እርሱ ጠባቂዬ መጋቢዬም ነው

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ሰው የአምላኩን ቸርነት ያውቅና ስጦታውን ይቀበል ዘንድ የእግዚአብሄርን አሳብ ማስተዋል እንደፈቃዱም እርሱን መፈለግ ይገባዋል።ነገር ግን ሁላችን ያን ልናደርግ ባለመቻላችን ከዚያም በላይ ደግሞ እንድናገኘው ፍላጎት ባለማሳየታችን ማድረግ ያለብንን ሁሉ ሰጪው እንዳያመለክተን መቀበል የነበረብንንም የርሱን በጎ ስጦታ በአንድነት እንድናጣ አድርጎአል።በመጽህፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የእግዚአብሄርን ባህሪ ጠንቅቆ የተረዳው ንጉስ ዳዊት ግን እግዚአብሄርን በመፈለጉ የተቀበለውን መንፈሳዊ በረከት በመዝሙሩ ገልጦታል፦

​​​​​​​​መዝ.23:5 በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው።

እግዚአብሄር ማዳኑን፣ጥበቃውን፣ቸርነቱንና ሀይሉን ያስታጠቀበት አሰራር ከእረኝነቱ በተነሳ ሀላፊነቱ የሚያደርገውና ያደረገው እንደሆነ በቃሉ ውስጥ ተገልጦአል፡፡እኛ ወደ አምላካችን ፍጹም መጠጋት ሲሆንልን እርሱ ደግሞ ስለእኛ ሙሉ በሙሉ ሀላፊነትን ይወስዳል፡፡ከታላላቅ ነገሮች አንስቶ ሰው ብዙም ልብ እስከማይላቸው ነገሮች ድረስ ወርዶ ያከናውልናል፡፡ እግዚአብሄር በሚያዘጋጅልን  ነገር የአለምን ተጽእኖ ሰንጥቀን ማለፍ እንችላለን፡፡እንደ እውነቱ ከሆነ የእርሱ እገዛ በሌለበት ሁሉ  አድርገነዋል ወይም አሳክተነዋል የምንለው ነገር ቢኖር ጠላት ሁልጊዜ የሚያየውና የሚከታተለው በመሆኑ ጊዜ ጠብቆ እርሱ እጅ መውደቁ አይቀርም፣ለእግዚአብሄር አደራ የተሰጠ ነገር ግን ከሁሉም ነገር ተጽእኖ ነጻ ነው፡፡

እስራኤል ከግብጽ የባርነት ምድር እንደወጣ ወዲያው የገባው በረሀ ውስጥ ነበር፡፡ያ የበረሀ ምድር የጥማትና የረሃብ እንዲሁም የሀሩርና የጉስቁልና ምድር ነበር፡፡ነገር ግን ይህን ህዝብ ከግብጽ በሀይሉ ያወጣ አምላክ በቀን የደመና አምድ ሆኖ ከቃጠሎ ህዝቡን ሊከልል፣በምሽት የእሳት አምድ ሆኖ ምድረበዳውን በብርሀን ሊያደምቅ፣ለውሀ ጥማታቸው ውሀን እያፈለቀ ሊያጠጣና መናን ከሰማይ እያዘነበ ሊመግብ ሀላፊነቱን ወስዶ ነበር፡፡እግዚአብሄር ይሄንን ሁሉ ሲያደርግ የእስራኤል ጠላቶች በዙሪያ ከብበው ይመለከቱ ነበር፡፡ህዝቡ ላይ የወረደ አንድ የሞገስ ቅባት አህዛብን ያስፈራና ያርበደበደ ስለነበር እስራኤል በሚውልበት የጦርነት አውድማ ሁሉ አሸናፊ ነበር፡፡በአዲስ ኪዳንም እግዚአብሄር ለህዝቡ የሚበላውና የሚጠጣው ሰማያዊ ገበታ (ክርስቶስን) አዘጋጀ፡፡በስጋውና በደሙ ውስጥ ያለ ህይወት ወደ እኛ ይተላለፍ ዘንድ ስጋዬን ብሉ ደሜንም ጠጡ አለ፡፡የኢየሱስ ስጋና ደም የአዳም ስጋና ደም አይደለም፡፡ምክኒያቱም ሰው እንኩዋን የሰውን የእንስሳን ደም እንዳይጠጣ ወይም ደም ውስጡ ያለን ስጋ እንዳይበላ እግዚአብሄር ራሱ አስጠንቅቆአል፡፡በአዲስ ኪዳን ግን አንድ አዲስ ነገር ተከሰተ፡-የክርስቶስ ስጋ ሊበላና ደሙ ሊጠጣ፡፡ይህ ትልቅ ነገር አይደለምን? አትብሉ ወይም አትጠጡ  ያለ ጌታ ቃልኪዳኑን አድሶ ብሉና ጠጡ የሚለውን አዘጋጀና እንዲያ ሲል አወጀ፡፡

​​​​​​​​ዮሐ.6:47-66 ”እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው:-እንግዲህ አይሁድ:- ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:-እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።….​​​ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።”

እግዚአብሄር ዘላለማዊ መብል በሰማይ ያዘጋጅ ዘንድ እንዳለው ለማመልከት ከሰማይ መናን ለሙሴ አውርዶ ሰጠ፡፡የህይወት መንፈስን እንዲያፈስ ሲያመለክት ከአለቱ ውሀ አፍልቆ በምድረበዳ ህዝቡን አጠጣ፡፡ያም አለት ክርስቶስ ነበር፡፡ዛሬም በኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደም ጠላታችንን ሞትን የምንረታበት ሀይል ተሞልተናል፡፡እሱ እንዳለው ስጋውን የመብላታችንና ደሙን የመጠጣታችን ምስጢር ድርብ ዋስትና ስላለው ነው፣እንዲህ የሚል፡- ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡

እግዚአብሄር ጠላት ዲያቢሎስ በሚያይና በሚሰማበት ሁኔታ ራሳችንን ዘይት ይቀባል፡፡ዘይቱ የደስታ ቅባት፣ማስተዋልን የሚሰጥና እውነትን ይዘን በሚያደባብን ጠላት ፊት እንድንቆም ችሎታን የሚያላብሰን ነው፡፡

​​​​​​​​መዝ.23:6 ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።

የእግዚአብሄር ህዝብ ሳይጠፋ አምላኩን መከተሉ የእግዚአብሄር ምህረትና ቸርነት ያለመጉዋደል በእርሱ ላይ ስለተትረፈረፈ ነው፡፡የእግዚአብሄር ያልተቆጠበ ስጦታ ከምህረት ጋር በእግዚአብሄር ፊት ህያው ያደርጋል፡፡እኔ የቆምኩት የሚጥለኝ ጠፍቶ አይደለም፡፡ያልወደቅኩት ደካማ ጠላት ስላለኝም አይደለም፡፡እንዲያውም በመንፈስ የሚጠላን ስጋውያንንም አስተባብሮ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ሊደመስሰን የሚችለው የጠላት ሀይል በእኛ ብርታት ምክኒያት ተገድቦ ስለቆመ አይደለም፡፡ነገር ግን የራሱ ልጆች አድርጎ የቆጠረን አምላክ ምህረቱን በእኛ ላይ ስላጠነከረ ነው፡፡ዳዊትም እንዲያ በመተማመን ሊዘምር የቻለው በእግዚአብሄር ፊት  ያቆመውን የአምላኩን የተትረፈረፈ ችሮታና ምህረት ስለቀመሰ ነበር፡፡የእግዚአብሄር ህዝብ ከአህዛብ በእግዚአብሄር ምህረት ይለያል፡- በእርሱ ከዘለላም መርገም ያመለጠ ነውና፡፡

እግዚአብሄር ቸርነቱን ለሰው ሁሉ አብዝቶአል፡፡ለአለማውያኑም ለህዝቡም እኩል ጸሀይን ያወጣል፣ዝናብንም ያዘንባል፡፡ቀኑ ለሁሉም ይወጣል፣ምሽቱም ለሁሉም ይሆናል፡፡ምድር ለሁሉም እኩል ሀይልዋን ትሰጣለች፡፡አየሩም ውሀውም አኩል ለህያው ፍጥረት ሁሉ ጥቅም ይውላል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው እርሱ ቸር አምላክ በመሆኑ ነው፡፡በቸርነቱ ላይ ግን ምህረትን ጨምሮ ለመረጠው ህዝብ ይሰጣል፡፡በምድር ላይ ያሉ ስጦታዎች ሁሉ የእግዚአብሄርን አባትነትና ፈጣሪነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡እግዚአብሄር ለፈጠረው ሁሉ ሀላፊነት ስላለበት ያን ያለመከልከል ያደርጋል፡፡እሱ እንደሚያውቀው ግን ሰው አምላኩን አላወቀም፡-አልቀረበውምና፡፡የቀረበው፣ቸርነቱን ያበዛለትና አምላኩ መሆኑን የተረዳ ግን ወደ እርሱ ይበልጥ ይጠጋል፡፡እግዚአብሄር ከፈጠረው ሰው ጋር እንዲህ ይወዳጃል፡፡ሰው አምላኩን ወደ ማወቅ ይመጣል፡፡ከእርሱ ጋር እንዴት መራመድ ባስተዋለ ቁጥር የራሱን ማንነት እየተረዳ፣የፈጠረውን አምላክ ታላቅነትም እያስተዋለ ይሄዳል፡፡ቅርበቱ እያደር ወደ ተጠጊና አስጠጊነት፣ወደ ሰጪና ተቀባይነት፣ወደ አባትና ልጅ ወዳጅነት….እያደገ ይሄዳል፡፡እንዲህ በፍቅሩ ያስጠጋውን ልጁን ጌታ ሁልጊዜ በምህረቱ ይከልለዋል፡፡ጌታ በፊቱ የሚያገልለውን ልጁን ሁሌም ይምረዋልና፡፡

​​​​​​​​መዝ.25:5-8 ”አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና።የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ።እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።”

በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሄር ምህረት  ሰውን ወደ እውነት በመምራት ይገለጣል፡፡እግዚአብሄር ሰውን ማዳን ሲፈልግ ወደ እውነተኛ መንገዱ ያስገባዋል፣በውስጡም ይመራዋል ያስኬደዋልም፡፡የእግዚአብሄር ቃል እውነት ነው፡፡ሰውንም እውነተኛ ያደርጋል፡፡እግዚአብሄር ሰውን ከሀጢያት ሊመልስ ሲያስብ ቃሉን ይልካል፣በዚያም የሚድንበትን መንገድ ያስተምረዋል፡፡የእግዚአብሄር ቃል የማይገለጥለት ትውልድ የእግዚዘአብሄር ምህረት አያገኘውም፡፡እግዚአብሄር እስራኤልን ተቆጥቶ በነበረ ጊዜ ቃሉን ፈጽሞ ከለከለ፡፡ህዝቡም ከምህረቱ ርቀው በራሳቸው መንገድ ብዙ ኩዋተኑ፣በዚያም ከመንገድ ላይ ጠፍተው ቀሩ፡፡ዳዊት የእግዚአብሄር ዝምታ ወደጥፋት እንደሚመራ ስላወቀ እባክህ ዝም አትበለኝ አለና ለመነ፡፡እግዚአብሄር ለልቡና ለነፍሱ የሚናገረው ሰው ከጥፋት ይድናል፡፡

1ሳሙ.3:1-4  ”ብለቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም:-እነሆኝ አለ።”

በካህኑ በኤሊ ዘመን ለእስራኤል የእግዚአብሄር ቃል ብርቅ እስኪሆን ድረስ ከምንጩ ደረቀ፡፡የካህኑ የኤሊ አይኖች በእርጅና መፍዘዝ እስከጀመሩበት ዘመን ድረስ እግዚአብሄር ዝም ብሎ ነበር፡፡የእግዚአብሄርን ድምጽ እንዳይሰማ ያደረጉ የሀጢያት ምክኒያቶች በእስራኤላውያን ዘንድ ነበሩ፡፡ከዚያ የከፋው ደግሞ ቃሉ ለካህኑ እንኩዋን መምጣት ማቆሙ ነበር፡፡እንዲያውም እግዚአብሄር የቀባውን ካህን ትቶ ገና አገልግሎት ምን መሆኑን የማያውቀውን ታናሽ ብላቴና ተናገረው፡፡ዔሊ ምንም እንኩዋን በአካል በቤተመቅደስ ቅርበት ውስጥ ቢኖርም እግዚአብሄርን በማሳዘኑ (በልጆቹ ልቅ መሆን) ምክኒያት እግዚአብሄር ካህኑን፣ልጆቹንና ህዝቡን ሊቀጣ አስቦ አልናገርም ፣አልገስጻችሁም ፣በራሳችሁ መንገድ ሂዱ ብሎ ተወው፡፡በሌላ በኩል ያን ትንሽ ብላቴና ለእስራኤል ነብይ አድርጎ ያስነሳ ዘንድ ወደ ታቦቱ ድረስ አቅርቦ ድምጹን ሲያሰማው እናያለን፡፡የእግዚአብሄር ድምጽ በህይወታችን መኖር የምህረቱ መኖር ምልክት ነው፡፡ቃሉ ሲዘጋ ሰማይ ይዛጋል፡፡ሰማይ ተዘግቶ መንፈሳችን በድርቅ ሲመታ የህይወት ሽታ ከእኛ ይርቃል፣. የመንፈስ ምሪት ቀርቶም የስጋ ፈቃድ ነገሮቻችን ሁሉ ይገዛል፡፡አእምሮአችን በዚያ ስለሚመራም ውድቀታችን መጥፊያችን ላይ ይሆናል፡፡