ኢያሪኮን መስራት? (2..)

ቤተክርስቲያን

ኢያሪኮ ፈርሶ እንደቀረ የተደመደመ ጉደይ ሆኖ ሳለ በአእምሮ ውስጥ ትዝታው አልለቅ ካለ የቀደመው ሀጢያት ከልብ ሊርቅ አልቻለም እንደማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ኢያሪኮን ለምን ረገማት? ኢያሪኮ ማለት ከተማዋ፣ አካባቢዋ ወይም የኑሮዋ ስርአት ብቻ ሳይሆን የአምልኮ ልማድዋን ተከትሎ የተፈጠረው ያልተገባ የህይወት አኑዋኑዋር ሁሉ ማለት ነው፡፡ ኢያሪኮ የአህዛብ ከተማ በመሆንዋ የአህዛብ ልማዶችን የተሞላች ስለመሆንዋ አያጠራጥርም፡፡ ልማዶችዋ እግዚአብሄርን የሚያስደስቱ አልነበሩም፡፡ ህዝቦችዋ ከእግዚአብሄር ዘንድ ፍርድን የሚስቡና የእግዚአብሄርን ትእግስት የሚፈታተኑ አመጸኞች በመሆናቸው ያች ምድር በነርሱ ምክኒያት መረገምዋ ግልጽ ነው፡፡ ግን እግዚአብሄር የጠላውን ስፍራ እኛ ስለምን ፈለግነው?
ዘኊ.25:1-4 ”እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር። ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ። እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው።”
ይፍረስ ተብሎ የፈረሰው ገመናችን ሲፈርስ በዚያ ቅጽበት ከእኛ ህይወት የተወሰደው በሰው ፊት ያለው ስድባችን ብቻ ሳይሆን የሰራነው በስውር ውስጣችን የተቀበረው ሀጢያትም ጭምር ሊያውም እስከ ወዲያኛው ላይታሰብ ነው፤ ሆኖም በእኛ በኩል አጥብቀን ጥንቃቄን ካልተጠባበቅን የተወገደው እንደተወገደ ሆኖ እንዳይረሳ ዳግም ወደዚያ ወደተውነው እናዘነብላለን፣ እርሱን በመሻትም ሆነ ዳግም በማነጽ ውስጥ ስንባዝን የደከምነው ለፍሬያማነት ሳይሆን የሞተውን ሀጢያት ዳግም የመፍጠር አጋጣሚ ለማምጣት ብቻ ይሆንና ያከስረናል፡፡ ሀጢያትም ያለጥርጥር ዳግም ወጥመድ ሆኖ በቀላሉ ላይለቀን ይጣበቅብናል፣ እርግማን ስለሆነ ያሰቃየናል፣ ያውከናል፣ ያቀጭጨናል፣ በእግዚአብሄር ፊት በነጻነት እንዳንመላለስ እንቅፋት ይሆናል፡፡ እንዲያ ስለሆነ ተቀባይነት መቼም አናገኝም፣ ሞገሱ ከእኛ ተገፍፎ ምንም ተስፋ እስካይቀርልን ይጥለናል፡፡ ተዉ የሚል እግዚአብሄር እስራኤልን እንዲህ ያሳስባል፡-
”እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፡- ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም።” (ዘኊ.33:50-53)
የእስራኤል ህዝብ ከግብጽ ሲወጣ ከስጋው ባርነትና ከመንፈስ እስራት ሊወጣ ባህር አቁዋርጦ ተጉዞአል፡፡ በሞአብ ሜዳ ላይ ደርሶ ሲሰፍር ደግሞ ከማዶ የምትጠብቀውን ምድር በተስፋ አስቦ ነበር በዚያ ያረፈው፡፡ እስራኤል ወደዚያች የማርና የወተት ምድር ከመድረሱና ተስፋውን ከመጨበጡ በፊት ትልቅ ቅጥር ሰብሮና አንኮታኩቶ ማለፍ ስለነበረበት ለዚያ ክንዋኔ መመሪያ ከአምላኩ ዘንድ ሊቀበል ይገባ ነበር፡፡ ህዝቡ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በተቀመጠ ጊዜ ከተማዋን በሩቅ አይቶ ስለእርሱዋ መልካም ነገር አስቦም ተመኝቶም ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በሩቅ እይታ ያየው መልካም ነገር በእግዚአብሄር ፊት ሊጠፋ የተቀጠረለት ስፍራ ነበር፡፡
እግዚአብሄር እያንዳንዱ እስራኤላዊ ልብ ብሎ በራሱ ዘመን ከእርሱም በሁዋላ ልጁ፣ የልጅ ልጁም በዕድሜው ሁሉ ሊወርስ በሚገባባት ምድር የሚያደርገውን ነገር በሙሴ አፍ ደጋግሞ አሳስቦአል፡፡ ይህም ህዝቡ ያደርገው ዘንድ፥ አምላኩ እግዚአብሔርን ፈርቶ እርሱ ለእርሱ ያዘዘውን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ይጠብቅ ዘንድና የእግዚአብሄርን ፍርድና ስርአት በመጠበቅ ውስጥም የሚገለጠው በረከት ዕድሜውን በደስታ ምድር እንዲያረዝምለት እግዚአብሄር የፈቀደው ነበር፡፡ ብቻ አምላኩ እግዚአብሔር እንዳስተማረው ያዘዛት ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድም ምን እንደሆነች እንዲያስተውል ይህ ማሳሰቢያ በሙሴ በኩል ተላልፎአል፡-
”እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካምም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።”
እግዚአብሄር ይህ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲጠበቅ ሲናገር ለእስራኤል በምላሹ በጎ ሊያደርግ በዚያም በኩል ህዝቡ ሳይዘናጋ ያከናወነለትን አምላክ እንዳይረሳ የሚያሳስብ ነበር፡-
”… አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤ በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ።” (ዘዳ.6:1፤2-20)
ሌላው የኢያሪኮ አይነት እንቅፋት በአለም ያለው የመንፈስ ጫናና ተጽእኖ ነው፡፡ አለም የሁሉም አይነት መናፍስት መናሀሪያ ናት፡፡ በተለይ አለማውያን በነጻነት ስጋዊነትን ስለሚያካሂዱ ለመንፈሳውያን ሰዎች የልማድ ፈተና ናቸው፡፡ የሚያሳርፉት ጫና መንፈሳዊነትን ለማኮሰስና ስጋዊ ለማድረግ የሚገፋ ቢሆንም ልቡ የሸፈተን አባብሎ ለማስጠም የሚጎትትም ነው፡፡ አህዛብ ህዝቡ እንዲስት ጦር መምዘዝ ሳያስፈልጋቸው በሚያባብልና በሚያስጎመጅ የአመጽ መስዋእታቸው ስቦአቸዋል፡፡ ከዚያ በሁዋላ የሆነው ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡
የአምልኮ ወረርሽኝ አንዱ የአለም መገለጫ ነው፡፡ የጣኦት አምልኮና የተለያዩ የመናፍስት አሰራሮች የእግዚአብሄርን ቃል ለማይሰማ ሰው እጅግ ፈተና የሚሆኑት ማባበልና መማረክ የሚያስችል ጉልበት ስላላቸው ነው፡፡ በአለም ውስጥ የባእድ አማልክት በምስሎች፣ በተቀረጹ እንጨቶች፣ ድንጋዮችና የብረት ስራዎች ላይ ተገልጠው ልብንና መንፈስን ድንጋይ ያደርጋሉ፤ እነዚህ ተጽእኖዎች ከህይወት ካልተወገዱና አምልኮአቸው ካልተሻረ መጥፋት የነበረባቸው ሆነው ሳለ እኛን አድነው ይይዙናል፣ ሁለመናችንን ወርሰውም ያጥለቀልቁታል፤ ታዲያ በመናፍስት አገዛዝና እንዲህ በታፈነ ማንነት በሀጢያት እስራትም ውስጥ እንዴት የእግዚአብሄርን ርስት መውረስ ይቻላል?
1ነገ.16:34፤ ”በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ።”
አኪኤል የነዌ ልጅ ኢያሱ ያጠፋትን በራሱም በእስራኤልም ፊት ቁጣ የምታመጣውን ኢያሪኮን መልሶ ሰራ፡፡ ደጆችዋን መስራቱን ተመለከተ እንጂ በዘመኑ ላይ የሚስበውን መአት አላሰበም፤ ህንጻዎችዋን መስራቱ ላይ አተኮረ እንጂ እግዚአብሄር በእርሱ ላይ የተናገረውን ልብ አላለም፤ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያደረገው መተላለፍ ጥቂት መስሎ ታይቶታል፡፡ ሆኖም እግዚአብሄር ያረከሰው ስፍራ በእኛ ሊጸድቅ እንዴት ይችላል? እግዚአብሄር የተጸየፈው ለህዝቡ እንዴት ሞገስ ሊሆን ይችላል? ለማያስተውል ህዝብ ግን ሁሉም ደህና ይመስለዋል፣ ጥፋትም ፈጥኖ ያገኘዋል፡፡
በሆነ ዘመን በሆነ ስፍራ ተገልጦ የሰራ ክፉ መንፈስ መልሶ መላልሶ ትውልድን እየፈለገ ይመጣል፤ በድሮው ሀይሉ፣ በድሮው ተንኮሉ፣ በድሮው እቅዱም ሊሰራ ሰውን ፍለጋ በተከታዩ ትውልድ ውስጥ ይገባል፡፡ በእርሱ መስመር የገቡትን ቢያገኝ የተለመደ ወጥመዱን ይዘረጋባቸዋል፣ ይጥላቸዋልም፡፡ መናፍስትን አቅልሎ ማየት ስንፍና ነው፡፡ የማይሞትና የማይሻሻል ፍጥረትን ለተሸለ ሁኔታ መጠበቅ ምን ለማግኘት ነው? በሆኑ ሰዎች ላይ ተገልጦ ክፋትን አመጽንና ባእድ አምልኮን ያለማመደ ጋኔን በልጅ ልጆች ላይ ዳግም ተነስቶ ያንኑ የአባቶች ሀጢያት ልጆችን ሲያለማምድ እንደነበር በቃሉ ውስጥ ተቀምጦአል፡፡ የኢያሪኮም የተረገመ መንፈሳዊ ልምምድ በተለያዩ ዘመናት በሰዎች ላይ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡
ኤፌ5:5 ”ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።”
የጣልነውን አጸያፊ ነገር ወደ ህይወታችን ዳግም የሚስበውን ሀይል አስተውለነዋል? ያ ሃይል ምኞት ነው፡፡ የተረሳውን ልማድ ማሰብ፣ ወደዚያ አስተሳሰብ ማዘንበል፣ ደጋግሞ ማሰላሰልም ብርቱ ምኞት በልብ እያቆጠቆጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ እስራኤላውያን በምድረበዳ እንዴት እንደተጎሳቆሉ በመዝ.106:14-29 ውስጥ መመልከት እንችላለን፡-
እስራኤላውያን በምድረ በዳ የተመኙት ምኞት እግዚአብሔርን እንዲፈታተኑት በር ከፍቶአል። እግዚአብሄር በዚህ ምኞታቸው ተቆጣ፣ የለመኑትን ግን ሰጣቸው፤ በሰጣቸው የምኞት ምግብ ስጋቸውን አረኩ፣ በወቅቱ ሆዳቸውን ሞሉ እንጂ ለነፍሳቸው ግን ክሳት ሆኖባቸዋል። እስራኤል ልበ-ደንዳናና ትእቢተኛ ስለሆነ እግዚአብሄር የላከውን አለቃ ሙሴን ናቀ፤ እግዚአብሔር የቀደሰውን አሮንን በሰፈር ተመቀኙ። የተመቀኙትን ወገኖች ልትቀጣ ምድር ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፤ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤ በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።
እስራኤላውያን የእግዚአብሄር ክብር በሚያስፈራ ግርማ በተገለጠበት በዚያ በኮሬብ በድፍረት ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ፣ እግዚአብሄርንም በደሉ።
እግዚአብሄር በዘዳ.4:15 ”እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ” ብሎ ያዘዘውን ስለምኞታቸው ሲሉ ቸል እንዳሉ እንመለከታለን፡፡
እግዚአብሄር ለነርሱ ማን ነበር? ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውና ያዳናቸው አምላክ እግዚአብሔር አልነበር? እነርሱ ግን ይህን ታላቅ አምላክ ረሱ። ነገር ግን እንደስራቸው መጠን አልነበረም፣ እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ወስኖ ተናግሮ ነበር።
የምኞት ክፋቱ መልካሙን ነገር ማስናቁ፣ የከበረን ማዋረዱ፣ ሰውን ከአእምሮ ማውጣቱ… ራሱ የተዋረደ መሆኑ ሳያንስ እኛን በውርደት ያኖረ መሆኑ፤ ከዚህም ሲያልፍ በዚያ ህይወት ያሉትን ማስናፈቁ፣ የተዋረደን ማስከጀሉ! እንዲሁ እስራኤላውያን በእግዚአብሄር እይታ ሞገስ ያገኘችውንና የተወደደችውን ምድር ናቁ፣ አእምሮአቸው ከከበረው ይልቅ የተዋረደውን የሚመርጥ ስለነበር ክብሩ አልገባቸውም፤ ቢናገርም በቃሉ አልታመኑም፣ ሆኖም ይህ ሁኔታ እጅግ አስጨናቂ ነገር ውስጥ የሚከት ነበር እንጂ አልበጃቸውም፡፡ አካሄዳቸው በተለይ ለእግዚአብሄር ባሪያዎች ፈተና ሆኖ ነበር፣ ሙሴና አሮን በምርጫቸውና በድርጊታቸው ብዙ ጊዜ ተጨንቀዋል፡፡ ስለዚህ አመጸኛ የእስራኤል ቤት ሳይታክቱ በድንኳኖቻቸው ውስጥ መሽገው አንጐራጐሩ፣ ስለእግዚአብሄር አዘውትረው ሲናገሩ በበጎ አልነበረም፤ ይህ የሆነው የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰሙና እንደ እግዚአብሄርነቱ ስላልተመለከቱት ነበር። ይህን ያየ አምላክ በምድረ በዳ ይጥላቸው ዘንድ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይበትን ዘንድ በየአገሩም ይሰድዳቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው፤ ለስቃይ፣ ለፈተና ለባርነትም አሳልፎ ሊሰጣቸው ወሰነባቸው። በኢያሪኮ ሜዳ በመጎምጀት ስሜት የተዋጠ እስራኤላዊ መጨረሻው መች አመረ? ህዝቡ ሁሉ ተሰባስበው በብዔል ፌጎር በእግዚአብሄር ላይ ተባበሩበት እንጂ፤ ተላልፎ የተሰጠ ይህ ህዝብ አጸያፊውን የሙታንን መሥዋዕት ሳይቀር በላ።

በ2ጴጥ.2:22 ላይ ”ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።” እንደሚል ባስተዋሉ ጊዜ ከህይወታቸው ክፉውን አውጥተው የጣሉ ሁሉ መልሰው ያንኑ ሲመኙ፣ በፍላጎት እጅ ሲሰጡና ተሸንፈው ሲሰጥሙ እግዚአብሄር አይቶ ተጸይፎአቸዋል፡፡
ሀጢያት ክፉ ልምምድ ሲሆን ሀጢያተኛውንም ሰው ሙት የሚያደርግ ነው፡፡ አንድ በሀጢያት ውስጥ ያለ ሰው ወደ ህሊናው ቢመለስና ህሊናው በወቀሰው ነገር ልቡን ትሁት አድርጎ በንሰሀ ሀጢያትን ከውስጡ አውጥቶ ቢያስወግድ መሀሪ አምላክ ሀጢያቱን ይቅር ብሎ ነጻ ያወጣዋል፡፡ ክፉ ምኞት ዳግም ሲመጣ መልሶ ካስተናገደውና ሳይጸየፈው እንደቀድሞ ልማዱ ከተቀበለው ግን ውሻ ወደ ትፋቱ እንደተመለሰው ወደ ተወው አጸያፊ ሀጢያት ተመልሶአል ማለት ነው፡፡ህሊና በጎደፈበትና ባልተስተካከለበት አጋጣሚ ሁሉ ውሰኔ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል፣ ትክክለኛ ሚዛናዊነት መስመሩን ከሳተ ወዲህ ስሜትም ፈቃድም ምኞትም ያለ ልጉዋም ወዳሻው ይነዳልና ያጠፋል፡፡ ይህ ክፉ ውድቀት ነው፣ የፈረሰውን የሚያስገነባ፣ የተተፋውን ዳግም የሚያስልስ፣ የሚያዋርድም አካሄድ ነው፤ የዚህ ነገር መጨረሻ ከፉ ፍሬ የሚያሳጭድ በመሆኑ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡