የጌታ ደቀመዛሙርት ቅድሚያ ሊሰጡዋቸው ከሚገቡ ነገሮች ፊት የሚገኘው (አውራና መሰረት የሆነው) የመንፈሳዊ ህይወት ጤንነት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ መንፈሳዊ ህይወት እንደ ስጋ ያለ ቁመና፣ ፍላጎት ወይም ስሜት ስለማይኖረው የጤንነቱ መለኪያ በስጋ ከሚደረገው ጋር አይመሳሰልምና የተለየ መፍትሄ የሚሻ ነው፡፡ መንፈሳዊ ህይወታችንን የሚመረምርና የሚያክም የእግዚአብሄር መሳሪያ የሆነው ህያው ቃሉ ነው፡፡ ቃሉ ስለሚሰራው ስራ መጽሀፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-
”የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስ ሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብ.4:12-13)
ተመርምሮ ያልተፈተሸ መንፈሳዊ ህይወት ይዘቱ ቁዋሚና ወጥ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ያልተጎበኘ፣ ያልተመረመረ፣ ያልጸደቀና ሞገስ ያላገኘ ህይወት ሲሆንም ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲህ በእግዚአብሄር ፊት መቅረብ ያልቻለ ስብእና በጸሎት መጠየቅና ጠይቆ መቀበል የሚችልበት አጋጣሚም አይኖርም፡፡
እየጠየቅን የማንቀበል ከሆነና እየጸለይን ፊቱ የማንደርስ ከሆነ ያለማመናችን ጉድለት ውጤት ብቻ እንደሆነ አድርገን ልንደምደም አይገባንም፤ የዛለ መንፈሳዊ ህይወት ውጤት መገለጫ ነው እንጂ፡፡ በዚህ ህይወት ውስጥ የሚታዩ ልማዶች አሉ፤ ቃሉ ሲገልጣቸው ይህን ይመስላሉ፡- ትመኛላችሁ፣ ትገድላላችሁ፣ ትፈልጋላችሁ፣ ትጣላላችሁ፣ ትዋጋላችሁ፣ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁ….
ትመኛላችሁ ሲል የፈለግናቸውን ነገሮች የራስ ለማድረግ በጎ አፈላለግ እየተከተልን እንዳልሆነ ሲያመለክተን ነው፡፡ ስጋዊ ምኞት በመራው አፈላለግ ነገሮችን ለማሳካት የምንሄድበትን መንገድ እግዚአብሄር አይቀበለውም፣ በዚህ ላይ በተመኘነው ልክ መቀበል ስለማንችል አመጽ ያረገዘ አሳብ እንሞላለን ማለት ነው፤ ውሳኔያችንም ከዚያ ቀጣይ ይሆናል፡፡
”በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ መጽሐፍ፡- በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፡- እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል።” (ያዕ.4:1-6)
የእግዚአብሄርን መንገድ ከልብ ሳንከተል ወደ ሁዋላ ሸርተት ካልን የሚከተሉን ነገሮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት እንችላለንን? ያን በአስተማማኝ መልኩ ካልመለስን በእግዚአብሄር ፊት መሆንና መቅረብ፣ መቆየት፣ እጁን መፈለግና ማግኘት አይሳካልንም፤ እንዲያውም ውስጣዊ ያለመረጋጋት/ያለመደላደል መንፈሳችንን እንዲያውክና እንቅፋት ሆኖ እንዲያቆጠቁጥ አመቺ ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡
”ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። አንተ እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ። እንደ ብልጥግና ሁሉ በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ። ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ። በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። ለባሪያህ መልካም አድርግ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ።” (መዝ.119:9-20)
ያለመረጋጋት ባጠቃው መንፈሳዊ ህይወት (አላማ ቢስና የእግዚአብሄርን ፈቃድ ባላስተዋለ ህይወት) ውስጥ ጉዞን መደዴ የሚያደርጉ የድግግሞሽ ልማዶች ቀስ በቀስ ካቆጠቆጡ ዝለት ያዝሉናል፤ ና እክሎች ሲበዙ በጊዜ ካልተገዙ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን የበረከት ጉዞ ለውጠው ድካም የተሞላ ያደርጉታል፡፡ መንገዱን ታካች አድርገውብን ስንደክም መንፈሳዊ ልምምዶቻችንን ያዘበራርቁታል፤ ዝብርቅርቅ ውስጥ የገባ ህይወትም የእግዚአብሄር አሰራር ይጋረድበታል፤ ከሚሆኑብን አንዳንድ ነገሮች መሀል የጎሉትን እንይ፡-
• እየጸለዩ ያለመጠበቅ
መቀበል ስለምንፈልግ እንጸልያለን፣ እስኪመልስ ግን በትእግስት መጠበቅ አንችልም፡፡ እንጸልያለን ግን ታግሰን መልሱን ለመቀበል አንወስንም፡፡ ትእግስት የሚባል ፈተና ስለሚያስጨንቀን በፊቱ መቆየት አንችልም፣ በምስጋና አንጠብቅም፤ ባለመጠበቅ ጠንቅም ጠላትን በህይወታችን ጉዳይ ጣልቃ እናስገባለን፤ ጠላት ያን ክፍተት ተጠቅሞም ውስጣችንን እየጎነተለ እንድናጉረመርም ይገፋፋናል፡፡ ለመሆኑ አኩርፎ እየተነጫነጨ ከለጋስ ፊት የቀረበ ለማኝ በምን ሞገስ የጠየቀውን ሊቀበል ይችላል? የራሱን እየጠየቀኮ አይደለም፣ ወይም ያበደረውን እያስመለሰም አይደለም፡፡ የለውም ስለዚህ እየጠየቀ ነው፣ ምናለ እንደለማኝ ዝቅ ቢል፣ ሞገስንም ቢቀበል? አንዳንዴ እግዚአብሄርን በቁጣ ስንጠይቅ በእርሱ ዘንድ ያስቀመጥነውን የራሳችን ንብረት ያለ ይመስላል፤ በዚያ መንፈስ እንደመታገስ ሳይሆን እንደማስገደድ ይዳዳናል፤ ያም ትህትናን እንዳንላበስ ያደርጋል፡፡ ትሁትና ታጋሽ ግን እየጸለየ ይጠብቃል፤ እየጠበቀም እንደተቀበለ አምኖ ያመሰግናል፡፡ እግዚአብሄር በፍቅር የቀረቡትን ጨርሶ ዝም አይልም፣ በእርሱ በሚተማመኑትም ይደሰታል፡፡ በፍቅርና በመታመን የቀረቡትን እስከ ረጅም ዘመን በሚደርስ መልስና በረከት እንደሚጎበኝ የዳዊት ጸሎት ያስተምረናል፡፡በሉቃ7:2-9 ውስጥ ያለውም ታሪክ ተመሳሳይ ነገር ያሳየናል፡-
”አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው፡- ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም፡- ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም፡- ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፡- ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፡- ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፡- እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው።”
ይህን መቶ አለቃ ተመልክተናል? የሚወደው ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ሳለ ስለ ኢየሱስ በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ እንዴት እንደ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን እንደለመነው? ልመናው ትእግስትን፣ ማክበርን፣ ዝቅታንና ፍቅርን የተላበሰ ስለነበር ያን የሚያውቅ ጌታ ጥያቄውን ይመልስለት ዘንድ እስከቤቱ ሊወርድ በቅቶአል፡፡ ኢየሱስ ወደቤቱ በቀረበ ጊዜ ዳግም ስለእርሱ የተናገረውን የትህትናና የእምነት ቃል ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፡- እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው።
አንዳንዴ ለመጸለይ እየሞከርንም የራሳችንን መፍትሄ በእግረ-መንገድ እንፈልጋለን፡፡ ከጎን መጠባበቂያ እቅድ (ፈረንጆች ፕላን ቢ እንደሚሉት) እናስቀምጥና ወደፊቱ እንመጣለን፡፡ ግን ይህቺ ጥበብ የምትመስል ነገር መልሳችንን ይበልጥ የምታርቅ ክፉ መፍትሄ ነች፡፡ ጠያቂ ጸላይ ነን፣ መፍትሄ አፈላላጊም ነን፡፡ ህሊናችን አትፀልይም እንዳይል ለውስጣችን ጸሎታችንን እናሰማዋለን፤ ከጸሎት በሁዋላ ግን ትግስት የለንምና በራሳችን ብልሀት መፍትሄ ለማምጣት እንደክማለን፡፡ እየጸለይን ቢሆንም ጸሎታችን በእምነት መጠባበቅ ስለሌበት ከእግዚአብሄር እጅ መቀበል አንችልም፡፡
• እያመኑ ያለመቀበል
በእግዚአብሄር ላይ ያለን እምነት ጠንካራ ሆኖ ሳለ የምንጠይቀውን ባለማወቅ ምክኒያት ላንቀበል እንችላለን፡፡ የሚሰጠን እንደፈቃዱ የሆነውን ስንጠይቅ መሆኑን መርሳት ያን ያስከትላል፡፡ ዞሮ ዞሮ መልሳችን ሲቆይ ትግስት በማጣት ከእምነት መንሸራተት አይቀርም፡፡ ሁሌም ቢሆን የራሳችን ብልሀት ነው የሚያደናቅፈን፡፡ እስቲ የምንጸልየው እንደቃሉ መሆኑን እርግጠኛ ሆነን እንጸልይ፣ እርሱ እንደተናገረው በእርግጥ እንቀበላለን (ያዕ.4:1-6)፡፡
ማር.11:24-25 ”ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት።”
እምነት ከእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ካልወጣ ምንጩ ተጠልፎ ከጠላት አሰራር ጋር እንዳይገናኝ ያስፈራል፡፡ በውስጣችን የምንሰማቸው መልእክቶች ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ድምጽ የወጡ እንደሆኑ መቶ በመቶ አምነን በነርሱ ላይ በመመርኮዝ የምንጸልይና የምንመሰክር አንጠፋም፡፡ ለምን ድምጾቹን ሰማን ሳይሆን የሰማናቸውን ለምን በቃሉ አልፈተሸናቸውም፣ ከእግዚአብሄር መሆናቸውንስ እንዴት እርግጠኛ ልንሆን አልቻልንም? ነው ጥያቄው፡፡ የምንጸልየውን እንድንቀበል የሚያስችል እምነት ግን እነሆ፡-
”የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ሮሜ.10:13-17)
• ሳያምኑ መፈለግ
እግዚአብሄር ሲፈለግ ከነሙሉ ክብሩ መሆን አለበት፡- በሙሉ ፍርሀትና ፍቅር ጭምር ማለት ነው፡፡ እንደሰፈር አማልክት ሊመጣም ላይመጣም ይችላል ወይም ሊያደርግ ወይም ላያደርግ ይችላል በሚል በተከፈለ አሳብ ሳይሆን ማለት ነው፡፡
ኢሳ.55:6 ”እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”
ያደርግ ይሆናል በሚል በተከፈለ እምነት ብቻ ሳይሆን በስሚ ስሚ ወይም ለእከሌ ስላደረገ ለእኔም ያደርጋል በሚል ግምት በልብ ሳያምኑ ውጤት መፈለግ ካለም አይገኝም፤ እኔም ልጁ፣ እርሱም/እርሱዋም እንዲሁ፣ ለነርሱ እንዲህና እንዲያ ካደረገ ለእኔም ይደረግ ማለት፡፡ ቢደረግ ጥሩ ነው፣ ግን አድራጊው ያደርገዋል ወይስ አያደርግም? ያን በጸሎትና በመጠባበቅ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡
የህዝቄዋ ልጆች ታሪክ ሳያምኑ መንቀሳቀስ የሚያስከትለውን አደጋ ያሳያል፡፡ እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ እንደሰበከ ለመስበክ፣ እርሱ እነደሰራ ለመስራት ተመኙ እንጂ እንደርሱ ወደ እግዚአብሄር ለመጠጋት አልወሰኑም፣ እንደርሱ ያለ የህይወት ይዘትም አልነበራቸውም፡፡በዚህ ምክኒያት የገጠማቸው ችግር አስደንጋጭ ነበር፡-
”አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ። ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም።” (ሐዋ.19:13-16)
• ያለ አላማ መጸለይ
በእግዚአብሄር ፊት ለመቅረብ የልብና የመንፈስ ዝግጅት ማድረግe ይጠይቃል፡፡ የምንቆመው ንጉስ ፊት ነው፣ ያውም የነገስታት ንጉስና የአማልክት ሁሉ አምላክ ፊት፡፡ ስለዚህ ለምንድነበር የቆምነው? ምን ልንል? ምን ፈልገን?
ዝግጅታችን እርሱን ከማሰብ ይጀምራል፤ ክብሩን ሀይሉን ዙፋኑን መላእክቱን የሚቀርብለትን አምልኮ በመንፈስ አለም ስላሉ መንፈሳዊ ክንዋኔዎች በሙሉ በውስጣችን ሊመላለስ አስፈላጊ ነው፡፡ በምድር ላይ ለሚገዙን ነገስታት እንዴት ያለ ክብር እንሰጣለን? ጥንቃቄያችንስ? የምንለብሰውን የምንናገረውን? ደስታችንን/ሀዘናችንንም ቢሆን የምንገልጥበት መንገድ ከመንደርና ከተራው አካሄድ የወጣ ፍጹም ሊሆን አይችልም/አይገባምም፡፡ ይሄን ጥቂት ክብር ወስደን ለሁሉ ፈጣሪ ሊሆን የሚገባውን ነገር ማሰላሰል ነው፡፡
ዕብ.12:22-24 ”ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።”
የመንፈሳዊውን ስፍራ መልክ በመንፈስ ላይ ማጋባት ውስጥን ለደስታ፣ ለንሰሃና ለምስጋና ያነሳሳል፡፡ የምቆመው ለካ በእንዲህ ያለ ታላቅ አምላክ ፊት ነው የሚለው አሳብ በፊቱ ለጸሎት የሚያቀርበኝ ነው፣ የርሱን ክብርና መገኘት የሚያስናፍቀኝ ነው፡፡
የዳዊት የዘወትር አላማና ጉጉት ምን ነበር?
መዝ.5:5-7 ”እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ። ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ። ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፤ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።”
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። መዝ.65:1-2 አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ጸሎት ይቀርባል። ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል።
በጸሎት ፍቅር መያዝ እንዴት ያለ መልካም ምርጫ ነው? ጸሎት ግን እንደ ፈቃዱና በአላማ ካልሆነ ምንም ጥቅም አለው፡፡
አሞ.5:14 ”በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።”