እግዚአብሄርን በማወቅና ባለማወቅ መሀል ያለው ልዩነት የሞትና የህይወት ያህል ዋጋ እንዳለው ጌታ ኢየሱስ በአጽንኦት ተናግሮአል፡፡ ጌታ በዮሐ.17:3 የተናገረው እንዲህ ይላል፡-
”እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”
በትንሹ ልባችን ስለርሱ ባወቅነው እውቀት ምክኒያት ያገኘነውን ታናሽ እምነት ይዘንና ወደ እርሱ ቀርበን አላፈርንም፤ እንዲያውም ከርሱ ጋር በምንኖርበት ዘመን ሁሉ ሳይነቅፈን አክብሮና ተሸክሞ አስጉዞናል፡፡ ይሁን እንጂ ጅማሬያችን ጥቂት ሆኖ አያስነቅፍ እንጂ ዘመናትን ከርሱ ጋር ተጉዘንም ባለን ኢምንት እምነት ላይ ተቸንክረን ከቀረንና ድንግዝግዝ ባለ መንገድ ውስጥ ከተፍገመገምን አይደሰትብንም፤ የሚያሻግር እውቀት አጥተን ወዲያ ወዲህ ስንል ለጠላት እንደምንጋለጥ ስለሚያውቅ ከተያዝንበት ጨለማ በቶሎ ወጥተን ብርሀን እንድናይ ይፈልጋል፡፡ በመንፈሳዊ ህይወታችን እንድንከሳ እርሱ ከቶ አይፈቅድም፤ ዘወትር ከእኛ እድገት ይጠብቃል፡፡
እግዚአብሄርን ማወቅ በሁሉም አቅጣጫ አስፈላጊ ቢሆንም እውቀታችን የሚሰፋው እግዚአብሄር እንዳበራልን መጠን ነው፤ እግዚአብሄር እንዲያበራልን ደግሞ ወደ እርሱ መጠጋት፣ መገኘቱ እስኪጎበኝም ፊቱን መፈለግ የተገባ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሊናገር ሲጣራ በአትኩሮት ወደ እርሱ መቅረብ ከምንም በላይ ዋጋ ያለው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምንም ነገር፣ በየትኛውም መንገድና ስፍራ ሊናገር ይችላል፣ ህያው ቃሉ በየትኛውም በኩል አልፎ ይመጣል፡፡ እርሱ የሁሉ ባለቤት አይደል ወይ? በምንም ነገር ቢናገርስ ቃሉ ከአፉ ይውጣ እንጂ ምን ያግደዋል፡፡
እግዚአብሄርን የሚያውቁ ባሪያዎች እባክህ ተናገረን ይላሉ፣ ይሉናም ይጠባበቃሉ፤ ስለ ፍጥረት፣ ስለስራው፣ ስለራሳቸው፣ ተጠግተውም ስለእርሱ ማንነት ይጠይቃሉ፣ እርሱም እንደፈቃዱ ለለመኑት ለእነርሱ በደስታ ይመልስላቸዋል፡፡ ከተነኩ በሁዋላ፣ ከበራላቸው በሁዋላ እንደ ቀድሞ እስካይሆኑ ድረስ እርሱን በማወቅ ማማ ላይ ጸንተው ይቆማሉ፡፡ ትውልድን የሚባርክ አምላክ በእውቀትና በእምነት ሲባርክ እንዲያ ያደርጋል፡፡ ንጉሱ ዳዊት አንደኛው ሰው ነበር፣ እርሱም በዚያ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሲናገር፡-
”ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል፤ እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፤ የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ፤ የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፤ አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ። በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ። በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” (መዝ.102:18-27)፡፡ ንጉሱ ራሱንና ፍጥረትን ባየበት አይን አምላኩን አላየም፡፡ ግን ለትውልድ መጻፍ የሚያስፈልጋቸው የእግዚአብሄር ስራዎች ተጽፈው የሚያስተውለው ትውልድም እንዲደሰትበት ሲመኝ እንመለከታለን፡፡ ትውልድ ያስተውል ካለው ውስጥ የሚከተለው ይገኛል፡-
ምድርና ሰማያት ይለወጣሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
አዎ እውነት ነው፣ እጅግ ታላላቅ ፍጥረታት ጸንተው በስፍራቸው ሆነው እያየናቸው ነው፤ ነገር ግን የፈጠራቸው ባለቤት ስላለ እርሱ ደግሞ ስለእነርሱ ያሰበው ነገር ስላለው ከነእርሱ መኖር በላይ የርሱ ፈቃድ በልጦ ተፈጸሚነትን እንዲያገኝ ማመን አለብን፡፡
”እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።” (ኢሳ.65:17-18)
እጅግ የገዘፉት እነዚህ ፍጥረታት አንድ ቀን መናወጣቸው እንደማይቀር ስናስተውል በፈጠራቸው ታላቅ አምላክ እንድንገረም ይሆናል፡፡ እግዚአብሄር ከእጆቹ ስራዎች ይልቅ ታላቅ ነው ሲባል የሚቀይራቸው እነርሱ ሆነው የማይቀየረው እርሱ ሰሪያቸውና ቀያሪያቸው ነው ማለት ነው፡፡ አይቀየርም ሲባል የተናገራቸው ድምጾች እንደማይናወጡ፣ እንደማይበገሩ፣ ዞር መለስ እንደማይሉ የሚያስረዳ ነው፡፡ እግዚአብሄር ዘመናት አይለወጡም፣ በዘመናት መሀል የሚገልጣቸው፣ አልፎም አስቀድሞ የተናገራቸው ተስፋዎች ሲሆኑና ሲፈጸሙ ይታያሉ እንጂ ከቃሉ ዝንፍ ሲሉ አንመለከትም፡፡
በኢሳ.51:6 ሲናገር፡-
”ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም።” ይላል፡፡
እግዚአብሄር ለውጣለሁ ያለውን በማይለወጥና በሚጸና ሊተካ፣ የሚጠፋውን ደግሞ በማይጠፋ ሊለውጥ እንደወሰነ በቃሉ ተናግሮአል፡፡ ዘመናት ነገሮችን ሲያስረጁ የማያረጅ አምላክ ሲያሳልፋቸው ኖሮአል፣ ይኖራልም፡፡ እርሱ ገና ሳይፈጠሩ በራሱ ዲዛይን ውስጥ አስገብቶአቸው ነበር፡፡ ከመፈጠራቸው በፊት ሁለንተናቸውን አይቶ መጀመሪያቸውን ብቻ ሳይሆን መጨረሻቸውን ተመልክቶአል፡፡ እርሱ የሚሰራቸው የሚጸኑት ጸንተው እንዲኖሩ የሚሻሩት ሊሻሩ ስራውን በዘመናት ውስጥ ይሰራል፡፡
ኢሳ.66:22 ”እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።”
በሐጌ.2:6-9 ላይ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሲናገር፡- አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ ይላል፡፡ ሰማይና ምድር በሚናወጡበት ወቅት አሕዛብ ሁሉ ይናወጣሉ፣ በምድር ላይ የተደረጉ ነገሮች ሁሉ ይሻራሉ፣ በሰማይ ውስጥ ያሉ ሰራዊቶች ይረግፋሉ፡፡ እግዚአብሄር መጽናት ያለባቸውን ሊተክል ይመጣል፣ ያኔ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠው ዕቃ ይመጣል፡፡
ዕብ.12:26-29 ”በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን፡- አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ዳሩ ግን፡- አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል። ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።”
ስለዚህ የሚናወጡትንና የሚጸኑትን ለይተን ያስተዋልን ሰዎች ልባችን በሚጠፋው ነገር ላይ እንዳይወድቅ፣ ዘላቂነት በሌለውና እግዚአብሄር ባላጸደቀው ነገር ላይም እንዳንደገፍ ያስፈልጋል፤ እንዲሁም የጸናውን የዘላለም አምላክ ልንታመንበትና ምርጫችን እርሱ እንዲሆን መወሰን ተገቢ ነው፡፡
ህይወትና ሞት ይቀያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
በህይወት ሂደት ውስጥ አንዱ አንዱን ይተካል፡- በህይወት ተሸናፊው ሞት በጊዜ ሂደት ይከሰትና ህይወትን ያሸንፋል፣ በሞት ላይ የበረታ የህይወት መንፈስ ይደክምና ለሞት እጅ ይሰጣል፡፡ የሞተው ከምድር ሲወገድ አዲስ የተወለደ ብቅ ይላል፣ ጊዜውን የጨረሰ ሲሸኝ አዲስ ባለ ጊዜ ብቅ ይላል፡፡ የጊዜ ፈጣሪም በዘመናት መሀል ስራውን ይገልጣል፡፡ የፈጠራቸውን ሁሉ በሰአታቸው ያመጣቸዋል፡፡ እነርሱን ሲለውጥ እርሱ ሳይለወጥ፣ እነርሱ ሲሄዱ እርሱ እነርሱን ሲሸኝ ይኖራል፣ የዘመናት አምላክ ሳይለወጥ ጸንቶ ይኖራል፡፡ እግዚአብሄርን ምትክ ሊሆነው የሚችል ማንም የለምና የማለወጥ ሆኖ ሌሎችን እንደለወጠ ለዘለአለም ይቀጥላል፡፡
መክ.12:1-7 ”የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፤ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፤ ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፤ የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፤ ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፤ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ፤ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፤ የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።”
ይህ አለምና ያኛው አለም ይቃያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ(አንዱ አንዱን ይተካልና)
”የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2ጴጥ.3:10-13)
ይህ አለም አልፎ ሌላ አዲስ አለም እንደሚመጣ እግዚአብሄር ቃል ገብቶአል፡፡ ይህች ምድር አንድ አለም የሚባል መናፍስትና የሰው ልጆች በእምነት፣ በልማድ፣ በአሳብ፣ በባህልና በመሳሰሉት ሂደቶች የተጋመዱበት ስርአት የሚኖርባት ስፍራ ናት፡፡ አለም የክፋት፣ የአመጽና የሀጢያት ቁዋት ነው፡፡ በአለም ያለ ነገር በሙሉ እግዚአብሄርን የሚያሳዝን በመሆኑ ጸንቶ የሚያቆይ ምክኒያት የለውም፡፡ በዚህ አለም ያለ የሰው ልጅ አሳብና እንቅስቃሴ ከጽድቅ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቃሉ በግልጽ የአለም ወዳጅ ሊሆን የሚሻ የእግዚአብሄር ጠላት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ይህን ውስብስብ ክፉ ስርአት አቅፋ የያዘች ምድር ዘላለም ትኖር ዘንድ ተገቢ አለመሆኑን የወሰነ አምላክ ከያዘችው አለም ጋር ትጠፋ ዘንድ ወስኖአል፡፡
ራእ.21:1-4 ”አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”
ምድር እንደተፈጠረችበት ቀን ጸንታ እንዳትኖር ምስኪኑ የሰው ልጅ በመተላለፉ ምክኒያት ተረግሞባት እርሱዋም እንድትረገም አድርጎአል፡፡ እርሱዋም የሰውን አመጽ፣ ግፍና በደል እያስተናገደች በመኖር ላይ ናት፡፡ ምድር እጅግ ብዙ ንጹሃን የሞቱባትና የፈሰሰውን ደማቸውን የጠጣች ፍጥረት ናት፡፡ ታዲያ በእግዚአብሄር ፊት ከአመጽ ልጆችዋ ጋር ጸንታ መቆም እንደምን ይቻላታል?
በምድር ያለው አለማዊ ስርአትም ቢሆን ህይወት ሳይሆን ሞት የሰለጠነበት ነው፤ አመጽና ሀጢያት በሚፈጠረው ኀዘን መጎሳቆል ያለበት፣ ፈተና፣ ጩኸትና ሥቃይም የጸናበት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ግን የሚያበቃበት አንድ ቀን ያለጥርጥር በአዲስ ሰማይና ምድር ስርአት መምጣት ይገለጣል፡፡
በአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ውስጥ እግዚአብሄር አዲስ ስርአት ይገልጣታል፡፡ ይህ አዲስ ስርአት አሁን በምድር ላይ እንዳለ በአመጽ የተሞላ፣ ከእግዚአብሄር ክልል እንደወጣውም አይነት አይደለም፡፡ በዚያ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ይሆናል፣ ከህዝቡም ጋር ያድራል፤ እነርሱም የሚያመልኩና የሚገዙ ሕዝቡ ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር በመሃከላቸው ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ ይህ አስደሳች አለም እጅግ ይናፍቃል፡፡
እግዚአብሄር ሳይለወጥ በዙሪያችን ያሉ ክስተቶች ይቀያየራሉ
የሁኔታዎች መለዋወጥ ምንን አመልካች ነው? በፍጥረታት ላይ የጸና ነገር እንደሌለ አመልካች አይደለምን? ታዲያ አለምን ያቀፈችው ምድርና ሰማያት ጭምር የሚለወጡ ከሆነ በውስጥዋ ያለው ጸንቶ እንዲኖር ለምን እንጠብቃለን፡፡ በሰው ዙርያ ያሉ ክስተቶችም ቁዋሚነት የላቸውም፣ በዘመናቸው ውስጥ ተለዋዋጮች ናቸው፡፡
ብርቱ አምላክ ሁሉን በጊዜ ይለዋውጣቸዋል፤ እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ስልጣን የላቸውምና ሊለውጡት አይቻላቸውም፡፡
መክ.3:1-9 ”ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ ለው፤ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው።ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው?” ይላል፡፡
ይህ ምን ማለት ነው? አሁን ደስ ያለው ቢኖር ደስታው ዘላቂ አይደለም፣ አሁን ተሳክቶለት የሞላለት ቢኖር ያስተውል የሚጸና ነገር የለምና መጉደልን ያስብ፣ እና ሌላም ሌላም፡፡ ነገር ግን መለወጥ የማያገኘው እግዚአብሄር ብቻ፣ ደግሞም የእግዚአብሄር የሆነው ብቻ!
ስለዚህ የማይናወጠውን መንግስት እናስብ፣ የማይለወጠውን ዘላለማዊ ልጅነትም እናስታውስ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖር እንደመላእክት የክብር ስፍራን ተቀብሎ በግልጥ እያዩት እያመለኩት መኖር! ይህ ነገር ቸል ሊባል ከቶ የማያስፈልግ ነው፡፡