እውነትን ፍለጋ(2..)

የእውነት እውቀት

እግዚአብሄር ትሁት ለሆኑ በልባቸውም ለሚፈልጉት ለእነርሱ እንዲህ ይላል፦
“እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። ባሪያዎቹ የእስራኤል ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱንም የአፉንም ፍርድ። እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና” (1ዜና16:10-17)
በቃሉ እንደተመለከተው እግዚአብሔርን መፈለግ ደስታን መፈለግ ነው፤ እግዚአብሄርን መፈለግ በህይወት ጸንቶ ለመኖር የሚያስችል ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሄር ህዝብ አምላካችሁን በብርቱ ፈልጉት ሲል መንገዱን ያሳያል፤ ወገኖች ከፈለጋችሁት ታገኙታላችሁና እርሱም ያጸናችሁዋልና፤ ደግሞ አስተማማኝ ክንዱን በመደገፍና ሁልጊዜ ከርሱ ጋር በመተማመን ለመኖር ያለማቁዋረጥ ፊቱን ፈልጉ፤ እርሱን ልታገለግሉ የተሾማችሁ ባሪያዎቹ መታሰቢያ የሆነች ድንቅ ስራውን አስቡ፥ ተአምራቱንም የሰጠውን የአፉንም ፍርድ አስቡ ይላል። እግዚአብሄርን የምንሻው፣ የምንታመንበትና የምንፈልገው እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ስለሆነ ነው።
ፍለጋው ግን በእስራኤል ልጆች ዘንድ እንዳለው እንደ ዳን ወገን በደቦ፣ በትርምስ፣ በሰዋዊ ፈቃድ ወይም በአህዛብ የአምልኮ ስርአት አይደለም፤ ምክኒያቱም በእንዲህ ይለ ትርምስ አካሄድ የእግዚአብሄር ክብር አይታይም፣ መንገዳችንም ጽድቅን አያመጣም።
ለእርሱ አምላካችን ተለይተን ከራሳችን መርህ ወደ እርሱ የህይወት መስረት እንድንመለስ ለሰዎች የወንጌል ጸጋን የሰጠው በዚያ የምስራች ፍጹም የህይወት ለውጥ እንድናገኝ ነው፤ እንዲሁም ወንጌሉ ይሰበክ ዘንድ እግዚአብሄር ያዘዘው ሰዎች በውስጣቸው የታተመው ግን በውስጣቸው ታፍኖ የተሰወረው የአምልኮ ተሰጥኦ እንደጠፋ እንዳያልፍ፣ ከድነት ባሻገርም ዳግም ሳይደበዝዝ ለእውነተኛው አምላክ እንድንገዛ ነው። ደግሞ የአብረሃም አምላክ እንዲመለክ የሚጋበዝበት ምክኒያትም በሰዎች ልብ የፈጠረው እርሱን የመሻት ፍላጎት እንዲሙዋላ ነው።
“የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር፦ ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ።”(2ዜና1:5-7)
የሰሎሞን ከእግዚአብሄር ጋር የጀመረው ጉዞ በሚታየው መልኩ ስኬታማ የሆነው ወደ አምላኩ ማደሪያ ስለተጠጋ ነበር፤ ሰሎሞን ከጉባኤው ጋር በአንድነት ወደ ማደርያው ተጠጉ፣ ራሳቸውን አቀረቡ፣ ወደ ህያው አምላክ በተጠጉበት አጠጋግም እርሱ ተገለጦአል። ሁሌም በምሪት ሊያመለክተን ወደ እኛ ሲቀርብ ፍለጋችን ይሳካ ዘንድ ቅድሚያ የሚያሳውቀን እርሱ ማን መሆኑን ነው። ከፊተኞች ወላጆቻችን (አዳምና ሄዋን) ውስጥ የጠፋውን የእውነተኛ አምላክ እውቀት ቀርቦ በብርሃኑ ያበራልናል። በየትኛውም ዘመን ያደረገው ይሄንን ነው፦ ለአብረሃም ቢባል ለይስሃቅ ደግሞም ለያእቆብ ያንን አድርጎአል። የአብረሃም የተስፋ ዘሮች በሙሉ ለአባቶቻቸው ተገልጦ የነበረው አምላክ እውቀት በጠፋባቸው ዘመን ሁሉ ደጋግሞ ይመጣና እውቀቱን ያበራ ነበር።እንዲህም ይላል፦
“አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ። እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር። እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።”(2ዜና.15:2-7)
እግዚአብሄር ሳይመጣ በፊት እስራኤል ብዙ ዘመን በራሳቸው ፈቃድ ተጉዘው ነበርና ያለ እውነተኛ አምላክ ምሪት ሲንከራተቱ ነበር፤ በነዚያ ዘመናት ጎስቋላና ተጠቂ ነበሩ። መንገዱን የሚመራቸው አጡ፣ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። እግዚአብሄርን በተዉበት ዘመን እርሱም ተዋቸው፣ በጠላት እጅ ሲንገላቱ ቆይተው በነቁ ጊዜ ግን ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ፈለጉት፣ እርሱን በፈለጉት ጊዜ እርሱም ተገኝቶላቸው ነበር። እስራኤላውያን በውድቀታቸው እስኪማሩ አምጸው ባያፈገፍጉ ኖሮ ለብዙ ዘመን ተትተውና ለጠላት ተጋልጠው ባልኖሩ ነበር።
ዛሬም ሰዎች የተበሰረልን የእውነት ቃል ተጽእኖ አሳድሮብን ወደ ፈቃዱ እንዳያመጣን ታግለነው ነው እንጂ በተገለጠው እውነት አማካኝነት ወደ እግዚአብሄር አላማ ውስጥ ፈጥነን የምንገባበት የተመቻቸ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ሰፊ ነው፡፡ ልብ በታሰረበት የአሳብ ሰንሰለት ተሰውሮ ከሚገኝበት ወህኒ እንዲወጣና ወደ አዲስ እይታ እንዲገባ የርሱ እውነት ሊገለጥ ይገባል፡፡
ታዲያ መቼ ነው ከራሳችን ክልል ወጥተን ወደ እግዚአብሄር አሳብ ውስጥ የምንገባው? እንዴትስ ነው ያን ማድረግ የምንችለው አያልን በትኩረት ካልጠየቅን መፍትሄው ቅርብ አይደለም፤ የዚህ ችግር መነሻ እኛው እስከሆንን መፍትሄያችን ጅማሬ የሚያገኘው ከእኛው ነውና፡፡
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፤ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ።”(ኢሳ.55:1-3)
እግዚአብሄር ውስጣችን ያለውን ስለሚያውቅ ጥማት አለባችሁ ይለናል፣ ውስጣችሁ ስር የሰደደና ምላሽ ያላገኘ ርሃብ አለና ንቁ ይለናል፤ ንቁ ወደ እኔ ተመልከቱ፣ የጥማታችሁ እርካታና የረሃባችሁ ፋታ ከእኔ ዘንድ ስላለ ኑ ይላል፣ስሙ ይላል። በመቅረብና በመስማት በረከት ህይወት፣ ምህረትና የዘላለምን ቃል ኪዳን እንድንቀበል ራሳችንን ማሸነፍ ግድ ነው።
የእኛ ትውልድና ዘመን ሰው ግን እኔና የእኔ የሚለውን የራስ ፍላጎት፣ ምቾትና መሻት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲከበርለት የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ ይሄ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የእግዚአብሄርን አሳብ እየተጋፋም የሚገኝ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሰው የራሱን ለመተው ባለመፍቀዱ በእግዚአብሄር አሳብ ውስጥ ሊገኝ አልቻለምና፤ ፍላጎቴን አትንኩ ካለ ቃሉን በእኔ ነገር ገደብ አትለፍ እያለው ነው፣ ምኞቴን አትቃወም እያለ፣ በእኔ ላይ ያየሀውን ችግር አታመልክተኝ እያለ ነው፣ ቃሉ የወደድከውና ለራስ ልታደርገው የምትሮጥለት ሁሉ አይበጅህም ብሎ አካሄድን ከተቃወመ ችግሩ የማን ነው? እኛ ካለን ከነገራችን ሁሉ እምቢታ የሚባል የታዛዥ መንፈስ ባላንጣ በልባችን ስላለ መዘዝ ነው የሆነው፡፡
በምህረቱ ብዛት መዳን አግኝተን በተንኮል ከምንመላለስበት የሚያሳፍር ስውር ነገር ከተነጠልን ወዲያም አስተውሎት ካጠረ በሌላ መልኩን በቀየረ ፈተና ልንታደን እንደምንችል የሚከተለው ቃል ያሳየናል፦
2ቆሮ.4:2 ”ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።”
ሰው ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ብቻ ሳይሆን በምህረቱ አጥር ውስጥ ገብቶ (ደህንነትን አግኝቶም) እንኩዋን በመስማት መታዘዝ ላይ እስካልደረሰ ድረስ አዲስ አይነት ልማድ አንቆ በተለየ የድግግሞሽ ህይወት እንዲመላለስ ያስተዋል፡፡ ይህ ከፊተኛው ችግር የከፋ ነው፤ ክርስትና አዲስ ህይወት ሆኖ ህያውነቱ በእኛ የሚገለጥ በአለምም በልዩነት የሚታይ እንጂ እንደ ተዳፈነ እሳት አመድ ለብሶ አለሁ ቢል የተጽእኖ ሀይሉ የደከመ ነውና ከንግግር ያለፈ የሚታይ ውጤት አይይዝም፡፡ ባለማወቅ ወይም በድፍረት የሚዳብር ልማድ የተገለጠውን የክርስቶስ ህይወት በእኛ እንዲዳፈን ያደርጋል፡፡
የፈረሰልን ከባቢ ግድግዳ በነፍሳችን ዙሪያ ቀድሞ የነበረ ሆኖ ሳለ እንደተወገደ አውቀንና ዳግም ብቅ እንዳይል መጠንቀቅ ሲገባን በእኛው እጅ ተመልሶ ከተገነባ እንዴት ያለ ጥፋት ነው የሚሆነው? የተፈታልን ሰንሰለት ላይ እጃችንን ማስገባትም ወዶ መታሰር ነው፡፡ የሀይል መንፈስ ያውም የትንሳኤ መንፈስ የሆነ የእግዚአብሄር መንፈስ እንዴት ያለ ነጻነት እንደሰጠን፣ በዚያ ብቃት እንዴት ባለ መፈታት እንሄድን እንደነበረ የምናውቀው ነው፤ ያን የሚያሳፍረውን ስውር መንፈሳዊ ተጽእኖ ከላያችን አንከባልሎ ያቆመን ህያው ቃል ከአለም ትምህርት ጋር ቢቀላቀል ግን አቅም እናሳጣዋለን፣ መስራት ያቆማልና፤ ፈጥኖም የሚያድነው እውነት እንዳይገለጥ ይሆናል፤ እንዲያውም ፍርድ አምጥቶ ያጠፋል፡፡ እውነት ግን አሁንም ይግዛን፤ ደግሞ እስከፈቀድን፣ እሺ እስካልን ምህረቱ ብዙ የሆነ አምላክ የንሰሀ ፍሬ እንደሚሰጠን እሙን ነው፡፡
”…ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።” (1ተሰ.4:10-12)
ከተገዙ አይቀር ምንም ሳይቀር ከነሙሉ ማንነት፣ ከተሰጡም አይቀር ምንም ሳይቆጥቡና ሳይሰውሩ ሲሆን እንጂ ያ ካልሆነ በተንኮል የመመላለስ አካሄድ ይሰለጥንብንና በዚያ መታሰር ይሆናል፣ ንጉስ ሰሎሞንን ደግመን እንይ፡-
“ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር።” (1ነገ.3:3)
ንጉስ ሰሎሞን በህዝቡ ፊት እግዚአብሄርን እንዲወድ ተመስክሮለታል፣ ህይወቱ ግን ከቀድሞው ደረጃ እያሽቆለቆለ ሄዶ ነበርና አምልኮና መስዋእቱ እንከን ያለው ሆነ፤ ያ ሰበብ ሆኖበትም ህይወቱ እንዲነቅዝ መንገድ ከፍቶበት ነበር፡፡ ሰሎሞን እግዚአብሄርን የሚወድድበት ምክኒያት ነበረው፤ እንዴት እንዳነሳውና እንደምን ባለ ከፍታ እንዳወጣው ያውቃልና ይወድደው ነበር፤ ልማዱ ግን ስለበረታበት ከፋበት፣ አንገላታው መጨርሻም ላይ ጣለው። አባቱ አስቀድሞ ሲመክረው እንዲህ ብሎአል፦
“አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።” (1ዜና.28:9)
ሰሎሞን በንግስናው ጅማሬ እንደሆነው ሊቀጥል ለምን አልቻልም? በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ይገኝ አልነበረምን? እርሱ ከህዝቡ ጋር በአንድነት የአምላካቸውን ፊት ይፈልጉት አልነበረም ወይ? ንጉሱ ከጊዜ ብዛት የአምላክ ነገር እየተረሳው ሄዶ ነበርና ከፊቱ ወደሚቆምበት የአህዛብ ጣኦት መለስ አለ፤ በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀርቦ እንዳልነበርና እጁን ወደ ሰማይ ወደ ህያው አምላክ እንዳልዘረጋ በአምላኩ በእግዚአብሄር ፊት ምናምንቴ ወደሆኑና ወደ ተናቁ ጣኦታት ማዘንበሉ ከፍተኛ ውድቀት ውስጥ እንዲጣል አድርጎታል። ከእግዚአብሄር ጋር የጀመረው ጉዞ ስኬታማ እንዳልነበረ ከአምላኩ ማደሪያ ሲርቅ የሚጥለው መንፈስ ሊጠጋው በቅቶአል፤ ህያው አምላክን የተጠጉ ወገኖች የተጠጉበትን አጠጋግ አጥፍተው ከእርሱ ሲርቁ እርሱም እንዳልተገለጠላቸው ሆኖ እስኪረሳቸው ይሰወርባቸዋል። በምሪት ይኖር የነበር ህዝብ በእንዲህ ያለ አስከፊ ነገር ውስጥ ወድቆ በጨለማ ሲርመሰመስ ማየት እጅግ አሳዛኝ ነው።
“ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም። ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ። ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም። በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ። ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው። ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም። እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው።” (1ነገ.11:4-14)