አንተ ግን ያው አንተ ነህ (1…)

የመጨረሻ ዘመን

ንጉስ ዳዊት የህይወት ዘመኑ ወደ ማለቅ ቢፈጥንም የፈጠረው አምላክ ግን ያለመለወጥና ያለመናወጥ ጸንቶ እንደሚኖር እጅግ ያስተዋለ ሰው ነበረ፤ ስለዚህ እንዲህ ሲል በመዝ.102:11፣23-28 ውስጥ ተናገረ፡-
”ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው።… የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ። በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።”
የእግዚአብሄር ዘላለማዊነት የሰው ልጆች መጽናኛ ነው፤ ሰዎች እርሱ በዘመናቸው ሁሉ አብሮነቱ ከነርሱ ጋር እንደሆነ ሲረዱ እጅግ ይጽናናሉ፡፡ በተናገረው ቃል የሚታመኑት የማይለወጥ አምላክ እንዳለው ያደርጋል ሲሉ ነው፡፡
ሚል.3:6 ”እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።” ይላል፡፡
እግዚአብሄር ፍርዱን ስላዘገየ ተለወጠን? ለእኛ ያለው ፍቅርስ ተለውጦአልን? ፈጽሞ አይሆንም!
ፍጥረታት ይቀያየራሉ፣ በተለያየ ሁኔታና ምክኒያት መለዋወጥ ይኖራል፡፡ የተፈጥሮ ጫና ለውጥ በአካልና በቁምና ላይ ይንጸባረቃል፡፡ ሰዎች በእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ከተለያየ ነገር ጋር ይገናኛሉ፡፡ የሚገናኙት ነገር አንድ ለውጥ የሚያወጣ ሲሆን ለምሳሌ፡-ሀሳባቸውን ይቀይራል፣ ፈቃዳቸው ይቀይራል፣ እውቀታቸው ይቀየራል (እንደማስተዋላቸው እድገት መጠን)፣ የሰውነታቸው ይዘት ይቀያየራል፡፡ ሀሳብ በተሸለ አሳብ ይዋጥና የቀድሞ ይዘቱ ይቀየራል፣ ወይም ሀሳቡን የሚያስጥል ነገር የያዘውን እንዲተው ያስገድደዋል፡፡ፈቃድም እንዲሁ ነው፣ ልባችን ወደ ተያዘበት፣ ነፍሳችን ወደ ተማረከችበት አዘንብለን የምንፈቅደውን ነገር እንተዋለን፡፡እውቀታችን በሌላ እውቀት ይሻራል ወይም ይሻሻላል፣ ቀድመን ያላወቅነውን ስናገኝም የተለየ አቅጣጫ ውስጥ ሊያስገባን ይችላል፡፡
እግዚአብሄር ግን ያው እግዚአብሄር ነው፤ ሁኔታዎች እግዚአብሄርን አይለውጡትም፡፡ እውቀት ተቀባይ ስላልሆነ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው ነገር የለውም፤ እርሱን ተጭኖ ፈቃዱንስ ቢሆን ሊያስለውጥ ማን ይችላል? እኔ እግዚአብር አልለወጠም ብሎአል፡- ስለዚህ በእድሜ፣ በቁመና፣ በአስተሳሰብ አይቀየርም፣ ተለዋዋጭ ማንነት የለውም፡፡
አምላካችን ሆይ ቃልህ አይቀየርም፤ ስለዚህ የቱን ያህል ዘመን ይርዘም ቃል ኪዳንህ በወሰንከው ጊዜ ይፈጸማል፤ ፈቃዱ አይቀየርም፡- ሰዎች እንዲድኑ ያለው በጎ ፈቃድ አልተለወጠም፣ የተለወጠው ወላዋይ የሰው ልጅ ነው (ሰው እንደ ቃሉ አይገኝም፣ እንደተናገረውም አያደርግም)
ፍጥረታት በእግዚአብሄር እጅ የተፈጠሩ ናቸው፤ ፈጣሪያቸው እንደተፈጠሩ ባሉበት ይዘት ለዘለአለም እንዲኖሩ አልሰራቸውም፡፡ ፍጥረቶች ሲፈጠሩ ጊዜ ስለተመደበላቸው በተመደበላቸው ጊዜ ውስጥ ከርመው በመጨረሻ እድሜያቸው እንዲፈጸም የወሰነው ጉዳይ ነው፡፡ በጊዜ ይወለዳሉ፣ በጊዜ ውስጥ ያድጋሉ፣ ይጎለምሳሉ፣ ያረጃሉ፣ ጊዜያቸው ሲደርስ (የተወሰነው ማብቂያ ጊዜ ሲደርስ) ይሞታሉ፡፡
መዝ.102:25-28 ”አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።”
አንተ አትለወጥም፣ ያው አንተ ነህ ብሎ እርሱ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው መሆኑን ቃሉ ያስታውሰናል፡፡ እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ መሆኑን ለማስታወስ እኛ ዘላለማዊ እንዳልሆንን ማሰብ ስለ እኛም መለዋወጥ ማስተዋል በቂ ነው፤ በእኛ ላይ በሚታይ ለውጥ ምክኒያት ሰውነታችን ማደግ፣ መበርታት፣መድከምና መሞት በሚባሉ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል። ምንም እንኳን ፍጥረት ቢለወጥና፥ ቢሞትም፣ እንደሚጠፋ መጎናጸፊያ ተጠቅልሎ ወደ መበስበስ ቢቸኵልም ከዚህ ሂደት ውጪ ያለው ኢየሱስ ግን በነዚህ ሂደቶች ማለፍ ሳይጠበቅበት ሕያው መሆኑ ይታያል፡፡ ደግሞ ሁሉ በርሱ ፊት ሳይለወጥ የተጠበቀ ነው፡፡ እኛም ህያው በሆነ በእርሱ ስንጎበኝ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ በሕይወት ትኖራላችሁ ያለው ይፈጸምብናል።
የአይሁድ ህዝብ በግብጽ ባርነት ውስጥ ሳለ በአካል በመጎዳቱ፣ በስነልቦና በመሰለቡ፣ በሀብት ማጠት በመደህየቱ፣ በእምነትና በእውቀት እጦት በመድቀቁና በመጎዳቱ፣ በመጋዙና በመዛሉ ኃይሉ ሊበረታ ስነልቦናው ሊነቃቃና እምነቱ ሊጸና ስላልቻለ በመንገድ ላይ በብዙ አቅጣጫ ተዳከመ ዛለም፣ መጨረሻ እንዳወጣጡ ወደ ምድሩ ላይመለስ በፍጻሜው መንገድ ላይ ቀረ፡፡ ይህ ህዝብ በጉዞው ርዝማኔና አስቸጋሪነት ውስጥ በአምላኩ የማይለወጥ ማንነት ላይ እምነት ማጣት ይታይበት ነበር፡- በቃልኪዳኑ ላይ ጥርጣሬ ነበረው፤ ምግብ ያዘጋጅ ይሆን ብሎ ጥርጣሬ፣ ወዳሰበልን ያስገባን ይሆን ብሎ ጥርጣሬ፣ ከጠላት ያድነን ይሆን ሲልም ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ያ ጥርጣሬው በፈጠረበት ያለማመን ማጉረምረም ውስጥ ነበር፡፡ ያለማመኑ በስተመጨረሻ እንደተስፋው ቃል ወደ ከነአን ሳይገባ እንደ አወጣጡ በተስፋ ሳይሆን በውድቀት መንገድ ላይ እንዲቀር አድርጎታል፡፡
መዝ.90:1-17 ”…የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና።የቍጣህን ጽናት ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ።በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን።አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ስለ ባሪያዎችህም ተምዋገት።በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን።መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ ይለናል።ባሪያዎችህንና ሥራህን እይ፥ ልጆቻቸውንም ምራ። የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና።”
ንጉስ ዳዊት እግዚአብሄር (መዝ.90:1-17) በዘመናት ቁጥር የማይለዋወጥ አምላክ መሆኑን ከማሰላሰል ባለፈ ለጠፊውና ታናሹ ሰው ደጋፊ መሆኑን በማስተዋል አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን ይለዋል። ግዙፍ ተራሮች ሳይወለዱ በፊት የሚፈጥርበትን ጥበብ የገለጠውን እግዚአብሄር፣ ምድርና የቀሩት ዓለማት ሳይሠሩ አስቀድሞ ዘላለማዊነት ያለውን አምላክ በምስጋና ያስባል። እነዚህ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የተንጣለሉ ግኡዛን በዘላለሙ አምላክ መፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን ሳይዛነፉና ሳይወድቁ በቃሉ ተደግፈው መኖራቸው እያስደነቀው ለእነርሱ በአደረገው ስራ አይን ለሰው የሚኖረው ጥበቃው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ እየታየው ያመሰግናል፣ ምህረቱንም በማሰብ አንተ ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም ይላል፡፡ አዎ ይህ ታላቅ አምላክ ጥፋትን ስለማይሻ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ይላል፡፡
ሺህ ዓመት በዘላለሙ አምላክ ፊት ምን ያህል ናት? እርሱዋ በአምላክ ፊት እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ናት። ሰባና ሰማንያ አመት የሚኖር የሰው ልጅ በዘላለሙ ጊዜ ውስጥ ሲገባ ኢምንትነቱ ይገለጣልና የሰው ዘመኖቹ የተናቁ ናቸው ያሰኛል፡፡ ከጥቂትነቱና ከመርገፉ አንጻር ሲታይም በማለዳ እንደ ሣር የሚያልፍ፣ ማልዶ እንደሚያብብና ፈጥኖ እንደሚረግፍ (በሠርክ ጠውልጎና ደርቆ እንደሚወድቅ አበባ) ተመስሎአል፡፡
ሚል.3:5-6 ”ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።”
ትውልዶች በተነሱ ቁጥር ስለአምላካቸው ማንነት ከአባቶች ካልተማሩ አዲስ የተነሱ አማልክትን ይከተላሉ፡፡ ትላንተ የነበረው፣ ዛሬም ሆነ ለዘላለም ሳይለወጥ የሚኖረው ብቸኛ አምላክ ችላ ሲባል ብዙ አዲስ የበቀሉ ጌቶች ስፍራ ይዘው፣ ተፈርተው፣ ለሰይጣን አምልኮ መንገድ አመቻችተውም ትውልዱን በእርግማን እንዲታሰር ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሄር ከነሙሉ ክብሩ በዙፋኑ ላይ ገዢ ሆኖ፣ ብቸኛ አምላክ ሆኖ፣ የነገስታት ንጉስ፣ የጌቶች ጌታና የአማልክት አምላክ ሆኖ ይኖራል፡፡
መዝ.93:1-5 ”እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ። አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።”
በፍጥረት ታሪክ እንደ እግዚአብሄር ያለ ክብር ያለው ሌላ አምላክ የለም፣ እንደ አብረሀም አምላክ፣ እንደ ይስሀቅና እንደ ያእቆብ አምላክ ያለ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም መረገጫው የሆነ አምላክ የለም፡፡ አማልክት የተባሉ በሰው ልጆች ምናብ ምክኒያት ተፈጥረው የተቀረጹና ሰውን በአምልኮ የሚያረክሱ ጣኦታት ምድርን ይሙሉ እንጂ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ሊኖሩ አይችሉም፡፡ መጽሀፍ በኢሳ.46:6-10 ላይ እንደሚናገረው፡-
”ወርቁን ከኮረጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፥ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራ ዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል። በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፥ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።”
ዘመናት ይቀያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ዘመናት የተፈጠሩት ወደፊት እንዲቆጥሩ ነው፤ ወደፊት እየሄዱ የሰውን ዘመን ያጠነጥናሉ፤ የነገሮችን እድሜ ይቆጥራሉ፤ የእግዚአብሄርን ተስፋ ቃል ፍጻሜ ለመግለጥ ጊዜን ይለካሉ፡፡ ለሰው የሚቆጠር ዘመን ግን ለእግዚአብሄር መሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ዘመንን ለሰው ፈጥሮአልና፣ ለራሱ ሳይሆን ለፍጥረት አዘጋጅቶታልና፡፡
ዘፍ.1.14-18 ”እግዚአብሔርም አለ;- ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።”
ሁኔታዎች ይቃያየራሉ፣ አንተ ግን ያው አንተ ነህ
ትላንት ከትናንት ወዲያ የነበርንበት ሁኔታ ዛሬ ላይ ላይኖር ይችላል፡፡ በአለም ላይ ያለ ነገር ሁሉ በማያቁዋርጥ ለውጥ ውስጥ ነው፡፡ እግዚአብሄርና መንግስቱ ብቻ የጸኑ ናቸው፡፡ በዘላለም ውስጥ እንቀጥል ዘንድ ግን እግዚአብሄር እድል ሰጥቶናል፡፡
መክ.12:1-7 ”የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፤ ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፤ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፤ የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፤ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፤ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ፤ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፤የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።”
በእኛ ላይ በሚሆን ነገር ስሜታችንና ፍላጎታችን ይቀያየራል፣ ቢሆንም እግዚአብሄርን አንተ ግን ያው አንተ ነህ ማለት ይገባናል፡፡ ምክኒያቱም ማግኘነትና ማጣት፣ ደስታና ሀዘን፣ ድካምና ብርታት ወዘተ… እየተፈራረቁ ቢመጡ የሚቀያይሩት እኛን (ውስጣችንንና ውጫዊ አካላችንን) ነው፡፡ ተጽእኖ አድርጎ ነገሮችን መለወጥ የሚችል እሱ እንጂ እኛ ወይም ነገሮቻችን አይደሉም፤ ስዚህ ከራሳችን የአመለካከት ክልል ወጥተን፣ እምነታችንንና እይታችንን አስፍተን የእግዚአብሄርን ነገር ብናስተውል የሚጨመርልን የርሱ መለኮታዊ እውቀት አለ፡፡ በእርሱ እውቀት ወደ እምነት መቅረብ፣ በእምነትም በጎነቱን መቀበል ይሁንልን፡፡