ካለፈው የቀጠለ…
የእግዚአብሄር እውቀት የእግዚአብሄርን ህልውና ያበስራል፤ አሰራሩን ይናገራል፤ አምላክነቱን ያውጃል። በእግዚአብሄር እውቀት መሰረት ላይ ያልቆሙ የሰው ልጆች ከእግዚአብሄር ስራ ጋር ይጋጫሉ፤ ባለማወቃቸው ጠንቅ ስህተት ትይዛቸዋለች፤ ለእግዚአብሄርም ቅጣት አሳልፋ ትሰጣለች፦
“እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ። እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።”(መዝ.73:11-12)
ይህ በጎ ያልሆነ አሳብ የተፈጠረው ባለማወቅ ምክኒያት በመሆኑ ባልሆነ አካሄድና መንፈሳዊ ባልሆነ ባለጥግነት ይታጠራሉ፤ ይህን የእግዚአብሄር በረከት ሳይሆን በድጥ ስፍራ መቀመጥ እንደሆነና፥ ወደ ጥፋትም መወርወር መሆኑን ንጉሱ በመዝሙሩ ውስጥ ይናገራል፤ የሚያገኛቸውን አስቀድሞ አይቶ፦ “ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ” አለ።(መዝ.73:18)
እግዚአብሄርን ማወቅ ግን በህዝቡ ዘንድ ክቡር ነው፤ ለርሱ ወገን ለመሆን የተጠራ እግዚአብሄርን ከማንነቱ፣ ከፈቃዱና ከዘላለም አሳቡ ጋር ያውቁታል እንጂ እንደ አህዛብ በድንግዝግዝ አይከተሉትም፤ እርሱም ባስቀመጠው መመዘኛ ሰዎችን ይመረምራል። በሁለት በኩል ይህን አኑሮአል፣ የመጀመሪያውን በነቢዩ ኢሳያስ መጽሃፍ ሲገልጠው እንዲህ ብሎአል፦
“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ።ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?” (ኢሳ.43:10-13)
በነቢዩ ዘመን እግዚአብሄር ለህዝቡ ማስገንዘብ ይፈልግ የነበረው እውቀት የእርሱ ማንነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መፈለጉን ያመለክታል፤ እግዚአብሄር ከአህዛብ አምላክ እንዴትና በምን ይለያል? ለሚሉ ጥያቄዎችም መልሱን በግልጽ አስቀምጦአል። እግዚአብሄር እርሱን ማወቅና ማመን እንዲጸና የእርሱን ማንነት ማስተዋል እንዲያስፈልግ ህዝቡና የእርሱን አምላክነት ሊያውጁና ሊያገለግሉት ለተጠሩት ማስገንዘቢያ ይሰጣል። እርሱን የማወቅ እውቀት ባህሪውን ከማስተዋል ጋር ከሆነ እነዚያ ባህሪዎቹ እርሱ ብቻ አምላክ እንደሆነ፣ በዙፋን ላይ በአንድ አካል ሆኖ የተቀመጠው (ኢሳያስ በራእይ እንዳየው) እርሱ መሆኑን፣ ከርሱ በሁዋላ ሌላ የመታወቂያ መገለጫ እንደሌለ(ሌላ አካል እንደማይገለጥ)፣ መድሃኒት ሆኖ ሲገለጥ እርሱ ራሱ እንጂ ሌላ አምላክ ሊሆን እንደማይችል፣ ይሄንን ደግሞ ለእስራኤል እንዳሳየ ወደፊትም ተገልጦ እንደሚያሳይ፣ ሳይፈጸም እንደተናገረ ደግሞም አስቀድሞ ሰርቶ እንዳሳየ፣ በዚህም ከጥንት ጀምሮ አምላክ ቢባል እርሱ ብቻ እንደሆነ ያበሰረ ነበረ። ይህን እውቀት በአዲስ ኪዳን ዘመን ከብዙ መቶ አመታት በሁዋላ ደግሞ ሲናገር በሚከተለው ቃል ላይ እናያለን (በሚዳሰስ አካል ውስጥ ስለነበረ ሌላ አምላክ እንደሆነ እንዳንገምት አደራ)፦
“የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” (ዮሐ.10:36-38)
በአዲስ ኪዳን ያለው የእግዚአብሄር ልጅነት የኛን ዘመን ያሰናክል ይሆን? ወይስ እግዚአብሄር አስቀድሞ የተናገረው በልጁ አካል ተገልጦ ከተናገረው የተለየ ነገር አለው? “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ…” ያለውን በአዲስ ኪዳን “አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።” ስላለ የመረጥሁት ባሪያዬ ምስክሬ ነው ያለውን ማጽናቱ አይደለምን? ቃሉ እንደገለጸው የመረጠው ክርስቶስ አብ በእኔ ውስጥ ነው በማለት መስክሮአል፣ የምናስተውለው እውቀት የተቁዋጠረበት የእግዚአብሄር አሰራር ተገልጦአልና።
– የመዳን እውቀት ነው
የመዳን እውቀት የሰው ልጅ ከምን እንደሚድንና በማን እንደሚድን የሚያሳውቅ እውቀት ነው።
ሉቃ.1:77 “እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ” የሚል ትንቢት ለመጥምቁ ዮሃንስ በተወለደበት እለት ሲነገርለት ነበር። እርሱም ልክ እንደተነገረው ቃል ለእስራኤል ህዝብ የመዳንን እውቀት ይሰብክ ያዘ። አባቱ ዘካርያስም በተወለደ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተይዞ ስለአዳኙ አምላክ ሲናገር ነበር፣ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ ያደረገው የእስራኤል ጌታ አምላክ ነው ብሎ አምላኩን ባረከ፤ በአዲስ ኪዳን የሆነው አዲስ ክስተት እንዳልሆነ ሲያመለክትም ገና ዛሬ ሳይሆን ድሮ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ ይናገር የነበረውን የኸውም በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን እንደሚያስነሳ የተናገረውን ፈጸመው አለ፤ ማዳኑም ካስጭናቂዎች መንፈሳዊ ጠላቶች መሆኑን ይናገራል፤ እግዚአብሄር በአባቶች ዘመን ሰርቶ እነዚያን አባቶች በምሕረት አኖረ፣ ከዚያ ባለፈ የእምነት አባት ለሆነው ለአብርሃም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ ይላል፤ በዚህ በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ ከመንፈሳዊ ጠላቶች እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ነጻነትን እደሰጠን ብስራት ያወጣል። የመዳን እውቀት ሰዎች አዳኙ ማን እንደሆነ በመግለጥ ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ የማድርግ ችሎታ አለው።
በዮሐ.4:21-26 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት አዳኙ ማን እንደሆነ ሲያስረዳት እንዲህ አለ፦
“ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ፦ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው።ኢየሱስ፦ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።”
በዚህም ዘመን መዳንና ማምለጥ የምንፈልጋቸው እጅግ ብዙ አስፈሪ ነገሮች ይኖሩናል፤ ከነዚያ አስፈሪ ነገሮች ሊታደገን የሚችለው ጌታ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ማስተዋል ደግሞ ጠቃሚ ነገር ነው፤ ሳምራዊትዋ ፦ መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል ያለችው ቃል ለመዳን መንገድ የከፈተላት በሩቅና በጭላንጭል ይዛው የነበረ እውቀት ነው፤ ያ እውቀት እንዴት ደግፎ ወደ እርሱ እንዳደረሳትም እንመለከታለን። ሃዋርያት ስለ አዳኙ ጌታ ሲመሰክሩ፦
“እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው።መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” ብለዋል (ሐዋ.4:11-12)።
እግዚአብሄር ከመንፈሳዊ ጠላት ብቻ ሳይሆን ከስጋ ጠላትም የሚታደግ አምላክ ነው፤ ያንን ሰው አስተውሎ እንዲታመንበት ያስፈልጋል፦
አስ.4:10-14 “አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፥ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው። የንጉሡ ባሪያዎችና በአገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር፥ እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም።አክራትዮስም የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ ነገረው።መርዶክዮስም አክራትዮስን፦ ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው። አንቺ፦ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ።በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”
ንግስት አስቴር በወገኖችዋ ከሚመጣው ጥፋት እንደምታመልጥ የተማመነችበት የንጉሱ ቤት እንደሆነ እንዳታስብ፣ ያ ከሆነ እንደማያስጥላት ይልቅ እምነትዋን በእግዚአብሄር አድርጋ በእርሱ አሳብ ውስጥ ሆናም ራስዋንና ህዝብዋን እንድታድን ጥሪ ሲቀርብላት እንመለከታለን። እርሱዋም በዘመድዋ መርዶክዮስ በኩል የመጣውን ተግሳጽ ሰምታ ፊትዋን ወደ አዳኙ አምላክ በማዞርዋ መድሃኒት ለርስዋና ለህዝቡ ሆኖአል።
የጌታ መድሃኒት ከበሽታ ይፈውሳል፣ ከአጋንንት ነጻ ያወጣል፣ ከእስራት ይፈታል፤ ይህን እውነት ያወቁ አይሁድ እስኪፈወሱ ተጠግተው አጋፍተውታል፦
ማቴ.4:23-25 “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።”
– የመጽሃፍ እውቀት ነው
የመጽሃፍ እውቀት አጠቃላይ እውቀት ሊሆን ይችላል፤ ብዙ ነገሮችን ከተለያዩ ምንጮች ልንገበይ እንችላለን። ይህ የመጽሃፍ እውቀት በተለይ መንፈሳዊ ከሆኑ ታሪኮች ጋር ተያይዞ የሚጻፍን ይመለከታል፤ በመሆኑም የእግዚአብሄርን ህዝብ ህይወት ታሪክ፣ ከእግዚአብሄር ጋር የሄዱበት መንገድ፣ መመረጣቸውን፣ በጉዞአቸው ያደረጉትን፣የገጠማቸውንና የሆነላቸውን የመሳሰለው ታሪክ ይነገርበታል፤ እንዲህ ያሉ መጽሃፍት እግዚአብሄር ራሱ ያጻፋቸው በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ እንደነ ዘሁልቁ ያሉ መጽሃፍት ናቸው፦
ዘሁ.33:1-4 “የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ። ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ።በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ። በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።”
በመጽሃፍት ውስጥ የሚገኙ የእስራኤል ታሪኮች ከእግዚአብሄር ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ብዙ ትርጉም አላቸው፤ ከእርሱ ጋር ሲጉዋዙ የሆኑትም ሆነ ያደረጉት ነገር በጎም ይሁን መጥፎ ለትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ ነው።
2ጢሞ.3:15 ” አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”
በመንፈሳዊ መጽህፍት እውቀት የበረታ አይሁዳዊ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው እውቀቱ ፍጹም ስላልነበረ ክርስቶስን ፈጽሞ ሊገልጥለትና ወደ ኢየሱስ ሊያደርሰው አልቻለም ነበረ፤ እርሱ የእውቀት ጥማት ስለነበረው ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን እንዲያውቅ የተነገረውን የምስራች ያለምንም ማቅማማት ሲቀበል እናያለን።
ሃስ.18:24 “በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።”
አጵሎስ በመጽሃፍ አማካይነት የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ ይሁን እንጂ እውቀትቱ የተገደበ ስለነበር የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር። እርሱም የሚያርሙትና እውነትን ፍጹም አድርገው የሚገልጡለት ሰዎች እስኪገናኙት በምኵራብ ገልጦ መናገር ቀጠለ። እነዚህ ጵርስቅላና አቂላ የሚባሉ ደቀመዛሙርት በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት። እርሱም ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ጀመር።
ሐዋ.13:26-32 “እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት።እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው።እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን”
1ነገ.11:41-43 “የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ።ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።”
– የእግዚአብሄር የክብሩ እውቀት ነው
በእግዚአብሄር እውቀት እየበረታን ስንሄድ የተለያዩ እውቀቶችን ከቃሉ እናስተውላለን፤ በበሰሉት ዘንድ ያለ እውቀት የቃሉን ወተት ከሚመገቡት ይለያል፤ ይህም የእድገት ጉዳይ ነው።
2ቆሮ.4:6 “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።”
የእግዚአብሄር የክብሩ እውቀት ወንጌል ነው፤ ወንጌል የእግዚአብሄርን ታላቅነትና የማዳን ስራ በክርስቶስ ተገልጦም ሰውን መታደጉን የምስራች የሚል ነው፤ በወንጌል እግዚአብሄር በስጋ መገለጡን አውቀናል፣ እግዚአብሄር አማኑኤል መሆኑን ተረድተናል፣ በክርስቶስ ሆኖ አለሙን ያስታርቅ እንደነበርና ክርስቶስ የእግዚአብሄር አብ የክብሩ መንጸባረቅና የባህሪው ምሳሌ እንደሆነ ይህ የክብሩ እውቀት አሳይቶናል።