እውነትን ፍለጋ(1..)

የእውነት እውቀት

“ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?” (ሚል.2:10)
አንድ አምላክ የፈጠረን መሆኑን መናገር በአንደበት ከመግለጽ ባለፈ አለማትን በሞላ የምንመረምርበትና የምናይበት የቃል ምስክር ነው። በቃሉ በኩል አለምን ለሚመለከተው ብዙ ነገር ያይበታል፣ የሚያጸና እውቀት ይገበይበታል፣ እውነትን የሚሻም ከሆነ ጥልቅና ሰፊ እውቀት ያገኝበታል። በአለማት ውስጥ ምን ያህል ብዛት ያላቸው ፍጥረታት በእግዚአብሄር ጥበብ ተፈጥረዋል? የሰው ልጅ ርቆ ሳይሄድ በዙርያው ያሉትን እንኩዋን ቢቆጥር አይጨርሰውም፤ ሌላው ቢቀር በኛ በያንዳንዳችን ሰውነት ላይ ያለውን እግዚአብሄር ቀጣጥሎና ገጣጥሞ ወደ አካልነት የቀየረው እያንዳንዱ ቅንጣት ተቆጥሮ ያልቃል ወይ? በጭንቅላቱ ላይ ያለውን ጸጉር ቆጥሮ የሚደርስበት አለ? የሴሎቻችን ብዛት፣ የአጥንቶቻችን፣ የደም-ስሮቻችንና የነርቫችን ርዝመት፣ ብዙ ብዙ ነገር ለማሰብ የሚያድግት ውስብስብ ነገር አለ። አለማት ላይ ያሉት አይነትና ብዛታቸው ይቅርና እኛ ራሳችን ወደ ውስጣችን ገብተን አፈጣጠራችንን ብንመረምር በመደነቅ እናመሰግናለን። ንጉስ ዳዊት እግዚአብሄርን በፍጥረቱ በኩል ሳይመለከተው አልቀረም፣ በራሱ አፈጣጠርም በኩል አስተውሎታል፣ ስለዚህ ስለቻይነቱ አብዝቶ መሰከረ፣አመሰገን፣ ተቀኘም።
መዝሙር 148:1-4 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት።
እንዲህ እያለ ነበር፦ እግዚአብሄርን የምታውቁ አመስግኑት፤ በሰማያት በዙፋኑ ላይ ያለ ጌታ ይመስገን፣ በክብሩ ዙሪያ ያላችሁ እናንተ መላእክቱ ሁሉ ታላቅነቱን ያያችሁ፣ ክብሩ ያበራላችሁ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ ሳታቋርጡ አመስግኑት። በሰማያት ላይ እንድትጸኑ በትእዛዙ በስፍራችሁ ያንጠለጠላችሁ ሃያል ክብርንም ያለበሳችሁ ፀሐይና ጨረቃ ሆይ አመስግኑት፤ ታላቅ ክብርን የደረበላችሁ ከዋክብትና የርሱን ታላቅ ብርሃን ያወረሳችሁ ሁሉ፥ አመስግኑት። ታላቅነቱን የምታውጁ እንደ መጋረጃ እርሱ የዘረጋችሁ እናንተ ሰማየ-ሰማያት ዝም አትበሉ ከፍ አድርጋችሁ አመስግኑት፣ ዳመናት በሰማይ ውስጥ አምላክ ያሰፈፋችሁ የሰማያት በላይም ውኃ። ጌታ ከሌሉበት ይወጡ ዘንድ የትእዛዛት ቃልን እርሱ ብሎአልና፥ ሁሎቹ ሆኑም፤ እርሱ ከቃሉ የተነሳ እንዲሆኑ ባዘዘ ጊዜ ተፈጠሩም፤ ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣቸው ይከብር ዘንድ ፍጥረቶቹ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። በህዋና በባዶ ስፍራ መንገዳቸውን ሳይስቱ በስርአት እንዲጉዋዙ አድርጎአል፣ አንዳቸው ከሌላቸው ሳይላተሙ የሚኖሩበትን የተመደበ አቅጣጫ ይዘው እንዲጸኑ ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ መንገዳቸውን አዞአል፣ ስፍራቸውን መድቦአል፣ ሁከት እንዳይሆንም የሚጸኑበትን ትእዛዝን ሰጠ፥ አንዳቸውም ተሳስተው አያልፉምም። በውሃ ውስጥ የምትጫወቱ እባቦች እግዚአብሄር አጥልቆ የሰራችሁ አስፈሪ ጥልቆችም ሁሉ፥ የፈጠራችሁን አምላክ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤ እግዚአብሄር ችሎታውን የገለጠባችሁ እናንተ እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤ ተራሮች ኰረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ፤ አራዊትም እንስሳትም ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾችም የሚበርሩ ወፎችም፤ የምድር ነገሥታት አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች የምድርም ፈራጆች ሁሉ፥ ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ የፈጠራቸውን የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ እርሱ እንደሰራቸው አስተውለው ከፍ ያድርጉት፣ በፍጥረቱ ላይ ጥበቡን ገልጦአልና በክብር የጥሩት፣ ስሙ ብቻውን ከፍጥረት ይልቅ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ሁሉም ወደርሱ የሚያወጣው ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው። ወደርሱ የጠራውን፣ ወገኔ ያለውን፣ የመንግስቱ ወራሽ እንዲሆን የመረጠውንም የሕዝቡን ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ እርሱም በክብሩ ስፍራ ሆኖም የቅዱሳኑን ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ።
የእግዚአብሄር ምስጋና እሱን ከማወቅና አድራሻውን ከማስተዋል ጋር ይቀርባል።
ወደር በሌለው ስፋት ጥልቀትና ርዝመት የተንሰራፋውን አጽናፈ- አለም ላስተዋለና በውስጡ የሚኖር እያንዳንዳንዱ ከግዙፍ እስከ ደቂቅ ያለውን ፍጥረት በመመርመር እያንዳንዱ ነገር በማን እጅ ውስጥ እንዳለ፣ ማንስ እንደደገፈው፣ እንዳኖረውና ከመጥፋት እንደተከላከለው ፍጥረት ሊያስተውል ይገባል፤ እግዚአብሄር የሁሉ አምላክና አባት ነው፤ ስለዚህ ማንም ለሌሎች ባለቤት ላልሆኑ በቅርብም ለተነሱ አማልክት ክብርን ሊሰጥ አይገባም። ግኡዛን ፍጥረታት ለእግዚአብሄር በራሳቸው ቋንቋ ምስጋና ካቀረቡ ህያው ፍጥረታት አፍና ድምጽ የተፈጠረልን እኛ እንዴት አብልጠን አናመሰግንም?
ምክኒያቱም ከተፈጠረው ቁጥር የለሽ ፍጥረት መሃል ከአዳም ዘርና ከመላእክት ውጪ ፈጣሪያቸውን እንዲያምኑ ፣ እንዲጠሩ፣ እንዲከተሉ አፋቸውን ከፍተው እንዲጠሩትና እንዲያመልኩት ሆነው የተፈጠሩ ሌሎች አልነበሩምና ስለፈጣሪው ማወቅ ግድ የሚለው ከነርሱ ውጪ አንዳችም የለም። ሰውና መላእክት ብቻ አምላካቸውን እንዲጠሩና እንዲያናግሩት ሆነው ተፈጥረዋልና።
በምድር ላይ የተፈጠርን ሰዎች እንደ መዝሙረኛው ዳዊት የእግዚአብሄርን ታላቅነት እያነሳሳን እንድናመሰግነውና እውነትን በማወቅ እንድንጠራው ያስፈልጋል። የፈጠረውን፣ ያበጀውን፣ ተቆጣጣሪውንና የሁኔታዎች ሁሉ ባለሙሉ ፈቃድ የሆነውን ይህን ታላቅ አምላክ በተለይ ሰዎች ይቀርቡት ዘንድ ያውቁትና ያምኑበት ዘንድ ፈቃዱ ነው፤ ያን ከማድረጋቸው አስቀድሞ እርሱ ብቸኛ አምላክ እንደሆነ የሚያውቁበት የልቦና መዋቅር በመንፈሳዊ ማንነታቸው ውስጥ ያዘጋጀላቸው ሲሆን እርሱን የሚያገኙበት የፍለጋ መስመርም በውስጣቸው ዘርግቶአል። ስለዚህ ሰዎች ልቦናቸው ማመዛዘን ደረጃ ላይ ሲደርስ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ፍለጋ ውስጥ እንዲገቡ ይሆናል፤ የሰዎች ልጆችም የኑሮ እርካታ አምልኮ ላይ የሚወሰን መሆኑን ይገነዘባሉ፤ በዚህ ምክኒያት የትም ይሁን መቼም ቢሮጡ፣ የውስጥ እርካታ፣ ማረፍያና መጨረሻቸው በአምልኮ ላይ የሚደመደም መሆኑን ተቀብለው ያን ማስተናገድ ይቀጥላሉ።
እግዚአብሄር እስራኤልን ገና ከግብጽ ምድር ወደ ራሱ ስፍራ እያወጣው ሳለ ቀድሞ ያሳሰበው ያን ነበር፤ እንዲህ አለ፦
“እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካምም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል።” (ዘዳ.6:3-13)
እስራኤል ሆይ መውጣትንስ ከባርነት ምድር በአምላክህ ትወጣለህ ግን ከዚያ በወጣህ ጊዜ ለኑሮህም ወዲያ ወዲህ እያልክ ስትሮጥ ሳለህ መዘንጋት እንዳይዝህ፣ እንዳትረሳ ቆም በል ለአምልኮ፣ ቆም በል አምላክህን እንድታስብ፣ ቆም በል አብሮህ ያለውን ፈጣሪ እንድታመልክና እንድትሰግድለት፣ ያደረገልህን እንድታስብና እንድታመሰግንም።
እግዚአብሄር የጠራውን እስራኤል አስተውለህ ስማኝ ይለዋል፣ለምን? ብዙ ክፉ ነገር ስለከበበው፣ በዚያ ውስጥ ካለ የክፋት መንገድና አሰራር እንዲድንና መልካም እንዲሆንለት ግን የምነግርህን ስማ ይለዋል። አዎ ላንተ ሊያደርግ ያለው ይህ ነገር ለነርሱ የተነገረ ተስፋ ስለሆነ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር ለነርሱ ቃል እንደገባው ላንተም እንደ ተናገረህ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር ገብተህ ልክ እንደ ቃሉ በምህረቱ ተከልለህ እጅግ እንድትበዛ፣ በዙርያህ ያሉትን ያልተመረጡትን በከንቱ የሚመላለሱትንም አህዛብ ሳትመስል ታደርጋት ዘንድ እርሱ የተናገራትን ትእዛዝ ጠብቅ ሲል ያሳስባል። እግዚአብሄር ያእቆብ ልብ እንዲልና እንዲያስተውል ደጋግሞ እስራኤል ሆይ፥ ስማ አለው፣ እስራኤል በግብጽ አገር ብዙ አማልክትን ስላየ ምናልባትም እነርሱን ስለተከተለ፣ አሁን ግን በፊቱ በሲና ተራራ በክብሩ የተገለጠው የአባቶቹ አምላክ ማንና ከማን ጋር እንደሆነ ልብ እንዲል ነበር፣ ስለዚህ ጠርቶ ተናገረው፦ እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን እግዚአብሔር ፊትህ በተራራው ላይ በሚነድ እሳት መሃል አሁን ድምጹን የሚያሰማህ እርሱ ብቻውን ያለ አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም ይህን ብቸኛ አምላክህን እግዚአብሔርን በማያመነታ ፍጹም ልብ፣ በማያነክስ ፍጹም ነፍስ ባልተከፋፈለ ፍጹም ኃይልህ ውደደው አለው።
ደግሞ ሲያስጠነቅቀው እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ካንተም አልፎ ለልጆችህም አስተምረው፥ ጊዜ አታባክን፣ ክፍተት አትፍጠር ይልቅ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው፣ በልብህ አብሰልስለው፣ ቃሉን በውስጥህ አመላልሰው በሚል ማሳሰቢያ እርሱን ካገኘ ወዲያ ዳግም እንዳይረሳው ያሳስበዋል።
መዝሙረኛው ዳዊት ያነሳቸው ፍጥረታት እንዲመለኩ የምንፈልጋቸው ሊሆኑ አይገባም፣ ይልቅ ፍጥረት በመሆናቸው የፈጠራቸውን ሊጠሩና ሊያመሰግኑ ተገብቶአቸዋል፤ ነገር ግን አእምሮ በከንቱነት ሲዟዟር፣ ህሊና መብራቱ ሲጠፋና ልብም አመጸኛ ሲሆን ነገሮች ይገለባበጣሉ፤ በዚያ ህይወት ውስጥ ያሉና እውነተኛውን አምላክ ያላገኙ በሚያሳዝን ሁኔታ ፍጥረትን ያመልካሉ፦ ለጸሃይ ይሰግዳሉ፣ ለጨረቃ፣ ለከዋክብት የሚሰግዱም አሉ። ድንጋይ ቀርጸው፣ እንጨት ፈልፍለውና ለርሱ መቅደስ ሰርተው ያመልኩታል። ወንዝንና ባህርን፣ ዛፍን፣ የባህር አሶችን ከፍ ሲልም ሰዎችን የሚያመልኩ በምድር ላይ ዛሬም ድረስ አሉ። ይህ ልምምድ ትክክል ባይሆንም ፍለጋው የሰው ልጅ ያለ አምልኮ መኖር እንደማይችል የሚያስገነዝብ ነው። በመሳ.18 ውስጥ ያለን አንድ ታሪክ በምሳሌነት እናያለን፦
እስራኤላውያን ንጉስ ባልነበራቸው ዘመን በመሳፍንት የሚመሩበት ወቅት ነበራቸው፤ በዚያን ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ስርአት አልነበረውም። ከኢያሱ ሞት በሁዋላ ህዝቡን በአንድ ልብ በስርአት የሚመራ ስላልነበረ ሁሉም የገዛ መንገዱን ይሄድ ነበረ። ያኔ አንድ የሚያሳዝን ታሪክ ተፈጥሮ ነበር፦ ከእስራኤል መካከል ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር። ህዝቡም ያለ እውነተኛ አምላክ እየባከነ እንደነበር ካለምሪት እየተጉዋዙ መሆኑና ከህይወታቸው ይዘት የሚታይ ነበር። ይህን ተከትሎ የነገዱ ሰዎች እግራቸው እንደወሰዳቸው እየተዙዋዛሩ ምድርን ያስሱ ነበር። ያን እያደረጉ ሳለ አንድ ቀን ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ አሰቡና ሰዎቹን፦ ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚህ ሰዎች ጉዞአቸውን ሲጀምሩ ዝም ብለው ወጡ እንጂ በሙሴ ዘመን ከእውነተኛው አምላክ ይቀበሉ እንደነበረው ባለ ምሪት አልወጡም። ሰዎቹ ተጉዘው ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ አስቀድሞ እሚያውቁት የነበረ አንድ ሌዋዊ በዚያ እንዳለ ተረዱ፤ ሲሰሙ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው፦ ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት። እርሱም፦ ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው።
ሚካ የሚባለው ሰው አምላክን ማምለክ እንደሚገባ ቢያውቅም እውነተኛውን አምላክ አላስተዋለምና በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ይጠራ ዘንድ ወደደ። ያን እያሰበ እያለ ሌዋዊ ሰው ተገናኘና በዚያ ደስ ተሰኘ። አምላክ ይሆነኛል ብሎ ያሰበውን ጣኦት ስላስቀመጠ ለጣኦቱ ካህን ትክክለኛውን ሌዋዊ በማግኘቱ ተደሰተ። ይህ ሰው በቤተ ልሔም ይሁዳ ከይሁዳ ወገን የሆነ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ ሌዋዊው ከሚቀመጥበት ከቤተልሄም ተነስቶ የወጣ ሰው ነበረ፤ ሌዋዊው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት እግሩ ወደ ወሰደው አቅጣጭ ይሄድ ዘንድ ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ እንደወጣ የእግዚአብሄርም ምሪት ሳይኖረው እግሩ እንደወሰደው ወዲያ ወዲህ እያለ ሳለ እንደ አጋጣሚ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ። ሚካም ሌዋዊውን ለጣኦት አገልጋይነት ቀደሰው፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ። ሚካም፦ ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ ሲል በራሱ ተጽናና። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ወደ ሚካ ቤት እንግዶች ደረሱ። እንግዶቹም ካህኑ የእውነተኛው አምላክ ካህን ሌዋዊ መሆኑን ስላዩ ፦ የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት። እርሱም፦ የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው። አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተነጥለውናለጥቃት ተጋልጠው አዩአቸው። ሰላዮቹ ወደ አገራቸው ተመልሰው ከወገኖቻቸው ከሚበዙ ሰዎች ጋር ሲመለሱ እንደገና ወደ ሚካ ቤት መጡ። ለመኖሪያቸው አገር ቢፈልጉና ለመቀመጫቸው ሰፈር ቢያገኙም አምልኮ እንደሚያስፈልጋቸው ስለተረዱ ለነርሱ ተገቢ ብለው ያስተዋሉት የሚካን አምላክ ነበር። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን በመሆናቸው ከዘነጉት አምልኮ ውስጥ ያስታወሱት ጥቂት ነበር፦ እርሱም ካህን፣ የካህኑንም ልብስ፤ ሆኖም አምላክ ከልባቸው ጠፍቶ ነበር። ከዳን ወገን የሆኑት የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ። ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ። ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፤ ወደ ሚካም ቤት መጡ። የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን፦ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው። ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት። ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ፦ ምነው በጣኦቴና በአምልኮዬ ላይ ምን እያደረጋችሁ ነው? አላቸው። እነርሱም፦ ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት። የዳንም ልጆች የነጠቁትን ጣኦት ይዘው መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፤ በዚያ የነበሩትን አጥፍተው ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት። የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፣ በእስራኤል ህዝብ ዘንድ እርግማን የሆነውን ጣኦት በመሃከላቸው አኖሩ፣ አመለኩትም፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ። ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ።
ዛሬስ ቢሆን? ውስጣችን ያለው የአምልኮ መሻት ጠፍቶአል ማለት እንዴት እንችላለን? ሆኖም ክህደት በሰው ልጅ ላይ በዛ እንጂ፣ ሰው አምላክን በተለያየ ትርጉም ተመለከተውም እንጂ። አምላክ ግን ያው ነው አይለወጥም፣ አምልኮው እንደፋሽን ከዘመን ወደ ዘመን አይገለባበጥም፣ እግዚአብሄር አይለወጥም፣ ስርአቱም እንዲሁ አይሻሻልም። ምን ቴክኖሎጂ ቢራቀቅ፣ ሰው ራሱን አምላክ ቢያደርግ ያለማመኑ አንዱን የአብረሃም አምላክ ከስፍራው እንደምን ፈቀቅ ሊያደርግ ይችላል?