የተሳሳተ ሀይማኖት ለምን ከመሰለኝ ይነሳል? መሰለኝ የስህተት መፈልፈያ ዋሻ በመሆኑ ነው፤ የጥርጥር መሰረት በመሆኑም የተሳሳተ ሀይማኖት ያስፋፋል፡፡ ሀይማኖቱ በሚመስል እውቀት ላይ በመመርኮዙና ግምታዊ ድምዳሜን በመቀበሉ ምክኒያት መንገዱን ይስታል፡፡ ቀጥ ብሎ ማደግ በሚገባው ወቅት ተንጋድዶ ከፍ ይላል፣ ከነአመሉ እንደተወላገደ ሽቅብ ይሄዳል፣ ያለእርምት ይጎለምሳል፣ ስርም ይሰዳል፣ በመጨረሻ ግን ማምለጥ በማይችለው የስህተት ወጥመድ ላይ ይቆማል፣ ይነከሳል፡፡ በተለይ ግምታዊ ትንታኔዎችን ተመርኩዞ ሰዋዊ ውሳኔዎች ላይ የሚደርስ መንፈሳዊ እውቀት መደምደሚያው እርግጠኝነት የሌለው ወግ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ያልታረመው መንፈሳዊ እውቀት በቃሉ ውሀ ልክ እየተቃና ሳይሄድ ሲቀር ዘግይቶም ቢሆን የሰዎች ፍልስፍናና ልብወለድ ትርክት ያጥለቀልቁታል፡፡
ጳውሎስ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም ከፍ ከማድግ ይልቅ ማዋረድ እንዲገባ ለምን ወሰነ? በኢየሱስ አካባቢ አንድ የተወናበደ አመለካከት እንደተነዛለት ያስታውቃል፡፡ የተማረው ትምህርት የተረጋገጠ እውቀት ሳይሆን ስማ በለው ስለነበረ የስህተት ውሳኔ ላይ ሲጥለው ይታያል፡፡ ክፋትና ወንጀል ሲሰራ የሀይማኖት አባቶች አግዘውታል፣ አበረታተውታል፣ እንዲያጠፋ እንዲገድልም ይሁንታ ሰጥተውታል፡፡
የአይሁድ ሀይማኖት ከህግና ትእዛዛት ባፈነገጠ መልኩ ወግና ልማዶች አጠንክረው ይዘውት ነበር፤ የተለየ እውቀት ላይ በመመርኮዝ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የመሳሰሉ ክፍፍሎች በውስጡ በቅለው ህዝቡ የነብያትን ድምጽ ተከትሎ ወደ ክርስቶስ እንዳይመጣ አድርጎአል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በእነዚህ የተለያዩ ክፍሎች ተጽእኖ ምክኒያት ህዝቡ ከቃሉ ውጪ በሆነ መልኩ ግምታዊ ድምዳሜን ተቀብሎ መንገዱን ስቶአል፡፡ ለዚህ አንዱ ምሳሌ የጳውሎስ ግምት ወጤት ነው፡፡ የርሱም ኑዛዜ ያን ያመለክታል፡-
ሐዋ.26:9-29 ”እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። ስለዚህም ነገር ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ።እኔም፡- ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ፡- አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።”
የሀዋርያው ጳውሎስ ታሪክ እንደሚያስረዳው የርሱ ትምህርትና እውቀት ወደ ኢየሱስ የመራው ሳይሆን ኢየሱስንና ደቀመዛሙርቱን የሚቃወም እርምጃ ውስጥ ያስገባው ነበር፤ የትምህርቱ ጉልበት የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም መቃወም እንዲገባ አስወስኖታል። ተቃውሞውን ከኢየሩሳሌም አንስቶ እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ ያዳርስ ዘንድም የሽማግሌዎችንና የካህናትን ይሁንታ ተቀብሎአል። የአይሁድ ትምህርት ጽድቅ የሚመስል አመጽ በውስጡ ስለፈጠረ ለዚያ በመታዘዝ ነፍስ እስከመግደል ቆረጠ፤ ይሄም የእውቀቱን አደጋ ያሳያል፡፡ በሐዋ.8:3 ውስጥ ሳውል ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ እንደነበር ተገልጾአል፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥም ነበር። እውነት የመሰለው ውሳኔና መንገድ አሳስቶ ከእውነተኛው አምላክና ከህዝቡ ጋር እንዲ ሊያጋጨው በቅቶአል፡፡
እዚህ ላይ በጉልህ እንደሚታየው የጌታ ትምህርትና የአይሁድ መምህራን ትምህርት ሁለት የተለያየ ሀይማኖት በእስራኤል ላይ ሊፈጥር ችሎአል፤ ሆኖም የጌታን ትምህርት ያስተማሩ በምድር ላይ ሰፍተው ሲጸኑ፣ የአይሁድ መምህራን ግን በተሳሳተ መንገድ ህዝቡን በመምራታቸው ጭራሹን ከፈቃዱ ያፈነገጡ ሆኑ፡፡
ሃዋርያው በጌታ ኢየሱስ አምኖ አገልጋዩ ከሆነ ወዲህ ቃሉን መሰረት ያላደረገ ትምህርት አፍራሽ እንደሆነ በመገንዘብ ደቀመዛሙርትን በሮሜ.16:17-18 ውስጥ ያስጠነቅቃል፡-
”ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።”
ከላይ በቃሉ ውስጥ የተመለከተው መለያየትንና ማሰናከያን ይፈጥራል የተባለውና አታላይነት የሚንጸባረቅበት ”መልካምና የሚያቆላምጥ ንግግር” ደቀመዛሙርት ላይ (በክርስትና ውስጥ) ተጽእኖ የሚፈጥርና ልብ የሚያታልል ሆኖ ተገኝቶአል፤ ያን ከግምት ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሀዋርያው ደቀመዛሙርትን ተጠንቀቁ የሚል መልእክት ልኮላቸዋል፡፡
እንደ ሀይማኖት ሰው እግዚአብሄርን ማስቀደም ስለሚያስፈልግ መሰረታችንን ቃሉ ላይ ማኖር አስፈላጊ ነው፤ ከዚያ ውጪ ለአማኝ ምንም ዋስትና የለውም፡፡ ሀዋርያው ከቀድሞው የተሳሳተ መንገዱ ስለተማረና የጌታን መንገድ ፈጽሞ ስላስተዋለ አማኞች መንገዳቸውን እንዲመረምሩ ያስጠነቅቃል፤ ከግምት አካሄድ እንዲጠበቁ፣ መንፈሳቸውን እንዲቆጣጠሩና ከቃሉ ውጪ አልፈው በራሳቸው መንገድ እንዳይገቡ በስህተትም እንዳይያዙ ያመለክታቸዋል፡-
1ቆሮ.4:6-8 ”ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ።አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር።”
የመሰላቸውን የሚያስተምሩ ምን ያህል ልቅ እንደሆኑ ቃሉ ያጋልጣል፡፡ ከተጻፈው ሳያዛንፉ በሚያስተምሩ መሀል መሽገው የልባቸውን ትምህርት ሲያስፋፉ የነበሩ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይሆን ምኞታቸውን የተከተሉ አደገኞች ናቸው፡፡ በወንጌል አስተማሪዎች መሀል እንደ አረም የበቀለ የሀሰተኞች ትምህርት ደቀመዛሙርት የተማሩትን በመቃወም ጥርጥር፣ መለያየትንና ማሰናከያን ሲያስቀምጥ ኖሮአል፣ ዛሬም አለ፡፡ ሃዋርያውም ከነዚህ አሰናካይ ሰዎች እንዲጠነቀቁ ከበካይ ትምህርታቸውም ይርቁ ዘንድ እንዲለዩ ደቀመዛሙርትን ደጋግሞ አሰጠንቅቆአል፤ እግዚአብሄርን የማይፈሩ፣ ለጌታ ፍቅር የማይገዙ፣ በድፍረት፣ በሽንገላ ቃልና በሚያታልል አቀራረብ ሰዎችን ያስታሉና፡፡
ኤፌ4:14-15 ”እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ”
የዚህ ማስጠንቀቂያው ግልጽ ነው፣ ማደግ ባለብን ሰአት እንዳናድግ የሚያፍገመግም የትምህርት ነፋስ አያናፈሱ ከሚያንሳፍፉን ሸንጋዮች እንጠበቅ የሚል ነው፣ ይህን ተግባራዊ ማድረግም የግድ ይላል፡፡ ያለበለዚያ እርግጠኛውን የወንጌል እውቀት መጨበጥ ተስኖን በግምት ተነጂና የከንቱ ትምህር ምርኮኛ ያደርገናል፡፡ በቆላ.2:6 ውስጥ የተቀመጠልን ምክር ይህን ያስረግጣል፡-
”እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”
እውነት በፍቅር በሚሰበክበት ማህበር አካባቢ የሚያንዣብብ የሀሰት ትምህርት ሲከሰት በፍጥነት ካልነቀሉት እግርን ወደማይገባ አቅጣጫ መምራቱና ማሳቱ አይቀርም፡፡ በተለይ በእምነት ባላደጉት ላይ ከሚያደርሰው ጥፋት አንጻር ይህ መንፈስ ጥንቃቄ ያሻዋል፤ ምክኒያቱ ደግሞ የመንቀል ዝንባሌው ከፍ ያለ በመሆኑና የተመሰረተበት የመሰለኝ አሳብ ይሆናል? አይሆንም? እያሰኘ በዋዠቀ እውቀት ላይ ስለሚያቆም፣ ከርሞም ገፍቶም ሲሄድ አሳችና ተቃዋሚ ስለሚያደርግ ነው፡፡
ያለመመራመር እውነትን እንዳናገኝ ይጋርዳል፤ ያልፈተሸነው ትምህርት በግምት እንድንወስን አስገድዶ ያልታሰበ ችግር ላይም ይጥለናል፡፡ ስለዚህ በግምት ከመወሰን ይልቅ የሚሻለው የሰማሁት እንዲህ ይሆንን? ብሎ በመመራመር መዳን ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች የሚሆኑ በቤርያ ገኙ የነበሩ ደቀመዛሙርቶች ናቸው፡-
ሐዋ.17:11 ”እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።”
- ያላረጋገጡ አማልክትን በአካል ያገኙ መሰላቸው፡-
ሐዋ.14:11-18 ”ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ፡- አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል አሉ፤በርናባስንም ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ ሄርሜን አሉት።በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ።ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን።እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው።ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው።””
- እውነትን ያላወቁ ፈላስፎች የዘላለሙ አምላክ አዲስ አምላክ መስሎአቸዋል፡-
ሐዋ.17:16-20 ”ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት።ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር።ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም። ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል? አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ።ይዘውም። ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና፤ እንግዲህ ይህ ነገር ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እንፈቅዳለን ብለው አርዮስፋጎስ ወደ ተባለው ስፍራ ወሰዱት።”
- ጌታ ኢየሱስ ስለክርስቶስ በመሰለኝ የሚነገረውን ሊያጠራ ፈልጎ የጠየቀው ጥያቄ ነበር፡-
ማቴ.22:41-42 ”ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ፡- ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም፡- እንኪያስ ዳዊት፡- ጌታ ጌታዬን፡- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።”