ሮሜ.8:5-12 ስለ እኛ ስለ ሰዎች ሲናገር፦
“እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም።“ ይላል።
ነገር ግን ከሩቅ የምናይ ምናልባት “ድሮስ ቢሆን እኛ ስጋ እንጂ መንፍስ አይደለን“ የሚል ጠንከር ያለ አቁዋም ልናሳይ እንችላለን።ግዴለም ስጋ ለባሽ መሆናችንን እንቀበል፣ግን መንፈስም አለን። ደግሞ ትክክለኛው እኛነታችን ውስጣችን እንጂ ከውጪ የደረብነው ስጋ አይደለምና በእርግጥ ከተነጋገርን አይቀር ስለ ትክክለኛው እኛነታችን እየመረመርን ሊሆን ይገባል።
መኖር የሚባለው ዘላቂ ህይወት ትርጉሙ የሚታወቀው ውስጣችን የምንለው እኛነታችን በትክክል ሲገለጥልን ነው።በተመሳሳይ ትክክለኛው ማንነታችን ውስጣችን ያለው የማይዳሰሰው ክፍላችን መሆኑን መቀበል ብቻ ሳይሆን ስለራሳችን ስናወራም ሆነ ስናስብ እርግጠኛ በሆነ መንገድ ቃሉን ተመርኩዘን መሆን አለበት። እኛነታችን ውጫዊና ውስጣዊ ይዘት እንዳለው እንደቃሉ ስንረዳ “የሥጋ ፈቃድ፣የሥጋ ነገር፣የመንፈስ ፈቃድ፣ የመንፈስ ነገር፣ስለ ሥጋ ማሰብ፣ ሞት፣ ስለ መንፈስ ማሰብ እንዲሁም ሕይወትና ሰላም“ የሚባሉትን ከላይ በቃሉ ውስጥ ያየናቸውን መንፈሳዊ ነገሮች በጥልቅ መረዳት እንችላለን።
የአፈጣጠራችንን ሁኔታ በተመለከተ ሙሉ ተደርገን ስለመፈጠራችን በ1ተሰ.5:23 ውስጥ ተመልክቶአል፦
“የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳቹሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።“
የተፈጠርነው በአላማ መሆኑን የምናስተውለው ሙሉ በተባለው እኛነታችን ውስጥ የተካተተው ክፍል ተጠቃልሎ ነቀፋ በሌለው የህይወት ይዘት መጠበቅ እንዳለበት ስናስተውል ነው።እያንዳንዱን ክፍላችን (መንፈሳችሁ ነፍሳችሁ ሥጋችሁም የተባለው በሙሉ) በእግዚአብሄር መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሄር ወደ ወጣበት እንደሚሸኝ ማስተዋል ይገባል።ለምሳሌ በመክ.12:7 ውስጥ እንዲህ ይላል፦
“አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።“
ነፍስ ከአንድ ምንጭ ስጋ ከሌላ ስፍራ ወጥተው ተጣመሩና ሙሉ ሰው ሆንን።ይህ ያስደንቃል። ፍጻሜ ላይ ግን ሁለቱም ወደ መጡበት አድራሻ የመመለሳቸው ሁኔታ ይፈጠራል።አመጣጣቸው ላይ የሰው ተጽኖ እንዳልነበረ ሁሉ መለያያቸው ላይም የመወሰን ስልጣን ሰው ዘንድ ሊኖር አይችልም።ይሄም አስደናቂ ነገር ነው።
ዕብ.4:12 “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል“
የራሴ ያልነውን የአካል ክፍል እንመልከት፣ የፈጠረን አምላክ ብቻ አንዱን ከአንዱ አጣብቆና አዋህዶ አስቀመጦአቸዋል። እንዲሁም እርሱ አንድ በአንድ በጥልቀት ሊመለከታቸው ይችላል።ነፍስና መንፈስ፣ጅማትና ቅልጥም፣ እንዲሁም የልብ ስሜትና አሳብ ተጣብቀው በውስጣችን ተቀምጠዋል፣ግን እንዴት በውስጣችን ተጣምረው እንዳሉ እኛ ባለቤቶቹ ራሳችን አናውቅም።ቆዳ ስር ተሰውረዋል ጥበበኛው አምላክ ግን ስውር ቢሆኑም ይመለከታቸዋል፣ የተጣበቁበትን ረቂቅ መስመር ሳይቀር ለይቶም ሊከፍላቸው ይችላል።
የሰውነትን ሁኔታ ወደ ማየት ስንመለስም፦ ከላይ ያየናቸው ጥቅሶች ሰው ሁለት ሰውነት እንዳለው ያመለክታሉ።
• አንደኛው ውስጣዊ ሰውነት ነው።ውስጣዊ ሰውነት ነፍስና መንፈሳችን ነው።
ኤፌ3:16-17 “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥“ ይላል።
ውስጣዊ ሰውነት የመንፈሳዊ ህይወት መሰረት ነው።አካላዊ ግንኙነት የማይደርስበት እንቅስቃሴ በውስጥ ሰውነት አማካይነት ይከናወናል።እኛ ሰዎች መንፈስ የሆነውን አምላክ የምንገናኘው በውሥጡ ሰውነታችን በኩል ሲሆን የአቀራረባችን ልክ የሚለካው ከርሱ ጋር ባለን መንፈሳዊ ግንኙነት ነው።ስጋዊ አካላችን እንደሚሰማው ያለ ስሜት ውስጣችን ላይሰማው ይችላል።ስጋችን ላይ የሚኖረው የስሜት ሁኔታ በመንፈሳዊው ሰውነታችን ላይ አይኖርምና።ሆኖም ያለክርስቶስ የሆነ ህይወት ውስጥ እስካለን ድረስ ውስጣችን በውጫዊው ሰውነታችን ፈቃድ፣ፍላጎትና ስሜት ተጽእኖ ስር ይኖራል።እንደዚያ ሲሆን መንፈሳችን በስጋዊ ፈቃዳችን ስር ይወድቃል ማለት ነው።
እግዚአብሄር ወደ እኛ የሚቀርበው በውስጣዊ ሰውነታችን በኩል ነው። እኛም ከርሱ ጋር የታረቀ ህይወት የሚኖረን የርሱን ጸጋ በቅዱስ መንፈሱ አማካይነት ስንቀበል ነው።አዲሱ ሰው በመንፈስ ቅዱስ የታደሰ ውስጣዊ ሰውነታችን ሲሆን ክርስቶስን በአዲስ ልደት የለበሰ ነው።ክርስቶስን በተስፋ የለበሰው ውስጣዊ ማንነታችን ደግሞ የክርስቶስን ባህሪይ በመለማመድ እስከጊዜው ከርሱ ጋር በሚቆየው ውጫዊ ሰውነት ላይ ተጽእኖውን ያሳርፋል።
ውስጣዊ ሰውነትን የሚያጠነክር ሃይል የእግዚአብሄር መንፈስ ነው።ሃይል የተሞላ ውስጣዊ ሰውነት ደግሞ የሚያድገው በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ነው።መለኮታዊ ባህሪዎችን ከክርስቶስ ተቀብለን መኖር የምንችልበትን ችሎታ የመንፈስ ሃይል ያጎናጽፈናል። ስጦታው ከእግዚአብሄር በነጻ የሆነልን ጸጋው ነው።የውስጥ ሰውነት እለት እለት በጸጋው መታደስ ያስፈልገዋል።ይህንም እግዚአብሄር በመንፈሱ ያደርገዋል።
• ውጫዊው ሰውነት ስጋና ደም ነው።የሚሞት ሰውነት ተብሎ ተጠርቶአል።
ቆላ.2:11-14 “የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ።በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።“
የአብረሃም ግርዛት ሸለፈትን ብቻ የሚያስወግድ ነበረ።ክርስቶስ ግን ሲገርዝ ስጋንና ፈቃዱን በሙሉ ከነፍስ ላይ በመግፈፍ ነው።አብረሃም የቁልፈቱን ስጋ ከእርሱና ከልጆቹ አስወገደ።ጌታ ኢየሱስ ግን ስጋችንን እንደ አሮጌ ልብስ በጥምቀት አሰራር በእምነት ገፈፈው።በአብረሃም ግርዘት ስጋችንን ባለመገረዛችን ከአብረሃም ተስፋ ተለይተን በደላችን ገድሎን ነበር።ይህን ሁሉ ታሪክ ግን ጌታ ወደ እኛ መጥቶ ቀየረው! ስጋችን ላይ የሃጢያት እዳ ጽህፈት ታትሞ ስለነበረ እግዚአብሄር ያን ዳግመኛ በእኛ ላይ ላይመለከት በደሙ አስወገደው።አስወግዶም ራቁታችንን እንዳንሆን ክርስቶስን በእምነት አለበሰን።ዛሬ በዚህ ስጋችን ብንኖርም አሮጌ ማንነታችንን ግን ገፍፎአል፣የመለኮት ባህሪም ተካፋይ ሆነናል።ነገ እርሱ እንዳለው ሲመጣ የሚበሰብሰው ስጋችንን ገፍፎ እስከመጨሻው ያስወግደዋል፣የርሱን ክቡር ስጋ አልብሶ እርሱን እንድንመስልም ተስፋ ገብቶአል።መጨረሻችን እንዲህ ባለ ክብር እውን ይሆናል።
የስጋን ሰውነት አፈጣጠር እንመልከት፦በአጥንት መዋቅር ላይ ተቀናጅቶ የተቀመጠው እርሱ በእግዚአብሄር ጥበብ ከአፈር የተበጀ አካል ሲሆን ውስጡ ባለው የህይወት እስትንፋስ ምክኒያት ህያው ሆኖ የሚንቀሳቀስ ነው።ስጋችን እንደ አንጎልና ልብ ያሉ ወሳኝ ብልቶችን የያዘ አካል ነው።እነዚህ ብልቶች የውስጥ ሰውነት ዋና መስሪያ ቤት ሆነው ያገለግላሉ። ህይወት በደም ውስጥ ተቅምጦ ይኖራል።ነፍስም የስጋ ህይወት ናት።
ስጋ ከግኡዙ አለም ጋር መንፈስ ከመንፈሳዊው አለም ጋር ሰውን ያገናኙታል።ሰው ከፍጥረት ሁሉ በተለየ በአንድ ጊዜ ሁለቱን አለማት መገናኘት እንዲችል ተደርጎ በግዚአብሄር የተፈጠረ ልዩ ፍጡር ነው። በስጋው ከዚህ አለም ጋር፣በመንፈሱ ከዚያኛው አለም ጋር ይወዳጃል፣ይህም ድንቅ ነው።
“ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።“ 1ቆሮ.15:50