ስለ እግዚአብሄር ቃል ምንነት ባለን እውቀት በኩል የተቀበልነው ትልቅ ስጦታ ቢኖር ተስፋው ነው፤ በተስፋው በኩል እግዚአብሄር በዚህ ጊዜና በዚህ ስፍራ ይህን አደርጋለሁ ብሎ ለሰዎች ቃል ይገባል። ቃሉ በዘመን ብዛት አይለወጥ፣ አያረጅ፣ አይቀየር፣አይታጠፍ ወይም አይጠፋም። ስለዚህ ይህ የእግዚአብሄር ተስፋ ጸንቶ እንደተነገረበት አውድ ትውልዶችን አልፎና አሳልፎ እስኪከናወን ያለመለወጥ ሲጸና ይታያል። አንዳንድ የእግዚብሄር ባሪያዎች የተቀበሉት የተስፋ ቃል ከነርሱ አልፎ ለብዙ ትውልዶች የሚሆን በረከት ሲሆን ይታያል፤ ለምሳኤ የአብረሃምና የዳዊትን ተስፋ ማየት እንችላለን።
በእግዚአብሄር የተነገረ ተስፋ እንዲህ ብርቱ ከሆነ የተስፋውን ቃል እናስተውል ዘንድ የቃሉን ምንነት ከይዘቱ ጋር ማመሳከርና ማዛመድ እንዲኖርብን ማወቅ ደግሞ አለብን፤ ያን ብርቱ የሆነ ማስተዋል ያገኘንም እለት ነው የቃሉ ይዘት የህይወታችን መሰረት እንደሆነ የምናውቀው።
በተስፋ እግዚአብሄር አደርጋለሁ ያለውን ሲገልጥልን እምነት ወደርሱ እንድንንቀሳቀስ ይረዳናል፤ የተቀበልነውም እንዲሆንልን በውስጡ የሚገኝ መለኮታዊ ተስፋ ያገኘናል፤ ተስፋ የእግዚአብሄር ቃል በባዶ የሚናገረው ወይም ላይከናወን የወጣ ቀለል ተደርጎ የሚወሰድ ንግግር ሳይሆን በተናገረበት ወቅት ፍጻሜው እርግጥ እንደሆነ የሚታመን መለኮታዊ ድምጽ ነው፤ ቃሉም በእርግጠኝነት የተስፋን ቃል የሰጠው የአብረሃም አምላክ የታመነ አምላክ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በአለም እየሆነ ያለውን ተመልከቱ፣ እጅግ ታላላቅ ቃላት የሚናገሩ ስለመፈጸመውም ነገር ምለው የሚያሳውቁ ስንት ናቸው? እነርሱ ግን ሰዎች ናቸውና እንዳሉት ሳይሆን እየቀረ ንግግራቸው ባዶ ተስፋ ብቻ ሆኖ ትዝብት ሆኖባቸው ሲያልፍ አይተናል። ተስፋችንን በእግዚአብሄር ላይ ያደረግን ግን ደስ ይበለን፣ የተናገረው የምድርና የሰማይ ፈጣሪ ነውና ያለው እንዲፈጸም እንመን፣ እንጠብቅም። እግዚአብሄር ለቃሉ ታማኝ እንደሆነው ሁሉ እኛም ለእግዚአብሄር ታማኝ መሆን እለብን።
‘’አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች።ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ።’’ (እብ.11:8-13)
ተስፋ ተፈጽሞ እንድናይ የምንናፍቅ ሁላችን በእርግጥ እንደተመኘነው ተፈጽሞ ማየት ከፈለግን የምናምንበትን የእምነት አካሄድ እናስተካክል፣ ማመን ማለት በዘፈቀደ የሰማነውን መቀበልና መከተል ማለት አይደለም። ነገር ግን ልናምን ስንነሳ የሚታመነው ነገር ምንጩ የእግዚአብሄር ድምጽ/ቃሉ መሆኑን እርግጠኛ እንሁን።
በእርግጥም በመሐላ እግዚአብሄር ተስፋ አድርጎልን ከሆነ አጠባበቃችንንም እንዲሁ እናስተካክል፤ የእግዚአብሄር ቃል ይሆናል ስላልነው ብቻ ለእኛ ላይሆን ይችላል፣ይልቅ የተስፋው አድራሻ ወደኛ የሚያመለክት መሆኑን እርግጠኞች እንሁን። አንዳንድ ነብያት የክርስቶስን መምጣት ከእግዚአብሄር ስለሰሙ በነርሱ ዘመን ይገለጣል ብለው ተጠባበቁ፣ የተስፋው ሙላት በነርሱ ጊዜ ስላልነበረ የጠበቁትን ሳያዩት ሞቱ። ከዚህ ሌላ የእስራኤል ተስፋን በአግባቡ ያለመጠበቅ የተገለጠውን ጌታ ያለመቀበል አስከትሎባቸው እናያለን።
ስለዚህ ሆኖ እንድናገኘው ከማመን ባሻገር እምነታችን ውስጥ የእግዚአብሄር ተስፋ ዘር ሆኖ ውስጣችን ህያው በሆነ አጠባበቅ እግዚአብሄርን መከተል አለብን፤ ለዚህ ሁሉ መፍትሄ የሚሆነው ቃሉን በእምነት ይዘን የምንጓዝበት ጽኑ የሆነ መንገድ ሲኖረን ነው:-
1. ለእረኞች የብሉይ ኪዳን ተስፋ መገለጥ
ብሉይ ኪዳን ለብዙ ዘመናት በምኩራብ ተነብቦ የለም ወይ? የተስፋውን ፍጻሜስ ይጠባበቁ የነበሩ ቅዱሳን ነበሩ አይደለም ወይ? የምስራቹ ግን በዚያ መጽሃፉ በሚነበብበት ስፍራና ወቅት አልተገለጠም? ምክኒያቱም ቃሉን የሚሰሙ ጆሮዎች ብቻ እንጂ ተስፋው ተፈጽሞ ሊያዩ የሚናፍቁ የእምነት ልቦች ጨርሶ አልነበሩም ማለት ነው፤ እረኞችስ? ልክ እንደ ንጉስ ዳዊት ዘመን የተስፋ ቃሉን ከልባቸው ሳይጥሉ ሁሌም በምድረ በዳ ነበሩ ማለት ነው፤ እንዲያውም እረኞቹ በዚያ ምድረበዳ ይጠብቁ የነበረው ለሃጢያት ስርየት የሚታረዱ የመስዋእት በጎችን ነበር፤ እነርሱ በመንፈሳቸው ይዘውት የነበረው የእግዚአብሄር በግ የመምጣት ተስፋ በእውን እስኪታይ በአካል ለብሉይ ኪዳን ማስተሰርያ የሆኑ የመስዋእት በጎችን ቀን ከሌሊት ጸሃይና ቁር እየተፈራረቀባቸው ይጠብቁ ነበር፤ ያን የሚያውቅ ጌታ ተስፋውን ፈጽሞ ሊያሳያቸው የምስራቹን በመልአኩ በኩል አበሰራቸው፤ በክብር ጠብቀውት ነበርና በምስራችቹ አከበራቸው፤ በስጋ የተናቁ ሆነው በምድረበዳ የሚያድሩ እነዚያ ደካማ እረኞች በእምነታቸው ግን ብርቱ ስለነበሩ እግዚአብሄር አስቀድሞ ወደ እነርሱ መጣና ደስ ይበላችሁ አላቸው፤ ያከበሩትን የሚያከብር ጌታ ሰው እንደሚፈርድ መልክና ቁመናን አይቶ አይፈድርድምና።
‘’በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ።ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ።’’ (ሉቃ.2:8-15)
2. የተስፋውን ቃል የተቀበሉቱ አላገኙትም
በሮሜ 9:4 ላይ ‘’እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና’’ እንደሚል እግዚአብሄር ወገኖቼ ላላቸው አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን የተናገራቸው የተስፋ ቃል ነበራቸው፤ እነርሱም ያን ይዘው በመቅደስና በምኩራቦቻቸው ጭምር እለት እለት እየደጋገሙ አንብበውት ነበር፤ እርሱም እመጣለሁ እንዳለው መጥቶላቸው ነበር፤ የሰባ ግብዣ ለናንተ አለኝ፣ እንዲያውም ከናንተ በላይ ለአህዛብ ይተርፋል ብሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን ሲመጣ ባይተዋር ሆኑበት፤ እንግዳ አደረጉት፤ የማያውቁት እስኪመስሉ አሳፈሩት፤ተከራከሩት፣ ዘለፉትም፤ እርሱ ግን በአንድ ከባድ ማስጠንቀቂያ አመጻቸውን ሲዘጋው እንመለከታለን፦
‘’እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል። ነገር ግን በሕጋቸው፦ በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።’’ (ዮሃ.15:22-25)
ለእግዚአብሄር ህዝብ የተወሰነለት እድል ፈንታ የሆነ መለኮታዊ በረከት ከርሱ ዘንድ እንዳለ ሁሉ በእኛ ዘንድ ደግሞ እግዚአብሄርን ማመን መጠበቅና መከተል ሊኖር ይገባል።
የተስፋ ባህሪያት
እግዚአብሄር ለህዝቡ የሚሰጠው ተስፋ አስደሳች ነው፣ እርሱ ለመረጠው ወገን የሚያስፈልገውን ያውቃልና በቅርብም ይሁን በሩቅም ሊያደርግ ያለውን ለህዝቡ ከማድረጉ አስቀድሞ በተስፋ ልብን ይሞላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተስፋን ባህሪ ማወቅ እግዚአብሄር ሲሰጥ አያያዙን እንድናውቅ ያግዛል፦
ተስፋ በሁለት የማይለወጥ ነገር የያዘ ቃል ነው
እግዚአብሄር የሚናገረው ስለሚያደርግ ነው፤ የተናገረውን የሚተካ ተለዋጭ አማራጭ ከቶ የለውም፣ የተናገረውን አያጥፍም፣ ወይ ተጸጽቶ አይሽረውም፤ ሁሉን የሚችል አምላክ እንደተናገረው ሊያደርግ ይችላልና፣ ሁሉን ቻይም ነውና። የሰዎች ቃል በመሃላ ሲሆን ተለዋዋጭ ሳይሆን ይጸናል፣ የእግዚአብሄር ደግሞ ከሰዎች ይልቅ እጅግ የጸናና የላቀ ነው። ይህን በማስተዋል ስናምን እግዚአብሄር በተናገረው የተስፋ ቃል ላይ ትልቅ መደገፍ ይኖረናል፦
‘’ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና፥ ለማስረዳትም የሆነው መሐላ የሙግት ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ’’ (ዕብ.6:16-18)
ተስፋ የሚሞላ ቃል ነው
ተስፋ ጊዜና ስፍራን ጠብቆ በተነገረው ቃል ልክ ይሆናል፤ ስለዚህ ቃሉን ለተቀበሉ ሁሉ ሲናገር እንዲህ ይላል፦
‘’በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ። በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤ እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።’’ (እብ.6:11-15)
ከላይ እንደተባለው ቃሉ የሚፈጸምበትን ጊዜና ስፍራ ይጠብቅ እንጂ መፈጸሙ አይቀርም፤ ሰነፎች ግን ተስፋ ሲቆርጡ ከንቱ ነገር ይናገራሉ፦
2ጴጥ.3:3-8 ‘’በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።’’
ተስፋ የሚወረስ ቃል ነው
ከእግዚአብሄር የምንቀበለው የተስፋ ቃል በእምነት ጠብቀን የምናገኘው የአምላካችን ውርስ ነው፤ ከርሱ የምናገኘው እንጂ በራሳችን የምንፈጥረው አይደለም፤ የእርሱ ችሮታ እንጂ እርሱ የሚከፍለን እዳ አይደለም፤ ከበረከቱ የሚያካፍለን በጎነቱ እንጂ ሰርተን ያገኘነው ደሞዝም አይደለም፣ ስለዚህ ፦
‘’በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ። በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤ እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ።’’ (እብ.6:11-15)
ተስፋ ይጠበቃል
ቃሉ ተስፋን የተቀበለ እስከምን እምነቱን ማስኬድ እንዲገባው ሲይሳይ በእብ.3:6 ላይ እንዲህ ብሎአል፦
‘’እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።’’
የምንቀበለው ወይም የተቀበልነው ተስፋ የህያው እግዚአብሄር ቃል በመሆኑ እኛ የምናልፈው በውጣ ውረድ ውስጥ ይሁን በተመቻቸ የህይወት መንገድ በርሱ ላይ ተጽእኖ ሊያርፍ ከቶ እንደማይችል ተመልክተን አጥብቀን ልንይዘው ይገባናል። ዮሴፍን እንመልከት፦ይህ ሰው በልጅነቱ ከእግዚአብሄር ታላቅ ራእይ ተቀበለ፤ ለሌሎች ይነገር ወይ አይነገር ሳያውቅ ለቤተሰቡ በሙሉ በመግለጥ እግዚአብሄር ለብቻው ያሳየውን አደባባይ አወጣው፤ ያም ብዙ ችግር፣ ፈተና፣ ውክቢያ እንዲሁም ባእድ አገር በባርነት እስከመሸጥ አድረሰው፤ የተናገረውን የማይረሳ አምላክ ግን ከርሱ ጋር የገባበት ድረስ እየገባ አጸናው፤ የነገረውን እስኪያደርግለት ድረስ ጠበቀው። ከወገኖቹ ከመጣበት ተንኮል፣ ከባእዳንም ፍርድና አመጽ ጋረደው፤ ዮሴፍ ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ተስፋው ሳይደክም፣ ሲታሰር እርሱ ሳይታሰር በሆነው ነገር ሁሉ ቃሉ እንደጸና በጊዜው ዮሴፍን ለክብር ገለጠው፤ እግዚአብሄር የነገረውንም አንዳች ሳያጎድል ፈጸመለት። ዋናው ነገር በነዚህ ዘመናት ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው ቁርኝትና እስከመጨረሻው ያሳየው ጽናት ነውና።
ዕብ.10:23 ‘’የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ’’