እስራኤልም ወደ ያእቆብ

የእግዚአብሄር ፈቃድ

እስራኤል ወደ ያእቆብ ወይስ ያእቆብ ወደ እስራኤል ነበር ለውጡ ?
ወንድሙን ያታለለው ያእቆብ የእግዚአብሄርን አላማ ያስፈጽም ዘንድ ማንነቱ በእግዚአብሄር ተቀይሮ ስሙ እስራኤል ተብሎ ነበር፡፡ አባቱን ሳይቀር በመመሳሰል ያሳተው ይህ ያእቆብ በፈቃዱ ብኩርናውን ካቃለለው ከወንድሙ ከኤሳው የፈለገውን ብኩርና በወጥ ገዝቶ ይቀበል እንጂ የፈጸመው አመጽ ችግር ላይ የሚጥለው ነበር፤ በወቅቱ አባቱና እናቱ ስለራሩለት ብቻ ከተግሳጽ አምልጦአል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ የነገውን እስራኤልን አይቶ በምህረት ተቀብሎታል፡፡
ከብዙ ዘመን በሁዋላ ግን በእስራኤል ስም የተጠራው ህዝብ የእግዚአብሄርን ስራ ዘንግቶ ወደ ቀድሞው የአባቱ ባህሪ ባፈገፈገ ጊዜ  ከእግዚአብሄር ተግሳጽ አላመለጠም፡፡ ከያእቆብ ወደ እስራኤል ተለውጦ በዚያ ስም ከተጠራው አባት የተገኘው ህዝብ እግዚአብሄር ያደረገውን ስራ መከተል ሲተዉና ህይወቱ ሲበላሽ ልማዱ የአሮጌው ያእቆብ ተግባር ነበር፡፡ ይኧው ልማዱ በ​​​​​​​​ኢሳ.48:1-6 ውስጥ ተመልክቶአል፡-
”እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ።የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል አሳይቼውማለሁ፤ ድንገት አድርጌዋለሁ ተፈጽሞማል።አንተ እልከኛ፥ አንገትህም የብረት ጅማት፥ ግምባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፤ስለዚህ፥ አንተ፡- ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር ሳይሆንም አሳይቼህ ነበር። ሰምተሃል፤ ይህን ሁሉ ተመልከት፤ እናንተም የምትናገሩት አይደላችሁምን? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲሶች ነገሮችን ከዚህ ጀምሬ አሳይቼሃለሁ።”
ህዝቡ የያእቆብ ቤት (እልከኛ፥ አንገትህም የብረት ጅማት፥ ግምባርህም ናስ የተባሉ) የሚጠሩት ግን በእስራኤል ስም (በእግዚአብሔር እንደተወደደና በርሱ ስም እንደታመነ) ነበር፡፡
እንደ እግዚአብሄር ቃል ከሆነ ዋናው አስፈላጊ ነገር  እስራኤል ተብሎ የያእቆብን ህይወት ማንጸባረቅ አይደለም፤ ወይም ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ ሆኖ የእግዚአብሄር ራእይ ማስፈጸሚያ በሆነች  ከተማ ውስጥ  በማይመጥን ህይወት መኖርና ለስም ብቻ መጠራት አይደለም፡፡ ነገሩ ከዚህ ያለፈ የህይወት ጥራት የሚጠይቅ ነው፡፡
ሆኖም ህዘቡ ለምን ከእስራኤልነት ወደ ያእቆብነት ቁልቁል መንደረደር አስፈለገው? ብለን እንጠይቅ፡፡
አይሁድ ራሳቸውን የያእቆብ ዘር አድርገው ብቻ መቁጠራቸው ዋጋቸውን በእግዚአብሄር ዘንድ ከፍ የሚያደርገው እንደሆነ አስበዋል፡፡ ከዚህም አልፈው የእግዚአብሄርን ስም መመከቻና መታበያ አድርገው ተጠቀሙበት እንጂ በትህትና እንደሚገባው አላከበሩትም፡፡ በልባቸው ኩራት የእግዚአብሄር መቅደስ የነበረባትን ከተማ ሲመኩባትም ቆይተዋል፡፡ ያ ግን በእግዚአብሄር ዘንድ ሞገስን አላስገኘላቸውም፡፡ ይልቅ እስራኤላውያን የትክክለኛውን እስራኤላዊ ማንነት የሚያንጸባርቀውን የቅድስና ህይወት ባለመኖራቸው እግዚአብሄርን አሳዝነዋል፡፡
ሌላውስ ቢሆን በስም ብቻ እግዚአብሄርን እንደሚከተል ለማሳየት ከሚለፋ በተግባር በተቀደሰ ህይወት አምላኩን ቢከተል ምን ነበረበት?
የኛ ዘመን ማንነታችንም በተመሳሳይ ዝለት የታነቀ ነው፡፡ ሀይማኖተኛ መባል እንጂ ሀይማኖት ላይ ያለው ትኩረት መላላት እጅግ ዋጋ ቢስ ያደረገን ስብራታችን ነው፡፡
ለእስራኤል በትንቢት የተነገረው እጅግ የበዛ ተስፋ ህዝቡን ከፍ የሚያደርግ ሆኖ ሳለ ከቃሉ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚያደርገው መንገድ ቁጣና ዘለፋ ያተረፈለት ነበር፡፡
እግዚአብሄር ሰዎች በራሳቸው እንዳይመኩና በስራቸው እንዳይዘናጉ ደጋግሞ ያስጠነቅቃል፤ ይሄም ሄዶ ከሀጢያት ህይወት እንደሚጥላቸው ስለሚያውቅ ከዚያ ያድናቸው ዘንድ ሊያስታውሳቸው ነው፡፡
ሁላችን ከውልደታችን ሀጢያተኞችና የማይታዘዙ ልጆች ነን፡፡ ፊተኛው ሀጢያት ባልተወገደበት ሁኔታ ውስጥ ካለን ደግሞ የግብር ሀጢያታችን ደግሞ ደጋግሞ የሚጎበኘን ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርገን ወደ እውነተኛውና መንፈሳዊው እስራኤል ማንነት እንቀየር የሚለው ጥያቄ ዛሬውኑ ሊያሳስበን ያስፈልጋል፡፡
​​​​​​​​ሚል.1:2-6 ”ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን፡- በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው። ኤዶምያስ፡- እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ። የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል።ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፡- እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ።እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም፡- ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ብላችኋል።”
የሀይማኖት ታይታ እንደምን ከፍ ያለና የገነነ እንደነበር እንመልከት፤ በስጋ የነበረው ከፍታም ቢሆን እንዲሁ፡፡ በዚያ ከፍታ ላይ የእግዚአብሄር ክብር ተጋርዶ ስለሚደበዝዝብን መንጠራራት እንጂ የራስ መዋረድ አይታየንም ወይም ጥፋት ውስጥ ተነክረንም አዘቅት ውስጥ እንዳለን አያሳስበንም፤ ምክኒያቱም በራሳችን የተለጠጠ ክብር ማማ ተጋርደናል፣ እራሳችን በፈጠርነው ዝና ተይዘናል፣ በካባው ተሸፍነናል፣ ራስ ወዳድነት አንቆናል፡፡ እንኩዋን የሰራዊት ጌታ ምን ተናገረኝ? እኔስ ወዴት ነኝ? የሚል ራስን መመልከቻ ንሰሃና እግዚአብሄርን መሻት ልናገኝ  ጥቂትም መንፈሳዊ ሽታና ማስተዋል ሊቀረን አይችልም፡፡
የያእቆብ ቤት በገነነ ሁኔታ የሚታይ ነገር ውስጥ እንደተደበቀ ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ በዚያ ሁኔታ ውስጥ በእግዚአብሄር አይን መች በሞገስ ሊታይ ቻለ? ያእቆብን እግዚአብሄር ወድዶት አልነበረምን? እርሱ ግን ስለምን ማታለሉን ቀጠለበት? ህዝቡ ለሰውም ቢሆን የሚገርም ነው፤ ሁሎቹም እግዚአብሄርን በልበ ደንዳናነት ይጠይቃሉ፤ ሳይፈሩ ይናገራሉ፣ አመለክንህ ተከተልንህ ይላሉ፤ ሆኖም ልማዳቸው  የተጠሩበትን ክብር የሚገልጥ አልሆነም፡፡
ነቢዩም የእስራኤላውያንን ጥያቄ ሲዘረዝር በእግዚአብሄር ላይ ያሳዩ የነበረውን ጥርጣሬ፣ ተስፋ መቁረጥና የሀጢያት ልማዳቸውን አጋልጦ በማውጣት ነበር፡፡ እነርሱ እንዲህ አሉት፡-

  • በምን ወደድከን? አሉት፡፡ (ሚል. 1:2)
  • ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? አሉት፡፡ (ሚል. 1:6)
  • እንዴት ስምህን አቃለልን? አሉት፡፡(ሚል. 1:7)
  • አንተን ያታከትነው በምን መንገድ? አሉት፡፡(ሚል. 2:17)
  • የሰረቅንህ በምንድ ነው? አሉት፡፡(ሚል. 3:7)
  • በምን መንገድ ዘረፍንህ? አሉት፡፡(ሚል. 3:8)
  • በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? አሉት፡፡(ሚል. 3:13)

እነርሱ ብዙ ይበሉ ይጠይቁም እንጂ በተቆረቆረ መንፈስ በእግዚአብሄር ለመገሰጽ በመፈለግ ያደረጉት አልነበረም፡፡
እግዚአብሄር ያእቆብን ወደድኩ ኤሳውን ግን ጠላሁ ብሎ ምርጫው ላይ ሳይጠራጠሩ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ጋብዞአቸዋል፡፡ ህዝቡ በተቃራኒው ለጥሪው ባልመጠነ አኩዋሀን የእግዚአብሄርን ምርጫ ዘንግተው ራሳቸውን ከኤሳው ልጆች ከኤዶማውያን ጋር ሲያነጻጽሩ ነበር፡፡
ተስፋውን ዘንግተው ወደ አታላዩ ያእቆብነታቸው ስለተመለሱ ሲወቅሳቸው እንዲህ ይላል፡-
​​​​​​​​ኢሳ.48:7-15 ”እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም ፡- እነሆ፥ አውቄአቸዋለሁ እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም።
አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደ ሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደተጠራህ አውቄአለሁና። ስለ ስሜ ቍጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳላጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ። እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና፤ ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም። ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች።”
እስራኤል ለእግዚአብሄር ቅዱስ ህዝብ ሊሆን የተጠራ ነበር፡፡ የንጉስ ልጅም ሆነ አገልጋይ እንደተጠራበት አጠራር ይኖር ዘንድ ይጠበቃል፣ ያለበለዚያ ካልተፈለገበት የዋለ እንደሆነ ራሱን ብቻ ሳይሆን ባለቤቱን ያስወቅሳል፡፡ ይሄም በእስራኤል ላይ ሆኖአል፤ ተለይቶ በተጠራበት ሁኔታ ውስጥ ሊቆይ ስለተሳነው እግዚአብሄር የተወውን የኤሳውን እጣ ተመኝቶ ነበርና፡፡
እግዚአብሄር ለአብረሃም ታላቅ ተስፋ ሰጥቶት ነበር፡፡ተስፋውም ከአብረሃም ወደ ልጆቹ ይስሀቅና ያእቆብ አልፎ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡ እስራኤል እንደ እስራኤልነቱ ጸንቶ በእግዚአብሄር የተወደደ ካልሆነ ማን ተስፋውን ጠብቆ ሊቆም ይችላል? ለአብረሃም የተሰጠው ቃልኪዳን በልጁ በኩል አልፎ ወደ ክርስቶስ ካላደረሰ አህዛብ እድል ፈንታው የጨለመ አይደለም? እስራኤል በእግዚአብሄር የተወደደ ሆኖ ሳለ የአታላዩን ያእቆብ ስራ ሊያደርግና የእግዚአብሄርን መውደድ ቸል ሊል እንደምን በቃ? ባልነቃበት ዘመን ሁሉ ይህ የእግዚአብሄር ህዝብ ተጎድቶአል፣ ተጎሳቁሎ ወድቆአልም፡፡
ጊዜ ሲመጣና የእግዚአብሄር ፈቃድ ሲገለጥ ለህዝቡ ምህረት መምጣቱ አይቀርም፣ ያም ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆነ የያእቆብ ምርኮ መመለስና የእስራኤል ማንነት መፈወሻ ነው፡፡
የቅርቡ መከራና ጉስቁልና ግን አስቀድሞ እግዚአብሄር ያወጣውን የምህረት አዋጅ እንደማይሸፍነው ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ማስተዋል ውስጥ እግዚአብሄር ለህዝቡ የሰጠው ሞገስ ሳይዘነጋ በደስታ ወደ አምላኩ በመመለስ እውነተኛውን እስራኤል መሆን ይቻላል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሲምር የህዝቡን ሀጢያት ይሸፍናል፣ የሚሸፍነውም በማያዳግም ሁኔታ ስለሆነ ህዝቡ በእርሱ ርህራሄና ይቅርታ ተደግፎ የአብረሃምን ተስፋ መጠበቅ ይቻለዋል፡፡
​መዝ.85:1-6 ”አቤቱ፥ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ። የሕዝብህን ኃጢአት አስቀረህ፥ አበሳቸውንም ሁሉ ከደንህ። መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፤ ከቍጣህ መቅሠፍት ተመለስህ። የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቍጣህንም ከእኛ መልስ። በውኑ ለዘላለም ትቈጣናለህን? ቍጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን? አቤቱ፥ ትመለሳለህ ታድነንማለህ፤ ሕዝቡም በአንተ ደስ ይላቸዋል። አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህንም ስጠን።”
​​​​​​​በኢሳያስ ትንቢት ውስጥ እንደተመለከተው ህዝቡ ወደ አምላካቸው በመቅረብና በማሰተዋል መስማት ከቻሉ ዳግም በእግዚአብሄር የተወደደውን እስራኤል ሊሆኑ እንደሚችሉ ቃሉ ያመለክታል፡፡
​​​​​​​​ኢሳ.48:17-22፤ ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ፡- እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤
ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ ይህንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፡- እግዚአብሔር ባሪያውን ያዕቆብን ታድጎታል በሉ። በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር።
የእስራኤል ቅዱስ ትእዛዙን የሰማ ያዕቆብን እንዲህ ይታደገዋል፡፡