እንደተከፈለልን ለመመላለስ ከወሰንን እግረመንገዳችንን ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን ስጦታ እንደ ክብሩ መጠን መያዝ እንዲገባን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የተሰጠን መዳን የተከፈለውስ የዋጋው ተመን ምን ያህል ነው? ስንል መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ መዳን ሰዋዊ የዋጋ ተመን ከቶ የለውም፣ ስለዚህ ልኬት አይወጣለትም፣ ተመንም አይተመንለትም፤ የሰው ክፍያ ሊመጥነው ሆነ ደረጃ ሊሰጠው አይችልም፡፡ ሰው ግን ያን ያገኘውን ታላቅ ነገር እጅግ ተጠንቅቆና አክብሮ በእውቀት ሊጠብቀው ይገባዋል፤ ሊያከብረው፣ ከተሰባሪ እቃ በላይ ሊጠነቀቅለት፣ ከውድ እቃ በላይ ሊሳሳለት ያስፈልጋል፤ መዳን ከህይወት ከወጣ መልሶ ለማግኘት አዳጋች ነውና፡፡ ቃሉ በ1ቆሮ.6:19-20 ላይ እንዲህ ይላል፡-
”ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
በዋጋ የተገዛነው እግዚአብሄርን በማክበር እንድንኖር ከሆነ የተከፈለልንን ዋጋ እንደ ክብሩ መጠን መያዝ ይገባልና ስሜታችንን ገትተን፣ አሳባችንን ተቆጣጥረንና ፈቃዳችንን በእርሱ ፈቃድ አስገዝተን በመጠን መኖርን የህይወት መርህ ልናደርግ ይገባል፡፡ በእግዚአብሄር የታመነ እርሱን የሚያከብር ህይወት መምራት ይገባዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምናገኘው ጸጋ የሚደገፈው የተከፈለልን ዋጋ ተከብሮ በእኛ ዘንድ እስከፍጻሜው ሲጠበቅ ስለሆነና ቀድመን ያልጠበቅነው በፍጻሜው ልናገኘው ስለማንችል ሁሉን በአግባብ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ቃሉ እንዳለው፡-
”…ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።”(1ጴጥ.1:13-21)
ስለዚህ የተዋጀንበት የክርስቶስ ደም እጅግ የከበረ መሆኑን ተረድተን እንደሆነ በጊዜያዊው ቤታችን (በስጋ ውስጥ ስናድር) ህይወታችንን በእግዚአብሄር ፍርሀት ልንጠብቅ ይገባል ማለት ነው፡፡
”መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።” (ቲቶ2:14) ሲል ቃሉ እግዚአብሄር ለምን አላማ እንደጠራን ያመለክታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለእኛ ነፍሱን ሰጠ፣ ስለምን? እኛን ከሀጢያት ሊያነጻና ህዝቡ ሊያደርገን፣ ነፍሱን ስለነፍሳችን ሰውቶና ያን ውድ ዋጋ ከፍሎ ሊታደገን፡፡ እንዲሁም በ1ጴጥ.3:18 ላይ ሲናገር፡-
”ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ”
እግዚአብሄር እንዴት ጠራን?
እግዚአብሄር በቅዱስ አጠራር ጠራን፡- እርሱ በቅዱስነቱ የታወቀ አምላክ ነው፣ ስሙ ቅዱስ ነው፣ ቃሉ ቅዱስ ነው፣ ስራው ቅዱስ ነው፣ ወንጌሉ ቅዱስ ነው፤ ቅዱስ/የተለየ ወገን እንሆን ዘንድም መቀደስ በሚችለው በወንጌሉ ጠርቶናል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ ነው ስንል የተለየ አምላክ መሆኑን በማመን ነው፡- መመሳሰል የሌለው፣ ፍጡር ያልሆነና እንደ አህዛብ አምላክ ረዳት የሌለው መሆኑን በማስተዋል ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ ስለሆነ በዚህ ምድር ላይ አማልክት የተባሉ የተፈጠሩና ግኡዝ የሆኑ ፍጥረታት በሚመለኩበት መንገድ እንደማይመለክ፣ እነርሱ በሚታመኑበት መንገድም እንደማይታመን ሊታወቅ ይገባል፡፡
ኢሳ.44:10-13”አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፤ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለካዋል፤ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል።”
ይህ የእጅ ስራ የሆነ ቅርጽ ከፍጡር ስለማይለይ ቅዱስ ነው ማለት አይቻልም፤ እውነተኛው አምላክም ምድርን ባስጨነቁዋት በእነዚህ ቅርጻ-ቅርጽና ሀሰተኛ አማልክት አይመሰልም፣ ከእነርሱ ጋር በአንድነት አይቆጠርም፣ እርሱ ፍጹምና ቅዱስ ነውና፡፡
እርሱ ”እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ። ሥርዓቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ነኝ።” ይላል (ዘሌ.20:7)፡፡
እንግዲህ እግዚአብሄር ቅዱሳን የምንሆንበትን መንገድ በቀረጸልን ስርአት በኩል የሚያስተላልፍልን ከሆነ እኛም ያን ማድረግና መጠበቅ ይፈለግብናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦናል፤ ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠርቶናል። በዳንንበት ወንጌል የምንኖርበት አካሄድ ይህ የእግዚአብሄር ስርአት እንደመሆኑ መጠን በዚያ አኩዋያ ሳንታክት መፈለግና ማድረግን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡
የእግዚአብሄር የወንጌል ምስራች አዋጅ ሰውን የመጥራትና በፍቅር የመማረክ ጉልበት ስላለው ልብን ሙሉ በሙሉ ይማርካል፤ የሰውን ባህሪና ፈቃድ ለእግዚአብሄር ያስገዛል፡፡ በዚህ ሁኔታ መዳን በህይወታችን ስራ ሲጀምር ከራሳችን የተሳሳተ አሳብ ሊያድን ይጀምራል፡፡ከእኛ የሚጠበቀው ለመለወጥ መፍቀድ ብቻ ነው፡፡
እንደ አጠራሩ የመመላለስ ውሳኔ ውጤታማነት የሚመሰረተው በዚህ የእግዚአብሄር ጥሪ ላይ እንደመሆኑ ሙሉ ትኩረታችን በርሱ ላይ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ወንጌሉ ለሰው ልጅ ሁሉ የሰላምና የእረፍት መንገድ ነው፡፡ ያለ እርሱ ጥሪ ጨለማ ህይወት ውስጥ እንኖር ነበር፤ በከንቱ ኑሮ ውስጥም ነበርን፡፡ በወንጌል ምርጫ ግን ነገሮች ሁሉ ተገለባብጠዋል፡፡ በቲቶ3:5 ውስጥ እንደተመለከተው ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ ነው ያዳነን፡፡
1ጴጥ.1:18-19 ”ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።”
እግዚአብሄር ሲጠራን ጥሪው ድንገተኛ አልነበረም፣ አጋጣሚም አልነበረም፤ ነገር ግን ዓለም ሳይፈጠር ባቀደው እቅዱ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን (ጻድቁን ለብሰን ነውር የሌለው የእግዚአብሄር ልጅ እንሆን ዘንድ መረጠን)።
እግዚአብሄር በፍቅር ጠራን፡- የተጠራነው በዚህ ደረጃ ከሆነ ለፍቅሩ የሚመጥን መልስ መስጠት ይገባል፣ ፍቅሩ ዋጋ አስከፍሎታልና፡፡
”መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴ.22:36-40)
እግዚአብሄርን መውደድና በፍቅሩ ጸንቶ መኖር ዘርፈ-ብዙ በረከት ያመጣል፣ የሚያምነውም ከአምላኩ ጋር ያለስጋት በሕይወት ይኖር ዘንድ ከእርሱ ጋር በፍቅር ተጣብቆ ሊኖር ይገባዋል፤ እግዚአብሄርም ህዝቡ እርሱን በፍጹም ልብ በፍጹምም ነፍስ ይወድድ ዘንድ ልቡን ይገርዛል፤ በሙሴ አፍ የተናገረውን መርገም ሁሉ በህዝቡ ጠላቶችና በሚጠሉት በሚያሳድዱትም ላይ ያመጣል።
ኤፌ5:2 ”ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።”
ሀጢያተኛን መውደድ የሀጢያተኛውን እዳ ክፍያ ይጠይቃል፡፡ የሀጢያት እዳ ክፍያ ሞት ነው፡፡ እርሱ ግን ሞቶ እኛ ህያዋን እንሆን ዘንድ እርሱ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ሞተ፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ የመጨረሻ ፍርድ የሆነውን የመስቀል ሞት ሊቀበል ለምን ተገባው? እግዚአብሄር ስለ ሀጢያተኛው ባለው ፍቅር ምክኒያት ነው፡፡ የፈጠረውን ሰው ለጠላት ትቶ በሩን መዝጋት ያልወደደ አምላክ አንድያ ልጁን በመሰዋት ፍጥረቱን ታድጎአል፡፡ ለዚህ የፍቅር ጥግ የሰው ልጅ መልስ እንዴት ሊሆን ይገባዋል?
ኤር.31:3-7” እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ። በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ።እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል።በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች። ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና።እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ስለ ያዕቆብ ደስ ይበላችሁ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፤ አውሩ፥ አመስግኑ። እግዚአብሔር ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ።”
እግዚአብሄር በምህረት ጠራን፡- ስለዚህ ለምህረቱ መልስ መስጠት ይገባል፣ ምህረቱ ርህራሄውን ገልጦአልና እንቅስቃሴያችን ጥንቃቄ ይገባዋል፡፡ ምህረቱን ቸል ብንል፣ በዘፈቀደ ህይወት ውስጥም ብንመላለስ በጣልነው ምህረት ቦታ ቁጣው ወጥቶ እንደሚያጠፋን ማሰብ ይገባል፡፡
ማቴ.16:26-27 ”ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።”
የእግዚአብሄር ምህረት የሰው ልጆች ትምክህት ነው፤ ምህረቱ ባይኖር ኖሮ የሚውጠን ጥፋት እጅግ ብዙ ነበር፡- ደካሞች የሆንን የሰው ልጆች ቅጣቱ ቢያልፍ ፍርዱ፣ ፍርዱን ብናመልጥ መቅሰፍቱ፣ መቅሰፍቱን ብናልፍ እርግማኑ ሊያገኘን የማይችልበት ሁኔታ እንዴት ሊኖር ይችላል? የእግዚአብሄር ሰፊ ትእግስት፣ ታላቅ የምህረት እጅ ግን ከዚህ ሁሉ ጉድ ይታደገናል፣ ላመንን ይህ ብርቱ ማስተማመኛ ነው፡፡
1ጢሞ.1:13 ”አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ”
ጳውሎስን ሊያጠፋ የሚችለው ፍርድ ሲከተለው አልነበረም ወይ? ሲፈጽመው የነበረው አመጽ ለፍርድ እያዘጋጀው ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነበር ድንገት ያመለጠው፤ ታላቅ የእግዚአብሄር ምህረት ፈጥኖ ስለቀረበው ከዚያ ጥፋት ተሰውሮ ዳነ፡፡ ለዚህም ነው ጳውሎስ ደጋግሞ የእግዚአብሄርን ምህረት አጉልቶ የሚናገረው፡፡በ1ጢሞ.1:14-15 ውስጥ እንዳለው፡-
”የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ።”
በማጠቃለያው የህይወትን መንገድ እንደተከፈለልን በመመላለስ እናጽናው በሚል መደምደሚያ ብናጠቃልለው፡- ይህንም የእግዚአብሄር የምህረት እጅ በእርሱ ዘንድ በጥንቃቄ እንድንመላለስ እንደሚረዳን በማሰብ ይሁን፣ በአካሄዳችን ሁሉ የማስተዋል ሀይል ከእርሱ ዘንድ እንደምናገኝም በማመን ይሁን፣ መንፈሱ አግዞን እንደፈቃዱ መሄድ እንደምንችል እርግጠኛ በመሆንና በቃሉ እንደተናገረው በሚሰጠን ጸጋ ሀይል ጸንተን እስከመጨረሻው ለመኖር እንደምንችል ያንም በመተማመን ይሁን፡፡