• ኢያሪኮ ይፍረስ
በሙሴ ዘመን የኢያሪኮ ከተማ የእግዚአብሄር ፈቃድ የሌለባት ስፍራና የአመጸኛ ህዝብ ምልክት የነበረች ነች፡፡ የአመጽ ልማድ የነገሰባት፣ ጣኦት የሚገዛባት፣ ስርአት የሌለባትና እግዚአብሄር የማይፈራባት ስፍራ ስለነበረች በርሱዋ ውስጥ የእግዚአብሄር ፈቃድ መገለጥ አይችልም ነበር፤ የከተማዋ ህዝብ እግዚአብሄርን ሳይሆን ጣኦትን የሚከተልና የሚያመልክም ነበር፡፡ ስለዚህ በርስዋ ያለ ምድር ከጣኦት የተነሳ የረከሰ ፣ ህዝቦችዋ ከእግዚአብሄር ጋር ሳይሆን ከአጋንንት ጋር የተጣበቁ ነበሩ፡፡ የዚያ አካባቢ ህዝብ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይሆን የሰይጣንን ፈቃድ ይፈጸም ስለነበር የእግዚአብሄር ህዝብ በዚያ ስፍራ አካባቢ በነበረው ቆይታ በከተማዋ መንፈስ እንዳይያዝ ሲል እግዚአብሄር ኢያሪኮ ትፍረስ አለ፡፡
እግዚአብሄር ህዝቡን ከአመጽ ህይወት የሚያርቅበት አሰራር አለው፡፡ በዚያ ታሳቢነት በብሉይ ኪዳን የተጠራው የእስራኤል ህዝብ ከአመጸኛ አህዛብ ጋር እንዳይቀላቀል ቀድሶት/ለይቶት ነበር፤ የጣኦት ምድርን ጨርሶ እንዲያጠፋ ዝክሩ እንዳይታሰብም ሲያደርግ በምድሩ ላይ በርትተው የነበሩ መናፍስት ዳግም የአገዛዝ ስርአት አዋቅረው እንዳይበረቱ በዚያ ያለውን አለም በመደመስስ ነበር፡፡
ዘኊ.33:50-56 ”እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም። …የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።”
• የኢያሪኮ መፍረስ የጣኦት አምልኮ ስርአት መፍረስ ነው
የጣኦት አምልኮ ስርአት መንፈስን ለአጋንንት አገዛዝ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ በአጋንንት ቁጥጥር ስር ያለ የሰው መንፈስም ነፍስን ለእርግማን አሳልፎ ይሰጣል፡፡
መፍረስ መሻር እንደመሆኑ እግዚአብሄር በዚያ ውሳኔ ጣኦታትን ከንቱ እንዲያደርግ ህዝቡን አዝዞ ነበር፡፡ የረከሰውም የጣኦት አምልኮ ምናምንቴ ሆኖ እንዲቀር በኢያሱ መሪነት የኢያሪኮ ስረ-መሰረት ተንዶአል፡፡
ኢያ.6:2-5 ”እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፡- ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱንም ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ይገባባታል።”
• የኢያሪኮ መፍረስ የእግዚአብሄር ህዝብ እንቅፋት መወገድ ነው
ኢያሪኮ በፈረሰች ጊዜ የማምለኪያ ስፍራዋ አብሮ ፈርሶአል፤ የሚያመልኩትም ህዝቦች በአንድነት ተደምስሰዋል፡፡ አምልኮው፣.አምላኪውና የሚመለከው ግኡዝ ነገር ጠፋ፤ ግን ከልብ ውስጥ ፍላጎት አብሮ ጠፍቶአል? ምኞቱስ ተቀብሮአልን?
• የኢያሪኮ መፍረስ የአጋንንት ምሽግ መፍረስ ነው
አጋንንት ምክኒያታዊ ናቸው፡፡ በስፍራ ይሰለጥኑና ዘመንን ይወርሱ ዘንድ በአለም ላይ ስርአታቸውን የሚዘረጉት የሰውን ፈቃድ ባገኙበት አጋጣሚ ብቻ ነው፤ ልብ ወደ እነርሱ እቅድ ካዘነበለ የእነርሱ ፈቃድ ውስጥ መውደቁ የማይቀር ነውና፡፡ ይህን የሚረዱት ክፉ መናፍስት ህዝቡን እግር ለእግር የሚከተሉት ባዘነበለበት ስፍራ ሁሉ ቀርበው ሊያጠምዱት ነው፡፡
• ኢያሪኮን መልሶ መስራት ለእግዚአብሄር ህዝብ የጠላት ምሽግ ማዘጋጀት ነው
ኢያሪኮ ትፍረስ ያለው እግዚአብሄር አይደለምን? የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ተላልፎ የልቡን ፈቃድ ያከናወነ ሰው የኢያሪኮን እርግማን ወደ ቤቱ ከመሳብ ውጪ ምን ያተርፋል? ለጠላት አመቺ ምሽግ አለመታዘዝ የሚባል ጠንቅ ነው፡፡ የማያስተውል ህዝብ የጠላትን ምሽግ በማደሪያው ይቆፍራል፡- ባለመታዘዝ በኩል፣ ባለማስተዋል በኩል፣ እውቀት በማጣት በኩል፡፡
• ኢያሪኮን መልሶ መስራት የጥንት ኢያሪኮን አምልኮ መሳብ ነው
ለዛሬ ዘመን ሰዎች ምድራዊቱዋ ኢያሪኮ ብዙም ትኩረት ላትፈጥር ትችላለች፡፡ ነገር ግን የርሱዋ ታሪክ የጥንቃቄ የአመጽ ምልክት ሊሆን የሚችል ነው፡፡ በውስጥዋ የሆነውን ማስታወስ ህዝቦችዋ የጠፉበትን ተግባር ያሳስባል፣ እግዚአብሄር ለክፋታቸው የመለሰውን ቅጣትም ያሳያል፡፡ በእርግጥ በርሱዋ ውስጥ በቀድሞ ዘመን ጥፋትን የሳበው የአጋንንት ስራ አሁንም እንዳለ ማስታወስ አለብን፡፡ እነዚያ ክፉ መናፍስት አልጠፉም፣ አልሞቱም፣ ገና ፍርዳቸውንም አልተቀበሉም፡፡ ያን ክፉ ስራቸውን እንደቀድሞ ከመስራት ምን ይከለክላቸዋል? (ከእግዚአብሄር ተግሳጽ በቀር)፡፡
• ኢያሪኮን መልሶ መስራት ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር መጣላት ነው (አፍርስ ያለው እግዚአብሄር ነበር)
እግዚአብሄር የተጸየፈውን ሲያስወግድ የምናይበት አጋጣሚ የሚያስተምረን ምንድነው? የጠላውን እርኩስ አድርገን ልንጸየፍ፣ የተቀበላቸውን በፍቅር ልንይዝ አይደለምን? የማይታዘዝ ህዝብ ግን በተቃራኒ መንገድ ይጉዋዛል፣ እስራኤላውያን እንዳደረጉት፡፡ ነገር ግን እነርሱ በተከተሉት የስህተት መንገድ ምክኒያት ጥፋታቸውን ከተቀበሉ እኛስ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?
• ኢያሪኮ ፈርሶ አልፈረሰም – እርሱ አፍርሶ፣ አመጸኞች መልሰው ገነቡት፡፡
እግዚአብሄር ጣኦትንና ጣኦት አምላኪዎችን እንደሚጠላ ሊያሳይ በኢያሪኮ ላይ ፍርድ ተናገሮ ነበር፡፡ ፍርዱም ይፈጸም ዘንድ በኢያሱ በኩል ጥብቅ ትእዛዝ ወጥቶ ያ ትእዛዝ ተፈጽሞአል፡፡
”በዚያን ጊዜም ኢያሱ፡- ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኵር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ። እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ወጣ።” (ኢያ.6:26-27)
ኢያሪኮን ዳግም የሚሰሩ እግዚአብሄር የጠላውን የሚያደርጉ ለቃሉም የማይታዘዙ ናቸው፡፡ አትስራ እምቢ፣ አትሂድ እምቢ፣ አታድርግ እምቢ… ሁሉን እምቢ በሚል እምቢተኝነት ጥፋት ውስጥ የሚገቡ ኢያሪኮን ከሚሰሩ ጋር አንድ ናቸው፡፡
”ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፤ ቃሌን አስተምራችኋለሁ። በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥ ምክሬን ሁሉ ግን ቸል ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልፈቀዳችሁ፤ እኔም ስለዚህ በጥፋታችሁ እስቃለሁ፤ ጥፋታችሁም በመጣ ጊዜ አላግጥባችሁ። ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ።” (ምሳ.1:23-27)
የጌታን መንገድ በመተላለፍ ፈቃዱን ከራስ ለመጣል/ለማቁዋረጥ መከጀል የፍዳ ዋጋ ያሸክማል፤ መቅሰፍት የሚስብ ድፍረት ህዝቡን አራቁቶአልና፡፡እግዚአብሄር ግን ቸር ነውና እልከኝነትን በመሻርም ወደ እርሱ የሚመራ መንፈሱን በመላክም ጭምር እንድንስተካከል ያግዘናል፡፡
ዕብ.2:1-4 ”ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።”
• እሱ አፈረሰው እኛ ለምን ሰራነው?
1ነገ.16:34 ”በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ።”
አኪኤል የተባለ አንድ ግድ-የለሽ ሰው በሰራው ጥፋት ቤተሰቡ ላይ እርግማን ሲያመጣ በዚህ ታሪክ ውስጥ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሄር ያፈረሰው ግድግዳ በአርግማን ምክኒያት የሆነ ስለነበረ ግድግዳውን መልሶ ማቆም ማለት እርግማኑን መልሶ እንደ መጥራት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከህይወታችን/ ከላያችን ያራገፈውን አዋራ በተለያየ ምክኒያት ስንነካካው መልሶ እንደሚያለብሰን ካወቅን የእግዚአብሄርን ቃል መጣል ፋይዳ እንደሌለው በመረዳት ሁልጊዜ ልንጠብቀው እንደሚገባ ለአፍታም መርሳት አይገባም፡፡
ኢያሪኮን የደመሰሰ አምላክ እስራኤልን በወረሰ ዘመን አክአብ የተባለ የእስራኤል ንጉስ ከሌሎች ነገስታት ይልቅ የእስራኤልን አምላክ ትቶ አማልክትን አመለከ፤ ልዩ ልዩ አማልክትን በመከተሉም የአግዚአብሄር ጠላት ሆነ፡፡ ንጉሱ የእግዚአብሄርን ህግ ተላልፎ ለጣኦታትንና ለምስሎች ሰግዶአል፤ በዚህ ስራውም እግዚአብሄርን እጅግ አስቆጣው፡፡
ብዙ ጊዜ ከፍ ያለ ሀጢያት ላይ የሚጥለን ውድቀት መነሻው ቀላል የመሰለ መተላለፍ ነው፤ አክአብ ይህንን ሂደት ከአህዛብ ሚስት በማግባት ጀምሮታል፡- አክአብ ከአህዛብ የመጣች ሚስት አገባ፣ እርሱዋም የጣኦት አምልኮ አስከትላ ወደ እስራኤል ገባች፣ ህዝቡን አስመለከች አሳተችም፤ ከዚያ በላይ በዘመኑ ኢያሪኮ ተሰራ፡፡
• ኢያሪኮ ለምን ይፍረስ? -ኢያሪኮአችን ፈተናችን ነው
በተለያየ ምክኒያት የኢያሪኮን ግንብ የመሰለ ክፋት በዘመናችን ውስጥ ብቅ ሲልና የጥፋት ምልክት ሲያቆም እግዚአብሄር ምልክቱ የትውልድ የጥፋት መታሰቢያ እንዳይሆን ይሽረዋል፣ ዳግም ላይታወስም ያፈርሰዋል፡፡ ችግሩ የፈረሰው እንደፈረሰ እንዳይቀር፣ የተከደነልንም ሀጢያት መታሰቢያው እንዳይረሳ እኛ ደካሞች አመጽን መልሰን እናነሳሳዋለን፣ የእግዚአብሄርን መቅሰፍትና እርግማን በርሱ እንጠራለን፡፡
• ኢያሪኮ በድምጽ ብቻ የሚፈርስ የጠላት ምሽግ ነው
የኢያሪኮ ቅጥር በእግዚአብሄር በኩል ለቆመ ሰው በድምጽ የሚፈርስ የአመጽ ግንብ ቢሆንም ከእግዚአብሄር ውጪ የማይደፈር ቅጥር መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ከተማዋ ብርቱ ህዝብና ጥበበኞች ያሉባት እንደመሆኑ ያነሰ እውቀትና የተዳከመ ጉልበት ይዞ የመጣን እንደ እስራኤል ያለ ህዝብ ማቆም ብቻ ሳይሆን መደምሰስም አይሳናትም ነበር፡፡ አንዲሁም ስጋዊ ነገራችን (እንደ ኢያሪኮ ብርቱ የሆነ ፈቃድ) በራሳችን ጉልበት ከላያችን ሊነሳ (መንፈሳዊነታችንም ያለ እግዚአብሄር መንፈስ እገዛ ሊያሸንፍ) ፈጽሞ አይችልም፡፡ ስለዚህ የስጋ ስራ ሊሞት የሚችለው በመንፈስ ሀይል ብቻ መሆኑን ተረድተን ለመንፈስ አሰራር ቅድሚያ እንስጥ፡፡ ያኔ ነው ግድግዳው ፈርሶ ወደ መንፈሳዊ ነገር መድረስ የምንችለው፡፡
• ስለ ኢያሪኮ – የአመጽ ምልክት ነው
ኢያሪኮ ውስጥ የሚኖር አመጽ ውስጥ ይኖራል፡-
በመንፈስዋ ውስጥ ይኖራል፣ ሲኖርም ኢያሪኮ ውስጥ በሰለጠነው መንፈስ ይመራል፣ ባይፈልግም መንፈሱ ይታገለዋል፡፡
ከተስማማ ቁጥጥርዋ ስር ይውላል ወይም ከተጋፋት በስርአትዋ ይገፋል፡፡ የተቀበላት በልምምድዋ ውስጥ ስር ይሰደዳል፣ ሲኖርም በዚያ የሚኖሩ አህዛብን ልማድ የርሱ በማድረግ ያ ይጠናወተዋል፡፡ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር መቀራረቡ አይቀርምና በህዝቡ ባህል ይዋጣል፡፡ በአምልኮ አንድነት ሰበብ አምልኮዋን ይጋራል፣ ቆይቶም በጣኦትዋ እስራት ይንበረከካል፡፡ ሲያመልክም ለአጋንንት ተላልፎ ይሰጣል፣ የተለማመዳቸው አጋንንት ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ ያደርጉታል፤ በእርስዋ ውስጥ እውነተኛ አምላክን መካድ ስላለ እርሱም በፈንታው ተውጦ ከሀዲ ይሆናል፣ ያን በማድረጉም እርግማን ይወድቅበታል፡፡
አመጽዋን ለመተባበር ድፍረት ያለው/በረሱዋም መንፈስ የተማረከ እነዚህ ሁሉ ክፋቶች ይወርዱበታል፡፡
ዘጸ.20:1-6 ”እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ። ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።”