እንደተከፈለልህ ተመላለስ (1..)

የእግዚአብሄር ፈቃድ

አይሁድ ሳለህ ተከፈለልህ፣ ወይስ አህዛብ ሳለህ?
1ቆሮ.7:17 ”ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።”
የተጠራንበት ወቅት ላይ ተማሪ፣ ወታደር፣ ቢሮ ሰራተኛ፣ የቤት እመቤት እንሆን ይሆናል፡፡ ትዳር ውስጥ ልንሆን እንችላለን፣ ያላገባን ልንሆን እንችላለን፣ የተፈታ ትዳር ውስጥም ልንሆን እንችላለን፣ መበለት ልንሆን እንችላለን፣ ጡረተኛ ወይም ሌላም ሌላም፡፡ በየትኛውም ህይወት ውስጥ እንሁን ብቻ እግዚአብሄር ወደ ህይወታችን ይምጣ እንጂ እግዚአብሄር በህይወታችን ጸጋን ያንቀሳቀሳል፡፡ የቃሉ ጸጋ ህይወታችንን ማስተካከል ይይዛል፣ በተመሳሳይ የጸጋው መንፈስ ምሪት ይጀምራል፣ የእውነት ጭላንጭል እየሰፋና እለት በእለት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ያኔ ቆም ብለን በራሳችን አሳብ ከመያዝና ሁኔታዎቻችንን በዘፈቀደ ከማተረማመስ ይልቅ ወደ ህይወታችን የመጣውን የእግዚአብሄር ፈቃድ በማስተዋል ካስተናገድን የህይወታችን ይዘትና አቅጣጫ መለወጡ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ወደ አስጠጋን የህይወት ይዘት ጸንተን እንቁም እንጂ ያለንበት ሁኔታ ሊያሳስበን አያስፈልግም፡፡ እግዚአብሄር መንገዱ ላይ ስንገባ የምናነሳውን አንስተን የምንጥለውን ጥለን ወደፊት እንድንራመድ መፍትሄ ይሰጠናል፡፡
ዘፍ.17:1-4 ”አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፡- እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ።”
እግዚአብሄር ወደ አብራም ሲመጣ አብራም በደካማ የእድሜ ክልል ውስጥ ነበረ፤ ቤተሰቦቹ በጣኦት አምልኮ ውስጥ ነበሩ፤ በዘመዶቹ ምቾትና ተጽእኖ ተከብቦ ይኖር ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ምክኒያት ሆነው ወደ እግዚአብሄር ጥሪ እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከነዚህ አሳሪ ምክኒያቶች ባሻገር አብራም የጠራውን ተመልክቶአል፣ ሳይሸነፍ ያለበትን ሁኔታ ጥሶአል፤ አይኑ የከበበው ሁኔታ ላይ ተተክሎ የቀረ ስላልነበር ወደ እግዚአብሄር ጥሪ አተኩሮቱን ቀይሮ ሁኔታዎችን ተሻግሮአል፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እራሱን ያስገባው አብራም ቃልኪዳኑን ተቀብሎ እግዚአብሄር እንደነገረው በፊቱ ይመላለስ ዘንድ ችሎአል፡፡
እግዚአብሄር ሲጠራን ወደ ጥሪው የሚቀበለን በንሰሀ ህይወት ውስጥ ሆነን ስንቀርብ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ ንሰሀ ከሄድንበት የስህተት ጉዞ እንዲመልሰን ሲያደርግ የተላለፍናቸውን/ጥሰን የሄድናቸውን ስርአቶች ተመልሰን ልንጠግን፣ ወደ ሁዋላ ያልናቸውንም ተራምደን እንድንሞላቸው የሚያስወስን ነው፡፡ በትዳር ላይ ትዳር የፈጠረ ቢኖር ወደጌታ ሲመጣ የትዳርን ህግ አክብሮ በንሰሀ ወደ ቀድሞ ሚስቱ ሊመለስ ሁለተኛዋን ጨርሶ ሊተው (ከስህተት መንገዱ ሊመለስ) ይቆርጣል፡፡ እንደ ዘኬዎስ ከደሀ ላይ የዘረፈ ለጌታ ፍቅር ታዝዞ የወሰደውን ለባለቤቶቹ ሊመልስ ቀጥሎ በተጠራበት ሁኔታ አምላኩን ሊያከብር የተንቀሳቀሰበት አጋጣሚ ይታያል፡፡
ሉቃ19:8-10 ”ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን፡- ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም፡- እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።”
በንሰሀ ወደ እግዚአብሄር ቤት የገባ እንደ ተጠራበት አጠራር በአምላኩ ፊት ሊመላለስ እንዲገባ ቃሉ ያስተምረናል፡፡
1ቆሮ.7:18-24 ”ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር። ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል። ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር።”
በአጭሩ ህይወታችን በኑሮአችን አይገዛ፣ ኑሮአችን (ምድራዊው) ህይወት (መንፈሳዊው) እንደሆነ አይቆጠር፤ ምድራዊ ኑሮን ከመንፈሳዊ ህይወት ጋር ማተካካት ከባድ ስህተት ውስጥ ያስገባል የሚለውን ማስተዋል ይገባል፡፡ የሰው ልኩ የተጠራበት መጠራት ነው፣ ማለት፡- ሊኖር የሚገባው ህይወት ለመዳን በተጠራበት የእግዚአብሄር አላማ ትይዩ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ሲሆን የምንመለከተውን እናውቃለን፣ ለመሆን የምንሻውን መሻት እንገነዘባለን፣ መዳረሻችንን እናሰላለን፣ ራእያችንን እናስተካክላለን፣ በአጠቃላይ መምሰል የሚገባንን አውቀን ልካችን ጋ እንደርስ ዘንድ እንዘረጋለን፡፡
ኤፌ4:1-5 ”እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።”
ቃሉ አንደሚያስረዳው የምንመላለስበት የህይወት ልክ መጠራታችን ስለሆነ የህይወት መመሪያችን መሰረት በርሱ ላይ ስር ሰድዶ በትጋት እንድናደርገው የተገባ ነው ማለት ነው፡፡ ትኩረታችን በቀድሞው/በአሮጌው የህይወት ስርአት እንዳይሆን ነው ዋናው የእግዚአብሄር አላማ፡፡ እርሱ በአዲስ ኪዳን ሲገለጥ ሁሉን አዲስ የሚያደርግበትን የዘላለም እቅድ ስለገለጠ ከእርሱ ፈቃድ ጋር የምንራመድበትን መንገድ ብቻ አተኩረንበት ልንኖር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ አዲስ የህይወት ስርአት ገብተን አሮጌውን እንዳንናፍቅም ነው ዋናው ማሳሰቢያ፡፡
ፊል1:27 ”ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።”
እንደሚገባ መኖር አተኩሮት ይፈልጋል፤ በእርሱ ብቻ ነው በአንድ ልብ መኖር የሚቻለው፡፡ በአብሮነት ለወንጌል ለመጋደል፣ በአንድ መንፈስ ለአምልኮ፣ ለአገልግሎትና ለጸሎት … ለመቆም ሲታሰብ እንደሚገባ መመላለስ የተባለ ልከኛ ህይወት ቀዳሚ ሆኖ ሊታሰብ ይገባል፡፡ የአመለካከት ዝብርቅርቅ እንዳይኖርና ሰላም ያለበት ግንኙነት በወንድሞች መሀል እንዲኖር እንደወንጌሉ አጠራር መመላለስ ወሳኝ ነው፡፡
1ተሰ.4:1-3 ”እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን። በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና”
ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ የሚለው ትእዛዝ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት መንገድ የሚጠቁም ስለሆነ ቸል ልንለው አይገባም። ዘላቂ ህይወት ከጠራን ጌታ ጋር የሚፈጠርበትን እንዲሁም እየበዛ የሚሄድ ህብረት የሚቻልበትን መንገድ በጸጋው ማግኘት የምንችለው በዚህ ነው፡፡በ 1ተሰ.2:11-14 ውስጥ ሲያሳስብ እንደሚለው፡-
”ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን የመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።”
የደቀ-መዝሙር ትህትናና ታዛዥነት አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠውን ሃይማኖት ለመቀበልና በርሱ ለማደግ የሚያስችል የለማ ልብና ባህሪ ነው፤ ታላቁ የወንጌል እድል ፈንታ እግዚአብሔር ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ እንዲጠራን ሲያደርግ የወንጌል ግዴታም ለእግዚአብሔር እንደሚገባ እንድንመላለስ ያዛል። እንደ ክርስቲያን ለተጠራንበት አጠራር ተገዢ ለመሆንና በጥሪው ውስጥ ለመጽናት ለወንጌሉ ታማኝ መሆን ይጠይቃል። የእኛ ብርቱ ሥራ እግዚአብሔርን ማክበር፣ ማገልገል፣ በመታዘዝ ማስደሰትና ለእርሱ ብቁ ለመሆን መሻት/መፈለግ ነው። አመጸኞችና ኃጢአተኞች ግን ለወንጌል ስለማይታዘዙ ከእግዚአብሔር ጸጋ ይጎድላሉ፡፡
1ጴጥ.4:1-3 ”ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና። የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።”
በኃጢአት ላይ በጣም ጠንካራ እና የጨከኑ ሙግቶች የምናደርገው በክርስቶስ መከራ ውስጥ ያለፈውን የሀጢያት ጉልበት ከተማርን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ኃጢአትን ሊሽር/ለማጥፋት ሞተ፣ ሆኖም ለክፉ መከራ ራሱን አሳልፎ በፈቃዱ ቢሰጥም በየትኛውም ኃጢአት ከቶ አልተሸነፈም፤ ፈተናዎች ሊያቆሙት አልቻሉምም፡፡ ይህን የሚያስተውሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሕይወታቸውና የተግባራቸው አካሄድ የገዛ ምኞታቸው ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን ያደርጋሉ። ስለዚህ በሁሎችም ዘንድ እውነተኛ መለወጥ እንዲህ በልብ እና በህይወት ሲሆን አስደናቂ ለውጥ ይሆናል። በአጠቃላይ ከዳንንበት ጊዜ አንስቶ በፍጻሜ እስከሚሆነው የመጠራታችን ማብቂያ ቅጽበት ድረስ ባለው ረጅም ዘመን ውስጥ እንድንመላለስበት የተወሰነው አካሄድ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳይሆን ተወስኖአል፡፡
አንድ ሰው በእውነት ሲለወጥ ያለፈውን የህይወት ዘመን ያስብና እንዴት እንዳለፈ በማሰብ ይተክዛል፣ ይጸጸታል፣ ላደረገው ነገር በጣም ያዝናል፡፡ በዚህ ማስተዋልም ከከባድ ክፋት መራቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ኃጢአት ከሚመሩ ወይም ክፉ ከሚመስሉ ነገሮች መጠበቅን ይማራል። ስለዚህ እንደተከፈለልን መመላለስ ላይ አተኩረን ቃሉን በምናጠናበት ወቅት ትኩረታችን ወደ ተከፈለልን ነገር እንዲያተኩር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለመሆኑ እግዚአብሄር ምን ከፈለልን? የተከፈለልን ማናችን ነን? ለምንስ ተከፈለልን? እግዚአብሄር እንዴትስ ጠራን? ከላይ ያነሳናቸው ጥቄዎች በሙሉ በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ መለስ አላቸው፡፡
እግዚአብሄር ምን ከፈለልን? ለምንስ?
ሮሜ.6:23 ”የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።”
እግዚአብሄር ስለሀጢያት ከተጻፈው ፍርድ ሊያሰጥለን የልጁን ነፍስ መክፈል ነበረበት ( ዕብ.10:1-10)፡፡
በሙሴ እጅ ለእስራኤል የመጣው ሕግ ፍጹም መዳንን ለእስራኤል የሰጠ ሳይሆን ለክርስቶስ መምጣት ጥላ ነበር፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ ጊዜው ደርሶ እስኪገለጥ ድረስ በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት እንዲጠበቁ ሆኖአል፡፡ መስዋእቱ በሕሊና የተሰወረውን ኃጢአት ስለማይሽር መስዋእቱ ዘወትር ሊቁዋረጥ አልተገባውም፤ መሥዋዕቱም በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ ሆኖ ይቀርብ ነበር፡፡ እስራኤል ያቀረበው የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ስለዚህ ሀጢያትን ሊያስወግድ እግዚአብሄር ራሱ አማኑኤል ሆኖ መጣ፡፡ ሀጢያታችንን ሊሽር ወደ ዓለም ሲገባም እንዲህ ተባለለት፡- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም።በዚህ ምክኒያት ሁለተኛውን ሊያቆም (በክርስቶስ የሰራውን ማዳን ሊያጸና) የፊተኛውን (የሙሴን ስርአት) ሽሮአል፡፡ በዚያም የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።
ሆሴ.13:12-14 ”የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል። ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው። ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች።”
የሰው ልጆች ስለ መተላለፋችን ቁስል ሆኖብናል፣ ስለ በደላችን ድቀት፤ ስለ አመጻችንም ተግሣጽ፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ይህን ሁሉ ሊያነሳልንና ቅጣታችንን ሊቀበል በፈራጆች እጅ ተላልፎ እስኪቆስል ተገርፎአል። ሀጢያታችን እንደ በጎች ተቅበዝባዥ አድርጎ አጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለና ህይወቱን ወደ ጥፋት መራ፤ እግዚአብሔር ግን ሊተወን አልፈቀደም፣ ስለዚህ የሁላችንን በደል ከእኛ ላይ አንስቶ በእርሱ ላይ አኖረ።
ጻድቅ ላይ የሚወድቅ የአመጸኞች ፍርድ እንደምን ብርቱ ነው? ጌታ ግን ያን ሁሉ ተሸከመልን፡- ስለዚህ ተጨነቀልን፣ ተሣቀየም በታላቅ ትእግስት የጨካኞችን ፍርድ ሲቀበልም አፉን ከቶ አልከፈተም፤ ሀይል፣ ስልጣንና ቻይነቱን አውልቆ ጣለና ጉልበት እንደሌለው ምስኪን ጠቦት ለመታረድ ተነዳ፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም እኛን ከሞት ለማዳን ጨክኖ በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ስለፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አደረገ፣ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፣ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፣ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር ተወገደ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አመጸኛ ስለነበረ ነው ወይ? እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ሊሸከምና ስለ ዓመፀኞችም ሊማልድ ነበር።
የተከፈለልን ማናችን ነን?
1ቆሮ.7:17 ”ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።”
እግዚአብሄር በውድ ልጁ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በደሙ ባደረገው ማዳን ቤዛነታችን የሆነውን የበደላችን ስርየት የሰጠን እኛ አመጸኞች የሰው ልጆች በሙሉ ነን። ሰው ከተባለ ፍጥረት መሀል ከሀጢያት ክፍያ (ሞትን ከሚያህል አስፈሪ ፍርድ) ሊያመልጥ የሚችል ማንም የለም፣ መቼም፡፡ የርሱን በጎነት ያመንንና የተቀበልን ግን እዳችን ተከፍሎአል፡፡ ምክኒያቱም እርሱ ከጨለማ ሥልጣን ስላዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ያገኘን ስለሆነና በማዳን ሀይሉ ከሞት ስፍራ ተግዘን ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት ስለፈለስን፡፡
ቲቶ2:14 ”መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።”
ለምንስ ተከፈለልን?
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ያቀርቡዋቸው መስዋእቶች በሥጋ ሥርዓት የሆኑ ስለነበር የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አልቻሉም። የሰውን ህሊና ከሞተ ስራ ማንጻት የሚችለው የጌታ ኢየሱስ ደም ብቻ በመሆኑም ጌታ ደሙን አፍስሶና ስጋውን ቆርሶ ለሰው ልጆች መስዋእት እስኪያቀርብ ድረስ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም ልዩ ልዩ የመታጠብ ስርአቶች በምሳሌነት አገልግለዋል፡፡

ዕብ.9:8-14 ”ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም። ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?”
በሙሴ የተሰጠው ህግ ከዘላለም ሞት የሚያድን ስላልነበር የህዝቡን ሀጢያት በሞቱ ሊያስወግድ የሚችለው ክርስቶስ ኢየሱስ መገለጥ ነበረበት፡፡ እርሱ ከሞተ ሥራ ሕሊናችንን የሚያነጻበትን ደሙን ለእግዚአብሄር አቅርቦአል፡፡
ሮሜ.8:3-4 ”ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ።”