አሮጌው ወይስ አዲሱ ሰው?[2/2]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ሰው ህያው የሆነ ነፍስና የሚረግፍ ስጋ ውህደት ነው።ህያው ነፍስ ከእግዚአብሄር እፍ ከተባለ የህይወት እስትንፋስ ስለተገኘች የምትጠፋ አይደለችም፣ ረቂቅና መንፈሳዊ ስለሆነች የመታየትም የመዳሰስም ችሎታ የላትም።ስጋ ግን የአፈር(ምድራዊ) ነው፣ ግኡዝ፣ የሚታይና የሚዳሰስ ጭምር።
ዘፍ.2:7 ይህን ያረጋግጥልናል፦
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።“
እውነታው እንደሚያሳየን የምድር አፈር ደቃቅ፣ አዋራ፣ የሚጨቀይ፣ የሚሟሟም፣ በተለየ ባህሪው የተለያዩ ማእድናት የተቀላቀሉበት የእግዚአብሄር ልዩ የፍጥረቱ ውጤት ነው።ከዚህ አፈር ብዙ ህያዋን ወጥተዋል፦አራዊት፣ ሳሮች፣ ዛፍና አታክልት፣ በመጨረሻም ሰው። በአፈር ላይ የእግዚአብሄር ጥበብ ተገልጦ የተለያዩ ነገሮች ከርሱ ስለወጡ በዚያ ስራ የፈጣሪያችን ኤልሻዳይነት ታይቶአል።ከዚህ ድንቅ አፈጣጠር ውስጥ የሰውን ለየት የሚያደርገው በፈጠረው የሰው አካል ላይ ተጨማሪ ጥበብ ተገልጦ ስለሚታይ ነው። ይኅውም የአምላክ እስትንፋስ ከአፈር ከተበጀው ሰው ውስጥ መግባቱ ነው።
የተፈጠረው ሰው መለኮታዊ ባህሪ ስለተካፈለ እንደ አምላኩ የማሰብ፣ የማስተዋል፣ የመነጋገር፣ የመግባባትና ከርሱ ጋር የመፈላለግ ዝንባሌ አለው። የትኛውም ግኡዝ ፍጥረት ይህን ሊያደርግ የተሰጠ ችሎታ የለውም፣ የአምላክን እስትንፋስ አልተካፈለምና።ያን አድርጎም ፈጣሪ በልዩ ጥበብ የሰራውን ሰው ሊፈልግ ሁልጊዜ ወደርሱ መምጣትን አላቁዋረጠም።በሚያደርገው ነገር ታላቁ አምላክ ሰውን ሲያሳትፈው ስናይ እግዚአብሄር በእስትንፋሱ ህያው ላደረገ ነፍስ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠ እናስተውላለን።
በሰው በኩል ያለው የልብ ዝግጅት ግን እጅግ ደካማ ነው። ምክኒያቱም በእግዚአብሄር በኩል የነበረውን ጥብቅ ወዳጅነት ሰው በማላላቱ የሰውና የእግዚአብሄር ግንኙነት በቶሎ ሊቆረጥ እንደቻለ በግልጽ ይታያል።እግዚአብሄር ግን የሰው ልጅ ያለያየነውን የግንኙነት መስመር ሊቀጥል ወሰነ፦
ኤፌ2:5 “ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥“ ተብሎ እንደተጻፈ።
እግዚአብሄርን በድለን ፍቅሩን በማጉደላችን ሞት ተከትሎ ቤታችን ገብቶ ነበር።ያ የሞት መርገም ህያው ሰው ተብለን በክብር እንዳንመላለስ ሙታን አድርጎናል፣ ለዘላለም ጥፋትም አሳልፎ ሰጥቶናል።የእግዚአብሄር ምህረት ግን ጨርሶ ስላልተቆረጠ በእርሱ ችሎታ አዲስ የግንኙነት መስመር ተከፍቶአል።
ኤፌ2:3-5 ”በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥”
በዚህ አለም የስጋ ህይወት ነፍስና ስጋ ተዋህደው ያሉበትን ይዘት ሲያመለክት የስጋ ሞት ደግሞ የስጋና የነፍስን መለያየት ያሳያል፡፡የእግዚአብሄር ቃል በምድር በህይወት እያለን ሙታን ብሎ ሲጠራን ግን ከእግዚአብሄር ጋር መንፈሳችን መገናኘት እንደማይችልና ሁለተኛው ዘላለማዊ ሞት ፍርድ እንደሰለጠነብን አመልካች ነው፡፡ሆኖም እግዚአብሄር ከሙት የህይወት ይዘት በርሱ መንፈስ ህያው ወደ መሆን ሲለውጠን በአዲስ የግንኙነት መስመር ከርሱ ጋር እንድንኖር አቅዶ ነው፡፡ይህ አዲሱ ኑሮ ከዚህ አለም የኑሮ ዘይቤ የተለየ፣ እቅድና ግቡ ከዚህ ምድር ያልሆነ ነው፡፡ አዲሱ ማንነት መንፈሳዊ ህይወት ያለው፣ በማይሞተው ነፍስ ላይ ትኩረት ያደረገና ዘላለማዊ መንግስትን ያማከለ ነው፡፡ አሮጌው ሰው የአሮጌ አስተሳሰብ ጉዋዳ፣ የሥጋችንና የልቡናችን ፈቃድ ታዛዥና አድራጊ እንዲሁም በሥጋችን ምኞት እንድኖር የሚመራን ስብእና ነው፡፡”ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን” ሲልም በአሮጌው ሰው ውስጥ ያለች ነፍስ ከታሰረችበት የዘላለም ሞት በእግዚአብሄር አሰራር ተፈትታ አዲስ ህይወት የተባለውን የክርስቶስ ህይወትን እንድታገኝ እግዚአብሄር እንዳስቻላት ያመለክታል፡፡ቃሉ አጽንኦት ሰጥቶም የሁለቱ ሰዎች ማንነት ላይገናኝ እንደተለያየ ይናገራል፡፡ ሁለቱን ሲለያቸውም የሚበሰብስና የማይበሰብስ ብሎ ነው፡፡
1ቆሮ.15:50 “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፡- ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።“
ቃሉ ከአፈር የተበጀው ስጋና ደም ዘላለማዊውን መንግስት ሊወርስ እንደማይችል የተናገረው እግዚአብሄር አንድ አዲስ ዘላለም መኖር የሚችል ስጋና ደም ነፍሳችን ልትለብስ እንዳላት ሲያመለክተን ነው፡፡
2ቆሮ.5:1-3 ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።
ቃሉ በጠንካራ ንግግር ለያይቶ ያስቀምጣል፣ ክብር የጎደለው ሰጋችን የሚበሰብስና ፈርሶ ወደ አዋራነት የሚለወጥ ፍጥረት መሆኑን።ይህ ስጋችን ሰማያዊውን ክብር ሊሸከም ስለማይችል በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ቦታ እንደሌለውም ግልጽ ነው። የሚሞተው ሰውነታችን በሰማያዊው ስፍራ ውስጥ ከነብዙ ድካሙ ሊኖር አይችልምና። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ሲባል ምድራዊ ፈቃድ ያለው ደካማው የሰው ልጅ ከነአሳቡ፣ ፍላጎቱና ማንነቱ ጋር ሰማያዊ ፈቃድ ካለው የእግዚአብሄር ከተማ ውስጥ ሊገኝ አልተፈቀደለትም ማለት ነው።
ዛሬ ማንነታችንን የሚለውጥ አምላክ ነገ ስጋና ደማችንን ይለውጣል። ይህም እግዚአብሄር እንደሚሰራበት አሰራር ይፈጸማል።
ፊል3:21 “እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።“
የቤት ለውጥ፡- ከፈራሽ ቤታችን ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እንድንገባ ሲደረግ ቤት እንለውጣለን።መቀየር የሚያስፈልገው ጊዜያዊ ቤት አላቂ ስለሆነ ተቀያሪ ያስፈልገዋል።በእግዚአብሄር እቅድ መሰረት ግን ተቀያሪው ስጋችን እንደቀድሞው ጊዜያዊ እንዲሆን እግዚአብሄር አልፈቀደም።የነፍስ ማደርያ ቤታችንን የሰራ አምላክ ከመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው ቤት ሊያዘዋውረን ነው ቃልኪዳኑ። ፈራሽ ቤታችን የተዋረደው ስጋ ነው።የማይፈርሰው ዘላለማዊ ቤት የክርስቶስ ስጋ ነው።በሃጢያት የተበከለ ስጋችን ደካማ፣ ክብር የሌለው፣ ሟችና ፈራሽ ነው። ቀድሞ ከተበጀበት የሚመለሰው ስጋችን ወደ ወጣበት አፈር የሚቀላቀል በመሆኑ ሰማያዊ ክብርን ሊያገኝ አይችልም።ከአፈር የተሰራው ሰውነት ወደወጣበት ከተመለሰ ተስፋ አድርጎ የሚጠብቀው ሰማያዊ ክብር አይኖርም።ሟች ስጋ ትንሳኤን የሚያገኝ ሳይሆን ተጥሎ ለሌላ ሰውነት ስፍራ የሚለቅ ነው።
መንፈሳዊ የሆነው ውስጣዊ ሰውነታችን ግን የሚጠብቀው ታላቅ ተስፋ አለ። እርሱም ጊዜያዊ ከሆነው ድንኩዋን መውጣትና ዘላለማዊ ወደ ሆነው ሰውነት ውስጥ መግባት ነው። ይህም ከጌታ ኢየሱስ የሚሰጥ ነው።
1ዮሐ.3:2 “ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።“
የእግዚአብሄር ልጆች በዳግም ልደት ልጅነትን ያገኙ ናቸው። ልጅነት ከእግዚአብሄር የጸጋ መንፈስና ደህንነትን ያስገኛል።የክብር ህይወት ያለበት ከሰማይ ጋር የሚገናኝ ማንነት ሁልጊዜ በእምነት የለበሰውን ክርስቶስን ይመስል ዘንድ እጅግ ይናፍቃል። የእግዚአብሄር ልጆች በእምነት ይሄዳሉ፣ በተስፋም ይኖራሉ።የጌታ የመምጣቱ ተስፋም እርግጥ ነው።
• እግዚአብሄር የማይጠፋ ዘር በውስጣችን ዘርቶአል። ይህ ዘር በውስጣችን የሚኖር ነው።በርሱም እግዚአብሄር በወሰነው ቀን ሰማያዊ አካል ይሰጠናል።
1ጴጥ.2:11 “ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ“
ውስጣዊ ሰውነት የሆነው ነፍስ ውጫዊ ሰውነት ከሆነው ስጋችን ሁሌም ብርቱ ትግል አለው። ሁለቱ በፍላጎት ይቃረናሉ ማለት ነው። እያንዳንዳቸው በየዝንባሌያቸው በሚያደርጉት ጉዞ በተቃራኒ አቅጣጫ መጓዝና መሳሳብ ይፈጥራሉ። በዚህ ምክኒያት አንዱ ለሌላው ባላንጣ ይሆናል። የስጋ ምኞትንና የመንፈስ አሳብን ማስታረቅ አይቻልም። በአንድ አካል ሆኖ መለያየት እስከሌለም በአብሮነት ለመኖር የግድ አንዱ ሌላው ላይ ሊሰለጥን ግዴታ ነው።
1ጴጥ.1:23-25 “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።“
በመጀመሪያ የተወለድነው ከሚጠፋ ዘር ነበር። ይህ ዘር የመጀመሪያው አዳም ነው። አዳም እንደ ሳር ጠውልጎ ማለት አርጅቶ የሚረግፍ ወይም ወደ አፈርነት የሚለወጥ ስጋ ለብሶ ነው ህያው ነፍስ የተባለው።
ሁለተኛ የተወለድነው ከማይጠፋ ዘር ከእግዚአብሄር ቃል ነው። እኔ የምትል ነፍስ አስቀድማ የሚጠፋውን ዘር ለብሳለች። በዳግም ልደት ግን የማይጥፋው ክርስቶስን፡፡
ዳግም በተወለዱና በተፈጠሮአዊ የሰው ሁለንተና ውስጥ የሚከተሉት ነገሮች ይታያሉ፡-
• ነፍስ ውስጣዊ ህይወታችንን የሚያመለክት ነው።
• አዲሱ ሰው ከማይጠፋ ዘር ስለተወለደ የክርስቶስ ማንነት ያለው ነው።
• አዲሱ ሰውነት በአዲሱ ሰው ውስጥ አለ።
• ለዘላለም የምንለብሰው ሰማያዊ አካል በእግዚአብሄር የታነጸ ዘላለማዊ መኖርያ ተብሎአል።
• ከአሮጌው ሰውነት ወደ አዲሱ ሰውነት የምንለወጠው ማንነታችን በመለወጡ ነው። ነገር ግን ስጋና ደማችን ሌላ አይነት ህይወት ይዞ እንዲኖር አይለወጥም፣ በስባሽ ነው፣ ፈራሽ ነው፣የሚከስም ነው።
• ስጋችን ደካማና ፈራሽ በመሆኑ እንደ ጊዜያዊ ድንኩዋን ይቆጠራል።
• ደካማ በመሆኑ በቀላሉ በበሽታ ይጠቃል፣ በሞት ከነፍስ ሲለይ በጥቂት ሰአታት ይፈርሳል፣ይሸታል።
• ከዚህ ጊዜያዊ ድንኩዋን የምንለየው የስጋ እድሜ ሲፈጸም/ስጋችን ከነፍሳችን ስትለይ ነው።
• በዚህ ድንኩዋን ውስጥ ስንኖር ከጌታ ርቀን እየኖርን መሆኑን እናውቃለን።ከድንኩዋን ስንወጣ ከጌታ ጋር መኖር እንጀምራለን።
• አሮጌው ሰውነት በአሮጌው ሰው ውስጥ አለ።
• የአሮጌው ሰው ማንነትም አሮጌው ሰውነት ውስጥ አለ።
• አሮጌው ሰው ከአዳም የተወረሰ ሃጢያት ያለበት ተፈጥሮ ነው።
• አሮጌው ሰውነታችን የሚያመለክተው ስጋና ደማችንን ብቻ ሳይሆን የያዘውን ማንነታችንም ነው።
1ቆሮ.15:47-50 ”የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው።የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።”