የመሰለንን ማድረግ በኑሮአችን ውስጥ የተለያየ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለአንድ ነገር ገምቼ እንደመሰለኝ ቢሆንና የገመትኩት ቢፈጠር ቢያንስ አስቀድሜ የጠበቅኩት ሆኖአልና በግምቴ ትክክለኝነት እመካለሁ፤ ደግሞም ነገሮች ከመሆናቸው አስቀድሜ መገመቴ ከቻልኩ ከአስቸጋሪ ሁኔታ ማምለጫ አገኝበት ይሆናል፣ ግምቴ ቢሳሳት ግን ተቃራኒ ውጤት ይፈጠራል፡፡ እርግጥ ነው ጥሩ ገማች አለም ትፈልጋለች፡፡ ይሄም በቦታው ተገቢ ነው፡፡ እንደ አየር ሁኔታ ትንበያ የመሳሰሉ ተግባሮች ዛሬ ላይ ሆነው የነገንና ከነገ በሁዋላ የሚመጣውን ሊገምቱና ይሆናል ያሉትን ሊያውጁ ይገደዳሉ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ግን ግምትን አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ ለምሳሌ በፍርድ ቤት ጉዳይ በግምት/በመሰለኝ መመስከር ከፍተኛ ጥፋትና ቅጣት ያስከትላል፡፡
ግምትን ወደ ሀይማኖት ስናመጣው ሁኔታውን ከፍርድ ቤቱ ጉዳይ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን (የሁለቱም ምስክር እርግጠኛ የሆነን መረጃ ይሻልና)፡፡ የሃይማኖት ግምትና መስሎኝ ይህን አሰብኩ፣ እንዲህ አደረግኩ፣ ያንን ወሰንኩ… ባይነት በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲያውም ቃሉ ይህንን ስህተት አጉልቶ ሊያሳየን ነው የሚፈልገው፡-
2ቆሮ.1:17-20 ”እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን? እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም።በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል።እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው።”
ከራሳችን ግምት በመነሳት ለሰዎች እርግጠኛ ሆነን የምንነግረው ነገር ማምታታቶችን በማስከተል ብዙ ውጥንቅጦችን ሊፈጥር ይችላል፤ በዚያ ምክኒያት የሰው አሳብ ተወዛውዞ ብዙ መናጋቶች ይፈጠራሉ፤ ልቦች ቅዝቅዝ ብለው ተአማኒነት ይጠፋል፤ አሉባልታዎች ተከትለውም የማህበሩ መፍረስ ያልያም መላላት ቀላል በሚመስል ግን የእግዚአብሄርን ቃል ባላማከለ እውቀት ምክኒያት ይከሰታል፡፡ ሃዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያንን አጥብቆ ይጠይቃል፡- በአገልግሎቱ ውስጥ ቃሉን የሚለዋውጥና የሚያሳፍር ውጤት ተከትሎ እንደሆን ይጠይቃቸዋል፡፡ በእርሱ ዘንድ የነበረ ትምህርት መለኮታዊ በመሆኑ ይሆንን ወይስ አይሆንን? እያሰኘ የሚያዋዥቅ ሳይሆን በእርግጠኝነት ትክክሉ አዎን የተሳሳተው አይደለም ብቻ እንጂ አንዴ አዎን ሌላ ጊዜ አይደለም በሚል ማመንታት የሚፈጥር ትምህርት እንዳላስተማረ ለደቀምዛሙርት አስረግጦ ይናገራል፡፡በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም (ነቢያት ከተናገሩት ያፈነገጠ ጥርጥር ውስጥ የሚከት አልነበረም)፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል (የሚመስል ሳይሆን የሆነ ነው) ሲል በዘመኑ ከነበሩ ስለ ክርስቶስ የመሰላቸውን ከሚሰብኩ አስተማሪዎች በተለየ እርግጠኛውን እንደሰበከ ያሳስባል። እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና (በብሉይ ኪዳን ስለክርስቶስ የተነገረው የተስፋ ቃል ሆኖ የታየው በክርስቶስ ነውና)፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው በማለት የነብያቱ ትንቢት በክርስቶስ መፈጸሙን (አሜን መሆኑን) እንዳይጠራጠሩ ይመክራቸዋል።
በመንፈሳዊ ህይወት የሚመስለን ነገር ሁለት አማራጭ ይዞ ይቀርባል (ውስጣችንን መንታ መንገድ ላይ ያስገባል)፤ ስለዚህ ግምታችንን ከተናገርንና ካደረግን በሁዋላ ጉዳዩ እንዳሰብነው ሳይሆን ሲቀር ወደ ሁለተኛው አማራጭ ዞር እንድንል ያስገድዳል፡፡ ይህ ድርጊት ከቃሉ የሚያጎድልና የእምነት ኪሳራ የሚፈጥር ነው፡፡የጌታ ደቀመዛሙርት የሆኑትን ማየት ይቻላል፡-
ሉቃ24:36-41 ”ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፡- ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው።”
ደቀመዛሙርቱ ግን የመሰላቸውን እንመልከት፡-ባዩት ኢየሱስ እርግጠኛ አልነበሩም፤ ሲያወሩ የነበረው ነገር እርግጠኛነት ስላልነበረው በአይናቸው ያዩት ኢየሱስ ምትሀት ሆኖ የታየ እንጂ በአካል በመሃከላቸው የተገለጠ እስካይመስላቸው ሳቱ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ስለ እርሱ እንዲሰብኩ ከዚያ ግምታቸው ጋር ቢተዋቸውስ ኖሮ? ትምህርታቸው ልዩ ወንጌል ፈጥሮ ለነፍሳት ጥፋት ምክኒያት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያለበለዚያ የእነርሱ ወንጌል አዋጅ ነጋሪነት ያበቃ ነበር፡፡ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? ሲል የጠየቃቸው የመሰለኝ ግምታቸው ከያዛቸው ድንጋጤና የልብ ማመንታት ጋር መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
በሀይማኖት ጉዳይ የመሰለኝ ድምደሜ ብዙ ጥፋት አስከትሎአል፤ በርሱ ሰበብ ሀይማኖቶች በእጅጉ ተፈልፍለዋል፡፡ ተመሳስሎ የታተመ መረጃ እውነተኛውን እንደሚያምታታ ሁሉ ኮፒ/ቅጂ ሀይማኖቶች ፈጽሞ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሀይማኖት አስጨንቀዋል፤ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠው ብቸኛው እምነት ለአለም እንዳይደርስ በአንቅፋት አጥረውታልም፡፡ ሀይማኖት የተባዛው እንደመሰለኝ የሚለው የትርክት ማእከል ቃሉ እንዳለው አምናለሁኝ የሚለውን ቅንነት ያለበት መንፈሳዊ አቁዋም ስለተካ ነው፡፡ ይህን ቃል እስቲ እንመልከት?
ይሁ.1:3 ”ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።”
ይሁዳ ምንድነው የሚለው? ሃይማኖት አንድ ነው፣ ይህ ቀረህ የማይባል ፍጹምም ነው፣ ለእግዚአብሄር የተለዩ ቅዱሳን ያን ሃይማኖት ተቀብለዋል፤ ስለዚህ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለተሰጠው ለዚያ ሃይማኖት እንድትጋደሉ መከራችኋሁ ነው የሚለው፡፡ የምክሩ ቃል ግን ለአለም አልሰራም፣ ምክኒያቱም አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ ሀይማኖት መኖሩ ቀርቶ በሺዎች የተመነዘሩት ናቸው አለምን የሞሉት፡፡
አምነው እርግጡን የሚናገሩ መሰረታቸው ህያው የእግዚአብሄር ቃል ስለሆነ ወደ ስህተት አያመሩም፣ አይመሩምም፡፡ ይህን ሁኔታ አስረግጠው ሲናገሩ፡-
•”መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም” ይላሉ (1ቆሮ.2:13)፡፡
የሰው ጥበብ ሰዋዊ ነገር አለበት፡፡ ሰዋዊ ነገር ያለበትን የሚስተምሩ ደግሞ በህዝብ መሀል አሉ፣ እነርሱ እውነትን የሚያረክሱ ናቸው፡፡ እውነተኛ አስተማሪዎች መሰረታቸውን ቃሉ ላይ ስላደረጉ ለስህተት ክፍተት አይሰጡም፡፡ የሚሰሙትን ሆነ የሚያዩትን መንፈሳዊ ነገር በቃሉ ፈትሸው/አስተያይተው ይቀበሉታል ወይም ይተዉታል፡፡
•የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን ይላሉ (2ቆሮ.2:17)
ቃሉ ሲበረዝና ሲከለስ ህይወት መስጠቱን ይተውና ሞት ያመጣል፤ ይህን ስራ የሚሰሩ ብዙ አስተማሪዎች አሉ፤ እነዚህን ሃዋርያው ቃሉን የሚሸቃቅጡ ይላቸዋል፡፡ ታማኝ ያልሆኑ ቅጥረኞች/ጥቅም ፈላጊዎች ቃሉን በሚያመቻቸው መንገድ እየጠመዘዙ ያወራሉ፡፡ ቃሉ እንደፈለገው ሳይሆን እነርሱ እንደፈለጉት እንዲሆንላቸው የራሳቸውን ህልምና ግምት ያክሉበታል፡፡
•ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን ይላሉ (2ቆሮ.4:13)
•ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን።(2ቆሮ.12:19)
አምናለሁኝ የሚለው ንግግር የእምነት ቃልና ጽናት ውጤት ነው፡፡ መሰለኝ ደግሞ ማመንታት አለበት፡፡ እናም በእግዚአብሄር ቃል ሳይሆን በኔ መሰለኝ ከተመሰረትኩም ጥፋት እንደሚያሰናክልኝ ግልጽ ነው፡፡ የመሰለኝ ጫና ብዙ መዘዝ አለውና፡፡ ለምሳሌ፡-
እንደመሰለው የሚሄድ ሰው ምክር መስማት ይከብደዋል፡-
እንደሚመስላቸው የሚሄዱ ሰዎች ራሳቸውን ማሸነፍ ስለማይችሉ የእግዚአብሄርን ድምጽና የእግዚአብሄርን ሰው ምክር አይሰሙም፡፡ ምክር ባለመስማታቸውም ወደ ሞት ወጥመድ እንደሚገቡ የሚከተለው ታሪክ ያሳያል፡-
ሐዋ.27:9-15 ”ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ፡- እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም ብሎ መከራቸው።የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር።ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ።ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ።ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን።… ”
ሁኔታዎች ሲዘገዩ የሚረሳቸው ሰዎች መስሎአቸው የሚወሰዱት እርምጃ ከባድ ጥፋት ያመጣባቸዋል፡፡ ከሃዋርያው ጳውሎስ ጋር የነበሩ መንገደኞች ወራቱ የከበደ እንደሆነ ቢያውቁም በመታገስ ሊያሳልፉት አልወደዱም፡፡ አሁን ልከኛ የመሰላቸው ነፋስ ዘግይቶ እንደሚገለበጥባቸው ልብ አላሉም፣ አላከበዱትምም፡፡ በዚህ ግምታቸው የወረደው ጥፋት ግን የእግዚአብሄርን አገልጋይ ሊያጠፋ እስኪገዳደር አደገኛ እንደነበረ የምናየው ነው፡፡ ለምን? ጳውሎስ እውነታውን ተረድቶ ሲናገር እነርሱ ግን በአቁዋማቸው የገፉት የሚሳካላቸው መስሎአቸው ስለ ነበር፡፡
የመሰለኝ አመለካከት ቃሉን በሚያቃልል ማንነት ምክኒያት ይፈጥራል፡-
ንጉስ አክአብ እጅግ መጥፎ ማንነት የነበረው የእስራኤል ንጉስ ነው፡፡ ይህ ንጉስ በአግዚአብሄር ላይ የሚሰራው ሀጢያት ታናሽ ነገር መሰለው፡፡ እግዚአብሄር ስለመተላለፉ የማይቀጣው እስኪመስል ድረስ የሚያሳፍሩ ድርጊቶችን አበዛ፤ የባእድ ልጆችን እንዳይጋቡ የከለከለውን ትእዛዝ ተላልፎ አደገኛና ነፍሰገዳይ እንዲሁም እግዚአብሄርን የማታውቅና የማትፈራ ኤልዛቤልን ወደ እስራኤል አመጣ፡፡ ኤልዛቤልም እስራኤልን በሚያጎሰቁል መንፈስ አስመታች፣ ምድሪቱንም በርኩሰትዋ በከለች፡፡
1ነገ.16:31-33 ”በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፥ ሄዶም በኣልን አመለከ ሰገደለትም። በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ። አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ።”
አመጸኞች መልካም ነገር ክፉ ይመስላቸዋል
በነቢዩ በኤርሚያስ ዘመን የነበሩ አመጸኞች ነቢዩ የነገራቸው የእግዚአብሄር ቃል መጥፎ ዜና ሆኖ ታያቸው እንጂ ለንሰሃ አልተዘገጁበትም፡፡ ውስጣቸው ቀድሞውኑ በክፋት፣ በግፍና አግዚአብሄርን በሚያስቆጣ ድርጊት ተሞልቶ ስለነበር ጻድቅ የነበረውን ነቢይ እስከመግደል በሚያደርስ እልህ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰባቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለምድራቸው የጥፋት በር ሲሆኑ እናያለን፡-
ኤር.38:4-6 ”አለቆቹም ንጉሡን፡- ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና አሉት።ንጉሡም ሴዴቅያስ፡- ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው አለ።ኤርምያስንም ወሰዱት በግዞት ቤቱም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት።”
መልካም ምክር መዳኛ መንገድ ይጠቁማል፤ በክፉ ሰዎች ዘንድ ግን ህዝብና ምድር የሚያቆረቁዝ የክፉት ምክር አለ፡፡ የእስራኤል አለቆች ከንቱ ተርጉዋሚዎችና መካሪዎች ሆነው በፈጥሩት ውዥንብር ህዝብን አሰናከሉ፡፡ እውነተኛውን ሰው በጉድጉዋድ ውስጥ ቀብረው በህዝቡ ላይ እንዳሻቸው ሊያደርጉ ሲንቀሳቀሱ መቅሰፍትን ሳቡ፣ አምልኮን ጣሉ፣ መጨረሻቸውም ጥፋት ሆነ፡፡
2ነገ.25:6 ”ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት። የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጡ፥ በሰንሰለትም አሰሩት፥ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት። በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ። የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ። ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም።”
ነቢዩ ”ይህን የመሰለውን ቃል” ተናገረ ሲሉ ያቃለሉት የምክርና የደህንነት ቃል ወደ ንሰሀ እንዳይመራቸው አድርገው በራሳቸው መከራ የጠመጠሙ አለቆች በዚያች ከተማ የቀሩትን ሰልፈኞችና ሕዝብ ጨምረው ራሳቸውን በሚያሳዝን ፍጻሜ ውስጥ አስገቡ፡፡