እንደመሰለኝ ቢሆን[1…]

የመጨረሻ ዘመን

ተፈጥሮአችን ስለሆነ ሰዎች እንደሚመስለን እንገምታለን፡፡እንደሚሰማንም እንናገራለን፣ሊሆን ይችላል ብለን፡፡መሰለኝን አምነን እንቀበላለን፡፡ብዙ ጊዜ መስሎን የነበረ አሳብ ውስጣችን ከርሞ ወደ ምስል ይለወጥና የአስተሳሰባችንን አቅጣጫ ይቀይረዋል፡፡መሰለኝ እያልን ፣ፈራ ተባም እያልን እንጀምራለን፣ ነገራችንን፡፡ከጊዜ ወደጊዜ እያሳደግነው ከሄደና በታናሽነቱ ካልገዛነው አድጎ ወደ እምነት በመቀየር በተራው ይገዛናል፣ደግሞም ይመራናል፡፡ የመሰለኝ ጉልበት የሚገለጠው በዝግታ ነው፡፡
እውነት በሚገኝበት ስፍራ ላይ ልብን በሙላት ማዘንበል ከግምት አስተሳሰብ ያወጣል፡፡”እከሌ እንዲህ ያለው ይህን ሊል አስቦ ነው፣ያን ያደረገው ይሄን ሊያደርግ ስላሰበ ነው፣የዚህ ነገር ጅማሬ አንድ ያልታሰበ ነገር ሊገለጥ/ሊመጣ ስለሆነ ነው…” የሚል የግምት ነገር/ እርግጠኛ ያልሆነ ነገር በውስጣችን ሊመላለስ ይችላል፡፡ከሀዋርያት ገጠመኝ ጋር ነገሩን ማየት እንችላለን፡-
ማቴ.16:6 ”ኢየሱስም፡- ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።እነርሱም፡- እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው፡- እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን?ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? አላቸው፡፡”
ያሰብነው፣ ያየነውና የሰማነው ነገር ከማስተዋል ጋር ወደ ውስጣችን የገባ ካልሆነ የተዛባ አተያይ ይፈጥርብናል፡፡በመሰለኝ ውስጤ የገባ እውቀት እርግጥ በሆነ ውሀ ልክ ካልተፈተሸ እኔንም እንደራሱ ያንጋድደኛል፡- የሚመስል ነገር አሳሳች ነውና፡፡
መሰለኝን የተላመዱ ሰዎች ውስጣቸውን በጣም ያምናሉ፣በራሳቸው ነብይ ይሆናሉ፡፡ስለዚህ ልባቸው ላይ የተፈጠረውን እስተሳሰብ በእረግጠኝነት ማስተጋባትና ማስረዳት ይይዛሉ፡፡
ሀዋርያት ያሉትን አይተናል፡-፡ጌታ ኢየሱስ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ ማለቱ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ስላላስተዋሉ ስለትምህርት የተናገረው ነገር ስለመብል የተነገረ መሰላቸው። መሰለኝ ከአምላክ ጋር በግምት እንድንመላለስ ያደርጋል፡፡ግምታችንም እርሱን ይሰውርብናል፡፡የመሰለኝ እንቅስቃሴ በልብ ያለመረጋጋትና ከእምነት የወጣ ግፊትን በቅዱሳን መሀል ይፈጥራል፡፡ከኢየሱስ ጋር ከነበሩ ደቀ-መዛሙርት መሀል ወደ ሁዋላ ያፈገፈጉት የመሰላቸውን ይዘው የቀሩት ናቸው፡፡
አማኝ በግምት ሲንቀሳቀስ እምነቱ ይዛነፋል፡፡ አነጋገሩ ሳይቀር ይወላገዳል፡-ከእርሱ የሚጠበቀው እርግጠኛው የእግዚአብሄር ቃል ሆኖ ሳለ የመሰለውን ማለቱ በጣም ያስገምተዋል፡፡በዚያ ሳያበቃ እምነትን የሚጎዳ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ግምታዊ አባባሎች፣ አሰተሳሰቦችና ውሳኔዎች ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ውጤት ይፈጥራሉ፡፡ እግዚአብሄርን በማመስገኛ አጋጣሚ ወደ ምሬት መግባት፣ ወደ ፍለጋ በመግቢያ ወቅት ሽሽትን መምረጥና የመሳሰለው ስህተት በግምታዊ ውሳኔ ይከሰታል፡-
ማር.6:48-52 ”ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር።እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና፡- አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው።ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።”
ሀዋርያቶች ከገጠማቸው ፈተና የተነሳ ፍርሀትና ውዥንብር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡በዚያ ፍርሀት ምክኒያት በሚያስጨንቃቸው ነፋስ ላይ እየተራመደ የመጣውን ጌታ ሊያውቁት አልቻሉም፡፡በመሰለኝ የሳሉት አንድ አካል የቀረባቸውን ጌታ በምስጋናና በደስታ እንዳይቀበሉት አድርጎአቸው እንደነበር እናያለን፡፡
በመሰለኝ የምንፈጥራቸው ታሪኮች ልባችንን ሲሞሉት በተስፋ መጠበቅ ያለብንን የእግዚአብሄር አሰራር ያጨልሙና የመጎብኛ ወራታችንን ያርቁታል፡፡ እግዚአብሄር ግን ሩህሩህ በመሆኑ በታወክንበት ግምታችን ውስጥ እያለንም ይመጣል፡፡ ሃዋርያቶች በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ስለነበሩ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎአል፡- በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።
ሃዋርያቶች ጉዞአቸውን ለብቻቸው ማድረግ አልነበረባቸውም፡፡ ጌታ ከነርሱ ጋር ባለመኖሩ ነበር በጉዞአቸው መሃል ስጋት የሚያሲዝ ችግር የገጠማቸው፡፡ እርሱ በእኛም ህይወት ውስጥ ከሌለ ለብቻችን የምንጉዋዘው ጉዞ እንደነርሱ በፍርሀትና በእክል የተሞላ ነው፡፡
በሉቃ2:43-48 ባለው ታሪክ ውስጥ ጌታ ኢየሱስ በብላቴንነቱ ወቅት ከመምህራንና ከቤተመቅደስ ጋር የነበረውን ቁርኝት እናያለን፡፡ሆኖም በዚያው ወቅት የነበረው የቤተሰቦቹ አመለካከት ከእርሱ አላማ ወጣ ያለ ሆኖ በመገኘቱ የብላቴናው ኢየሱስ መልስ የነርሱን ግምት የሚገስጽ ነበረ፡፡
”ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር።ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፡- ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው።እርሱም፡- ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።”
እነማርያም ከኢየሱስ ጋር ስላልነበሩ ብዙ ነገር አምልጦአቸዋል፡፡በቤተመቅደስ የተናገራቸውን የማስተዋልና የጥበብ ቃሎች አልሰሙም፡፡ እነርሱ የተመለከቱት የርሱን ከነርሱ ጋር አብሮ ያለመጉዋዝና የት ገባ በሚል ያደረጉት ብርቱ የድካም ፍለጋ ነበር፡፡ በቤተመቅደስ የተደረገውን ታላቅ ነገር ባለመከታተላቸው በዚያ ስፍራ መቅረቱን እንደጥፋት እስኪያዩ አሳስቶአቸዋል፡፡ለስህተታቸው መነሻው ኢየሱስ አብሮአቸው እየተጉዋዘ ስለመሰላቸው ነው፡፡መሰለኛቸው ግን ብዙ የልፋት ጉዞ ጨምሮባቸዋል፡፡
ከመቅደስ አካባቢ (ከእግዚአብሄር ነገር) በራቅን ጊዜ እርሱ ከእኛ ጉዞ ጋር እንዳልሆነ ስለማንረዳ ለብቻችን መኩዋተን ይተርፈናል፣ እርሱ ከእኛ ጋር ያለ ስለሚመስለን ብዙ እንርቃለን፡፡ ራሳችንን ፈትሸን ጌታን ከእኛ ህይወት ስናጣው ከጉዞአችን ማፈግፈግ፣ ወደ ሁዋላ መመለስና በብርቱ ድካም እንደገና የሁዋሊት መንደርደር ስለሚሆን ጊዜያችንን፣ እውቀታችንንና ጉልበታችንን ማባከን ይፈጠርብናል፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ ጌታ በመሀከላቸው ሳለ ሳያስተውሉ ብዙ ነገር ይነጋገሩ ነበር፡፡
ሉቃ24:36-40 ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፡- ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው።
ጌታ በመሀከላቸው የተገኘው እጅግ ያስፈልጋቸው የነበረውን ሰላም በነርሱ ላይ ያውጅ ዘንድ ነበር፡፡በአዋጁ ምክኒያት አሜንና ምስጋናቸው እንዳይወጣ ግን አንድ የማያውቁት ፍርሀት ፈጥኖ ያዛቸው፡፡ የሚያውቁት ጌታ ጠፍቶባቸው አንድ የሚመስል ማንነት በፊታቸው ተገለጠ፡፡ጌታን ካዩት በላይ በልባቸው የመጣው አሳብ በርትቶ ከእውነት ሲያወጣቸው እናያለን፡፡ ይህ መሰለኝ የሚባል ነገር የስህተት ግርግር ከፈጠረ በቀላል የሚያበቃ ሆኖ አይታይም፡፡በመንፈሳዊ ጉዳይ በተለይ ከፍ ያለ መዘዝ የሚስብ ነው፡፡አንድ ምሳሌ ከዚህ በማስከተል እንይ፡-
ዮሐ.11:11-15 ”… ከዚህም በኋላ፡- ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፡- ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት።ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው።እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ፡- አልዓዛር ሞተ፤እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው።”
ከጌታ የማይለዩ ደቀ መዛሙርት የርሱን ድምጽ ዘወትር እየሰሙ ቢመላለሱም የተናገራቸውን የህይወት ቃላት እስካላስተዋሉ ድረስ ይከስራሉ፡፡እንቅልፍ- ሞት በሚለው የጌታ ትርጉዋሜና እንቅልፍ – መተኛት በሚለው የደቀመዛሙርቱ እሳቤ መሀል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡
እነዲሁም እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች አስተሳሰብ ምክኒያት በእግዚአብሄር ስራና ትምህርት ላይ ችግር እንደሚፈጠር ቃሉ ያስጠነቅቃል፡፡
1ጢሞ.6:3-5 ”እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።”
በኛ ዘመንስ እንደመሰላቸው የሚናገሩ ወገኖቻችን ብዙ አይደሉም ወይ? በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ግንኙነት ደግሞም በሀይማኖት አካባቢ ብዙ ነገር እርግጠኛ እውቀት እንደሆነ ተሰናድቶ ይናፈሳል፣ ይሰማል፡፡ከመሰላቸው አሳብ ተነስተው የአለምን ወይም የአገርን ያልያም የማህበረሰብን ይዘት ተንትነው ሲያበቁ ከዚያ ውስጥ የራሳቸውን ማጠቀለያ በማስቀመጥ ህዝቦችን የሚያወዛግቡ ብዙ ናቸው፡፡መነሻቸው ግምት/ቢሆን እንደሆነ የምንዘነጋ ነገር ግን ትንታኔያቸውን የምር አድርገን የምንሞግትላቸው ስንት ነን? ያን የሚያደርጉ ወገኖች ግን ተሳስተው የሚያሳስቱን ናቸው፡፡
ከሁሉ በላይ ሀይማኖት እጅግ ተመሰቃቅሎአል፡፡ለመስማት የናፈቀ እውነትን መስማት እንዳይችል፣ ማንበብ የፈለገ ህይወት የሚገኝበትን ቃል እንዳያነብ ወይም ማረጋገጫ ያለበትን የእርግጡን ነገር የፈለገ ያን የልቡን መሻት እንዳያገኝ ስንቶች ቃሉን በረዙት፣ ሸቃቀጡትስ? 1ዮሀ.1፡1-4 ውስጥ ያለ የእግዚአብሄር ቃል ይህንን ሁኔታ በፅሞና እንድንከታተል ይጋብዛል፡፡
”ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።”
በዘመናችን ላለን የሰው ልጆች ስለ ህይወት ቃል ማን ይንገረን? – እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን ያሉት የቃሉ አገልጋዮች ይንገሩን። እውቀት በአለም ላይ የነገሮች ሁሉ መነሻ መሆኑ አይካድም፡፡ያለ እውቀት የሆነ ሁሉ ከጥፋት በስተቀር ሌላ አላመጣም፡፡እውቀት ግን ከአዋቂዎች ዘንድ ሊሰጥ የግድ ነው፡፡መንፈሳዊውም ነገር እንዲሁ፡፡የዚህ የመንፈሳዊው አለም ጉዳይ መንፈሳዊ እውቀት ካላቸው መሰማት አለበት፡- ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ማለታቸው እርግጡን ተናጋሪዎች ሊሆኑ የሚችሉት እነሱ ብቻ ስለመሆኑ የሚያሳምን ነው፡፡
እኛ ግን የሚያጠፉ መንፈሳዊ ትርክቶችን ስንሰማ አድገን ጎልምሰናል፡፡ለምሳሌ ከልጅነታችን አንስቶ (በእርግጥ ከዚያም በፊት ነበር) ክርስቶስ ይመጣል በዚህ አመትና በዚህ ወር ጠብቁት ብለው ሲያሳስቡንና ሲያስጠብቁን ቆይተው እንዳሉት ሳይሆን ሲቀር ያሸማቀቁን ብዙ ናቸው፡፡እነርሱ ግን እንደኛ ሳይሸማቀቁ ዘመን እየለዋወጡልን ማሳሰቢያቸውን ቀጥለዋል፣አረ አሁንም እየተነበዩና ብዙ ሰውን እያሳመኑ ይገኛሉ፡፡ መስሎአቸው ሊሆን ይችላል ያን ያደረጉት ብለን እንውሰድላቸው፣ ግን ስንቱ በስህተታቸው ተስቦ ወደቀ፣ ስንቱ አማኝ በረገገ፣ የስንቱስ አእምሮ ተናወጠ?