እግዚአብሄር የተናገረውን በጊዜው ይፈጽማል‹2..›

የመጨረሻ ዘመን

እግዚአብሄር የተናገረውን እንደተናገረው ልክ/ ፍጹም አድርጎ በትውልድ መሃል በጊዜው እንዲገልጠው የተመቻቸ ስፍራ/ማረፍያ ልብ ይፈልጋል፡፡ በአዲስ ኪዳን ሊሆን የተጠበቀው፣ የሆነውም ይህ ነበር፤ ስለዚህ የእግዚአብሄር መልአክ የእግዚአብሄርን ስራ ሊያውጅ ሲገለጥ ወደ ሁለት ቤተሰቦች ዘንድ ሄደ፡- ወደ ካህኑ ዘካርያስና ወደ ማርያም ቤት፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ እልሳቤጥ በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። ማርያም ለዮሴፍ የታጨች ጸጋ የሞላባት ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ተብሎ የተመሰከረላት ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የተባለችም ልጃገረድ ነበረች። እነዚህ ሰዎች ህይወታቸውን ለእግዚአብሄር አላማ ያዘጋጁ እንደ ጌታ ፈቃድም የሄዱ ስለነበር ጊዜው ሲደርስ መልአኩ እነርሱን ይጎበኝ ዘንድ ወደ ቤታቸው መጣ፡፡ ዛሬስ ራሱን ለእግዚአብሄር ስራ የሚያዘጋጅ ማን ነው? እግዚአብሄር ግን የተናገረውን በጊዜው ሲፈጽም ሰው ሊያደርገው የሚገባውን ነገር ቃሉ ያመለክታል፡፡
በጊዜው እንዲሰራ ሰው እንዲያምንና እንዲጠባበቅ እግዚአብሄር ይፈልጋል
ዘኊ.9:1-6 ”ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤ በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት። ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው። በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ።”
– በጊዜው ስራውን እንደ ቃሉ መፈጸም – ያለመዘግየት
የእስራኤል ህዝብ ፋሲካን በተቀጠረው ጊዜ ያደርጉ ዘንድ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸው ነበር፡፡ ስራቸውን ማዘጋጀት፣ ልባቸውን ለአምልኮ ማዘጋጀት፣ ሰፈራቸውንም ለንጉሱ ማመቻቸት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር እየተከናወነ ባለበት ወቅት ራሳቸውን እንደሚገባው ያላዘጋጁ ሰዎች ከህዝቡ መሃል ተገኙ፡፡ በፍርድ መሃል ምህረት ማድረግ የሚወድ አምላክ ግን በዚያ ጣልቃ ሲገባና በእግዚአብሄር ፊት የህዝቡ ደስታ ወደ ሀዘን እንዳይለወጥ ሲወስን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሄር በወሰነው ስፍራና ጊዜ መገኘት ለስርአቱም ራስን ማስገዛት ከሚመጣ ቁጣ እንደሚያተርፍ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ እስራኤላውያን ልባቸውን ትሁት አድርገው የእግዚአብሄርን ዝግጅት ለመካፈል ባደረጉት ሙከራ ውስጥ የእግዚአብሄር እገዛ ስህተታቸውን እየሸፈነና ጉድለታቸውን እየሞላ ደስታቸውን ፍጹም አድርጎታል፡፡
– ሥርአቱንና ፍርዱን ከስራው ጋር መጠበቅ
በሀዋርያት ዘመን የእግዚአብሄር መንፈስ ተንቀሳቅሶ አዲስ ነገርን በአማኞች መሀል በፈጠረ ጊዜ አናንያና ሰጲራ የተባሉ ክርስቲያኖች በጉባኤው መሀል ነበሩ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስት አማኞች በመንፈስ ሆነው በእግዚአብሄር ስራ በመደሰታቸው ለስራው ተበባሪ ይሆኑ ዘንድ ለራሳቸው ቃል ገብተው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚያን ዘመን የተገለጠው መንፈስ እየሰራ የነበረው ስራ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ በመንፈሱ እንቅስቃሴ አካባቢ ሊጠበቅ ይገባ የነበረው የርሱ ስርአትና ፍርድ ግን ተዘንግቶ ነበር፤ ያንም በቃሉ ውስጥ የምናየው ነው፡-
ሐዋ.5:1-4 ”ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፥ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። ጴጥሮስም፡- ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።”
ጊዜ፣ ስፍራና የቃሉ ትእዛዝ በእግዚአብሄር ስራ መገለጥ
እግዚአብሄር ያዘዘው ፋሲካ የሚፈጸምበት ጊዜ አስራ አራተኛው ቀን ነበርና በዚያ ቀን የሚከናወነው በአል ዝግጅት ለቀኑ ተጠናቅቆ ነበር፣ ስፍራውም በሲና ምድረ በዳ ሲሆን ድርጊቱም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ስለነበረ የእስራኤል ልጆች በዚያን ቀን በተወሰነው ስፍራ ፋሲካን አደረጉ፡፡(ዘኊ.9:1-6) በጊዜውና በተወሰነው ስፍራ ሊያከናውኑ የተሳናቸው ግን ቃሉን ለመፈጸም እንቅፋት እንደሚገጥማቸው የሚከተለው ቃል ያሳያል፡-
2ዜና.30:2-3 ”ካህናቱም በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉምና ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተመካክረው ነበር።”
የእግዚአብሄርን ጊዜ ያልጠበቀ ስራ ከርሱ ዘንድ መልስም ሆነ ሞገስ እንደማያሰጥ ያስተዋሉ አለቆች ሌላ ያስተዋሉት ነገር በአመቺ ጊዜ እግዚአብሄር በወሰነውም ሰአት ምህረትን የሚሰጥ መሆኑን ነው፡፡
በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሰዎች በጊዜ ለሚገለጠው የእግዚአብሄር አሳብ የሚሰጡት ግብረ-መልስ ስለ እግዚአብሄር ስራ፣ አላማና እቅድ ያላቸውን እውቀት አመልካች ነው፤ ለእኛ ለትምህርታችን በቃሉ ውስጥ መቀመጣቸውም እኛን ለማስተማር በመሆኑ ቸል ሳንል ለተስተካከለ አመለካከት እንደ ግብአት ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡
– ከእግዚአብሄር ጊዜ ወደ ሁዋላ ለሚዘገዩ ሰዎች እግዚአብሄር ይናገራል፡-
ሐጌ.1:2-11 ”የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡- ይህ ሕዝብ፡- ዘመኑ አልደረሰም፥ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል ብሎ ተናገረ።የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፡-በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ።የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ።ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።”
የእግዚአብሄር ጊዜ ደርሶ ወደ ሁዋላ ማለት፣ መዘናጋት ወይም ማንቀላፋት እርግማንን እንደሚጠራ ቀጥሎ የተናገረው የቃሉ ክፍል ግልጽ ያደርገዋል፡-
”እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነው። ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ከልክላለች። እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ።”
– በእግዚአብሄር ጊዜ ለሚተጋው ባርያ ግን ሞገስም ሽልማትም ይሆናል፡-
ማቴ.24:45-46 ”እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው”
– በእግዚአብሄር ጊዜ በሚለግመው ባርያም ፍርድ ይሆናል፡-

ሉቃ12:45-47 ”ያ ባሪያ ግን፡- ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል።የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል”
– በእግዚአብሄር ጊዜ የተስፋው ቃል የተሰጣቸው ህዝቦች ከእግዚአብሄር ፈቃድ በተቃራኒው ቆመው ስለነበር ፍርድ ውስጥ ወድቀው ነበር፡-
ሉቃ20:10-16 ”በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት።ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት።ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት።የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ።ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ።ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል?ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ።”
– የእግዚአብሄርን ጊዜ በተስፋ ለሚጠብቁ የሚሆን የማበረታቻ ቃል አለ፡-
ገላ.6:9-11 ”ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ።”
– በጊዜው እግዚአብሄር ያለው አይቀርም
2ጢሞ.4:2-4 ”ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።”
1ጴጥ.5:6-7 ”እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”
– ዝቅ ብለው እግዚአብሄርን ያገለግሉ ቀና የሚደረጉበት ጊዜ ይመጣል፡-
1ጴጥ.5:6 ”እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ”
ለፍጥረት ሁሉ ጊዜ ተመድቦለታል በጊዜው ካልተመለሰም ፍርድ ውስጥ ይገባል፡-
እግዚአብሄር የሚጣራበትና የሚያሳስብበት ዘመን አለው፡- እነዚህ ዘመናት ለሰው ልጅ የመዘጋጃ፣ የመታሰቢያ፣ እግዚአብሄርን የመፈለጊያና ማስጠንቀቂያዎች ይሆኑ ዘንድ በቃሉ ውስጥ ተቀምጠዋል፡-
በኖኅ ዘመን ስለሆነው ቃሉ የሚጣመለክተው ነገር አለ
በሎጥ ዘመንም እንዲሁ የሆነ አለ
የመጐብኘትሽ ዘመን የሚለው አለ
የተሰሩት መኖሪያ/ህንጻዎች ሁሉ የሚፈርሱበት ዘመን አለ
የአሕዛብም ዘመን አለ
የመጽናናት ዘመን አለ፡፡
የመታደስ ዘመን አለ፡፡
እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን አለ፡፡
ከዘላለም ዘመን የተሰወረው ምሥጢር የታየበት ዘመን አለ፡፡
የሚያስጨንቅ ዘመን የተባለ ጊዜ አለ፡፡
ሰዎች ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን አለ፡፡
የእንግድነታችሁ ዘመን የተባለልን ጊዜ አለ፡፡
እነዚህን ዘመናት ከቃሉ ማስተዋል ማለት ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር ተስማምቶ መሄድ በመጨረሻም መዳን ማለት ስለሆነ እነዚህን ዘመናት በማስተዋል ማጤን የግድ ነው፡፡ ዘመኑን እናውቃለን እያሉ ሲያውኩ የነበሩትን የእስራኤል አዋቂዎች ግን ጌታ በተግሳጽ ሲናገራቸው ነበር፤ እንዲህም ብሎአቸዋል፡-
ሉቃ12:56 እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው?
የእኛን ዘመን አተኩረን ስንመለከት ደግሞ በዚህ ትውልድ መሀል ብዙ የእግዚአብሄርን ጊዜ ያልጠበቁ ስራዎች በሰዎች ሲሰሩ እናያለን፡፡ የእግዚአብሄርን የስራ ዘመን ሳያስተውሉ ትውላዳቸውን ለርሱ ስራ መሾም፣ ጊዜው ሳይደርስ ጊዜውን ያልዋጀ እንቅስቃሴ ማድረግ እግዚአብሄርን እንደመቅደም ይቆጠራል፤ በእግዚአብሄር ነገር እግዚአብሄርን መቅደም ደግሞ ሞገስ የማያሰጥ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ለጠላት አሰራር የሚጋልጥ ነው፡፡
ለዚህ ችግር መፍትሄ የምናገኘው የእግዚአብሄር ጊዜ እስኪመጣ የኛን ጊዜ በትእግስት በማሳለፍ፣ ከእኛ ጊዜ ወጥተን (በእኛ ጊዜ ውጤት ከመጠበቅ ወጥተን) ወደ እግዚአብሄር ጊዜ በመግባት(እግዚአብሄር በሚሰራበት ጊዜ ለመገኘት በመዘጋጀት) ነው፤ ያኔ የሚሰራውን ስራ ከነውበቱ ፍጹም በሆነ መልኩ (ያለምንም ነቀፌታ ሆኖ) እናገኘዋለን፡፡ እኛም በሚሰራው ስራ ተካፋይ ለመሆን ስለምንታደል የምህረቱና የበረከቱ ተካፋይ እንሆናለን፡፡ ነቢዩ ዕንባቆም ታላቂቱን የእግዚአብሄር እጅ የሚጠብቅ ነቢይ ስለነበር ስራውን ለማየት በሚጉዋጉዋ መንፈስ እግዚአብሄርን በጸሎት ሲያስቸኩል በዕን.3:2 ላይ ይታያል፡፡
አዎ መፍራትስ ዝናህን ሰምቼ ፈርቻለሁ ግን ከመአትህ ይልቅ ምህረትህን ስለምታስቀድም ማረንና በዘመናችን ስራህን እንይ!