እንደሚጠበቀው መመላለስ

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ወደ ከበረው ዘላለማዊ መንግስትና ወደ ቅዱሳን ማህበር ሊገባ የወሰነ አንድ ትውልድ ቅድሚያ የነፍሱን ደህንነት ሊያረጋግጥና አስተማማኙን መንፈሳዊ ማህተም ሊታተም ይገባዋል (ዮሀ3፡5)፡፡ ያን ማረጋገጫ በቅዱሱ አምላክ ስም በሚሆን የሀጢያት ስርየትና የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሚቀበል መሆኑን የቃሉ አጠራር ያረጋግጣል፡፡ ይሄ እርግጠኛና እጅግ አስፈላጊ የሆነ የእግዚአብሄር አሰራር ወደ መንግስቱ የሚያስገባ ቢሆንም ታላቁ ድል ሙሉ የሚሆነው እግዚአብሄር በሚሰጠው ቀሪ እድሜ በማህበሩ ውስጥ እንደሚገባ በመመላለስ ሩጫን መጨርስ ነው፡፡
ወደ መንግስቱ መግባትና በመንግስቱ ውስጥ መመላለስ እኩል ዋጋ እንዳለው ቀለል ባለ ምሳሌ ብናይ፡- አንድ በጥብቅ ጥበቃ የተከበበ ግቢ ውስጥ መግባት ያስፈለገው ሰው ቢኖር ቅድሚያ ወደ ቅጥር ግቢው የመግቢያ ፈቃድ/ማለፊያ እንደሚያስፈልገው ያ ካልሆነ የቅጥር ክልሉን ከፈቃድ ውጪ በማለፉ እንደሚጠየቅ ይታወቃል፤ ከዚያ አልፎም ተገቢውን ቅጣት ስለመተላለፉ ይቀበላል፡፡ ሆኖም ስርአቱን ጠብቆ ቢገባ እንደገና በግቢው ውስጥ ይንቀሳቀስ ዘንድ የግቢውን ስርአት መከተል የግድ ይለዋል፤ ወደ ግቢው መግባትም ሆነ በግቢው ውስጥ መንቀሳቀስ እኩል ህጋዊነትን ይጠይቃሉ፡፡ በቅዱሳን ማህበር ውስጥ የሚኖር የአካሄድ ስርአት ከላይኛው ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል፡- ወደ ማህበሩ መቀላቀልና በማህበሩ ውስጥ በስርአት መመላለስ እኩል ዋጋ አላቸው፣ ሁለቱም ከእግዚአብሄር የተገኙ ናቸውና፡፡ ማህበሩ መለኮታዊ ፈቃድ እንዳለበት በቃሉ በኩል እንይ፡-
1ጢሞ.3:14-15 ”ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።”
በቃሉ ውስጥ ያለ በእግዚአብሄር ማህበር የሚኖር መርህ ምን ይላል (ኤፌ4)፡-
1. እንደሚገባ ተመላለስ
በእግዚአብሄር ህዝብ መሃል ያለ የኑሮ ስርአት አቅጣጫ አለው፣ የሚገባ አካሄድ፡፡ እንደሚገባ ለመመላለስ የሚሻ ለአእምሮ የሚመች መንፈሳዊ ህይወትና ምሳሌነት ያለው ኑሮ ሊኖር ይገባዋል፡፡ የሚገባ ሲሆን የሚመችና የማይቆረቁር ባህሪን በተላበሰ አኩዋሀን፣ ዝግ፣ ስክንና ማስተዋል ያለበት አካሄድ ያለውም ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እርሱ በሚፈልገው መንገድ መራመድ፣ በሰውም ፊት ቅንነትን በሚገልጥ መንፈስ መመላለስ ተገቢነት አለው፡፡
ኤፌ4:1 ”እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ” ሲል ይመክራል ሀዋርያው፡፡
በእለት ተእለት ኑሮአችን ውስጥ የሚኖረን አካሄድ ልኩ የተጠራንበት አጠራር ነው፡፡ የተጠራነው በቅዱስ አጠራር ስለሆነ ቅዱሱን ጌታ አይተን የእምነትን ሩጫ መሮጥ ተገቢ ነው፡፡ በተገቢው መስመር መመላለስ በእግዚአብሄር ፊት ሳይታጡ ተጠንቅቆ መኖር ያስችላል፣ ስለዚህ ፡-
– መመላለስ በተወሰነልን የመሮጫ መስመር ላይ ሆነን – ፈር ባልለቀቀ አካሄድ እንድንኖር በሚያስችል መልኩ፣
– መመላለስ በጽድቅ መንገድ – እውነትና ትህትና ላይ ተመስርተን፣
– መመላለስ ትግስት ባለበት አካሄድ – ጌታ ኢየሱስን በመጠባበቅና ያሳሰብነውን እስኪመልስ እንድንታገስ በሚያስችለን መልኩ፡፡
ማንኛውም አማኝ የሚመላለሰው እይታውን ከጌታ የደህንነት ስራ ላይ አድርጎ ቢሆን ስራው ስኬታማ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሰጠን ተስፋ ድላችንን ማጽኛ በመሆኑም ትምክህታችን እርሱ ነው፡፡
2. በፍቅር ታግሰህ ኑር
ትግስት ምቾት የሚሰጥ የመቀበያ መንገድ አይደለም፡፡ ሰው የሁኔታዎችን ያለመመቸትና አስቸጋሪነት እያየ በትእግስት የጌታን መልስ ከጠበቀ ግን ሽልማቱን ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር በመጠበቅ ውስጥ የሚገጥመውን በትእግስት ችሎ መኖር ነው፡፡
ኤፌ4:2 ”በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ” አለ፡፡
ኑሮን በዚህ አለም ላይ የምንኖረው በእግዚአብሄር እርዳታ ነው፡፡ የሚያደናቅፍ ጠፍቶ አይደለም፣ የሚጥልና የሚያቃጥል አጥተንም አይደለም፣ እንዲያውም በየእለቱ ልባችንን የሚያርሰው ስጋት እንዴት ያቆማል እያልን ነው ቀኑን የምንኖረው፣ ሆኖም ግን በሁሉም አቅጣጫ የሚጠብቀንና የሚዋጋልን የሰራዊት ጌታ ስላለ ጭንቀቱን ታግሰን እናልፈዋለን፤ ይህን ተረድተን በፍቅሩ መታገስ ከቻልን ቀኑን በሙሉ አሸናፊነት የኛ ነው፡፡
ዮሐ.16:33 ”በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ሲል የሚናገረውን የድል አምላክ በትእግስታችን ውስጥ ካስገባን አሸናፊ ያደርገናል፡፡
3. የመንፈስን አንድነት ጠብቅ
አንዱ ደቀመዝሙር ከሌላው ጋር በአንድ ልብ ይመላለስ ዘንድ አይገባውምን? እየኖርን ያለበት መንፈሳዊ ቤት እኮ የእግዚአብሄር መንግስት ክልል ነው፡፡ የተለያየ ትምህርት፣ እቅድ ወይም አስተሳሰብ ያለው ማህበር በአንድነት ማዝገም ይሳነዋል፡፡ ለመንጠባጠብም ምክኒያት ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ አካሄዳችን የእግዚአብሄር ፈቃድ መገለጫ ምክኒያት እንዲሆን ከፈለግን በእርሱ መንፈስ አንድነት አንድ መለኮታዊ ግብ ላይ መድረስ ይገባናል፡፡ ሳንገልጽ ማለፍ የለብንም የምንለው መለኮታዊ ግባችን፡- ዘላለማዊ ህይወት፣ በመንግስቱ ለዘላለም መኖርና እርሱን ፊት ለፊት እያዩ መኖር ነው!
ኤፌ4:3 ”በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።”
የመንፈስ አንድነት ለእግዚአብሄር ህዝብ ሰላማዊ ህይወት መሰረት ነው፡፡ ትህትና ያለው አቀራረብ፣ መንፈስን ላለማሳዘን የሚደረግ ጥንቃቄና ደካማን ያለነቀፋ መሸከም ካደገ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ህይወት በተግባር በሚተረጎም እምነት ይገለጻልና ያን ማድረግ ግዴታ ነው፡፡
4. እውነትን በፍቅር ያዝ
ለአካሉ እድገት እንዲጠቅም ሆኖ የሚገለጽ መዋደድ ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡ አዲስ ለሚወለዱ የጌታ ልጆች መጽኛ መንገድ ነው፣ አዳዲስ ሰዎች እንዲመጡ መንገድ ነው፣ ጌታን በቤተክርስቲያን ማንገሻ መንገድም ስለሆነ ነው፡፡ እውነት ከፍቅር ጋር ተያይዞ መሄድ ከቻለ ቅንነት እንጂ ቅንአት የለ፣ መሸከም እንጂ መጣል የለ፣ መንፈሳዊነት እንጂ ስጋዊነት የለ!
ኤፌ4:14-16 ”እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ
ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።”
5. የሚጠፋውን አሮጌ ሰው አስወገድ
በአእምሮ መንፈስ በመታደስ አሮጌውን ሰው ማራገፍ ይጠበቃል፣ በመንፈሳዊ ህይወት ሂደት ውስጥ፡፡ አሮጌው ሰው አሮጌ ልማድ ይዞአል፣ አሮጌ እውቀት ይዞአል፣ ከምንም በላይ አስቸጋሪውንና ፈታኝ ዳገት የሆነውን አሮጌ ባህሪ ይዞአል፡፡ ከአለም ላይ የሸመትናቸው ልማዶች ለአዲሱ ሰው ማንነት አዋራ ናቸውና በቃሉና በመንፈሱ መራገፍ ይገባቸዋል፡፡ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና ከሰፈራችን ሁሉ ወስደን የግላችን ያደረግናቸው አመሎች እጅግ ጠር ናቸው፣ ለመንፈሳዊነት፡፡ ስለዚህ በቃሉ ሞረድ ተፍቀው መወገድና ለአዲሱ ማንነት ስፍራ መልቀቅ አለባቸው፡፡
ኤፌ4:22 ”ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥”
6. አዲሱን ሰው ልበስ
በመንፈስ ስንገረዝ አሮጌ ሰውነታችን ተገፍፎልን አዲስ ልብስ የሆነው ክርስቶስን ለብሰናል፡፡ ለብሰን ላናወልቅም ተጠርተናል፡፡ መቼ ነው ልብሱ የሚወልቅብን? አሮጌውን ሰው ወደ ህይወታችን ስንጎትት፣ ማንነታችን ላይ ስንደርብም አዲሱ ልብስ ይወልቃል፡፡
ኤፌ4:24 ”ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”
7. እውነትን ከባልንጀራ ጋር ተነጋገር
ቃሉን ባማከለ መልኩ መነጋገር ውሸትን ለማስወገድ ብቸኛው መፍትሄ ነው፡፡ ከጉዋደኛ ጋር እውነትን መነጋገር፣ ከትዳር ጉዋደኛም ጋር እንዲሁ በእውነት አብሮ መሆን፣ ማሰብ፣ መነጋገርና መጠባበቅ ከእግዚአብሄር ልጆች የሚጠበቅ ነው፡፡
ኤፌ4:25 ”ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”
8. ሀጢያት አታድረግ
ቃሉ ተቀያይሞና ተጨቃጭቆ በኩርፊያ መከራረምን ይጠላል፡፡ ምክኒያቱ ግልጽ ነው፡- ጊዜ ጊዜን እየወለደ ሲሄድ ቅያሜ ስርና ቅርንጫፍ ማውጣት ይጀምርና ለመነቀል አዳጋች ይሆናል፡፡ እስቲ እናስበው፣ አንድ ቀን ያደረ ቅያሜ ሳምንት ከከራረመው ጋር እንዴት ይወዳደራል? ተቀያይሞ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን መለያየትም ሊመጣ ይችላልና፡፡ ቅያሜው ቂም ሆኖ ልብ ውስጥ ከተቀበረ በሁዋላ እንዴት ያለ ታላቅ ሀጢያት ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል ይቻላል፡፡
ኤፌ4:26 ”ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥”
9. ለዲያቢሎስ ፈንታ አትስጥ
ጥላችን አድሮ ሲከራርም ባላንጣችንን ዲያቢሎስን ይጋብዛል፤ ሰላምን መሀከላችን አልጠራንምና ጠላት ሳይጋበዝ መሀላችን ዘው ይላል፡፡ እድል ስለሰጠነውና ክፍተት ስላበጀንለት ፈጥኖ ይደርስብናል፡፡ በመወደድ ካላባረርነው ፈንታ ሰጥተነዋል፣ በመከባበር ካላራቅነውም ጎረቤት አድርገነዋል፡፡ በመተሳሰብ ካልተካካስን ቂመኛነታችንን ይጠቀምበታል፣ በልክ በመኖር ፈተና ውስጥ እስካልገባን ድረስ ደግሞ ሁልጊዜ በቅርባችን ነው፤መቼም ይሄንን አንርሳ፡፡
ኤፌ4:27 ”ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።”
10. መልካም ስራ
ቃሉ ስራ የሚለው ይህ መልካም የተባለ ስራ ጌታ ለደህንነታችን የሰራውን አይነት ስራ ሲያመለክት አይደለም፡፡ ጌታ የሰራውማ ሰው ያቃተውን ነው፡፡ ሰው ከሀጢያት መንጻት አልቻለም፣ ሀጢያትን ማሸነፍ፣ ሞትን ማምለጥ አልቻለም፡፡ ይህንን የሚችል ጌታ ግን ሰራው፤ ሰውን ከአሸናፊው ሀጢያትና ሞት በሰራው ስራ አስመለጠው፡፡
ነገር ግን ዳግመኛ ከማይጠፋ ዘር እስከተወለድን ድረስ፣ የርሱን መለኮታዊ ባህሪ በመካፈላችንም አላማውን አስፈጻሚ መሆናችንን በመልካም ስራ የምናሳይ ነን፡፡ መውደድ የምንችለው እርሱ ፍቅርን ስለሰጠን ነው፤ በጎ የምንሆነው በጎነትን በውስጣችን ስላስቀመጠ ነው፡፡
ኤፌ4:28 ”የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።” ይላል፡፡
በማጠቃለያው እንደሚጠበቀው መመላለስ፣ ቃሉ በሚመራው መሰረት መሄድ ነው፣ መታዘዝ ነው፣ መፈለግ ነው፣ የራስን መተው ነው፣ ትቶም የርሱን መቀበል ነው፡፡ መመላለሳችን ያለእርሱ እርዳታ እንደማይሳካ አምኖ መከትልም ነው፡፡