ስለ አለም ማወቅ ያለብንን ነገር ከመሰረቱ አንስቶ በሙሉ እውቀትና ማስረጃ ገልጦ የሚያሳውቀን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ብቻ ነው፤ የሚከተለው ቃል ታላቅ ነገር ይናገራል?
‘’ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።’’ (እብ. 11:3 )
ቃሉ ከአንድ በላይ ብዛት ያላቸው ዓለሞች እንዳሉ በማስረዳት እነርሱም በእግዚአብሄር ቃል እንደተዘጋጁ ያሳያል። እነዚህ አለማት የሚታዩ ፍጥረታት ሲሆኑ የትኞቹም ቢሆኑ ከእግዚአብሄር እቅድ ውጪ ያልተፈጠሩም ናቸው። በሌላ በኩል አለም የሚለው ቃል ግኡዝ ፍጥረታትን ከማመልከቱ በተጨማሪ በዚህ ስም የሚጠሩ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ እንማራለን።
ስለዚህ ዓለም የተሰኘ ስም ለምን ለምን ነገሮች እንደተሰጠ ለማየት በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ስፍራቸውን መፈለግ ጠቃሚ ይሆናል፦
ከላይ ያየነው ቃል እግዚአብሔር የፈጠረውን ግዑዝ ነገር በሙሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከሰማይና ከምድር ጋር በአንድነት ዓለም እያለ እንደሚጠራ አይተናል። በሐዋ.17:24-28 ላይ ያለውም ቃል ይህን ያጠናክራል፡-
‘’የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፦ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።’’
በዚህ ቃል ላይ ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ የፈጠረ ሕያው እግዚአብሔር እንደሆነ እናያለን። በሰማይ ውስጥ ታላላቅ ፍጥረታት ይገኛሉ፤ የሰማይም ታላቅነት ከሰው ልጆች ማስተዋል በላቀ ሁኔታ እጅግ የሰፋና የጠለቀ ነው፤ በውስጡ የተሸከማቸው ፍጥረታትም ብዛትና መጠናቸው ሰው ከሚያስተውለው እጅግ ይልቃሉ። እነርሱን የፈጠረ አምላክ እንደምን ያለ ታላቅ ነው? ምንኛ ጥልቅ ነው? ተነግሮለትስ ያበቃል ወይ? ማንነቱስ ከእኛ ማስተዋል የላቀ አይደለምን? ከነዚህ ፍጥረታት ባሻገር ፈጣሪያቸው እንደምን ታላቅ እንደሆነ በዚህ ብናስተውል፤ ከምንም በላይ ስለወደደን ቀርቦናልና፣ ስለዚህ በመሃከላችን ተገኘ፣ አማኑኤል ሆነ፤ ታየ፣ ታመነም። ይህ እውቀት ግን ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው፣ ሰማይን ያየና ግዝፈቱን ልብ ያለ መልሶም የሰውን ታናሽነት ያስተዋለ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ሆነ የሚለው የምስራች ከአእምሮው በላይ እንደሚሆንበት ማሰብ ይቻላል፤ ይህን እውቀት እምነት ከሆነ እንጂ የስጋ አእምሮ ሊቀበለውም እጅግ ያዳግተዋል፤ አማኝ ግን ስሌት እንቅፋት ሳይሆንበት እምነት ይደግፈዋል። ይህን ግዙፍ ዓለም የሰራ አምላክ በፈጠረው ሁሉ ላይ የከበርና በእያንዳንዱ ላይ አዛዥ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ቃሉ በምድር ላይ የሚኖረውን የሰው ልጅ በአንድነት አለም ይለዋል። የሰው ልጅ ( በተለይ በሃጢያት ውስጥ ያለና ከእግዚአብሄር ፈቃድ ርቆ ያለ ) ከሌሎቹ ፍጥረታት በተለይ ተነጥሎ በእግዚአብሄር ሲጠራ አለም ተብሎአል። በዮሃ.3:18-20 ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፦
‘’ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።’’
ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር የወረደው የሰውን ልጅ ለማዳን ነው፤ መከራ የተቀበለው፣ በመስቀል ላይ የተሰቀለውና ሞቶ የተቀበረው፣ ከሙታንም ተነስቶ በክብር ያረገው የሰውን ልጅ ለማዳንና በመንግስቱ ተቀብሎ ለዘላለም ሊያኖር እንጂ ለሌሎች ለምሳሌ እንደ መልአክት፣ ሰማይና ምድር፣ እንስሳትና እጽዋት ላሉ ፍጥረታት ሲል አልነበረም።
‘’የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።’’ (ዮሃ. 6:33)
በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ ስለ ሰው ልጅ መዳን ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል፣ ይህንን የእግዚአብሄር ምህረት ያለማወቅ ነገር እጅግ የሚያሳዝን ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ዓለም የሚለው ሃጢያትና ሃጢያተኞች የሚኖሩበት መንፈሳዊ ስርአት በዚያ ውስጥ የሚገለጠውንም አሰራር ነው። በዚህ አለም ውስጥ ሃጢያተኛ መናፍስትና የሰው ልጆች በሙሉ ተዋንያን ናቸው።
‘’በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።’’ (2ጴጥ. 2:22-24)
‘’አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።’’ (1ዮሃ. 2:14-17)
‘’ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።’’ (1ዮሃ. 4:1)
‘’የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።’’ (እፌ. 6:12-13)
ይህ አለም የክፋት መንፈሳውያን የሰለጠኑበት አሰራር አለበት፣ የክፋት መናፍስት ስለነገሱ ጨለማው የበረታ ነው፤ በዚህ አለም ውስጥ በተንሰራፋው የክፋት አሰራር ምክኒያት ሰዎች ተገዝተውና በልማዶቻቸው ተይዘው ይመላለሳሉ፣ የሚያዙበት ወጥመድም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮት እና በአለም ያለ መመካት ናቸው።
‘’ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።’’ (1ዮሃ. 2:1-2)
ከሰው ልጅ ማን ቅዱስ እንደሆነ መናገር ይችላል? ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ ስለተባለ፤ ስለዚህ በምድር ላይ ያለ የሰው ልጅ ሁሉ ሃጢያተኛና የሃጢያት ልማድ ባለቤት በመሆኑ አለም የሚል ስም ቃሉ ሰጥቶታል። ጌታ ኢየሱስም ለአለሙ ሁሉ ሃጢያት መስዋእት ሊሆን መጥቶአል።
‘’ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።’’ (ገላ. 6:14)
እንዲሁም ሊመጣ ያለ በእግዚአብሄር የተዘጋጀ አለምም አለ፦
በእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ ውስጥ የመጨረሻው ግብ ያለው ነገሮችን ሁሉ (በሰማይና በምድር ያሉ ሁሉ) በክርስቶስ የመጠቅለሉ ክንዋኔ ላይ ነው። በርሱ በኩል ጽድቅ፣ ቅድስናና መዳን ለሰው ልጆች ከተከናወነ በሁዋላ የዚህን አለም ስርአት ዘግቶ እንዲያውም አጥፍቶ የአዲስ አለም ስርአትን ይከፍታል። ቃሉ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦
‘’አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።’’ (ራእ. 21:1-4])
እግዚአብሄር ያዘጋጀልን ዘላለማዊ አለም ከፊታችን ይጠብቀናል፣ የዚህን ዓለም ደስታ እንድንቀምስ እግዚአብሄር በዚያ ያለውን የደስታ ኃይል በጥቂቱ እያሳየን በማኖር ላይ ነው፣ የእግዚአብሄር መንግስት ጽድቅና በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታ ናት እያለ በዚያ ያለውን አለም ይነግረናል፤ እንድናጣጥመውና እግዚአብሄር ሊሰጠን ያሰበውን እንድንናፍቅም ያደርጋል። በአዲሱ አለም እግዚአብሄር ብቻ በህዝቡ መሃል በዘላለማዊ የክርስቶስ ሰውነት ሆኖ በልጆቹ መሃል ይኖራል፤ ድል የነሱት ፊት ለፊት ያዩታል፤ የዚህ አለም ስርአት የለምና ሰቆቃ ይቀራል፣ እግዚአብሄር ብቻ ይነግስበታልና የህማም፣ የደዌ፣ የጉስቁልናና የመሳሰለው አስለቃሽ ነገር ያልፋል። ይህን ደስታ ቀምሰው ሃይሉንም ተካፍለው ወደ ሁዋላ ያፈገፈጉ ከባድ ነገር እንዲገጥማቸው አያጠራጥርም፦
‘’እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።’’ ይላል (እብ. 6:4-7)።
የካዱ ሰዎችን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻለው ለምንድነው? አዎ እነዚህ ሰዎች ተካፍለው የነበረው ታላቁን የእግዚአብሄር ስጦታ ነውና፣ አዘጋጅቶ ቀን እየጠበቀለት ያለውን የመንግስቱን ደስታ ቀምሰዋልና፣ የዘላለም ቤቱን ደስታ አውቀዋልና ከዚህ እውቀት ቢወድቁ ሌላ ሊያነሳቸው የሚችል የቱ ትምህርት ሊሆን ይችላል?
‘’ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።’’ (1ዮሃ. 5:4-7)
በእርግጥም የሚመጣው የዘላለም ደስታ የተሞላበትን የእግዚአብሄር መንግስት ለማየት በዚህ ምድር ላይ ያለውን የአመጽ አለም ድል ማድረግና ወደ ጌታ ደስታ መሻገር አስፈላጊ ነው፤ ያን የሚያስችል እግዚአብሄር በመንገዱ ስለሚመራን እርሱን ተከትሎ የመኖር ፊተኛ አማራጭ እናድርግ፤ አምላካችን አሸናፊ ህይወት እንዲኖረን የድል ሃይል አዘጋጅቶ በአዲስ ልደትና መለኮታዊ ባህሪ ተካፋይ ባለው ህይወት ላይ አኑሮአልና።
‘’እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት። ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና።’’ (እብ. 2:4-5)
‘’ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና።እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል።እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን። ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ።’’ (1ዮሃ. 4:3-7)
‘’ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።’’ (1ዮሃ. 5:4-7)
አምላካችን ግኡዙን አለም ታግለን እንድናሸንፍ አላሳሰበንም፣ ይልቅ የጨለማ ስርአት የሰፈነበትን የክፉ መናፍስት አገዛዝም ያለበትን ያን አሰራር ታግለን በእምነት በአምላካችን ሃይል ድል እንድናደርግ የሚረዳንን ጸጋ ሰጠን። ሃጢያትን ያሸነፈና ዲያቢሎስን ከእግራችን ስር የጣለ ጌታ በእምነት በህይወታችን ከሰራ የክፋትን መንፈሳዊ አለም በእርግጥ እናሸንፋለንና።