ማወላወል (መቶ በመቶ) አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን ልትቀበለውና ልታምነው የተገባ መሆኑን አውጆአል፣ ሀይል የተባለ ሰው ያለው መንፈሳዊ ጉልበትና የአምልኮ መሰጠት ለሌላ ለማንም አምልኮ ሳይውል ይህን እውቀት ለገለጠው አምላክ ብቻ እንዲሆን እግዚአብሄር እስራኤልን አስተምሮአል፡፡
• እግዚአብሄር ብቻ ገዢ እንደሆነ አስተውለው ሊከተሉት የሚገባ መሆኑን ተናግሮአል
ኢሳ.43:14-16 ”የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል…”
የእግዚአብሄር ህዝብ ሲፈራ አይኑን ከአምላኩ እንደሚያነሳና በሁኔታዎች ላይ እንደሚደገፍ የሚታይ ክስተት ነው፡፡ የደነገጠን ልብ የሚያደፋፍርና የሚያጽናና አምላክ መጥቶም ህዝቡ ያስፈራውን ጠላት እንዳይቀበል፣ መፈራት የሚገባው ግን ንጉሱ አምላክ እርሱ ብቻ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ጠላት ምንም ያህል ቢጋፋ ማስፈራራቱ የሚቀጥለው ንጉሱ አምላካችን እስኪገለጥ ድረስ ብቻ ነው፤ ነገር ግን አሰራሩን ያስተዋሉ በትእግስት የእግዚአብሄርን ስራ እየሰሩ እየታገሱና ጨክነው እየጠበቁ ይቆያሉ፡፡ እርሱ በፍጻሜው ሲደርስ ያስፈራሩ ጎረቤቶች፣ ሀሰተኛ ነቢያቶችም ሳይቀሩ በእግዚአብሄር መምጣት ይደነግጣሉ፣ ያፍራሉም፡፡ የነነህሚያ ታሪክ ያንን ያስተምረናል፡-
ነህ.6:9-16 ”እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፡- እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፤ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ። እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና። በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ።…እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር።ቸይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር።ቸአምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦብያንና ሰንባላጥን ያስፈራሩኝም ዘንድ የወደዱትን ነቢይቱን ኖዓድያን የቀሩትንም ነቢያት አስብ። ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ። ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፥ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ።”
በነህሚያ ታሪክ ውስጥ እንደሚታየው የጠላቶቹ አሰራር መራቀቅና የሴራቸው ስውርነት መብዛት ቢጎላም እግዚአብሄር መጥቶ ህዝቡን እስኪረዳ ድረስ የነርሱ ዛቻ ከማስፈራራት አልፎ ሊሄድ አልቻለም፡፡ እግዚአብሄርንና አሰራሩን በማወቅ ስንቆም የሚታየን መምጣቱ እንጂ እየመጣ የሚሄደው የጠላት ፈተና፣ ስውር አሰራር እንዲሁም የሚከታተለው የመከራ ጫና አይደለም፡፡ ድል ድል ነው፣ ማሸነፍ ማሸነፍ ነው! ከዚህ ውጪ ስለጠላት ሁኔታ ማውጣትና ማውረድ የሚፈጥረው ልብን የሚያሸፍትና እግዚእብሄርን ከመጠበቅ የሚያንሸራትት መንፈስ ውስጥ መስጠም ነው፡፡ ንጉስ ዳዊት የእግዚአብሄር እርዳታ እስኪመጣለጥ ድረስ በብዙ ትእግስት እግዚአብሄርን ጠበቀ፣ ሲጠብቅ ግን ነፍሱን እያበራታ፣ ስትዝል እየገሰጸ፣ የአምላኩን ታላቅነት እያሰላሰለ፣ በእምነት እየተናገረም ነበረ፤ የርሱ ማሸነፍ ይሄን ታላቅ ተጋድሎ ጠይቆአል፡-
መዝ.18:1-6 ”አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ።የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ።በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።”
መዝ.30:8-12 ”አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ። ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን? እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ሆነኝ። ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ። አቤቱ አምላኬ፥ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።”
መዝ.121:1-3 ”ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።”
ከመነሻው እንደተባለው ሰማያዊ እውቀት ሲጎድል ብዙ ጉዳትና መንፈሳዊ ስብራት እንደሚገለጠው ሁሉ ከላይ እንደምናየው እንደ ንጉሱ ዳዊት ያለ መረዳት ያለበት መለኮታዊ እውቀት ከእግዚአብሄር ጋር እንደሚያኖር፣ ምህረትንና በረከትን እንደሚያስከትል ማስተዋል ይገባናል፡፡ ካለማስተዋል መጉደል እንደሆነው አይሆንም፣ እርግጡን ካለመረዳት በሚመጣ መምታታት አይከሰትም፣ የልኡል እውቀት እስካገዘን ድረስ የማስተዋል እጦት አይገጥመንም፣ አካሄዱን እስከተረዳን ድረስ የጉዳት ጠባሳ በህይወታችን ውስጥ አይታተምም፣ ከዚህ ይልቅ የእውቀቱ ብርታት ይለውጥና መለኮታዊ ጸጋን ያስገኝልናል፣ ምህረትና ደህንነት ገንዘባችን ይሆናል፡፡
መለስ ስንል ይህ እውቀት እስራኤልን ሊያድን፣ ርስታቸው ላይ ሊያኖርና ሊያጸና የሚችል መለኮታዊ እውቀት ሆኖ ሳለ እስራአላውያን ከዚህ እውቀት ጋር ስላልተዋሀዱ በብዙ ሲታገሉትና ሲወድቁም ታሪካቸውን እንደሞሉት የምናየው ነው፡፡ የሚያስተውልም ትምህርቱ እኔንም ይመለከተኛል ይበል፡፡
ብዙ እውቀት በምድር ላይ ቢኖርም ሰማያዊው እውቀት ግን የላቀና አምላካዊ ፈቃድ ያለበት ነው፡፡ ምድር ላይ የተከማቸ እጅግ የበዛ እውቀት የምድርን ምስጢር ይገልጥ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ጥበብ ለእግዚአብሄር ምስጢር ፍጹም ባዳ እንደመሆኑ ወደ የትኛውም መንፈሳዊ ከፍታ የሰውን ልጅ ማድረስ አይቻለውም፡፡
በዳን.2:20-22 ውስጥ ”ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፡- ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።”