እውቀተ መለኮት(1…)

የመጨረሻ ዘመን

ምድራዊ መንግስታት እውቀትን እንደ ስልጣኔ በር ቆጥረው ህዝባቸው ያውቅ ዘንድ ይለፋሉ። በሁሉን አቀፍነት አንጻር ይህ እውቀትን የማግኘት፣ የመረዳትና የመቀበል ዝንባሌ የትውልድ ማስቀጠያም ተደርጎ የሚቆጠር ነው፤ ምክኒያቱም ያላወቀ የማያስተውልና ወገንን ጠቃሚ ስለማይሆን ነው። በመንፈሳዊ ጉዳይም ከዚህ የላቀ አስፈላጊነት ባለው ሁኔታ እውቀት አትኩሮት ይሰጠዋል።
በምድራዊ እውቀትና በሰማያዊው መሃል ግን ከፍተኛ ልዩነት ያለበት ነጥብ አለ፣ እርሱም የእውቀት መገኛው/ምንጩ የተለያየ መሆኑ ነው፤ ስለዚህ የምድራዊ እውቀት ምንጭ ተፈጥሮአዊ ክስተትና ሞላው ሆኖ አካሄዱ የሚያተኩረውም የሚታዩትን ፍጥረታት በሙሉ በመርመርና በማወቅ ላይ ነው፤ መንፈሳዊው እውቀት ግን በማይታዩ መንፈሳዊ ምስጢራት ላይ ያተኮረና እውቀቱን የሚገልጥልንና የሚያስተምረንም እግዚአብሄር መሆኑ ነው።
ዘኊ.24:16 “የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።” ይላል።
በእግዚአብሄር ቃል ብርሃን ምክኒያት የልዑልን እውቀት የሚያውቅ የታደለ ሰው በመሆኑ የአምላክን ምስጢር ያስተውላል። የእግዚአብሄር እውቀት ሰማያዊ ነውና መገለጥ ይፈልጋል። ከማይታይ የእግዚአብሄር መንግስት በመውጣቱም በመንፈስ ቅዱስ መገለጥ የሚበራ ነው፤ በቃሉ ብርሃን እግዚአብሄር ሲታወቅ ወደ እርሱ ነገር ይደረሳል፤ የሰው ልጆች እውቀቱን ተሞልተው እንደሆን ከእርሱ ዘንድ ያለው በረከትና ምህረት እንዲያገኛቸው የታወቀ ነው።
2ዜና.1:10-11 “አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና። እግዚአብሔርም ሰሎሞንን፦ ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ”
የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ከእግዚአብሄር ዘንድ ማግኘት የሚገባው ታላቅ ነገር እንዳለ ገብቶት ነበር፤ አስተውሎ ባደረገው ልመናም ከእግዚአብሄር ዘንድ መሻቱን ተቀብሎአል፤ ንጉሱ የእግዚአብሄርን ጥበብና እውቀት በመቀበሉ በአለም ከነበሩ፣ ካሉና ከሚኖሩ ሁሉ በላይ ታላቅነትን አግኝቶአል። በህዝቡ በእስራኤል መሃል ባለሞገስ ነበር፤ በአምላኩ የተወደደ ይዲድያ ተብሎም ተጠርቶ ነበር፤ የተገለጠለትን እውቀትና ጥበብ ይዞ በኖረበት ዘመን ንጉሱ ከብሮአል።
ኢዮ.26:2-4 “ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው! ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት!ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ?”
ወደ እግዚአብሄር ለተጠጋው ሰው ብዙ እውቀትን እንደሚገልጥለት ያን የቀመሰው ኢዮብ በመደነቅ ያስረዳል፤ እውቀቱም ከአምላክ ጋር የሚያቀራርብ እርሱን በማወቅ መጠጋትና አብሮ መጉዋዝ እንዲቻል የሚያደርግ ነው።
ምሳ.1:2-6 “ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥ብልሃትን ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ ለጐበዛዝትም እውቀትንና ጥንቃቄን፥ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባንና ቃልና የተሸሸገውን ነገር ለማስተዋል።”
ጥበበኛ ሰው የእግዚአብሄርን እውቀት እንዲቀበል በማስተዋል ይሰማል፣ እውቀትንም በዚያ ይጨምራል። እንዲሁ ከጨለማ እንወጣ ዘንድ ብርሃን የሆነ የህይወት ቃል ከእግዚአብሄር መቀበል ይገባናል።
እግዚአብሔር ለታመኑት ጥበብን ይሰጣል፤ ሰዎች ቃሉን ቢተማመኑና ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ቢጠብቁ ወደእርሱ ይወጣሉ፤ ቃሉን የሚያስተውሉ እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን እንዲያከማች ያውቃሉ፤ በአለም ላይ ለሚኖር ንጥቂያ እጅ ሳይሰጡ በሰማያዊ እውቀት በመደገፍ ያለ ነውር ለሚሄዱትም እግዚአብሄር ጋሻ ነው።የእግዚአብሄርን እውቀት የሚሻ ቃሉን ቢቀበል፥ ትእዛዙንም ታግሶ በልቡ ሸሽጎ ቢይዛት፣ ጆሮው ጥበብን እንዲያደምጥ ያደርጋል፣ ልቡንም ወደ ማስተዋል ያዘነብላል። ይህ እውቀትን የመቀበያ ጥበብ ነው (ምሳ.2:3-5)። ቃሉ የአምላክን እውቀት መቀበያ ብሎ የሚያስተምረውን ጨምሮ ሲያስረዳ፣ ረቂቅ እውቀትን መጥራት፥ ለማስተዋልም ድምፅን ማንሳት፥ እርስዋንም እንደ ብር መፈለግ፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ መሻት ስለመሆኑ ያስረዳል።
ምሳ.2:10 “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና” ስለሚል።
– በመንፈስ የሆነ እውቀት
አንድ ልዩ እውቀት ለሰው ልጅ የተጠበቀ ተገኝቶ የራስ ሲሆንም ለበረከት የሚሆን አለ። ይህ እውቀት ከእግዚአብሄር አፍ ይወጣል፤ ከእርሱ የወጣው እውቀት መንፈሳዊ ነው፤ ልብን የሚያቀና፣ ለዚህ ክፉ አለም ከተወሰነ ጥፋት የሚያስመልጥና ደኅንነት የሚሰጥ ነው፤ እግዚአብሄርን የምናውቅበትና እግዚአብሄርም ሊያነጋግረን የሚፈልገው በቃሉ ባለው በዚህ መንፈሳዊ እውቀት ነው።
መንፈሳዊ እውቀት በአጠቃላይ የመንፈሱ አለም ነገር ብስራት ነው፤ መንፈሱ አለም ውስጥ ያለው በሰዎች ዘንድ ሊታወቅ የሚችለው ከዚያው የሚወጣ እውቀት ሲገለጥልን ነው። የመንፈስ እውቀት ምንጭ እግዚአብሄር ነው።
ምሳ.2:6-9 “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።”
እግዚአብሄር ለአገልግሎት ከመላኩ በፊት በመለኮታዊ እውቀት ያስታጥቃል፤ ይህን በብሉይ ኪዳን ዘመን አድርጎ አሳይቶአል። ይህን አሰራር ለሙሴ ሲያሳውቀው በሚከትለው የቃሉ ክፍል እናያለን፤ እግዚአብሄር ሙሴን ህዝቡን እንዲያወጣ በእውቀት ልኮታል(ዘጸ.3:13-14)፤ ከግብጽ የወጣው ህዝብ እርሱን እንዲያመልኩት ፈለገና የታቦቱ ማደሪያ የሆነ ድንኩዋን እንዲሰራ በዚያም ለሚኖረው እቃ ሁሉ በሥራ ለሚከናወነው ነገር ሁሉ እግዚአብሄር ሰው መርጦ ብልሃትን ሰጠ፣ በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት። በዘጸ.31:1-11 እንዲህ አለ፦
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ። የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፥ ገበታውንም ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ ጋር የነጻውን መቅረዝ፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ ለሚቃጠል መሥዋት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፥ በብልሃት የተሠራውንም ልብስ፤ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን የጣፋጭ ሽቱውንም ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ።”
እግዚአብሄር ለቤቱ ስራ እጅግ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ በመንፈሱ ጥበብን፣ ብልሃትንና እውቀትን ሰጥቶ ሰዎችን ያሰማራል። እርሱ በመንግስቱ ያለውን አደራረግ ሰው ያለእንቅፋት ያከናውንለት ዘንድ እውቀቱ ወሳኝ ነው፣ ሰው እውቀቱን ወደ ተግባር ይለውጠው ዘንድ ጥበብና ማስተዋልን ጨምሮ ያገኛል። ሙሴ ከሰማይ አንድ እቅድ ቢቀበልም እንደተቀበለው አድርጎ በምድር ላይ የሚያከናውንለት፣ የሚገነባለትና አሳምሮ የሚጨርስለት ሰው ያስፈልገው ስለነበር ያን ሰው እግዚአብሄር በመንፈሱ አዘጋጀና ወደ ሙሴ አቀረበው።
በሌላ በኩል የእግዚአብሄር መንግስት ከሰማይ ስለሆነች በምድራዊ መንገድና አሳብ አትታወቅምና ሰማያዊ እውቀት ሊገልጣት ይገባል፤ ሰማያዊውም እውቀት ከአርያም የሚወርድ ነው፤ ከእግዚአብሄር ዘነድ የሚመጣው እውቀት ለተለያየ አላማ ሲሆን እውቀቱ ሲገለጥ እንሰራው ዘንድ የታዘዝነውን ያለአንዳች መሰናክልና ስህተት ማከናውን እንችላለን። ሰዎች የእውቀት ምንጭን በትክክል ሲያውቁ ከእርሱ መንፈሱን ያገኙ ዘንድ ይፈልጋሉ፣ ይጠማሉ።
1ቆሮ.12:7-11 “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።”
ከእግዚአብሄር በዳግም የተወለዱ መንፈሳውያን እጅግ የታደሉ አዲስ ፍጥረቶች ናቸው፣ እንዲህ የሚያናግረው የእግዚአብሄር መንፈስ እገዛ ከአለም አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ውሳኔ አለቆ ስለሚያወጣቸው ነው፤ ሁኔታው በአለም እውቀት ከቶ የሚሆን አይደለም፤ እግዚአብሄር የሰውን አእምሮ ሲቆጣጠር የተለየ የመረዳት እውቀት ውስጥ ስለሚያስገባው (አለማዊ እውቀት እንዳልሆነ ግን ልብ ይባል) ስጦታው የላቀ ነው። በእግዚአብሄር መንፈስ የሚነገር እውቀት ህይወትን የሚለውጥ፣ ከእውቀቶች ሁሉ የላቀ የእግዚአብሄር ጥበብ የተገለጠበት ነው።
– የእግዚአብሄር እውቀት
የእግዚአብሄር እውቀት እግዚአብሄርን እንድናውቅ የሚያስችል ትምህርት ነው፤ ትምህርቱም በእግዚአብሄር ቃል ላይ የተመሰረተ ነው። የእግዚአብሄር እውቀት ባልተገለጠበት ዘመን ሁሉ ህዝብ መረን ይወጣ እንደነበር ከእስራኤል ህዝብ ታሪክ እንማራለን። እግዚአብሄር ካልተገለጠ ጣኦታት ይበረታሉ። እውነቱ ሳይገለጥ ከቀረ ሃሰተኛ መናፍስት ልዩ አማልክትን ለሰው ልጅ ያሳውቃሉ። ይህን ችግር የሚያስወግድ የእግዚአብሄር ትምህርት ብቻ ነው።
ዘዳ.32:15-18 “ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት።እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ። የወለደህን አምላክ ተውህ፥ ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።”
ለዝንጉ ህዝብ እውቀቱን በባሪያዎቹ አፍ ጨምሮ በመላክ ልባቸውን የሚያቀና አምለክ ከሃሰት ሃይማኖት ይታደጋል፤ አስቀድሞ በሙሴና በነቢያት ዘመን እግዚአብሄር ሲያስተምር ህዝቡን ከጥፋት ታድጎአል፤ ህዝቡን በሙሴ በኩል ከሰበሰበ በሁዋላ እግዚአብሄር ስለራሱ እንዲህ አለ፦
ዘዳ.32:39-41 “አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።”
የእግዚአብሄር እውቀት እግዚአብሄርን ከአማልክት ነጥሎ ያጎላል፣ ያሳያልም፤ የእግዚአብሄር እውቀት እግዚአብሄር አንድ አምላክ መሆኑን የሚያሳውቅ ትምህርት ነው። አንድ መሆኑ ሲታወቅ ብቸኛ አምላክነት ይገለጥልናል፣ ከእርሱ ሌላ በግራም በቀኝም ሌላ እኩያ እንደሌለው እናውቃለን፣ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እርሱ ብቻ መሆኑንም እውቀቱ ያሳየናል፤ ምድርና ሰማይን የሞላው እርሱ ብቻ በመሆኑ ሌሎች እኩያ አማልክት ሊኖሩ እንደማይችሉ ስለምናስተውል ከርሱ በቀር የምንወደውም የምንፈራውም አምላክ የተባለ አይኖርም። ይህ እውቀት በየትውልዱ ሊገለጥ ይገባል፤ ያም በመሆኑ ለምሳሌ በነእዝራም ዘመን ካህናት ተግተው ህዝቡን ያስተምሩ ነበር፦
ነህ.8:6-9 “ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።ደግሞ ኢያሱና ባኒ፥ ሰራብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሳባታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቆሊጣስ፥ ዓዛርያስ፥ ዮዛባት፥ ሐናን፥ ፌልያ፥ ሌዋውያኑም ሕጉን ያስተውሉ ዘንድ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡም በየስፍራቸው ቆመው ነበር። የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር። ሐቴርሰታ ነህምያም ጸሐፊውም ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፤ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና።”
ሃዋርያት የሚያስተምሩት እግዚአብሄርን የሚያሳውቅ እውቀት የላቀና የሰውን ህይወት መለወጥ የሚችል ስለመሆኑ ይመሰክራሉ፦
2ቆሮ. 10:3 “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።”
አንዱን አምላክ በሚገልጥ ትምህርቱ ሃዋርያው ጳውሎስ ለአዲስ ኪዳን ትውልዶች ጥብቅና ጥልቅ ትምህርቱን እንዲህ ተናግሮአል፦
1ቆሮ.8:5-7 “መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም”
በእግዚአብሄር የተሾሙ ቅዱሳን በተሾሙበት ዘመን ሁሉ ህዝቡን እግዚአብሄርን ማወቅ ያስተምሩ ነበር። በአዲስ ኪዳንም ሃዋርያት የመጀመሪያውን ትምህርት ከጌታ ተቀብለው አሰራጭተዋል። የእግዚአብሄር እውቀት በሰው አእምሮ ላይ የሰለጠነውን አጋንንታዊ እውቀት ድል አድርጎ ነፍሳትን ለጌታ የመማረክ ጉልበት አለው። ቃሉ በመንፈስ ስለሚሰበክ የመንፈስ ቅዱስ ሃይል በትምህርቱ ውስጥ አልፎ የሰውን ልብ የመንካትና የመለወጥ ስራ ይሰራል። የእግዚአብሄር የወንጌሉ እውቀት በሚሰበክበት ስፍራ ሁለት ነገር ይከናወናል፦ በቅድሚያ አለምን የማረከውን አጋንንታዊ እውቀት ይሻራል፣ ከዚያ አስከትሎ ከአጋንንት ትምህርት ነጻ የወጣውን ግለሰብ አእምሮ በመማረክ ከራሱ እውቀት ነጻ ያወጣዋል።