እግዚአብሔር እረኛዬ ነው[2/3]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

​​​​​​​​መዝ.23:2 በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል።

አምላካችን ማሰማርያ መስክ ያለው አምላክ ነው፡፡መስኩ ማረፍያ ያለው ፣ ምግብና መጠጥም  የተሞላ ስለሆነ የአቅርቦት አጥረት ከቶ አያጋጥመውም፡፡የመስኩ ባለቤት የመስኩን ልምላሜ ይቆጣጠራል፣ባእዳን ረግጠው እንዳያረክሱት ዘወትር ያጠራዋል፡፡በመስኩ ላይ የሚሰማሩ በጎች ባለቤታቸው አንድ ብቻ በመሆኑ የእርሱን ድምጽ ይለያሉ፣ምሪቱን ያስተውላሉ፡፡የእረፍት ውሀ በጎቹን በመስኩ ላይ በእረፍት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ያለ ፍርሃትና ጥርጣሬ ይጸኑ ዘንድ ጌታ  ይመራቸዋል፡፡ስለዚህ እርሱ እንዲህ አለ፡-

​​​​​​​​ዮሐ.4:14 እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።(ለሳምራዊትዋ ሴት)

በእግዚአብሄር መስክ ላይ ለተሰማሩ በጎች የእግዚአብሄር ዋስትና አለ፡፡ነፍሳቸው በእርካታ እጦት ላትቅበዘበዝ፣ከቃሉ ረሀብ የተነሳ ላትዝል ዋስትና ጌታ ኢየሱስ ገብቶላታል፡፡ከአለም የምንቀበለው በረከት በቶሎ ስለሚሙዋጠጥ እጥረት ይገጥመዋል፡፡አለም የጥማት ምድር ናት፡፡የረሃብ መስክና ልምላሜ የማይገኝባት ደረቅ ናት፡፡ዛሬ በእርስዋ ላይ ተስፋቸውን ያደረጉ በድርቅ ዘወትር የሚመቱ ናቸው፡፡ውስጣዊ እርካታ የሌላቸው መፈጠራቸውን የሚራገሙ በአምላካቸው ላይ አጉረምራሚ ናቸው፡፡

​​​​​​​​ኤር.2:13 ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጕድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል።

የጌታን ድምጽ የመስማት ችሎታ የሌላቸው፣በነፍሳቸው ድርቅ ያጠቃቸው ናቸው፡፡ይህ በአለማዊነት ለሚመላለሱ ልጆች ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ዘንድ በልባቸው ለኮበለሉም የእግዚአብሄር ልጆች ጭምር ነው፡፡የህይወት ምንጭን ትተው ህይወት ሊሰጡ ወደማይችሉ አማልክቶች የዞሩ ሁሉ በድርቅ የተመቱ ናቸው፡፡ታዛዥ ሳይሆኑ አመጸኞች በመሆናቸው ከለምለሙ የእግዚአብሄር ስፍራ አፈነገጡ፡፡በዚያም የደረቀና የውሀ ምንጭ የሌለበት ምድረበዳ ገጠማቸው፡፡አለከለኩ፣የምድረበዳው ትኩሳት አጎሰቆላቸው፣በእንዲያ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ እንኩዋን  ልባቸውን ወደ ፈጣሪያው አልመለሱም፣ንሰሀ አልገቡም፡-

​​​​​​​​ኤር.2:6 እነርሱም። ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ ጕድጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም።

ይልቅ በቀድሞ ዘመን የመራቸውን አባታቸውን ወደሁዋላ ተመልሰው በንሰሀ በመፈለግ ፋንታ በእልሃቸው ገፉበት፡፡ስለዚህ የተመላለሱባቸው ባዶ ጉድጉዋዶች ህይወታቸውን ሊያረኩ ተሳናቸው፡፡ 

እግዚአብሄር ግን ሁሌ ልባችንን በቃሉ ሀይልና በመንፈሱ ጸጋ ሊያለመልመው ይፈልጋል፡፡የምንበላው እንዳናጣ ና ነፍሳችን ዳግም እንዳትከሳ ቃሉን ፣በጥማትም እንዳትቃጠል የምትረካበትን የህይወት መንፈስ ሊሰጣት ፈቃደኛ ነው፡፡ግን አሁንም ወደ መስኩ ተመለሽ ይላል፡፡በዚያ ብቻ ልምላሜና የእረፍት ውሀ ይገኛልና፡፡ ሁልጊዜ የእኛ ስፍራ ከእርሱ መጠበቂያ አካባቢ ፈቀቅ ካለ፣እሱን የምንጠባበቅበት ትግስትም ከተሙዋጠጠ እሱ ሊጎበኘን ሲመጣ ስለማያገኘን ከመንፈስ በረከት ጋር ሳንገናኝ እንተላለፋለን፡፡ጌታን ሲመጣ የሚሰሙት መንፈሳዊ ጆሮአቸው የተከፈተ ወገኖች ብቻ ናቸው፡፡ዘወትር በጸሎት መጠበቂያ ስር የሚገኙ፣በቃሉና በመንፈሱ የረሰረሱ፣የእግዚአብሄር ተስፋ ልባቸውን የሞላና መተማመን ያላቸው ናቸው፡፡ዙሪያቸውን ሳይሆን ውስጣቸውን በእምነት የሚዳስሱ ወገኖች ዛሬ ያስፈልጋሉ፡፡እግዚአብሄርን አግኝተው ከእርሱ ጋር ሌሎችን የሚያገናኙ እነርሱ ሰዎችን ወደ እግዚአብሄር የልምላሜ መስክ የሚያመጡ ናቸው፡፡