አለማዊነት(2..)

ቤተክርስቲያን

በዳኑ ሰዎች ላይ ያሉ ተግዳሮቶች በብዙ አቅጣጫ የሚታዩ ሲሆን ተግዳሮቶቹም በዋናነት ለመንፈሳዊ ህይወት ችግሮች ሆነው የሚኖሩ ናቸው። ነፍሳት በጌታ ኢየሱስ ቤዛነት ብቻ ከጥፋት በመዳን ህያዋን ሲሆኑ ቤዛነትን በሰጣቸው ጌታ ታምነው መኖር እንዲገባቸው የዳኑበት መሰረት ያሳያል። ሰዎች ንስሐ ስንገባ፣ ኃጢአታችንን ስንተው፣ ክርስቶስን በልባችን ስንቀበልና በዳግም ልደት ከውሃና ከመንፈስ ስንወለድ በእውነት ድነናል፤ አሁንም ግን በህይወት ዘመናችን ስንኖር የበለጠ በመንፈስ እያደግን፣ የውጭ ተግዳሮትን እየተቋቋምንም የተቀበልነውን መዳን በህይወታችን ማስቀጠል አለብን፤ ያን የሚያስችል ጉልበትም በመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ጸጋ የምንቀበለው ነው። እንዲያም ሆኖ ከዳንንበት ቀን ጀምሮ፣ ዓለማዊነት በሚባል መንፈሳዊ አሰራር እየተናጥን ትግል ውስጥ እንገባለን። ዓለማዊነት አንድ ተግዳሮት ያለበት መንፈሳዊ ስርአት ሲሆን ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ሁልጊዜ ይጋፋል፤ አለማዊነት ባለማቋረጥ የሚገዳደር የመንፈሳውያን ጠላት በመሆኑ አዘውትሮ የሚገጥመን ሁሌም ወደ እኛ የሚመጣ እንደ እድሜያችን እና እንደ ህይወታችን ደረጃ በተለያየ መንገድና ገጠመኝ የሚያገኘን ነው። ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ህይወታቸው አንጻር የእግዚአብሄርን ቃል በመመርኮዝ ዓለማዊነትን አተኩረው ሊመረምሩትና ሊያውቁት አስፈላጊ ነው፣ የአለማዊነትን ባህሪይ ጠንቅቀው መረዳትም ያስፈልጋቸዋል፤ ይህን ችግር በጥልቀት ከአምላክ ቃል አንጻር በመፈተሽ አንድ የተሻለ መንፈሳዊ የህይወት ደረጃ ላይ መድረስ ተገቢ ነው።
በእግዚአብሄር ቃል እውቀት በመታነጽና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ ተግዳሮትን እንመክታለንና፦
‘’ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።’’ (ቲቶ2:14-15)
ዓለማዊነት ለጠላት አሰራር ሁኔታዎችን አደላድሎ የማቅረብ ችሎታ አለው፣ እንዲሁም እኛን ለእርሱ፤ በተለይ እኛነታችንን (ባህሪያችንን) ወደ አመጽ እንዲያዘነብል፣ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር በሚጋጭ መንገድ ላይ እንድንራመድም ሁኔታዎችን የሚያመቻች ነው። በአማኞች መሃል (በተለይ በቀላሉ ተስቦ በሚፈተነው ክፍል መሃል) አለማዊነት ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር ይታወቃል፤ በዚህ በኩል ወጣት አማኞች ይጠቀሳሉ፤ አለም ወጣቶችን እጅግ ትፈልጋለች፣ ሰይጣንም እንዲሁ ይፈልጋቸዋል። ሰይጣን ወጣቶችን የሚያገኘው በአለም በኩል መሆኑ ደግሞ የሁለቱን ትብብር ያሳያል። በዛሬ ጊዜ አለም ለወጣቶች የሚያስደስቱና የሚያጓጉ ብዙ ነገሮችን ታቀርባለች።
አለምን አጓጊ የሚያደርጉ ነገሮች አሉአት፣ እነዚህም ወጣቶችን ይፈትናሉ፦ ለምሳሌ ፋሽኖች፣ አዝናኝ ፕሮግራም፣ ፊልም፣ የወሲብ ምስል፣ ማባበያ ማስታወቂያ፣ ልብወለድ መጻህፍት፣ መዋቢያዎች፣ ዳንስ፣ አደንዛዥ እጾች፣ መጠጦችና ሌሎች ብዙ ነገሮች አይናቸውን ጆሮቻቸውን፣ ምናብ እና ፍላጎታቸውን የሚወርሩ፣ የሚሰርቁና በአጠቃላይ ማንነታቸውን የሚበክሉ ናቸው። ወጣቶች በነዚህ ልምምዶች ሲዋጡ በመንፈሳዊ ህይወታቸው ድካም ያገኛቸዋል፣ መፍዘዝ አንቆ ይይዛቸዋል፤ ስለዚህ ከአለም የሚለዩበትን ትምህርት ካላሳወቅናቸው በነርሱ ዘንድ ሊኖር የሚገባው የመለያ መስመር የት ሊያርፍ እንዳለው አያውቁም። የአለም መንፈስ በቀጥታ ቅድስናን ያጠቃል፤ ጥቃቱ በአይን አምሮት በማባባበልና በስጋ ምኞት በማጥመድ ስለሆነ ስር ሰድዶ ያለህመምና ያለመጎርበጥ ስራውን ይሰራል፣ አለሳልሶ በመውጋትም ይጥላል።
በሌላ በኩል ክርስቲያኖች በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ታንጸው የማይበረቱ ከሆነ (በቃሉ ላይ ታምነው እንደእግዚአብሄር ቃል መኖር ካልቻሉ) ከአለማዊነት መራቅ አይችሉም፣ አለምን፣ ስጋንና ሰይጣንን በሚቆጣጠር የላቀ ጸጋ እስካልተሞሉ ድረስ ሊቋቋሙት አይችሉምና። የጽድቅ ጉልበት ሲርቅም አማኞች ከሃጢያት የመለየት አቅም አጥተው በዓለም ስጦታ (አለም በምታቀርበው ማባበያ) ላይ ይደራደራሉ፣ እንዲያውም አለምንና ተጽእኖዋን ዘንግተው በርሱዋ ያለውን ነገር መቀበል፣ መለማመድና በዚያ መደሰት ምንም ጉዳት እንደሌለው እስከመገመት ይደርሳሉ። አልፈውም ሰውን ለትብብር በመጋበዝ በቃልም ሆነ በተግባር ደጋፊ ይሆናሉ።
በቤተክርስቲያንና በአለም መካከል ሁልጊዜ የድንበር መስመር ሊኖር አስፈላጊ ነው፤ በአለምና በክርስቲያን መሃል የተቃርኖ ጥል አለና፦
‘’ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።’’ (ዮሃ.15:18-19)
በዚህ ትውልድ ውስጥ ብዙ የክርስትና እምነትን እንከተላለን በሚሉና በዓለም ልጆች መካከል መለያየት አይታይም። ከነርሱ አካሄድ ጋር እውነትን የምንወድ ሁሉ መንገዳቸውን ተላምደን እንደሆን ቤተክርስቲያንን በአለም እንዲሁም አለምን በቤተክርስቲያን ውስጥ እናገኛለን ማለት ነው። እንደዚህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ በሰፊው አውራ ጎዳና እንደ መጓዝ ነው፣ እርሱ ደግም ወደ ጥፋት ግዞት የሚያደርስ ነው። በበዛው የክርስትና ስም እምነት ውስጥ የተለያየ መንፈስ የሚያንጸባርቁ አሳች አስተማሪዎች ዛሬ በድፍረት ወርሰዋል፣ የተፈረደባቸው ሰባኪዎች የሚያባብሉ ሸንጋዮች ሆነው የሚሰማቸውን እየካቡ ነገር ግን ሰሚውን በጽድቅ ቃል ሳይነቅፉና ሳያስከፉ በቤተ እምነታቸው ውስጥ የስጋ ትምህርትን በግልፅ ያስተምራሉ። ቃሉ ግን እንድንጠነቀቅ ያስተምራል፦
‘’የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።’’ (ሮሜ.12:2)
እኛ ግን በየትኛውም መንገድ ጽድቅን ካስበለጥንና የእግዚአብሄርን ቃል የምናከብር ከሆነ፣ አላማችን መሆን ያለበት በእውነት የጌታን እውቀት እየተናገርን ለመገለጡ ቀን ዝግጁ በሆነች ቤተክርስቲያን ውስጥ መዘጋጀት ነው።
የአማኞች ፈተናዎች
‘’ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።’’ (ገላ. 1:5)
አንድ ሰው ሲድን ከነፍሱ ቀጥሎ ሊፈወስለት የሚገባው የበዛ ነገር ይገጥመዋል፤ ህይወቱ በሙሉ እስኪፈወስ በሚያልፍበት ሂደት ውስጥ የአለም እንቅፋት መስቀሉ ይሆናል። አዲስ ክርስቲያን በቤተሰብ መሃል ሲድን፣ ከቀሩት የቤተሰቡ አባላት ዘንድ የተለያዩ ተግዳሮት ይመጣል፤ የቤተሰቡ አባሎች እንደርሱ አዲስ ህይወት ስላልተቀበሉ በአሮጌው ህይወት ውጊያ ውስጥ ይገባሉ፣ በሃሳብና በምግባር ይቃረናሉ፤ በነርሱ ዘንድ የከረመው ያልተለወጠ ማንነት አዲሱን ማንነት ይገዳደረዋል፤ በዚህ ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ።
‘’በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።’’ (ኤፌ. 2:3-4)
አንድ የተለወጠ አማኝ ግን በጌታ ፍቅር ተይዞ ሲጓዝ አስቀድሞ የሚያውቀውን አካሄድ እያራገፈ ይሄዳል። ይህን በመለማመድ ከአለም የተወረሰው ልማድ እየተረሳ የጽድቅ መንገድ እየተለመደ ይሄዳል። ለምሳሌ አስቀድሞ የለመድነው ፊልም ወይም ቴሌቪዥን ላይ ከማተኮር ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ስንመርጥ አዲስ ነገር ይሆናል፣ ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ማድረግ፣ ከዓለማዊ ወዳጆች ጋር በማይመች አካሄድ ከመሄድ መቆጠብ፣ ወደ አማኞች ህብረት ማዘንበል፣ እግዚአብሄርን ማምለክና ማገልገል ላይ መሰጠት፣ በእረፍት ቀን (በተለይ በእሁድ በጉባኤ እለት) ለስጋ የሚሆኑ እቅዶችን ከማውጣት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ማድረግ ባህል ይሆናል፣ ይህም ለብዙዎች ወዳጆቻችን ላይመች ይችላል ለእኛ ግን ህይወትን ያበረታል።
አንድ ደቀመዝሙር በአዲሱ ህይወቱ ውስጥ ለሚያሳልፈው ውሳኔ እና በህይወቱ በተፈጠረው መንፈሳዊ አሰራር ቤተሰቦቹ ቅር ሊሰኙበት ይችላሉ፤ ሌላ ሳይሆን በአዲሱ ህይወቱ ላይ የሚታዩ የጽድቅ ነገሮች ሊኮንኗቸው ስለሚችሉና የቀድሞ ህብረታቸው ሊቋረጥ ስለሚችል ያን በምስጋትም ጭምር ሊያኮርፉ ይችላሉ። አንዱ የቤተሰብ አባል ተነስቶ ሲቃወም፣ ሌላው ሁኔታዎችን አበላሸህ ብሎ ሲነቅፍ፣ በሃይማኖትህ ምክኒያት የቤተሰብ እምነት ተበላሸ በሚል ውዝግብ ሲፈጥር፣ ከፍ ሲል ደግሞ ስደት ሲነሳ ብዙ ፈተና በላይ በላይ ይደራረባል። ችግሩ ስር ሲሰድና ሲጸናም አባትና እናት፣ ወንድሞችና እህቶች ጭምር በቀጥታ ተቃውሞ ውስጥ ይገባሉ፣ እስከ መለያየትም ይደርሳሉ። በትምህርት ቤትም ባሉ ጓደኞች ተመሳሳይ ችግር ሊፈጠር ይችላል። እንግዲህ ይህ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ከአለም ወደ አማኞች የተሰነዘረ ግብረ-መልስ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ደቀመዛሙርት በጌታ የተነገረው ተስፋ በልባቸው እንዲጸና አለምንም እንዲያሸንፉና በእርሱ በአምላካቸው እንዲጸኑ ከእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ መመሪያዎችን እንዲሁም ከእግዚአብሄር አገልጋዮች ምክር፣ ምሪትና እርዳታ ሊቀበሉ ያስፈልጋቸዋል።
አለምን የምናይበት ትክክለኛ እይታ
ያደገ ክርስቲያን፣ በቃሉ የሚደገፍ አማኝ፣ ደቀመዝሙር የሆነ፣ አጥንት መጋጥ የሚችል፣ የጽድቅን ነገር የሚያስተውል፣ ቅድስናን መርሁ ያደረገና እግዚአብሄርን በጽድቅ ለማገልገል ሰውነቱን ቅዱስ መስዋእት ሊያደርግ የወሰነ ነው። ለዚህ አማኝ ስለአለም ያለውን ግንዛቤ ከቃሉ ለማስተዋል አዳጋች አይሆንም፤ መታዘዝ የለመደ ልቦና ስላለው ቃሉ ወደ መራው ማዘንበል ይችላል። በስጋ ያለው ግን እርሱ ጽድቅን ስለማይለይ በአለም አሰራር ይፈተናል፤ ምክኒያቱም እርሱ ገና የቃሉን ወተት የሚመገብ (ጠንካራ ተግሳጽ፣ ምክር፣ ትእዛዝ የመሳሰሉትን መታገስ የማይችል)፣ በእምነቱ ደካማ፣ ወደ ደቀመዝሙርነት ገና ያላደገ፣ የጽድቅን ነገር የማይለይም በመሆኑ እንዲሁም ጠንካራ የቅድስና ትምህርትና መርህ በህይወቱ በሙላት ስለማይገለጥ በአለም ሊፈተን ይችላል።
ደግሞ በስም ብቻ ክርስቲያን የተባለ ነገር ግን ህይወቱን በባዶ ልፋት የሚመራ፣ እግዚአብሄር በማያውቀው መንገድ ላይም የሚጓዝ ከአለም ጋር ፍርድ ውስጥ ያለ አለ። የጌታ ቃል ግን፦
‘’ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?’’ ይላል (1ዮሃ. 5:4-5)።
በአለም መንፈስ ላይ የሰለጠነ ህይወት የሚያሳየው አዲስ ባህሪይ አለ፦ በቃሉ ላይ የተደገፈ አዲስ ግብ ያለው፣ በመንፈስ ምሪት አማካይነት አዲስ ዓላማና አዲስ ራእይ የተቀበለም ነው። በአለም ያለውን ምኞትና አምሮት ያሸንፍ ዘንድም እለት እለት ወደ አምላኩ የሚቀርብበትን ጸጋ ከእግዚአብሄር የሚቀበል ይሆናል።
‘’ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።’’ (1ዮሃ. 5:18-19)
ከእግዚአብሄር የተወለደ ሰው በመንፈስ የሚቀበለው አንድ ጸጋ ስለሚያግዘው አለምን የሚመለከተው የህይወት ህግ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል ነው። ስለዚህም መንፈሳዊ ሕይወቱንና እድገቱን ለመጠበቅ፣ ራዕዩን ግልጽ ለማድረግ እና ጌታውን በታማኝነት እና በቅድስና ለማገልገል፣ ከዕለት ወደ ዕለት ከዓለም ንክኪ ራሱን እያነጻ ይኖራል።
አለምን የመረጠ ሰው በመልክዋ ጉልበት ይታለላል፣ አለም ወደ ራስዋ በመሳብ በጉልበትዋ ብዙዎችን አንበርክካለችና። በተለይ የምትበረታው በርስዋ ላይ በተነሱና ጽድቅን በመረጡ አማኞች ላይ ነው፤ በርስዋ ዘንድ ያለውን ሁሉ በመንፈግና የማትመች በመሆን ፊታቸውን ያዞሩ ቅዱሳንን ትቀጣለች። ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ የሰጠን ተስፋ በአሸናፊነት ያቆመናል። እንዲህ ስላለ፦
‘’ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።’’ (ዮሃ. 15:18-19)