ክርስቶስ ኢየሱስ በመልከጼዴቅ ምሳሌነት ብዙ ባህሪውንና ተልእኮውን ለአለም ገልጦአል፡፡ የሚከተሉት ነጥቦች ይህንን እውነት የሚያሳዩ ናቸው፡-
• የዘር ሀረግ አልነበረውም
ክርስቶስ ባህሪም ሆነ የዘር ሀረግ ከሰብአዊ አባትና እናት አልወረሰም፣ ስለዚህ ምድራዊ ጅማሬም ማለቂያም የለውም፡፡ የክርስቶስን ምድዊ የዘር ሀረግ መቀጣጠል የተሳናቸው እስራኤላውያን የዮሴፍንና የማርያምን የዘር ሀረግ እየሳቡ ከርሱ ጋር ሊያስጠጉ ሞክረዋል፡፡ቃሉ ግን እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው ይላል(ራእ.1:8)፤ ስለዚህ ሰብአዊ የዘር ሀረግ ከአልፋ ሊነሳ ኦሜጋ ላይ ሊያርፍ አይችልም (ከኤደን ገነት ተነስቶ እስከ አለም ፍጻሜ ብቻ ቢጉዋዝ ነው እንጂ)፤ እንዲያ የርሱን ባህሪ ከዚህ አለም የዘር ቆጠራ አሻግረን ማየት ይበጃል፡፡ ያን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ለማመልከት ሲባል የመልከ ጼድቅ የህይወት ታሪክ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አልተተረከም፡፡ የሰው ልጆች አመጣጥ በሚተርከው የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል (ዘፍ.14) ውስጥ ስለ መልከ ጼዴቅ ማንነት፣ ቤተሰብ፣ የዘር ሀረግ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ምክኒያቱም የእግዚአብሄር ፈቃድ የክርስቶስን ምንጭ በርሱ በኩል ማሳየት ስለፈለገ ከሰብአዊ የዘር ሀረግ ውስጥ መልከ ጼዴቅን አውጥቶት ነበር፡፡
መልከ ጼዴቅ መች ተወለደ፣ የት ተወለደ፣ ማን ወለደው፣ ቤተሰቡስ? ማንም ምንም ስለርሱ ሊናገር የሚችል የለም፡፡ ይህን ያስተዋለ ክርስቶስ ከምድር እንዳልሆነ በመልከ ጼዴቅ በኩል ተነግሮት ነበር ማለት ነው፡፡
በዕብ.7:3 ውስጥ ”አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል” ይላል፡፡
አዳም አባቱ አይደለም (ዮሴፍም)፣ ሄዋን እናቱ አይደለችም (ማርያምም)፡፡ ያ ማለት የህይወቱ መነሻ በእናቱ ማህጸን አልጀመረም፣ በእግዚአብሄር ውስጥ የነበረ ህያው ቃል ነበርና፤ ከእግዚአብሄር ውስጥ ወጥቶ በማርያም ማህጸር ውስጥ ሰው ሆኖ ተቀይሮአል፣ አድጎአልም፤ ቃል ስጋ ሆነ እንደተባለ፡፡ በግልጽ አነጋገር የክርስቶስ ምንጭ የወንድ ወገብ ሳይሆን መንፈስ የሆነ እግዚአብሄር ነው፡፡
1ቆሮ.15:45-47” እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።”
• አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም
ክርስቶስ ምድራዊ እናትና አባት በእውነት እንደሌሉት እናስተውል ዘንድ መልከ ጼዴቅ የትውልድ ቁጥሩ ከመጽሀፍ ውጪ ሆኖአል፡፡ ትውልድ ከሌለው ወደ ሁዋላ ዞረን መፈለግ የምንችለው ሰብአዊ አባትና እናት አናገኝም፡፡ ለምሳሌ የኢየሱስ ወላጅ አባት ጸራቢው ዮሴፍ ነው ብለው አይሁድ ያምኑ ነበር፤ ግን በሁለቱ መሀል የሚያገናኝ የዘር ሀረግ የለም፡፡ ክርስቶስ በማርያም ማህጸን ውስጥ ሲረገዝ ማርያም ድንግል ነበረች (ከእጮኛዋ ጋር ሳትገናኝና የዮሴፍን ዘር ሳትቀበል እንዲሁ ድንገት አርግዛ ተገኘች)፡፡ እስራኤላውያን በክርስቶስ ስራና ትምህርት ሲገረሙ የማን ነው ልጅ ሲሉ ይጨነቃሉ፣ ይጠይቃሉ፡፡ጭንቀታቸው ስለሚገባው ጌታ ሁሌም መልሱ ግልጽ ነበር፡፡
ዮሐ.8:38-43 ”…እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።
መልሰውም፡- አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም፡- የአብረሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት። ኢየሱስም አላቸው፡- እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው።”
የጌታ ኢየሱስ ንግግር ላመነው ግልጽ ነው፡- ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ (ከውስጡ በራሱ ፈቃድ አውጥቶ/ወልዶ በምድር ላይ እንድገለጥ አደረገ) እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና ሲል አሳሰበ። ማርያም ልጅ ከአብራኩዋ ከፍላ ለአይሁድ ያበረከተች ሳይሆን ከእግዚአብሄር ወጥቶ ልጅ የሆነ ቃልን በማህጸንዋ ተሸክማለች፣ የእግዚአብሄር አላማ ስለነበረ፡፡
ገላ.4:4 ”…ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።”
እግዚአብሄር ክርስቶስን እንደወለደው በቀጥታ በአለም ላይ ሊገልጠው ይሳነው ነበር ወይ? (ለእግዚአብሄር ግን የሚሳነው የለም እንጂ)፡- ከዚያ ይልቅ አንድ ጥልቅ ምስጢር ያሳይ ዘንድ ነበረው፡፡ እርሱንም ቃሉ ሲናገር፡- እግዚአብሔር ልጁ ከሴት እንዲወለድ የፈለገው ከሕግ በታች ሆኖ እንዲወለድ፣ ለሰው ልጅ መከራ ተቀብሎ ከሕግ በታች ያለነውን ሰው የተባልን ፍጥረቶች በሙሉ ይዋጅ ዘንድና የእግዚአብሄር ልጆች ያደርግ ዘንድ ነው፡፡
• ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም
ራእ.1:17-18 ”ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።”
እግዚአብሄር ራሱን ከእኛ የጊዜ መለኪያ ሊያወጣ ሲወድድ በሚገባን ቁዋንቁዋ ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ ይላል፡፡ የሰው ልጅ ቀን መቁጠር የሚችለው እየኖረበት ካለው ጊዘ አንጻር መሆኑ ይታወቃል፣ ያለፈውማ ትዝታ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ እድሜ ከተወለደበት ቅጽበት አንስቶ እስከ እስትንፋሱ ፍጻሜ ድረስ ወደፊት እየተቆጠረ ይሄዳል፣ ዘመኑ እንዲያ ይቆጠራል፡፡ እግዚአብሄር ግን መጀመሪያውና መጨረሻው ላይ በአንዴ ቆሞ ይናገረናል፡፡ ስለዚህ ቃሉ ለዘመኑ ጥንት ነው አለ (ዘመን እንቆጠር ዘንድ ስንጀምር የማይቆጠር ቀን ውስጥ ወደ ሁዋላ ስለሚገባብን በደፈናው ጥንት፣ እሩቅ ዘመን አንልለታለን)፡፡
አስገራሚ ስራ ይሰራል ጌታ ኢየሱስ፣ መጀመሪያና መጨረሻ ሆኖ በመሀል ሞቼ ነበርኩ ይለናል፡፡ ሞቱ መጀመሪያና መጨረሻነቱን ይቆርጣል ወይ? ሞቱ ቀኑን የሚቆጥር ሳይሆን ወደ ሲኦል አካባቢ ወርዶ በሞት ላይ የሚሰራውን ስራ ሲያሳይ እንጂ ዘመኑ የትም ስፍራ ላይ ሊቆረጥ የሚችል እንደኛ አይነት አዳም አይደለም፡፡
ቃሉ በአጽንአት ሲናገር፡-”ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው” በማለት ነው (ዕብ13:8)፡፡
• አብረሃምን ባረከው፣ ከርሱ አስራት ተቀበለ
ዕብ.7:4-16 ”የአባቶች አለቃ አብርሃም ከዘረፋው የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ። ከሌዊ ልጆችም ክህነትን የሚቀበሉት ከህዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ ከእነርሱ አሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው፤ ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል። ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው። በዚህስ የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ያስወጣሉ፥ በዚያ ግን የሚያስወጣ በሕይወት እንዲኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና። እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም። በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው።”
አብረሃም ወደ እግዚአብሄር መንግስት ለሚመጡ ሁሉ የእምነት አባት ነው፣ ቀድሞ የእግዚአብሄርን ማዳን ያመነው እርሱ ነው፡፡ ከአብረሃም ወገብ ውስጥ ሊወጡ ያሉ ትውልዶችም ብዙ ናቸው፡፡ ከነርሱም መሀል የክህነት አገልግሎትን የሚቀበለው ሌዊ ይገኝበታል፡፡ ሌዊ ግን እንደ ካህንነቱ ሰውን ከመባረኩ በፊት በሌላ ካህን ሊባረክ ችሎአል፡፡ ምሳሌነቱም በምድር ያለው ካህን ራሱ ሰማያዊና ፍጹም ካህን የተገባው መሆኑን ነው፡፡
• ክህነቱ ከሌዊ አገልግሎት ውጪ ነበር
እግዚአብሄር ለክህነት አገልግሎት ይቆም ዘንድ ከእስራኤል መሀል ሌዊና ዘሩን መረጠ፡፡ የሌዊም ልጆች የመቅደሱ አገልጋዮችና ካህናት ሆነው እስከ ብሉይ ኪዳን ፍጻሜ አገልግለዋል፡፡ ኪዳኑ ሲለወጥ ግን የክህነቱም አገልግሎት ጭምር መለወጥ ነበረበት፡፡ ከእንግዲህ በአዲስ ኪዳን ካህን ሌዊ ብቻ መሆኑ ቀረ፤ ሊቀካህናትም በየጊዜው እንደሚነሱ ሳይሆን አንድና አንድ ብቻ ሆኖ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፣ እርሱም ክርስቶስ፡፡ እግዚአብሄር ቃልኪዳኑን ስለለወጠ ክህነቱ፣ የክህነቱ አገልግሎትና አገልጋዮቹ ተቀይረዋል፡፡
ዕብ.7:17-28 ”አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና። ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።”
ሊቀካህናት ክርስቶስ እንደመሆኑ በእርሱ በኩል በልጅነት ስልጣን ምክኒያት ሰዎች ክህነትን ሊቀበሉ ችለዋል፡፡ እግዚአብሄር በኪዳኑ በኩል እርሱን ያገለግሉ ዘንድ ከተለያዩ ወገኖች የመረጣቸውን ካህናት አድርጎ ቀብቶአል፡፡የሁሉ ካህናት አለቃ ግን ክርስቶስ ነው፤ ካህናት መስዋእት በራሳቸው ማዘጋጀታቸው ቀርቶአል፤ በእግዚአብሄር የተዘጋጀ የመስዋእት በግ ሌላ ሳይሆን ሊቀካህናቱ ክርስቶስ እራሱ ነው፡፡ የሌዊ ክህነት የእንስሳን ስጋና ደም ይዞ በእግዚአብሄር ፊት ይገባ ነበር፤ መስዋእቱ ለህዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ጭምር ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን መስዋእት ለራሱ ይዞ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ክርስቶስ መስዋእት ራሱ፣ መሰዋእቱን አቅራቢ እራሱ፣ እንዲያውም መቅደስ ራሱ በመሆን አዲስ የመስዋእት፣ የአገልግሎት፣ የእርቅና የአምልኮ ስርአት ዘረጋ፡፡
ዕብ.10:10-22 ”በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል።አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። …የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም።እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤”
በአዲሱ የእግዚአብሄር ኪዳን በህያውና ዘላለማዊ ደም የአምልኮ፣ የአገልግሎትና የጽድቅ መንገድ በክርስቶስ ሞት ተመርቆ ተከፍቶአል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ቀርበን ለመቀደስ የእንስሳት እርድ ስርአት ተሽሮ ተመትቶ የቆሰለውና ተሰቅሎ የሞተው በህያው መንፈስ ሀይልም ከሞት የተነሳው የክርስቶስ ስጋ ተሰጥቶናል፡፡ የአሮን ልጆች ዛሬ አያስፈልጉንም፤ መስወእትን አንድ ጊዜ ተሰውቶ በእግዚአብሄር ቀኝ (በድካም ሳይሆን በመለኮት ሙላት እያበራ በዙፋን ላይ) በተቀመጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ዘላለማዊ አገልግሎት ሁሌም መገልገልና መፈወስ ችለናልና፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዘላለማዊ ደህንነታችን በእግዚአብሄር ከተረጋገጠ፣ የማይሻረው ሊቀ ካህናት በዙፋኑ ሆኖ ስለኛ ህያው ሆኖ መኖር እንደሚሞግትልን ካወቅን፣ በደሙ የምንነጻበት ዘላለማዊ ዋስትናም ከእርሱ ዘንድ እንዳለ ካወቅን በእርሱ ላይ እንታመን፡፡ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት እንደሚወስደን አውቀናልና በደሙ ታጥበን በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በፍቅር ድፍረት እንግባ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ላይ ያለው ታላቅ ካህን፥ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ሊረጨንና ሰውነታችንን በጥሩ ውኃ ሊያጥበን የታመነ ስለሆነ በዚህ በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ፡፡