እግዚአብሄር ሲናገር፡-”ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም” ይላል (ኢሳ.45:23)፡፡
እግዚአብሄር ይናገር እንጂ የተናገረው መሆኑ/መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ስልጣን ያለው ቃል አሳቡን ማከናወን እንደማይሳነው እንኩዋን ህያው አምላክ ከሰው የሆነ ባለስልጣንም በችሎታው አይጠረጠርም፡፡ የእግዚአብሄር ንግግር ለመከናወኑ እርግጠኛ/እውነት በመሆኑ ሲናገር የሰሙት ሰዎች የተናገረውን ቃል በደስታና በተስፋ ይዘው ይጠባበቁታል፡፡ መጠበቅ እንዲህ እንደምንለው ቀላል አይደለም፡- ትግስት ይጠይቃል፣ እምነት ይጠይቃል፣ ጊዜም ይጠይቃል፡፡ ቢሆንም የታመኑት ሁሉን ተቀብለው እርሱን ይጠባበቃሉ፡፡ እግዚአብሄርም በተስፋ፣ በደስታና በእምነት በሚጠባበቁት ደስ ይሰኝባቸዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ባህሪ የተረዱ ስለተናገረው ቃሉ በደስታ ያውጃሉ፡-
መዝ.119:100-105 ”ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።”
በእግዚአብሄር አሳብ በኩል ስንመለከት ቃሉ እንዲፈጸምልን የምንፈልገውን ያህል እግዚአብሄር ያሰበውን በህይወታችን እንዲሰራ መፍቀድ፣ እንደ ፈቃዱም እንዲገልጠው የልብ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ልብ የእግዚአብሄርን ቃል ሲፈቅድ እግር ወዳሻው እንዳይነጉድ ያግዳል፣ ቃሉን ደግሞ ለመታዘዝ ይወስናል፡፡ አሳባችንን አሳቡ እንዲገዛው መንገዱም መንገዳችንን እንዲቃኝ ልብን ዝግጁ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ እርሱ ፈቃድ ውስጥ መግባት፣ የእርሱን ምሪትና እርዳታም ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ሰማይ ከእኛ ምድር ከፍ ብሎ እንደሚገኝ ያህል የእርሱ አሳብ ከአሳባችን፣ ፈቃዱም ከፈቃዳችን፣ ከፍ ያለ መሆኑን ከተረዳን የእርሱ የሆነውን ነገር በእግረ-መንገድ የምንቀበለው አድርገን እንደማናቃልለው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።
ኢሳ.55:8-11 ”አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”
እግዚአብሄር የነገረን ነገር በእኛ ውስጥ ሆኖ እንዲኖርና ተፈጽሞ እንድናይ ተስፋና እምነት መሰረታዊ ናቸው፡፡ ተስፋና እምነትም በተዘጋጀ ልብ ውስጥ የሚተከሉ የልብ ማጽኛ ናቸው፡፡ ተስፋ ነገን ያኖራል ያስጠብቃልም፣ እምነት ቃሉን በልባችን ያሳድራል፡፡ ሰው በሰማው የህያው እግዚአብሄር ቃል ተስፋ ሲያደርግ እግዚአብሄር የነገረውን በጉጉት ይጠባበቃል፤ እግዚአብሄርን በትህትና ያሳስባል፣ ይጸልያል፡፡ በሌላ በኩል እግዚአብሄር የተናገረውን ተስፋ በማድረግ ነገሩ በእርግጥ ይፈጽማል የሚል እምነት በልብ ሊሞላ ይገባል፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሄርን መለመን አይቻልም፣ እርሱም ያለእምነት የምናደርገው ነገር ላይ አይደሰትም፡፡
በአለም ላይ ያሉ የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ እየኖሩ ያሉት እግዚአብሄር እንደፈጠራቸው በአላማ እንጂ እነርሱ መሆን በሚፈልጉት መንገድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰዎች በውስጣችን በሚመላለስ አሳብ እየተመራን ለመኖር እንሻለን እንጂ የመኖራችን መሰረት በእግዚአብሄር አላማ ላይ የተመሰረተ ነው ብለን አናስብም፡፡
በአለም ላይ እየሆነ ያለ የማያቁዋርጥ ለውጥ አለ፤ እየሆነ ያለው ለውጥ እንዴት እንደሆነ ማስተዋል የሚቻለው ከሚታየው ለውጥ ጀርባ ያለውን የለውጥ ሀይል ማስተዋል ሲቻል ነው፡፡ ንጉስ ሰለሞን በነገሮች ላይ ከሚካሄደው ድርጊትና ተጽእኖ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ለውጥ ሁዋላ ያለው የእግዚአብሄር እጅ ስለመሆኑ በቃሉ ውስጥ ያሳያል፡፡
መክ.3:11-15 ”ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።”
ከላይ እንደተባለው ሁሉም ነገር ያለው እርሱ በፈጠረው መንገድ ነው፣ ለእኛ እንደመሰለን ጨርሶ አይደለም፡፡ በልባችን ያለው የአለም ገጽታ፣ እውቀትና ወግ ግን በእግዚአብሄር ስራ ላይ ያለንን ግምት ያመሰቃቅለዋል፡፡ ያም ሆኖ የእግዚአብሄር የእጆቹ ስራ ውበትና አድናቆት በእኛ የሚሰርጸው እኛ ባለንበት የህይወት ይዘት ሊሆን አይችልም፡፡ የማይለወጥ አምላክ በፈቃዱ የሚሆነውን ነገር ማንም ሀይል በራሱ አንዳች ማድረግ ካልቻለ የሰው ልጅ አመለካከት በሚፈጥረው ድምዳሜ/ማጠቃለያ መመካት ስህተት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ በምናየውና እግዚአብሄር በሚገልጠው አሰራር መሃል ባለው ልዩነት ምክኒያት በማያስተውሉት ዘንድ በእግዚአብሄር የተሰሩት ስራዎች እየደበዘዙ ውበታቸውን ማየት ይሳናል፡፡ ያን ያለመቻል ሁኔታ አንዱ ከሌላው ቀጥሎ ሊፈጸም ያለውን የልኡል አምላክ እቅድ ከመገንዘብ ውጪ ያደርጋል፡፡
እግዚአብሄር የሰራው ፍጹም ነው
ዘዳ.32:4 ”እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።”
በእግዚአብሄር ፊት የእጆቹ ስራዎች ሁሉ ውብ ናቸው፣ አቅዶ ስለሰራቸውና እቅዶቹ ፍጹም ስለሆኑ፡- ለእርሱ በጋ እንደ ክረምት፣ ወበቅ እንደ ቅዝቃዜ፣ በረሀም እንደ ውርጭ አንድ ናቸው፡፡ ብርሀንና ጨለማ በሰው ፊት ሲታይ ይበላለጣል፡- እኛ ቀንን እንደምንወድ ምሽትን አንወድም፡፡ ብርሀንን እንደምንመርጥ ጨለማን አንመርጥም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ግን ሁሉም እኩል ናቸው፣ አስፈላጊነታቸው በእርሱ ዘንድ ቦታ አለው፣ ውበታቸው በእርሱ የተረጋገጠ ነውና፡፡
በተመሳሳይ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የሰጠው ህግና ስርአት በሰው ዘንድ እንደ ሸክም የታየ ነው፡፡ ሰው ለምን እንዲህ ያለ ዝንባሌ አሳየ? በእግዚአብሄር የተሰራውን ስራ በራሱ ስሜት ስለተረጎመው ወይም በአስተሳሰቡ ልክ ስለመዘነው ነው፡፡ ቃሉ ሲናገር፡-
”ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው።”(1ጢሞ.1:8-11)
ለምን ሰው እንደሚገባ ሕግን ሊሰራበት ተሳነው? ህጉ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን ሲል ማረጋገጫ ተሰጥቶት የለምን?
መልካም የሆነውን ህግ የሰጠ አምላክ በደለኞችና የማይታዘዙ፥ ዓመጸኞችና ኃጢአተኞች፥ ቅድስና የሌላቸውና ርኵሳን፥ አባትና እናትን የሚገድሉ… የመሳሰሉ የሰው ልጆች በክፋታቸው ስራውን ስላቃለሉ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ጊዜ የማያስተውል ህዝብ ይጎዳል
በሌላ በኩል የጊዜ ያለመገጣጠም ሁሌም ለእኛ መሰናክል ሆነው እናገኘዋለን፣ ችግሩ ግን ከሌላ ሳይሆን በእኛው የአቅም ማነስ ምክኒያት ነው፣ ማስተዋል የሚሰጠው መንፈሳዊ ሀይል ስለሌለ የእግዚአብሄርን ጊዜ ያለማወቅ ሁኔታ ተፈጥሮብናል፡፡ ስለዚህ በጊዜ አለመገጣጠም ምክኒያት እኛ የምንጠብቀው ነገርና እግዚአብሄር የሚያደርገው ስራ ሳይጣጣም ይቀራል፡- ደህና ነው ስንል ሁከት፣ በረከት ነው ስንል መርገም፣ ብርሀን ነው ስንል ጨለማ፣ ተሰብሰቡ ሲባል መበተን፣ እንደዚሁ ሌላም የማይገጥም ነገር የሚፈጠረው ዘመኑን ባለመዋጀት ምክኒያት ነው፡፡
1ተሰ.5:1-5 ”ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና።ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም”
ዘመናትንና ወራትን ያውቁ የነበሩ ወንድሞች እኮ ዘመኑን የመዋጀት ማስተዋል ነበራቸው፡፡ ዘመኑ ይዞ የመጣው አጋንንታዊ ሁኔታና እግዚአብሄር በተወሰነው ዘመን እያደረገ ያለው ልዩነቱ ምንድነው? ቀጥሎ ሊሆን ያለውስ? በዚያ አንጻር አለም ላይ የሚከሰተውስ ነገር ምንድነው? እኛስ ምን ማድረግ ይገባናል?… የመሳሰለውን ጥያቄ በመንፈስ ተመልሶ ስለሚያገኙት ጥንቁቅ ናቸው፡፡
ዘመናትና ወራት የእግዚአብሄርን እቅድ ይገልጣሉ፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆነው ግን እግዚአብሄር በወሰነው ሰአት ነው፡፡ ችግሩ ባላስተዋልነው ዘንድ የእግዚአብሄር ጊዜና የእኛ ጊዜ ተዛንፎአል፤ እና በሁለት መንታ አስተሳሰብ እናነክሳለን፡- አንደኛ ነገሩ የእግዚአብሄር ሆኖ ሳለ የእኛ አድርገን እንቆጥራለን ሁለተኛ እንደራሳችን የቆጠርነውን ነገር በራሳችን ጊዜ ተከናውኖ ማየት እንሻለን፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ስህተቶቻችን አንድ ሆነው ከባድ መዛባት በህይወታችን ያመጣሉ ማለት ነው፡፡ የሚከተለው ታሪክ በእግዚአብሄር ጊዜ ላይ ያለንን መዛነፍ ችግር ያሳያል፡-
ሐዋ.1:4-8 ”ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፡- ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፡- ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም፡- አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።”
የጌታ ፈቃድ ሀዋርያት በኢየሩሳሌም ቆይተው የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ጊዜ እንዲጠባበቁ (በአለሀምሳን እንዲጠባበቁ) ሲሆን የነርሱ ፈቃድ ደግሞ ለእስራኤል መንግስት ተመልሶ ማየት ነበር፡፡ ጌታ ግን ቸር ነውና አቃናቸው፤ እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አሳብ ጸንተው ቆይተው ቢሆን ኖሮ እግዚአብሄር በጊዜው ከሚሰራው ታላቅ ስራ በጎደሉ ነበር፣ ያውም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ሳይቀበሉ በቀሩ ነበር፡፡
በእግዚአብሄር ፊት የሚመላለስ ህዝብ ካለበት ሀላፊነት ዋናው እግዚአብሄር የሚያከናውናቸውን ስራዎች እንደቃሉ ማስተዋል መቻል ነው፡፡ ቃሉን መመርመር፣ መርምሮም መቀበል፣ ዝግጁ፣ ታዛዥም መሆን ተጠባቂ ነው፡፡ ያለማወቅ ግን ያለማመንን ይፈጥርና የእግዚአብሄርን ጊዜ እንዲስት ጥፋቱንም እንዲያፋጥን ያደርጋል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት የሚቆመው የእስራኤል አምላክ ካህን ዘካርያስ አምላኩ የላከለትን ታላቅ የምስራች አስተውሎ ቢሆን ኖሮ ከራሱ አልፎ ለህዝቡ ታላቅ ደስታን የሚያበስር አጋጣሚ ባገኘ ነበር፡፡ ጊዜውን መዋጀት የሚችል ጸጋ ስላልነበረው እግዚአብሄር ከብዙ ዘመናት በሁዋላ እስራኤልን ለማናገር መውረዱን አላወቀም፡፡
ሉቃ1:13-21 ”… መልአኩም እንዲህ አለው። ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።… በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን፡- እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው፡፡መልአኩም መልሶ:- እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው።”
ካህኑ በእግዚአብሄር ፊት እያገለገለ እያለ በጊዜው የሚፈጸመውን የእግዚአብሄር ቃል ገና አላስተዋለም፤ በዚህ ምክኒያት የመልአኩን የምስራች ቃል ማመን ተሳነው፡፡ እንዲያውም ከነበረበት ሀላፊነት አንጻር እግዚአብሄር እንደፈለገው ሆኖ ስላላገኘው እግዚአብሄር የተናገረው እስኪፈጸም ዲዳ እንዲሆን አደረገው፡፡ ዘካርያስ በቤተመቅደስ ያየውን ታምራት ሳይናገር፣ የሰማውን የምስራችም ሳያበስር ከእግዚአብሄር አገልግሎት ገለል ብሎ በዲዳነት አሳለፈ፡፡ የነብያት ቃል ዘመኑን በመጥቀስ ጭምር ያመለከተውን የጌታ ቀን ካህኑ ያለማስተዋሉን ልብ እንበል፤ በሚል.4:5 ውስጥ የተመለከተው የነቢዩ ኤልያስ መላክ የተነገረው ለእስራኤል ቤት በተለይ ለራሱ ለካህኑ ዘካርያስ ቤት መሆኑን ያን ሳያውቅ በእግዚአብሄር ፊት ቆሞ ያለእውቀት እጣን ሲያጥን ነበር፡፡
በእግዚአብሄር መገኛ አካባቢ በእግዚአብሄር መገኘት ያለመነካት ከባድ ድካም ነው፤ በእግዚአብሄር መቅደስ ውስጥ የእግዚአብሄርን ታምራት ያለማመንም ሌላው ድካም ነው፡፡