እየጠየቁ ያለመቀበል{1..}

ቤተክርስቲያን

መዝ.4:2-8 ”እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? እግዚአብሔር በጻድቁ እንደ ተገለጠ እወቁ፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል። ተቈጡ፥ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ፤ በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ። የጽድቅን መሥዋዕት ሠዉ፥ በእግዚአብሔርም ታመኑ። በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።”
ምን ይሆን ጉድለቱ? ከማን ይሆን ጥፋቱ? “የጽድቅን መሥዋዕት ሠዉ፥ በእግዚአብሔርም ታመኑ። በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው።” እያለን ነው፡፡ በጎውን ማን ያሳየናል ብሎ መደናገር የሚያሳጣውን ቀጥሎ እንመልከት፡-
– እየጸለዩ ያለመጠበቅ፣
– እያመኑ ያለመቀበል፣
– ሳያምኑ መፈለግ፣
– ያለ አላማ መጸለይ፣
– እንደቃሉ ያለመቅረብ፣
– በጌታ ደስ ያለማሰኘት፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ስንጉዋዝ ለምን እነኚህ ነገሮች ሊያገኙን ቻሉ?
በቅድሚያ መፈለግ ያለብንን ካላወቅን የጠየቅነውን ልንቀበል፣ ልናገኝም አንችልም፡፡ ከእግዚአብሄር የሆነውን ከመቀበላችን በፊት እግዚአብሄር አምላክ እንዲሆነን መፈለግ ተገቢ ነውና፡፡ እርሱን ሳይፈልጉ እጁን መፈለግ አይቻልም፡፡ እርሱን ሳያገኙ የእጁን ማግኘትም አይቻልም፡፡ ብዙ ጊዜ መቀበል ያለብንን ነገር በቅጡ ስለማናውቅ የሚበጀውን መጠየቅ ሳንችል እንቀራለን፡፡
ኢሳ.31:1-2 ”ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል።”
ሲቀጥል መጠየቅም፣ መናገርም፣ ብሎም መፈለግም ቅርበትን አጥብቆ ይሻል፡፡ ወደ እግዚአብሄር የቀረበ እምነቱን በህይወቱ ውስጥ ትርጉም ባለው መንገድ ሊያሳይ እንደቃሉ ሊኖረው ይገባልና፤ ሰው በእግዚአብሄር ሲታመን በሁሉ አቅጣጫ እግዚአብሔርን ያስቀድማል፤ እግዘአብሄር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? ሲል ፍርጥም ይላል፡፡ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው ሲል አምላኩ በጠላቱ ላይ የሚፈጥረውን በቀል አስቀድሞ በማየት ነው።
የልብ አይናችን ሲከፈትና እይታችን ሲሰፋ በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል ብለን በነገራችን መሀል እግዚአብሄርን ጣልቃ እናስገባለን። ሀያላን የሚባሉ በሀይላቸው ሲመኩ ሰዎችም በእነርሱ ተስፋ ሲያደርጉ በየእለቱ የምናየው ነው፤ ሆኖም በሰዎች ላይ የሚደገፉ ስንፍና ያደርጋሉ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ አያገኙም፡፡
እስራኤላውያን ከረዳታቸውና ከአዳኛቸው ላይ አይናቸውን አንስተው በስጋ ላይ ሊደገፉ የሞከሩት የእርሱን መንገድ ቸል ብለው ነው፡፡ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! ሲል የሚያስጠነቅቀውም ክፉውን ነገር ሲያመጣ የተደገፉባቸው ስጋዊ ሀይሎች ጭምር እንደሚጠፉ ስለሚያውቅ ነው፡፡
በሌላ በኩል የእግዚአብሄርን ፈቃድ ባለማወቅ ምክኒያት የምንፈጥረው ስህተት ብዙ መዘዝ እንደሚያመጣ አስቀድመን ለማየት መሞከር ይገባናል፤ ስህተቱ ፍላጎታችንን ከፈቃዱ ጋር ያጋጫልና፡፡ ተጋጭተን ከእግዚአብሄር ጋር ጥለኞች በሆንንበት የህይወት ይዘት ውስጥ ምን አይነት ልመና ወደ እርሱ ልናቀርብ ይቻለናል? መልስስ ከእርሱ እንዴት መጠበቅ እንችላለን? የሚበጀው ግን ቅድሚያ ከአሳቡና ከፈቃዱ ጋር መስማማትና ምህረትን መቀበል ነው፡፡ እግዚአብሄር በነቢዩ አሞጽ በኩል ለእስራኤል ያንን ያሳስባል፡፡በአሞ.5:4-15፡-
”እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላል፡- እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ። በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።” ይላል፡፡ እግዚአብሄር ያንን የተናገረበት ምክኒያት ሲገልጽ ደግሞ እንዲህ ብሎአል፡-
”… ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ፥ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልመውን፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸውን፥አምባውም እንዲፈርስ በብርቱ ላይ የድንገት ጥፋት የሚያመጣውን ፈልጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው። በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ። ድሀውንም ደብድባችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም። ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ፥ በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና።”
ህዝቡ በአምላካቸው መገኘት አካባቢ ይተገብሩት የነበረው ክፉ ልማድ ወደ ጥፋት እየመራቸው መሆኑን ቸል ብለዋል፤ ቸልታቸው ስላላስፈራቸው ምኞታቸውን ብቻ እንዲከተሉም ተገድደዋል፡፡ ነገር ግን ክፉ የነበረው አፈላለጋቸውን መርምረውና አግኝተውት ቢሆን ኖሮ ምን በጎነት እንደሚያገኛቸው ቃሉ እንዲህ ያስገነዝባል፡-
”… ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል። በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል። ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል።” (አሞ.5:15)
በእርግጥ ጸልየን የምንቀበለው ከሰጪው እጅ ላይ ቢሆንም መቼና እንዴት የሚሉ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት ግን በራሱ በአማኙ መንፈሳዊ አቁዋም መስተካከል ልክ ነው፡፡ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ ያለውም እስራኤላውያን የህይወት ይዘታቸውን በንሰሀ አስተካክለው በይቅርታው ሊጎበኛቸው ፈልጎ ነበር፡፡
ጌታ እንድንለምነውና እንዲሰጠን ስለሚፈልግ ለምኑ፣ ፈልጉና አንኳኩ ሲል ያበረታታናል፤ ልመናችን እንደቃሉ እስከሆነ ድረስና ፍላጎታችንም ፈቃዱን እስካልተቃወመ ድረስ የፈለግነውን እንድምናገኝ እርግጥ ነው፡-
ማቴ.7:7-11 “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው?ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?” በማለት አስተማማኝ ዋስትና ሰጥቶናል፡፡”
እግዚአብሄርን በመፈለግ የሚገኝ ነገር
እግዚአብሄር በኢሳ.45:19 ውስጥ ሲናገር ”በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፡- በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ” አለ፡፡
እግዚአብሄር በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም የሚል ማስተማመኛ ከሰጠን ጠይቆ ለመቀበል እርሱን መፈለግና መጽናት ይገባል ማለት ነው፡፡ ፍለጋው በመሰላቸት ሳይሆን በጽናት እርሱን በመጠበቅ ሲሆን ውጤታማ ነው፡፡ በጽናት መፈለግና ከርሱ መጣበቅ ማግኘትን ብቻ ሳይሆን በቤቱ ተተክሎ መጽናትን የሚያህል ዋጋ አለው፡-
1ዜና.16:11፤ ”እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።”
በእምነት በሆነ ምስጋናና አምልኮ እግዚአብሄር ሊከብር ያስፈልጋል፤ እኛም በዚህ አሳብ ለፍቅሩ ተሸንፈን ጠላቶቻችንን እናሸንፍ፤ እግዚአብሄርን የሚያከብሩ ሁሌም የከበሩ ናቸውና፡፡ ይህን የሚከተል በእምነት በመዳን እለት እለት ይለመልማል፤ በዚያም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ተስፋ በህይወቱ ስለሚጸና ወደ እርሱ መጠጋቱ እለት በእለት ከእርሱ የሚቀበለውን በረከት ያበዛለታል፡፡
2ዜና.15:2-6 ”አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፡- አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ። እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር።”
ከእስራኤል ታሪክ እንደምንማረው ህዝቡ ብዙ ዘመን እውነተኛ ባልሆነ አምላክ ታምኖ ነበር፤ በባእድ አማልክት ተወርሶ በነበረበት ዘመንም እግዚአብሄር በርቀት ስለነበር ስርአቱን መሰዊያውንም ተዉት፡፡ በንሰሀ ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ ግን የራቃቸው አምላክ ቀረቦአቸዋል፣ እነርሱም አግኝተውታል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በሆኑበት ዘመን እርሱ ከእነርሱ ጋር ሆነ፤ በዚያን ዘመን ሲፈልጉት ሁሌ ተገኘላቸው፡፡
በመፈለግ ውስጥ ህዝቡ የሚከለከለው ነገር አለ
ወደሌላ አማልክት ፊታቸውን የመለሱ እግዚአብሄርን ስለተዉ ልመናቸው አይሰማም፣ ክእርሱ ዘንድ መልስ አያገኙምም፤ እንዲያውም ወደ ሌላ ድምጽ እንዲዞሩ ጥፋትም እንዲገጥማቸው ማሰናከያ ይሆንባቸዋል፤ ይህም መርከስና ከእግዚአብሄር ፊት መሰወር ያመጣል፡፡
ዘሌ.19:31 ”ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” ብሎአል እግዚአብሄር፡፡
የበዙት የእስራኤል ነገስታት በጣኦት/ በአማልክት ተይዘው ከፊቱ ስለጠፉ በችግራቸው ሳይደርስላቸው ቀርቶአል፡፡ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉስ በእግዚአብሄር ስላልታመነና እግዚአብሄር ስለተወው በጨነቀው ጊዜ ወደ መናፍስት ጠሪ ፊቱን መልሶ ነበር፡፡ ፊትን ከህያው አምላክ መልሶና ባእድ አምላክ ፈልጎ የድል መልስ መጠበቅ አይቻልም፡፡
1ሳሙ.28:7 ”ሳኦልም ባሪያዎቹን፡- ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፤ ባሪያዎቹም፡- እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት።”
አምላክ እያለ ወደ ክፉ መናፍስት መሄድ፣ ጻድቁ እያለ እርኩሳንን መሻት የእምነት መሳት ያመጣው ተጽእኖ ነበር፡፡ የነገሮች ባለቤት እያለ ያልተገባውን መንፈስ መጠየቅ ቁጣን መቀስቀስ ነው፡፡ የእርኩስ መናፍስትን እውቀት መፈለግ ምን ማለት ነው? ከእግዚአብሄር ይልቅ በአጋንንት መታመንስ ምንን የሚያመላክት ነው? ሳሙኤል በነበረበት ዘመን ንጉስ ሳኦል ወደሌላ አማልክት እንደሄደ አናነብም፤ አዎ፣ በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመሩ ሰዎች በሚኖሩ ጊዜ ምድሪቱ ሳትቀር ታርፋለች፣ ያ በሌለበት ሁኔታ ግን መናፍስት ጠሪዎች ሰውን ከክፉ መናፍስት ጋር በማገኛኘት ነፍስን ያስጨንቃሉ፣ እግዚአብሄር ከሰው ጋር እንዲለያይና ምድሪቱ በመርገም እንድትመታም መንገድ ይከፍታሉ፡፡
እኛስ ብንሆን ከዚህ መንገድ በምን ተሽለናል? ከእስራኤል መንገድ የራቅን ነንን? ምድራችን ለምን ተዋረደች ብለን ራስን መመርመር ማስተዋል ነው፡፡ የክፋት አሰራር እርቃናችንን ስላስቀረን፣ ምድራችን ላይ የተሰወረ መናፍስታዊ አሰራር እውነትንና እውነተኛውን አምላክ እንዳንቀርብ ስላደረገ ጠፍተናል፤ የሀሰተኛ ነቢይ መንፈስ ትውልዱ ለአብረሃም አምላክ እንዳይገዛ በማድረግና በተለያየ የእምነት አገዛዝ በመከፋፈል መንፈሳዊነትን አሳጥቶናል፣ የመናፍስት አሰራር እንዲህ አገራችንን ውድቀት ውስጥ ወርውሮአታል፡፡ ብዙ የእምነት መሪዎችና አንቀጽ አነብናቢዎች አንዱን አምላክ ሳይሆን ብዙ መናፍስትን እየሳቡ በተለያየ መንገድ ህዝባችንንና ምድራችንን በእርግማን እያስመቱ ነው፡፡ ከምእራቡ አለም የሚገባ ስጋዊ ጥበብና ታክቲክ አማኞችን እንደ ቅርጫ ተቀራጭቶአል፤ አፍሪካዊው ባእድ አምልኮ ጭራሽ ፍልስፍናው ላይ ተደርቶ ጥንቆላና ልዩ መናፍስት ሳቢነትን አለማምዶአል፡፡
1ሳሙ.28:9-12 “ሴቲቱም፡- እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው። ሳኦልም፡- ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት።ሴቲቱም። ማንን ላስነሣልህ? አለች፤ እርሱም። ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ።ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን፡-። አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው።”
መናፍስት ጠሪዋ ያለችውን ልብ ማለት ያሻል፤ እርሱዋ እንዲህ አለች፡- “ሳኦል የተባለው ንጉስ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ያደረገውን ታውቃለህ?” እርሱ የሳሙኤል ዘመኑ ሳኦል ሲሆን አሁን ያ ማንነት የለም፤ አሁን ያለው ሳኦል በመናፍስት የተጠቃውና የእግዚአብሄር መንፈስ የራቀው ሳኦል ነው፡፡ አዲሱ ሳኦል አእምሮውን የሳተ ነበርና በእግዚአብሄር ስም ስለመተት ምሎ ሴቲቱን ወደ ሙዋርትዋ እስከማስገባት ደርሶ ነበር፡፡
እምቢተኛና ክፉዎችን ያሳውራል
ዘፍ.19:11 ”በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።”
እግዚአብሄርን የማያምኑ ክፉ ትውልዶች የጻድቅ ሰዎች ጠላቶች ሆነው ቢነሱም ባደረጉት ነገር በቅጣት የሚጎበኙበት ወቅት አለ፡፡ የሰዶም ሰዎች እጅግ ጸያፍ ስራ የተሞሉ መሆናቸው ሳያንስ የጻድቁ ሎጥን ነፍስ በአመጻቸው ያስጨንቁ ነበር፡፡ በእርሱም ዘንድ ያለ እምነቱ በዚያው ልክ መፈተኑ አልቀረም፤ ቢሆንም በመከራ ቀን እግዘአብሄር የጻድቃንን ነፍስ ከጥፋት ይታደግ ዘንድ እንደተናገረው አደረገ፡፡
በአዲስ ኪዳን በማያምኑት ላይ የሚወርድ ቅጣት በነፍስ ሞት ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ጥፋቱ እጅግ ይልቃል፡-
ሮሜ.1:26-28 “… ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ስለሚል ማለት ነው፡፡