አዲስ ኪዳን ምልክት  (2..)

የእግዚአብሄር ፈቃድ

​​​​​​​​የአዲስ ኪዳን ምልክት ሰው
በብሉይ ኪዳን የነበረ አንድ ነቢይ በህይወቱ የተከናወነ አዲስ ልምምድ ማስተናገዱ ከግርምት ባለፈ ለትውልዱ የሚያበስረው ትልቅ ምልእክት ነበረው፡፡ ​​​​ነቢዩ ዮናስ  ይባላል፣ ይህ ነቢይ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሄር ፊት የሚኮበልልበት ሰበብና ጥሪውን ወደ ሁዋላ የሚያደርግ ድካም ገጥሞት ነበር፤ እግዚአብሄር ግን መኮብለሉን አይቶ ሳይተወው በመከታተል እስከተደበቀበት ስፍራ እስከ ጥልቅ ድረስ ወርዶ የሚያስተምረውን እርምጃ ሲወስድበት ይታያል፡፡ ይህ ነቢይ የኮበለለበት ማረፊያ  ስፍራ አሳ አንባሪ ሆድ  ቢሆንም አሳ አንበሪው በእግዚአብሄር የተዘጋጀ ማስተማርያ ስፍራ ነበርና ነቢዩ በርሱ ሆድ ውስጥ ሶስት ቀን ከቆየ በሁዋላ በእግዚአብሄር ትእዛዝ ተተፍቶ ወደ ምድር ወጥቶአል፡፡ በወቅቱ ነቢዩ የራሱ ስራ ጸጽቶት ባደረገው ንሰሀ እግዚአብሄር እንደማረው አስቦአል፤ የእግዚአብሄር አላማ ግን ከነቢዩ ንሰሀ ያለፈ ነበረ፡፡ ስለዚህ በነቢዩ ህይወት ለትውልዱ የሚተላለፍ የእግዚእብሄር ስራ ምልክት ተገልጦ ነበር፡፡ የነነዌ ህዝብም ዮናስ የንሰሀ ምልክት ሆኖትና ስብከቱን አስተውሎ ንሰሀ ገባ ከጥፋትም ተረፈ፡፡ ጌታ ኢየሱስ በአይሁድ መሀል በተመላለሰ ዘመን ግን የመዳን ምልክት ይሆን ዘንድ የሚፈወሱትን እየፈወሰ፣ የሚተውን እያነሳ፣ ከአጋንንትም ነጻ እያወጣ ሲዞር ልብ ያለና ያስተዋለው ከትውልዱ ማን ነበር?
ክርስቶስ ዮናስ ወደ አሳው ሆድ እንደገባ ወደ መቃብር ገባ፣ ዮናስ በሶስተኛው ቀን ከአሳ ሆድ እንደወጣ ክርስቶስም ከመቃብር ውስጥ ወጣና ትንሳኤን አወጀ፡፡
ሉቃ11:29-30 ”ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል።”
ጌታ ኢየሱስ ለአዲስ ኪዳን ትውልድ ከእግዚአብሄር ዘንድ የተገለጠ የእግዚአብሄር የምህረት ምልክት ነው፤ ወደ ገዛ ወገኖቹ ሲመጣ ወገኖቹ ይህን ምልክት ማስተዋልና እንደ ነነዌ ህዝብ ፈጣን ምላሽ መስጠት አልቻሉም፤ ይልቅ መዳንን ሊቀበሉ ሲገባ እነርሱ የእንቅፋት ድንጋይ ሲያኖሩ ነበር፡፡
ትውልድ ሁልጊዜ የሚገረምበትን ምልክት ይፈልጋል፣ በዚያም ያደንቃል፣ ስለእርሱ ይነጋገራል፣ መልሶ ግን ከልቡ አውጥቶ ይረሳዋል፡፡ የአለም ምልክት የሆነ ወቅት ሰውን በግርምት ከመሙላት ውጪ ዘላቂነት የለውም፤ ለምሳሌ በሰማያት ጭፍራዎች ላይ የሚታይ ድንቅና ምልክት ትውልድ አይቶ ሲገረምባቸው፣ ሲደነቅባቸውና ሲደነግጥባቸው ቢታይም አንዳችም ወደ እግዚአብሄር የሚያቀርብ ተጽእኖ በህይወታቸው ፈጥሮ መለወጥ ሳይችሉ ያዩና የሰሙትን ፈጥነው እንዲረሱ ይሆናል፡፡ የጌታ ምልክት ግን ትውልድ ማሳሰቢያና ማንቂያ ሲሆን የማይጠፋም  ነው፡፡
ምልክትን የማያስተውሉ የሀይማኖት ሰዎች ተስፋ የተሰጠውን የአይሁድ ህዝብ ወደ ስህተት በመምራት ለከፍተኛ ጉዳትና ሰቀቀን ዳርገዋል፣ ቃሉም ያን ሲያመለክት በማቴ.12:38-40 ውስጥ ይታያል፡-
”በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፡- መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን ​አሉ። ​​​​​​​​እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።”
የእስራኤል ክፋት በጻፎችና ፈሪሳውያን ላይ ጎልቶ የሚታይ ነበር፤ ለምን? እነርሱ ሰምተውና አስተውለው የጌታንም ቃል ተከትለው በዚያ ምልክት ብርሀን ህዝቡን ወደ ንሰሀ ማቅረብ ሲገባቸው በሴራ የተተበተበ አካሄድ ውስጥ ተቀርቅረው ተገኝተዋል፡፡ ፈሪሳውያን በዚያን ወቅት ቀርበው ጌታን ምልክት የጠየቁት ከእርሱ የህይወት ቃልን ለመቀበል ሳይሆን በዘዴ ህዝብ ከእርሱ እንዲርቅ አስበው ነበር፤ እርሱን ለመስማት ወስነው ሳይሆን ላለመቀበል አሲረው ያቀረቡት ጥያቄ ነበር፡፡ ምልክት ሲጠይቁ በጥያቄያቸው ውስጥ ትህትና አልነበረም ይለቅ ጥያቄአቸው እርሱን አንቀበልም የሚል ስሜት ያለው ነበር፡፡ ምልክት እንድናይ እንወዳለን ሲሉ የሚሰጣቸውን ምልክት መክሰሻ ለማድረግ ፈለጉ፡፡ እርሱ ግን ሌላ ምልክት አያስፈልግም አለ፡፡
አመንዝራነት ያለመጥገብ ረሀብ ነው፣ ያለመርካት ስሜት ነው፡፡ ትውልድ አሁን በምድር ላይ እየታየ ባለው እጅግ ብዙ ምልክት ሳይረካ፣ ሳያምንና በዚያ ሳይጠነቀቅ ከጌታ ሌላ ምልክት ይጠይቃል፡፡ ትውልዱ ከበቂ በላይ እየሆነ ባለው በዚህ ሁሉ ምልክት አልረካም፡፡
​​​​​​​​ኤር.32:20-24 ”እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል። በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ።ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርንም የምታፈስሰውን ምድር፥ ሰጠሃቸው፤እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ ያደርጉም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው።እነሆ የአፈር ድልድል፥ ሊይዙአትም እስከ ከተማይቱ ድረስ ቀርበዋል፤ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፥ የተናገርኸውም ሆኖአል፤ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ።”
የነቢዩ ዮናስ ራስን መስጠት
ከላይ እንዳየነው ኢየሱስ ምልክት እንደሚሰጥ ቃል ሲገባ የሰጠው ምልክት ሌላ ሳይሆን የዮናስን ህይወት ነበር፤ ዮናስ መርከብ ውስጥ ያለ ህዝብ ከሚጠፋ እኔን አሳልፋችሁ ስጡ እንዳለ ህዝቡ ከሚጠፋ አንድ ሰው/ ክርስቶስ ስለህዝቡ ሁሉ ሀጢያት ሊሞት እንደተገባው አመልካች ነበር፡፡ ሞት ግን ጌታን ይዞ አላስቀረውም፣ እንዲሁ ዮናስን የዋጠ አሳ ውጦ አላስቀረውም ይልቅ በሶስተኛው ቀን ተፋው፡፡ በተመሳሳይ ምድር ጌታን ይዛ ማስቀረት አልቻለችም፡፡
​​​​​​​​ማቴ.16:1 ”ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፡- በመሸ ጊዜ፡- ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ ማለዳም፡- ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ።”
ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ስምምነት የሌላቸው የሀይማኖት ክፍሎች ቢሆኑም በጌታ ላይ ለማሴር ግን ህብረት ፈጥረዋል፡፡ በስራው አያመሰግኑም፣ ትምህርቱን አይከተሉም፣ በማዳኑም አይታመኑም፡፡ ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ እጅግ የበዛ ታምራት በመሃከላቸው አድርጎአል፡፡ ያ ሁሉ ማዳን፣ ፈውስ፣ ምህረት፣ ይቅርታ፣ ከእስራት መፈታት ሳያሳምናቸው ሌላ እነርሱ ብቻ የሚፈልጉት አይነት በነርሱ ፈቃድም የተመሰረተ ምልክት ለትውልዳቸው ፈለጉ፣ እርሱ ግን ገሰጻቸው፣ አላመኑበትምና፡፡ እግዚአብሄር በሰው ፈቃድ አይመራም፣ ይህን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው፤ ጌታ ለምን በስጋ መምጣት አስፈለገው? ወደ ገዛ ወገኖቹ መቅረብስ ለምን ወሰነ? ስለቃልኪዳኑ አይደለምን? ህዝቡ የሚጠባበቀውን ተስፋ ሊጨብጥ እንዲያስፈልገው ስለሚያውቅ አይደለምን? ስለሚክዱ አመጸኞች ግን ሲናገር፡-
​​​​​​​​ዮሐ.15:22-25 ”እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል። ነገር ግን በሕጋቸው፡- በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።”
​​​​​​​​ሉቃ11:16-20 ”ሌሎችም ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል።እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል እንዳወጣ ትላላችሁና ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።”
የተከለከለ ምልክት
ምልክት ሁሉ የተፈቀደ ነው ማለት አይደለም፣ ምልክት ሁሉ ተገቢ ነው ማለትም አይደለም፣ ወይም ደግሞ ምልክት የአንድ ነገር ትክክለኛነት/ የምንነቱ መገለጫ ነው ማለት አይደለም፡፡ ምልክት አብዛኛውን ጊዜ የነገር ጫፍ፣ የሙሉ ምስል አመልካች ጥላ ነው፡፡
ስለምልክት አይነት ስንመለከት ማየት፣ ማስተዋል፣ መከታተልና መገንዘብ ያለብን የምልክት አይነት አለ፤ ምልክት ጠቃሚ እንደሆነው ሁሉ መጠንቀቅና መሸሽ የተገባው አላስፈላጊው የምልክት አይነትም አለ፤ አንዱ ምሳሌም የሚከተለው ነው፡-
”እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውምና ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።” (​​​​​​​​ኤር.10:1-5)
አህዛብ የሚፈሩት ምልክት አንዱን አምላክ ለሚያመልክ ህዝብ መታሰቢያ ሊሆን አይገባም እያለ ነው ቃሉ፤ እግዚአብሄር ሲፈቅድ ብቻ ለህዝቡ ምልክት ይሰጣል፡፡ ጌታ የሚሰጠው ምልክት ደግሞ የሰማይ ፊት ላይ የሚገለጠው ገጽ ሳይሆን ዘመንን ለማመልከት የሚሰጠው ማስገንዘቢያ ነው፤ ይህም ትውልድን በየዘመኑ የሚያሳስብ ወደ እርሱም የሚጠራ ይሆናል፡፡
የአህዛብ ነቢያት በጥንቆላ የሚታመኑ የሚከተሉዋቸውንም በታምራት ለማሳመን ከሰማዩ ፊት ጋር የሚያስተዋውቁ ብቻ ናቸው፡፡ ሰማይና ምድርን የሰራ አምላክ ግን እርሱ ይመለክ ዘንድ ከአህዛብ ከንቱ ልማድ እንድንወጣ ያሳስባል፡፡
​​​​​​​​ኤር.31:21-22 ”ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።”
እግዚአብሄር በሚሰጠው ምሪትና በሚሰጠው ምልክት መመራት ከልባሞች ሁሌ ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሄር ባሳየው ነገር ላይ ልብን ማጽናት ከእግዚአብሄር ጋር በሰላም እንደሚያኖር ከህዝቡ ታሪክ እንማራለን፡፡ የሰው እጅ ስራ ግን አጥፊ ነው፤ የሰው ፈቃድ የእግዚአብሄርን አሳብ ሊሞላ ከቶ አይችልምና፡፡ በዚህ ሁልጊዜ ከቃሉ ጥንቃቄ ስንጎድል ለስህተት አሳልፎ የሚሰጠን ሰው ወለድ ችግር እንደማያጣን የሚታይ ነው፡፡
ቅድስና  የጌታ ህዝብ ምልክት
የመለያ ምልክት በእግዚአብሄር ውሳኔ የተቀመጠ በመሆኑ ምልክቱ ለልጆቹ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመናፍስቱ አለም ምልክታችን መለያችን ነው፡፡ ምልክታችን ጠላት በእኛ ላይ እንዳይሰለጥን በእግዚአብሄር የተቀመጠ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ነገር ግን ደካማና ወደ ሁዋላ የተንሸራተተ ህይወት ሲኖር በምልክቱ መጥፋት ምክኒያት ለጠላት መጋለጥ ይሆናል፡፡
​​​​​​​​2ጢሞ.2:19 ”ሆኖም፡- ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም፡- የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል።” ይላል ሀዋርያው፡፡
ጌታ በእኛ ላይ ይህን ሲወስን ማህተሙን ለጠላት ማስጠንቀቂያ አድርጎ፣ እኛ በእርሱ ዘንድ  የእርሱ መሆናችን ማረጋገጫ   እንዲሆንም በማለት ነው፤ የሚያስደስተውም የእርሱ ማህተም ለእኛ መተማመኛ ለጠላታችን ፍርሀት ነው፤ እንዲህ ባለ ጥበቃ የሚያኖር አምላክ ዘወትር ሊመለክ ይገባዋል፣ ሊፈራ ይገባዋል፣ ስሙ ከፍ ሊልም ይገባዋል፡፡ ጌታስ ለእርሱ የሆኑትን ባተማቸው ማህተም ያውቃል፣ ህዝቡም ደግሞ ስሙን በልቡ በማኖር አምላኩን ያውቃል፡፡
​​​​​​​​ራእ.14:1-2 ”አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።”