አንዳንዴ ከራስ በሚመነጭ ፍላጎትና አስጨናቂ ስሜት፣ እረፍት ከማይሰጥ አሳብ፣ ከሰው ከሚመጣ ግፊት ያልያም የሁኔታዎች መወሳሰብ በሚፈጥረው አለመመቸት ጥብብ ጭንቅ ሲለን መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ለመዝለል በሚል የምንሄደው አደገኛ አካሄድ አለ፡፡ ነገሩ ጎልቶ ሳለ እርሱን ላለማየትና ላለመስማት እንሞክራለን። እስጨንቆ የሚገፋ ሀይል እስከማናቆመው ድረስ ወጥሮናል፣ እናም አሳሳቢነቱ ስለሚሰማን መፍትሄ በምንለው መንገድ እንሄዳለን። የሆነው ያ የማንፈልገው ውጤት ህሊናችንን ሲታገለን፣ እኛም ልናሸንፈው ስንገጥመው፣ ደግሞ በየእርምጃችን እየጮሀ ሲያስጨንቀን…እንደዚያ እያልን እንቆያለን፣ ሆኖም መጨረሻ ምሽታችን ላይ ስንዝል ከትግሉ ለማምለጥ ስንል ከእውነታው ማፈንገጥ እንመርጣለን፡- በሽሽት።
ከራስ ሸሽቶ ወደ ራስ በሰላም መግባት እንደማይቻል በብዙ ማስረጃ ልናየው የምንችለው ነው። አስቀድሞ እውነትን ላለመቀበል ነበር የሸሸነው። ሩጫው ሲያቅተን ግን ተስፋ በመቁረጥ ሸሽት እናቆማለን፣ ትተን ወደዚያው የራሳችን ጉዳይ እንመለሳለን፣ እጅም እንሰጣለን። ከሽሽት ተከትሎ የሚመጣ ተስፋ መቁረጥ እንዳይቆጣጠረን የመጣውን በማስተዋል ማቆምና መመርመር ወደ ጥፋት ከማምራት ይታደጋል፡፡
በሌላ በኩል የሚያሸሹን የውስጥ ብቻ ሳይሆኑ የውጪ ግፊቶችም እንደሆኑም ማወቅ አለብን፡፡ ሰላምን የሚያሳጡ፣ እረፍት የሚነሱና አእምሮን የሚያውኩ ጉዳዮች በተመሰሳይ ሁኔታ ተጽእኖ ያስከትሉብናል፡፡ በነዚህም ምክኒያት ሽሽታችን ከውስጥ ግፊት፣ ከውጪ ግፊት አልፎ ተርፎም ከእግዚአብሄር ፊት ሊሆኑ እንደሚችሉ ማየት እንችላለን፡፡
• ከውስጥ ግፊት ሽሽት
ከውስጥ ግፊት ሽሽት ከህሊና ጥሰትና ከስጋዊ ስሜት ግፊት ይነሳል፡፡ የህሊና ግፊት (በጎ ተጽእኖ ነው) አንድ ሰው ጥፋት በሰራ ጊዜ ውስጡ ያለ ዳኝነት ሲሞግተው የሚከሰት ነው፡፡ ያጠፋውን ጥፋት እንዲያስተካክል፣ ከሳተበት መንገድ እንዲመለስ ያልያም የበደለውን ይቅር እንዲልና እንዲክስ እንዲስተካክልም ውስጡ ይሞግታል፡፡ በሙግቱ መሀል ግን አድርግ የሚለው ድምጽ ሲያስገድድ አእምሮም አላደርግም ወይም አልችልም ሲልና ሸሽትን ሲመርጥ የሚፈጠር የውስጥ ትርምስ አለ፡፡ ሽሽቱ በሙግቱ መሃል ያለ ተሸናፊነትና ህሊናን ባለመቀበል ምክኒያት የሚፈጠር አመጽ ነው፡፡ ቢሆን ኖሮ ለዚህ ሙግት ብርቱ መፍሄ እሺ ባይነት ነበር፡፡
የህሊና ፍርድ በሰውም በእግዚአብሄርም ፊት የሚያቆም ነው፡፡ህሊናን ፖሊስ አድርጎ ውስጣችን ያቆመ እግዚአብሄር ነው፡፡ ይህን የሚያደርግበት ምክኒያት የሰው ልጅ ከጥፋት ሁሉ እንዲድና ወደ ራሱ እንዲመለስ ነው፡፡ የሚከተለው ታሪክ ይህን ያስተምረናል፡-ከባለታሪከኞቹ እንደምናየው ስራቸውን ይዘው የመጡት እነዚህ ሰዎች በህሊናቸው በኩል በመጣው የእግዚአብሄር ተግሳጽ ላይ ስላላመጹ ወቀሳውን ታዝዘው ከጥፋት ተመልሰዋል፡፡
ዮሐ.8:3-9 ”ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፡- መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፡- ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ…”
የስሜት ግፊት (በጎ ያልሆነ ተጽእኖ ነው) የፍላጎትን ጫና አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ራስን መግዛት ጉልበት ሲያጣ በስሜት መሸነፍ አይቀርም፡፡ ያን አስተውሎ መስተካከል ካልተቻለም ከራስ መሸሽ ይፈጠራል፡፡ በስጋችን ላይ የሚፈጠር ስሜት ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ስሜታችን እንዳያሸንፈን ካልታገልን ለስሜታችን እጅ እንሰጣለን፣ የሆነው ከሆነ በሁዋላ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ያደረግነውን መልሰን ላለማሰብ መጨነቅ እንጀምራለን፣ ሰላምም እናጣለን፡፡ አስቀድሞ ስለጥፋታችን አንድ ያወቅነው እውቀት ይኖራል፡፡ ሆኖም ስሜታችንን ያረካነው ያን እውቀት ጥሰን ስለሚሆን ፍትጊያችን የሚሆነው ከዚያ እውቀት ጋር ነው፡፡ ያን ተከትሎ ውስጣችን በብርቱ ትግል ይወጠራል፣ ተከታዩ ሽሽትም ብዙ ዋጋ ይስከፍላል፡፡ ለምሳሌ ዳዊት አታመንዝር የሚለውን ህግ እያወቀ ቃሉን ጥሶ ወደ ምንዝር ሄደ፣ ከዚያ የሆነው ሁሉ ሆነበት፡-
”እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፥ ረባትንም ከበቡ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም:- ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም። አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት። ….በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው። በደብዳቤውም:- ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ።… ኬጢያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ።….የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች። የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።”(1 2ሳሙ.11:1-26)
እኛነታችንን ከሚዋጉ እንድንሸሽ ግን ታዘናል፡-
1ጢሞ.6:10-11፣22 ”ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።”
• ከውጪ ግፊት ሽሽት
የነገሮች/የሁኔታዎችና የሰዎች አስተሳሰብ ጫና ተጽእኖ አለው፡፡ ያ የሚያሳድርብን በጎም በጎ ያልሆነም ተጽእኖ ነው፡፡ በጎ የሆነ የሰው ተጽእኖ ወደ ራስ የመሰብሰብ አስተዋጽኦ አለው፡፡ መልካም ምክር፣ ስጦታ (ገንቢ እውቀት) እና ደጋፊ ድርጊት የመሳሰለው በጎ ውጤት ያመጣል፡፡ በተቃራኒው የሰው አመለካከትና ተግባር በሰው ስነልቦና ላይ ፍርሀትን፣ ጭንቀትንና መሰናክልን ሲፈጥር በሰው ህይወት ማፈግፈግ ይከሰታል፡፡ የሰው ተጽእኖ ሰውን ካለበት የህይወት ይዘት መንቀል እንደሚችል በሚከተለው ታሪክ ውስጥ እናያለን፡፥
1ሳሙ.20:1” ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ፡- ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው።”
ዳዊት እየሸሸ የነበረው በልቡ የታተመውን የአምላኩን ቃልኪዳን ይዞ እንደነበር ልብ ይሉዋል፡፡የንጉሱ ማሳደድ ዳዊት ከራሱ ነገር እንዲሸሽ (የተሰጠውን ቃል ኪዳን እንዳያገኝ) ብርቱ ፈተና ሆኖበት ነበር፡፡ አምላኩ የገባለትን ቃል እስኪፈጽም ድረስ ብላቴናው ዳዊት ለዘመናት በየዱር መንከራተት ነበረበት፡፡ የጠበቁትን የማያሳፍር አምላክ ግን በጊዜው የሸሸውን ብላቴና ወደ ራሱ መልሶ ክሶታል፡፡