አልፋ ኦሜጋ ካህንና ንጉስ[1…]

የእውነት እውቀት

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ (በእብራይስጥ ሲጠራ መሲህ/የተቀባ) የተባለ፣ ሁለተኛው ሰው ሲል ቃሉ የጠራው፣ የሰው ልጅ ሲል እርሱ ራሱን ያስተዋወቀው ለእግዚአብሄር አላማና የዘላለም ፈቃድ አስፈጻሚነት የተቀባ ሰማያዊ ሰው ነው፡፡ ሰዎች እርሱን ማን ሲሉ እንደሚጠሩት ጠየቀ፡-
” ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና፡- ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፡- መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም፡- ኤልያስ፥ ሌሎችም፡- ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፡- ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ።”(ሉቃ9:18-20)
የክርስቶስ ልዩ ቅባት እርሱን ሰማያዊ ንጉስ አድርጎ አስነስቶታል፡፡ ክርስቶስ ለእግዚአብሄር መንግስት ሊቀ ካህናትና ለሰማይ ልጆች የሀጥያት ይቅርታ የእግዚአብሄር በግ እንዲሆን ከእግዚአብሄር ተወልዶአል፡፡ የክርስቶስ ቅባት ሰዎች የሚቀቡት ቅባት አልነበረም፤ ምክኒያቱም ያለሀጢያት ሆኖ መቆምና ከላይ የተጠቀሱትን ማንነት ሊላበስ የሚችል ከሰው መሀል ማንም ስለሌለ፡፡
የእስራኤል ሰዎች ክርስቶስ ኢየሱስን ከአይሁዳዊ አባትና እናት ተወለደ በሚል እውቀት ብቻ ነበር የሚያውቁት፤ እርሱ ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው ሊያከናውነው ላቀደው ስራ ያዘጋጀው (የቀባው) ሰው ነው፡፡ ለእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ ማሰፈጸሚያነት የተዘጋጀ ሰማያዊ ሰው ስለሆነም ከአዳም ልጆች የተለየ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ ሲመላለስ ከአይሁድ በተለየ መንገድ ተመላልሶአል፣ ሲኖር በልዩነት ሲሞትም በልዩነት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ተሰቅሎ ሞተ። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለው ከእግዚአብሄር የተወለደና ከሰዎች የተለየ ማንነት ስላለው ነው፡፡
ሐዋ.2:22-24” የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።”
ስለዚህ እርሱ ፡-
• ስለህዝቡ እንደ ሊቀካህናትነቱ በመለኮት ፊት ይታያል (መንፈስ በሆነው አብና ስጋ በሆነው አዳም መሀል የገዛ ደሙን በማቅረብና የክህነት አገልግሎትን በመፈጸም የሰው ልጅ ወደ መለኮት ያለመከልከል እንዲደርስ ያደርጋል) በጠላቶች ፊት ተዋግቶም ለህዝቡ ይመክታል፣ ይማልዳልም (በእግዚአብሄር ፊት የደሙ ድምጽ ታጥበን ስለመንጻታችን ይናገርልናል)፡፡
• ራሱ ንጉስ እንደመሆኑ በህዝቡ ላይ ይሰለጥናል፣ ቤተክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ይመራል፣ አጋንንትን ከህዝቡ እግር በታች ይቀጠቅጣል፡፡
• የእግዚአብሄር በግ እንደመሆኑ ባፈሰሰው ደሙና በቆረሰው ስጋው ምህረትን ለታመኑበት ይሰጣል፣ ስጋውን በማብላትና ደሙንም በማጠጣት በሰው ውስጥ የዘላለም ህይወትን ይፈጥራል፡፡
በተለምዶ እንደምናውቀው ግን ሰው የወንድሙን ስጋ ሊበላ ደሙንም ሊጠጣ አይቻለውም፡፡ ስጋውን ቢበላ ደሙንም ቢጠጣ እንደ ጨካኝ አውሬ በሰው ዘንድ መቆጠሩ አይቀርም፣ ያስፈርድበታልም፡፡ እንዲህ ያለን ሰው በእብሮነት ለደቂቃም ሊቆይ ሆነ ሊያየው የሚሻ ከቶ አይገኝም፡፡ ክርስቶስ ግን ምድራዊ አዳም ስላልሆነ ደሜን ጠጡ ስጋዬንም እነሆአችሁ ብሉ ሊል ችሎአል፤ አለምም (የሰው ዘርም) ያን ሳይጸየፍ ወይም ሳይጠራጠር ተቀብሎታል፡፡ የክርስቶስን ስጋ ለመቁረስና የደሙን ጽዋ ለመጠጣት ድፍረት የሆነኝ የዘላለምን ህይወት ከእርሱ እካፈላለሁ የሚለው እምነት ነው፣ እርሱ ህይወት የሚሰጥ እንጂ እንደ እኛ ያለ በሀጢያት የረከሰ ስጋና ደም ያለው አይደለም፡፡
1ቆሮ.10:16-18 ”የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን?”
መልከ ጼዴቅ የሚባል የሳሌም ንጉስ አብርሃም የወንድሙን ልጅ ከምርኮ አስመልሶ ወደ ሀገሩ ሲጉዋዝ ድንገት መንገድ ላይ ተገናኘው፡፡ የእግዚአብሄር አላማን ሊያስፈጽም ከወገኖቹ ተለይቶ የወጣው አብረሃም በድንገት አንድ ልዩ ሰው ተገናኘ፡፡ ይህ መልከ ጼዴቅ የተባለ ሰው ለአብረሃምና ለዘሩ ስለክርስቶስ ማንነትና አገልግሎት አመልካች ምሳሌ ሊሆን በመንገዱ ላይ የተገለጠ ሰው ነበር፡፡ እርሱ የሳሌም ንጉስ (ይህች ስፍራ በሁዋላ ኢየሩሳሌም ተብላ የተጠራችው የዳዊት መናገሻ ከተማና የሰማዩ ንጉስ ከተማ ምሳሌ ንጉስ) እንደነበር መጽሀፍ ቅዱስ ያመለክታል እንጂ ስለሌላ ማንነቱንና ስለትውልዱ አያብራራም፡፡ ስለእርሱ የቀደመ ታሪክ በመጽሀፍ ያለመተረኩ የእግዚአብሄር አላማ እንደነበርም ያመለክታል፡፡
ይህን ስንመለከት ግን በመልከ ጼዴቅ ክህነትና ንግስና ውስጥ የክርስቶስን ማንነት እናያለን፡፡ ንጉስ ካህን ነው ሲባል ምድራዊን መንግስት የሚገዛ ሰው ሰማያዊውን የእግዚአብሄር መንግስት አገልጋይም ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከመልከ ጼዴቅ በፊትና በኋላ ታይቶ፣ ተሰምቶና ሆኖ የማያውቅ ልዩ የአገልግሎት በር ነው፡፡ ዖዝያን የሚባል የእስራኤል ንጉስ በአንድ ወቅት በካህናት ቦታ ገብቶ ሲያጥን እግዚአብሄር ቀስፎት እናያለን፡፡ የዚህ ፍርድ ምንነት የሚያሳየው ንግስናና ክህነት መቀላቀል የማይችሉ መሆኑን በእግዚአብሄር ፈቃድ ግን ለተለየ አላማ መልከ ጼዴቅ በእግዚአብሄር እንደተዘጋጀ እናያለን፤ ይህ የሳሌም ንጉስ የክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ ለእምነት አባት ለአብረሃም ተገለጠ፡፡ መልከ ጼዴቅ ከዚህ ማእረግ ጋር ሲገለጥ አንድ ሰማያዊ ንጉስና ካህን ወደፊት ይነሳ ዘንድ እንዳለው በምሳሌነት አሳይቶአል፡፡
ዘካ.6:12-13 ”… የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል…”
በብሉይ ኪዳን በኢየሩሳሌም ውስጥ መቅደስ የሰራ ንጉስ ሰለሞን እንዲሁም የክርስቶስን መድሀኒትነት፣ ክህነትና ንግስና አመልካች በሆነ ስምና ሹመት የተነሱ ሁለት ሌሎች ሰዎች ተነስተው ነበር፡፡ የክርስቶስን መድሀኒትነት የሚተነብይ ስም የያዙ ሁለቱ ኢያሱዎች ነበሩ (የስማቸው ትርጉዋሜ እግዚአብሄር ያድናል የሚል ነበር)፡፡ እነዚህ ሰዎች በስማቸው የኢየሱስን መድሀኒትነት በስልጣናቸው ንግስናውንና ክህነቱን በብሉይ ኪዳን ዘመን የገለጡ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ኢያሱ የነዌ ልጅ ሲሆን እርሱ እስራኤልን ከግብጽ ወደ ከነአን የመራ የእስራኤል አለቃ ነበር፡፡ ኢያሱ የነበረው አለቅነትና መሪነት ክርስቶስ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያለውን ንግስናና የመንፈሳውያን እሰራኤል መሪ መሆን ያሳያል፡፡ ኢያሱ በዘመኑ እስራኤልን ከምድረ-በዳ ጉዞ ጀምሮ እስከ ከነአን ምድር ድረስ በመምራት ህዝቡ ከግብጻውያን ጥፋት እንዲድንና ርስቱን እንዲወርስ አድርጎአል፡፡ በመጨረሻ እስራኤልን የመራው ታላቁ መሪ ኢያሱ አርጅቶ ሞቶአል፡፡ ጌታ ኢያሱስ በእግዚአብሄር መንግስት ንጉስ በመሆን ህዝቡን እስከ ጽዮን የሚመራ፣ ከጠላት ፍላጻ ጠብቆ እስከ አለም መጨረሻ (እንዲሁም እስከ እግዚአብሄር መንግስት መድረሻ) ድረስ የሚያድን ነው፤ ዘመኑ በእድሜ የታጠረ ስላልሆነ ከአለም ፍጻሜ በሁዋላም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም የህዝቡ እረኛና ንጉስ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ሁለተኛው ኢያሱ ታላቁ ካህን ሲሆን እርሱም በነቢዩ ዘካሪያስ ዘመን ታላቅ ካህን ነበረ፡፡ የእርሱም አገልግሎት ንጉሱ ኢየሱስ ደሙን በማቅረብ ለህዝቡ ሊቀካህናት ሆኖ እንደቆመ ይናገራል፡፡ የክርስቶስ ከህነት ግን እንደ ኢያሱ በጊዜ የታጠረ ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ዘላለማዊ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሁለቱ ኢያሱዎች ምሳሌ ተመስሎ በዙፋኑ ላይ ንግስናውንና ክህነቱን ይዞ ይቀመጣል፡፡
ዕብ.7:20-25 ”እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”
መልከ ጼዴቅ ሁለት የእግዚአብሄርን አገልግሎቶች ማለትም ንግስናና ክህነትን አጣምሮ በመያዝ ተገልጦ ነበር፡፡ ስለዚህ እንደ ንጉስነቱ የሳሌም ንጉስ ነበር፡፡ እንደ ካህንነቱ አብረሃምን የባረከ፣ እግዚአብሄርንም በምስጋና የባረከ የልኡል እግዚአብሄር ካህን ነበር፡፡
እንዲሁም ክርስቶስ በመልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀካህናት ነው፤ ይህንም በታማኝነት አከናውኖአል፡፡ ስለሀጢያታችን ራሱን መባና መስዋእት አድርጎ አቅርቦአል፣ የእግዚአብሄር በግ ሆኖ ደሙ እንዲፈስ ስጋውም እንዲቆረስ ሰጥቶአል፡፡
ዕብ.2:17 ”ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።”
ክርስቶስ ክህነቱ እንደ አሮን (እንደ ኢያሱም) የተገደበ አይደለም፣ ነገር ግን የማይለወጥና ዘላለማዊ ነው፡፡ አሮን ለክህነት ከወገኖቹ መሀል የተመረጠና አገልግሎቱ በዚህ አለም በነበረው ቆይታ የተወሰነ ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ከትውልዱ ከእስራኤል መሀል የተመረጠ ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ እናትና ያለአባት ምድራዊ አድራሻ ሳይወሰንለት የተሾመ (የተቀባ) ነበር፤ ክርስቶስ የእግዚአብሄር ልጅ ስለሆነ እድሜና ስፍራ የገደበው አይደለም፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱ በሹመቱ ልክ ሳይለወጥና ሳይወሰን ለዘላለም የቀጠለ ነው፡፡
ራእ.1፡4-6 ”ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።”
መልከ ጼዴቅ ከርስቶስ ኢየሱስንና የመጣበትን አላማ ለማመልከት እግዚአብሄር ያዘጋጀው ልዩ ሰው ነበር፡-
• መልከ ጼዴቅ ንጉስና ካህን መሆኑ ስለክርስቶስ ምን ያመለክታል?
ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም የበላይ ሀላፊ እንደሆነና ሲወለድ ልጅ ብቻ ሳይሆን ሀያል አምላክና የሰላም አለቃም እንደሆነ የነቢዩ ኢሳያስ ትንቢት አመልካች ነበር፡፡ የመልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉስና ካህን መባሉ አሰቀድሞ የክርስቶስን ማንነት ለማመልከት ነበር፡፡
ዕብ.7:1-2 ”የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው።”
• የሳሌም ንጉሥ
መለከ ጼዴቅ ከነአን ምድር ያለች ሳሌም ንጉስ ነበር፡፡ ሳሌም በሁዋላ ኢየሩሳሌም የተባለች የእስራኤል ነገስታት ከተማ (የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ምሳሌም የሆነች) ነች፡፡ የሳሌምን መንግስት የሚያስተዳድር ንጉስና በዚያ ላለ ህዝብ ካህን የነበረ መለከ ጼዴቅ አመጣጡ ምስጢር ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉስ ይሁን እንጂ መቼ እንደገዛ፣ እንዴት እንደገዛ፣ ምን ያህል ዘመን እየገዛ እንደኖረና የመሳሰው ነገር ሳይታወቅ በእግዚአብሄር አሰራር እነዚህ ምስጢሮች ውስጥ የተገኘ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ምክኒያት መልከ ጼዴቅ የክርስቶስን የዘላለም ንግስና በምሳሌነት ሊወክል ከመቻሉም ሌላ ንግስናውና የንግስናው ስርአቶች ከእግዚአብሄር የተሰጡ መሆናቸውን አመልካች ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ በሳሌም ላይ መንገሱ በሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም በዙፋኑ ላይ የሚገዛውን ክርስቶስ የሚያሳይ ነው፡፡
ዕብ.4:14-16 ”እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”
ጌታ ኢየሱስ የሰላም ንጉስ ነው፡፡ ሰላምና እርቅ በሞቱ በኩል ለሰው ልጆች ሆኖአል፡፡ ሰዎች በሀጢያት ምክኒያት ከተፈረደብን ከኤደን ገነት እርግማን ጀምሮ ክርስቶስ እስከተገለጠበትና የመስቀሉን ስራ እስከፈጸመበት ጊዜ ድረስ በቁጣና ፍርድ ስር ሆነን እንጠበቅ ነበር፡፡ ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር ተጣልተን መለያየታችን ሳያንስ አይሁድና አህዛብ ሁለት ጎራ ሆነን በጥል ውስጥ ነበርን፡፡ በዚያ ምክኒያት ከክርስቶስ ውጪ ያሉ አይሁድ ዛሬም ከአህዛብ ጋር የፍቅር ህብረት አያደርጉም፡፡ ነገር ግን የክርስቶስ ደም በእኛ ላይ ሲረጭ ብቻ ቁጣው እንደሚበርድና ምህረት እንደሚወርድ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ያ ምህረት እርቅ ይዞ መጣ፣ እርቁም ሰላም፡- ሰላም በሰዎች መሀል ሰላም በሰውና በፈጣሪም መሀል!
ኤፌ2:13-18 ”አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።”
• የልዑል እግዚአብሔር ካህን
ንጉሱ በዙፋኑ ላይ ነግሶ ክብርንና ምስጋናን የሚቀበል በህዝቡም ላይ የሚሰለጥን ብቻ ሳይሆን ህዝቡን የሚቤዥ ለህዝቡ በጽድቅ የሚቆም ሊቀካህናት ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ ንጉስና ካህን በመሆን የኢየሩሳሌም ገዢና ንጉስ ብቻ ሳይሆን የህዝቡ የበረከት ምክኒያት ነበር፡፡ በ2ዜና.26:16 ውስጥ እንደምናነበው ንጉስ የክህነትን አገልግሎት ሊያገለግል እንደማይገባ ያን ቢያደርግ ግን ከእግዚአብሄር ዘንድ መቅሰፍት እንደሚጣበቅበት ተገልጦአል፡፡ ይሁን እንጂ መልከ ጼዴቅ ምሳሌነቱ ለሰማያዊው ንጉስና ሊቀካህናት ለክርስቶስ ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ ሁለት በረከት አውጥቶአል፤ አብረሃምንና እግዚአብሄርን ባርኮአል፡፡ ንጉስ ፈራጅ ሲሆን ካህን ይቅርታ ለማኝና ምህረት አውራጅ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ያለው ንጉስ እንዲሁ ወደ እርሱ የሚመጡትን ከፍርድ አውጥቶ ይምር ዘንድ ይቅር ባይነትንና ምልጃን አቅራቢ ሊሆን ተገባው፡፡
2ቆሮ.5:18-21 ”ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”
እግዚአብሄር በአዲስ ኪዳን የገለጠው አሰራር ልዩ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ከሰው መሀል ካህናት መርጦ በእነርሱ በኩል የሀጢያት መስዋእት እየተቀበለ ህዝቡን ሲምር እንደኖረው ሳይሆን ልዩ መስዋእት በበግ የተመሰለ ከገዛ ቃሉ ሰውነት አዘጋጅቶ በዚያ ሰውነት ውስጥ አድሮአል፤ ይህም ሁለት ስራን ይሰራ ዘንድ ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ ያቀደው እንደሆነ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ በዚያ ሰውነት ውስጥ ያደረ አምላክ በንጉስነት እርቅን የሚቀበል ሆነ፤ ሰውነቱ እንደ በግ ሰውነት ሊታረድ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ ፈቀደና ባፈሰሰው ደሙና በቆሰለው ስጋው ሰዎችን ወደ ራሱ ሊያቀርብ፣ ሊታረቅና ሊያጸድቅ ወደደ፡፡ ይህ የአዲስ ኪዳን ታላቅ ምስጠር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር የሚለው አዋጅ ይህን አመልካች ነው፡፡
ዕብ.5:5-10 ”እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፡- አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፡- አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል።እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።”