ዕብ13:8 ስለ ጌታ ኢየሱስ ማንነት እንዲህ ይላል፡-
”ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።”
ጌታ ኢየሱስ ሞቶ አልነበረም ወይ? የሚሉ አሉ፡፡ አዎ ሞቶ ነበር፣ ሞቱ ግን ዘላለማዊነቱ ላይ ምን ተጽእኖ ነበረው? እርሱ ራሱ ስለራሱ ተናግሮአል፡-
”ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።” (ራእ.1:17-18)
የእርሱ በስጋ መሞት የታቀደ ስራ እንደነበረው ሞትና ሲኦል ላይ ባደረገው ነገር ይታያል፡፡ ከዘላለም እስከ ዘላለም ያው የሆነ ጌታ በስጋ ሞቶ በመንፈሱ ህያው በመሆን በዚያ በመንፈሱ በወረደበት ስፍራ ሞትንና ሲኦልን ድል ሲነሳ ይታያል እንጂ ትናንትና፣ ዛሬና እስከዘላለም ያው መሆኑ ሲለውጥ አይታይም፡፡
ነቢይና ንጉስ የነበረው ዳዊት በመዝሙር መጽሀፉ ውስጥ የገለጣቸው የእግዚአብሄር ስራዎች የፍጥረታትን የህይወት ገጽታና የእርሱን የጸና ዘላለማዊነት አመልካች ናቸው (መዝ.102)፡፡ ዳዊት ሲናገር ዘመኖቼ የሚላቸው ጊዜያቶችን (የሰው ልጆችን
የምድር ቆይታዎች የሚወክሉ ጊዜያቶችን) ሲያሰላስል እንደምን አናሳ እንደሆኑ ተመለከተ፤ በፍጥነት እንደሚቆረጡ አስተውሎም በጥላ መሰላቸው፡፡ ጥላን አስተውለን ከሆነ ትምክህቱ በራሱ ህልውና ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በውጪ አካል ላይ የተደገፈ መሆኑን፣ በራሱ ስፍራና ጊዜ ኖሮት መደገፍ እንደማይችል እንዲያውም የሚከተለው አካሉ በዞረ ጊዜ ከስፍራው እንደሚነቀል፣ ከዚያ እንደሚወገድና መታሰቢያው እስኪታጣ እንደሚረሳ አመልካች ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ምድር ያለው የእኛ ህይወት ነገር እንደዚህ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሂደት ሲያልፍ ዘወትር የሚመለከት የበላይ የሆነ ጌታ ደግሞ አለ፤ በአርያም ከፍ ያለ፣ ሁሉ በሁሉ የሆነ፣ ትላንት በነበረበት ሁኔታ ዛሬም ያለ፣ ነገም የሚኖር እንዲሁም ለዘላለም የማይለወጥ ነው፡፡ ዳዊት ስለእርሱ ሲናገር አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው ይለዋል። ያለመለወጡን ስላየ፣ የማይናወጥ መሆኑን ስላስተዋለ፣ በፈጠራቸው ላይ ባለቤት ሆኖ እንደፈቃዱ የሚለዋውጣቸው እርሱ መሆኑን ስላስተዋለ ተናገረ፡፡
የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት።
መዝ.90:1-6 ”አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል።”
ፍጥረታት ይቃያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ፍጥረታት በእግዚአብሄር እጅ የተፈጠሩ ናቸው፤ ፈጣሪያቸው እንደተፈጠሩ ሆነው ለዘለአለም እንዲኖሩ አልሰራቸውም፡፡ ፍጥረቶች ሲፈጠሩ ጊዜ ስለተመደበላቸው በተመደበላቸው ጊዜ ውስጥ ከርመው በመጨረሻ እድሜያቸው እንዲፈጸም የወሰነው ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ሳሉ ግን መጠጊያ ከእርሱ ሌላ ማን ይሁናቸው? ብዙውን ጊዜችንን በምድር ጉዞአችን ላይ የምናሳልፈው በእግዚአብሄር ላይ ባለን የመጠጊያነቱ ትምክህት ውስጥ አይደለም፤ ይልቅ በራሳችን ጉልበት በመታመን ስንደክም ይታያል፣ በአእምሮአችን ብልሀት ነገሮችን ፈር ለማስያዝ የምንደክመው ድካም ይበዛል፤ ጥረታችን ባልከፋ ግን ስንቱ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ተከናወነ? ያን አካሄዳችንን ከተሸከመው ጥፋቱ ጋር የሚያይ አምላክ ለዚህ ጥሪ ሲያቀርብ የሰው ልጆች ሆይ ተመለሱ ይላል፡፡
አላስተዋልንም እንጂ የትውልዶች ሁሉ እድሜ ሺ ዘመናት ያህል ተደምረው ቢቀርቡ እንኩዋን በእግዚአብሄር ፊት እንደ አንድ ቀን ሆነው የሚታዩ ናቸው፤ ታዲያ ከእርሱ አሳብ ውጪ የሆነ ጉዞአችን ለምን ይሆን? ከፈቃዱ ውጪ የሆነ ኑሮአችንስ ለምን ይረባን? የእግዚአብሄር ሰው ሙሴ ከእግዚአብሄር ፈቃድ አኩዋያ ሆኖ የጸለየው ጸሎት የእኛን አካሄድ በእግዚአብሄር ፊት እያቀረበ እንደነበረ ግልጽ አድርጎታል፣ ለምን? እንደ ብርቅ የቆጠርናቸው የኛ ዘመኖች ከንቱ ነገር እንደተሞሉና የተናቁ እንደሆኑ አይቶ ነበርና፣ እድሜአችን እንደማይጸና በተረዳበት ስፍራ እርሱ ሲመስለው በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል አለ፣ ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል አለ፣ ፈጥኖ እንደሚጠፋና እንደሚረግፍ ሲያመለክት ጭምር፡፡
ዳዊት የአምላኩን የጸና ማንነት ባስተዋለበት አተያይ ውስጥ አንተ አትለወጥም ያው አንተ ነህ ብሎ እርሱ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው መሆኑን ያስታውሰናል። እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ መሆኑን ለማስታወስ ስለ ሰውነታችን ሞት እና ስለ ወዳጆች መወገድ ቃሉ ይናገራል። ምንም እንኳን ሁሉም ነገር ቢለወጥም፥ ቢሞትም፥ እንደሚጠፋም መጎናጸፊያ ተጠቅልሎ ወደ መበስበስ ቢቸኩል ሁሉን በቃሉ ደግፎ የያዘው ጌታ ግን ሕያው ነው፥ ስለዚህ ሁሉም ነገር እንደ እርሱ ፈቃድ የተጠበቀ ነው፣ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ በሕይወት ትኖራላችሁ ብሎአልና።
ሚል.3:5-6 ”ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።”
መዝ.93:1-5 ”እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ። አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።”
የምንኖረው ሳትጠፋና ሳትዛባ በቃሉ እንድትጸና በተደረገች አለም ውስጥ ነው፤ ቢሆንም አለም ስትኖር የሚያናውጡአት ክፋቶች ከእርስዋ ጠፍተው አይደለም፡፡ የሰው አእምሮ ምድርን በብዙ እጥፍ ሊያጠፋ የሚችል የጦር መሳሪያ ፈጥሮአል፡፡ ጦርነቶች ከቤተሰብ እስከ አገራት ድረስ በየእለቱ ይፈጸማሉ፡፡ ክፋት በክፋት ላይ ተደራርቦ የሰውን ልጅ አስጨንቆ ቢይዝም በእግዚአብሄር ምህረት የእግዚአብሄር መንፈስ ሁሉን በየስፍራው ተቆጣጥሮ ይዞአል፡፡ የከዋክብትና የጸሀይ ሀይላት ተናውጠው ምድር እንዳትጠፋ እግዚአብሄር ሁሉን አጸንቶ ጠብቆአል፡፡ በማያቁዋርጥ ሂደት ውስጥ ያሉ ፍጥረቶች ማብቂያ ቢኖራቸውም አካሄዳቸውን የሚቆጣጠር አምላክ አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁሉ አኩዋሃን ውስጥ የሚኖሩ የሰው ልጆች የማይናወጥ አምላክ እንዳለ ቢያስተውሉና በእርሱ ቢታመኑ እንደማይጠፉ እንዲያምኑ አስተማማኝ ቃል ይሰጣቸዋል፡፡
መዝ.102:23-28 ”በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ። በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው።”
ዘመናት ይቀያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ዘመናት በእግዚአብሄር የተፈጠሩ የጊዜ ርዝመት መለኪያ ናቸው፡፡ አለም ስትፈጠር በዘመናት መለኪያ ተሰፍራለች፡፡ እንዲሁም በአለም ውስጥ ያሉ ሁሉ ፍጥረታትም ቢሆኑ የዘመናት መለኪያው እድሜአቸውን ሰፍሮ አስቀምጦአል፡፡ ሆኖም ለእያንዳንዳችን የተሰጡ ዘመናት በውስጣቸው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ይዘዋል፡፡ ዘመናት ጅማሬም ፍጻሜም አላቸው፡፡ እንዲሁም ዘመናት በፍጥረት ላይ ተጽእኖ አላቸው፣ ተጽእኖአቸው ግን በፍጥረታት ላይ እንጂ በፈጣሪ ላይ አይሆንም፤ ስለዚህ የጊዜ ተጽእኖ እግዚአብሄርን ሊያስረጀው አይችልም፡፡ ደግሞም ዘመናትን በእኛ አንጻር ብናመዛዝን፣ በውስጣቸው በሚያልፈው የእግዚአብሄር ፈቃድም አንጻር ብንቆጥራቸው የእግዚአብሄር ክቡር አሳብ በእኛ ዘንድ ይከብራል፡፡
ዳን.2:20-21 ”ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ፡- ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።”
ጊዜያትንና ዘመናትን የሚለውጥ አምላክ በእኛ ዘመኖች ውስጥ የሚፈጽመውን ዘላለማዊ ፈቃድ ሲገልጥ አላማው የእኛን ህይወት በመቃኘት ዘመናቶቻችንን ወደ ዘላለማዊው የእግዚአብሄር ዘመናት ማሻገር ነው፡፡ አንድ ሰው ዘመንህን እግዚአብሄር ወስዶ የእርሱን ዘላለማዊነት ሊያወርስህ ፈቅዶአል ሲባል ምን ሊመልስ ይችላል? ይህ ሰው በነገሩ እውነታ
ማር.10:28-30 ”ጴጥሮስም፡- እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፡- እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”
ሁኔታዎች ይቃያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
የተወለደው ሊያድግ፣ ያደገው ሊጎለምስ፣ የጎለመሰው ሊያረጅ፣ ያረጀው ሊረግፍ አልተፈጠረምን? የነገሮች በጊዜ አንጻር መቀያየር በአንድ በኩል ጸንተው የማይቆዩ ነገሮች ሁሉ ዘላለማዊነት የሌላቸው መሆኑን ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል የፈጠራቸው እርሱ ያሳደጋቸው፣ እንዳሳደጋቸውም እርሱ ራሱ እንደሚሽራቸው አመልካች ነው፤ ያም ብቻ ሳይሆን እርሱ ከእነርሱ የላቀ ሆኖ የበላይና በፈቃዱ የሚያኖራቸው ዘላለማዊው አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን መስካሪ ነው፡፡
ዕብ.1:10-11 ”ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ”
ምድርና ሰማይ ይቀያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ሰማይና ምድር ምንም ግዙፍ ቢሆኑ፣ የፍጥረት ሁሉ መነሻ ቢሆኑና ምንም በነርሱ የእግዚአብሄር ፈቃድ የተፈጸመ ቢሆን እግዚአብሄር እነርሱን አንድ ቀን እንደ አረጀ እራፊ ቆጥሮ በአዲስ ሊለውጣቸው እቅድ እንዳለው ቃሉ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ሰማይና ምድር አመጸኞች መናፍስትንና የሰውን ልጅ አስተናግደዋልና ለቅዱሳን የተገቡ አልሆነም፤ ስለዚህ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ሊተኩ እግዚአብሄር ፈቃዱ ሆኖአል፡-
ራእ.21:1-8 ”አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። … በዙፋንም የተቀመጠው፦ እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። አለኝም፦ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ። ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።”
ህይወትና ሞት ይቀያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ (አንዱ አንዱን ይተካል/ያሸንፋል)
1ቆሮ.15:19-22 ”በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።”
የዘላለም አምላክ የሰውን ልጅ ከማይጠፋ ዘር ሲወልድ የሚጠፋው ጊዜያዊና አሮጌ ሰዋችንን ሽሮ አዲስና የማይጠፋ ለዘላለምም የሚኖር ሰው እንድንሆን በመፍጠር ነው፤ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን አሳብ በዚህ ምድር ብቻ የተወሰነ አድገው የሚቆጥሩ ግን ሁሉ ምስኪን አማኞች ናቸው፡፡
1ቆሮ.15:47-52 ”የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።”
ይህ አሮጌ አለም በአዲስ አለም ይለወጣል፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ራእ.21:3-5 ”ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው፦ እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”
ይህ አለም/ስርአት የሰቆቃና የጩሀት አለም ነው፣ ስጋት የተሞላበት፣ ፍርሀት የነገሰበት፣ እንባና ሀዘን ያለበት ነው፤ እግዚአብሄር ከዚህ ሰቆቃና ዋይታ ካለበት አለም ጋር ዘላለማዊ ቃልኪዳን አላደረገም፤ በእርግማን የተሞላ አለም በመሆኑ ጻድቃንን በመልካም ሊያኖር አልቻለም፡፡ ይህ አለም የእግዚአብሄር ጠላት ነው፣ የእግዚአብሄር ጠላቶች የሆኑ አመጸኞች የሚርመሰመሱበት አለምም ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህንን አለም ስላልወደደው ይቀይረዋል፤ ልጆቹን ለዘለአለም የሚያኖርበትን አዲስ አለም በሚመጡት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ውስጥ ሊፈጥርም ቃል ገብቶአል፡፡
2ጴጥ.3:10-12 ”የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል”