እግዚአብሄር ሲመለከት አለማዊነትን ከሃጢያት አለያይቶ አይደለም፤ ያም ሆኖ ቤተክርስቲያን አለማውያንን ለማዳን ስትል በርዋን አስፍታ ከፍታ በርህራሄ እንድትቀበላቸው እግዚአብሄር ፈቅዶአል። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ነፍስን ለማዳን ባቀደችው አካሄድ ውስጥ ልትጠነቀቅና አለማዊነት እንዳያጠምዳትና እንዳይረባባትም በመጠባበቅ ተልእኮዋን ልትፈጽም ተገቢ ነው፤ ሰይጣን ሾልኮ ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ አለማዊነትን ይዞ ስለሚገባ መንፈሳዊ ህይወትን በመበረዝ ቤተክርስቲያንን ያዳክማል። አለማዊነት የተቆጣጠራቸው አማኞች ሲበዙ ጽድቅ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ያኔ ቤተክርስቲያን ሃይል አልባ ሆና ተልእኮዋን መወጣት ያዳግታትና ጉዞዋን ታቆማለች። ይህን አብዝታ በመጠንቀቅ በእግዚአብሄር ህዝብ ላይ ክፉ መንፈስ እንዳይገዛ ቤተክርስቲያን ማስተማርና ቃሉን መስበክ ይገባታል።
‘’ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።’’ (ገላ.1:5)
እኛ አማኞችን በሙሉ አለም ከተሸከመችው የፍርድ ክፋት እንዲታደገን ጌታ ኢየሱስ ደሙን እስከማፍሰስ ደርሶአል፣ ስለዚህ ዳግመኛ በአለም አሰራር ሲያዝ የጥፋት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ልብ ማለት ይገባናል። በጎ ካልሆነ ነገር ግን ክፉ የዓለም መዘዝ ባለው ኑሮ ላይ ተጣብቀን ብንገኝ እንደምንጠፋ የተገለጠ ነው፣ ኢየሱስ ግን ከዚያ ያድነን ዘንድ በእኛ የፍርድ ቦታ ሆኖ ሞተ፤ ከዚህ ከተፈረደበት ክፉ ዓለም ጥፋት ያድነን ዘንድ በርህራሄ የተመለከተን ጌታ ስለ ኃጢአታችን ራሱን አሳልፎ ስለሰጠ የመዳን እጣ ፋንታ ሊደርሰን ችሎአል። ይህ መዳናችን ዋስትና ሆኖ ከሚመጣው የአለም ቁጣ ይታደገናል። እንግዲህ በቀረልን ዘመን በጌታ ሆነን የእርሱ የጽድቅ እቃ መሆን አለብን።
አለማዊነት ኮትኩቶ ባሳደገው ለአምላክ የማይመች መጥፎና ጠማማ ትውልድ መካከል ስንኖር በብዙ የማይመቹ ልምምዶች እንከበባለን፣ በልቦና አሳባቸው ተጽእኖ ስር እናንልፋለን፣ እንፈተናለን፣ እንተቻለን፤ በፍትጊያውም ብዙ መልካም ነገሮችን እንነጠቃለን፤ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ማለፍ እንዲገባን አስቀድመን ማወቅ ለአእምሮና ለልብ ዝግጅት የሚረዳ ነው።
ነገር ግን ከዚህ አድካሚ ጉዞ በላይ ጎልቶ የሚታይ ነቀፋ የሌለው ህይወት እየኖርን በውስጥ ይዘታችን የዋሆችና ጽድቅ ያሸነፈው ማንነት ያለን ልንሆን ይገባል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ነውር የሌለባቸው ታዛዥ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ጸጥታ ያለበት፣ የተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት መኖር አለብን፤ በዚህ ማንነት ውስጥ በኢየሱስ ከመታመንና እርሱን ከመጠባበቅ ባለፈ ማንጎራጎር ሳይኖር ክፉ አሳብ ሳይገዛንም ልንኖር ተጠርተናል፤ በዚህ ሁኔታ አለማዊነትን አሸንፈንና እንደ ክርስቲያን በአለም ያሉ ወገኖቻችንን በርህራሄ እየተመለከትን፣ በእነርሱ መካከልም የሕይወት ቃል እያቀረብን ስንኖር በዓለም እንደ ብርሃን እንደምንታይ ቃሉ ይመሰክርልናል።
‘’በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።’’ (ፊል. 2:16-17)
በአለም የገዛው ስጋዊ ምኞት ጽድቅን ለመመኘት የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥር ወይም ለበጎ ነገር መቅናት የሚያስተምር ሳይሆን በክፉ ምኞት ስር እየሰደድን እንድንሄድና በክፉ መናፍስት አሰራር እንድንጠቃ የሚዳርግ ልማድ አለው። እኛ ግን ለአለም የምንሸነፍ ሳንሆን በአለም ለሚኖሩ እየራራን፣ እነርሱን ለመቀበልም የዋሆች ሆነን (ነገሮችን ሁሉ በቅንነት እያየንና እያደረግን) እንድንሰማራ ይጠበቅብናል። አለምን አሸንፈን በመቆም ሌሎችም አሸንፈው ከግዞታቸው እንዲወጡ ለማድረግ ምሳሌ የሚሆን ህይወት መኖር አለብን።
‘’ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ’’ (2ጢሞ. 2:22-23)
ሃዋርያው በመልእክቱ ወጣቱን አገልጋይ አጥብቆ የሚመክረው ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ሽሽ በማለት ነው፤ የጎልማሳነት ምኞት ስሜት ተኮር ስለሚያደርግ፣ ማስተዋል የጎደለው አመለካከት ስላለበትም ያን ነገር እንዲጠነቀቀው ያሳስበዋል። እርሱ ከዚህ ክፉ የጎልማሳነት ምኞት እንዲርቅና እንዲሸሽ ያስቸኮለው ውጤቱ አስከፊ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፦
‘’ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።’’
1ዮሃ. 2:17-18 ላይ የሚገኝ ቃል በአለም ስለሚገለጡ ነገሮች ጥብቅ ማሳጠንቀቂያ ይሰጣል፦ አለም በሰይጣን የተቀናጀ መንፈሳዊና ስጋዊ የሆኑ አሳቦችና ድርጊቶች የያዘ ስርአት ነው፤ ይህ የረቀቀ መንፈሳዊ የክፋት አሰራር ተደራጅቶ የሚገልጥበት ስርአት ከያዘን ወዲያ በቀላል የማንወጣው፣ በቀላል የማናመልጠው፣ በቀላልም የማናሸንፈው ሂደት አለው፤ ቃሉም ይህን ስርአት እንደተራ ገጠመኝና ኑሮእንዳንቆጥርና ራሳችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ የአለምን ባህሪ አጉልቶ ያሳየናል። ቃሉ እንዲህ ይላል፦
‘’ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።’’
ደግሞ ልብ ሊባል የሚገባ አንድ ነገር አለም በሰይጣን አሰራር የተሸነፈ የሰው ልጅም መሆኑን ነው፤ የሰይጣን ስውር እጅ በተጽእኖ የሚንቀሳቀስበት የአዳም ዘር ሁሉ ነው፤ በአጋንንት ባህሪያት የተዋጠ ስብእና የነገሰበት ነው፤ ሰይጣን ለሰው እንደየስሜቱ፣ እንደየአምሮቱና እንደየምኞቱ የተቃኘ ስርአት ዘርግቶ ስጋ ለባሽ እንዳይነቃ በሞት ውስጥ የሚያስተኛበት አሰራር የዘረጋበት ነው። አለምን ያልተረዳን ሰዎች ብንሆን እንኳን ፈጽሞ አንፈልገው፤ አለም በሰይጣን የተሸነፉ ሰዎች የተቆጣጠሩት ስርአትም በመሆኑ አለማዊ ሰዎች የሚሆኑትን፣ የሚያደርጉትንና የሚመኙትን አንከተል።
በአለም ውስጥ ገዢ የሆነ ልምምድ አለ፣ ያም ልምምድ የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ሲሆን ሁሉም አለማዊ ሰው ኑሮውን ያያያዘው ከነዚህ ነገሮች ጋር ነው፤ መነሻውና መዳረሻው በዚህ አስተሳሰብና ድርጊት የተያዘ ሰው ስለእግዚአብሄር ነገር ማስተዋል ፈጽሞ ይሳነዋል፤ አእምሮን የሚያሸንፉ፣ ልብን የሚዘጉ፣ ነፍስን የሚረቱ መሆናቸውን አዳምና ሄዋን ላይ የሆነውን ያስታውሱናል፤ የአለም ፍቅር መሰረቶችም ጭምር የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ናቸው፤ እነዚህ የአለም መሰረቶች ከእግዚአብሄር ፍቅር የሚለያዩ ናቸው፣ የሰውን ስሜት የሚረቱ ናቸው፣ ልብን ከእግዚአብሄር ስለሚያርቁ ሰውን ከሰው ያፎካክራሉ፣ ያከራክራሉ፣ ያጣላሉ፣ ያጠላላሉም፤ እግዚአብሄርን እንዳንወድና የሚታየውን አለም የሙጥኝ እንድንል፣በዚያም እንድንዘፈቅ ያደርጋሉ።
‘’በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።’’ (2ቆሮ. 11:1-3)
ሄዋን በሰይጣን ተንኮል በአይን ማባበል በኩል ስለተታለለች ውስጥዋን ሰይጣን በገዛበት ምኞት በኩል ሊጥላት በቅቶአል፤ ለአምላኩዋ የነበራት ቅንነት የተከለከለን ነገር ተላልፋ በማድረግዋ ወዲያው ተበላሸ፤ በአይንዋ በገባ የመብላት ምኞት ሃጢያት ላይ ወድቃለች። ዛሬም ያ ሃጢያት የሚስብ ድርጊት አለምን አሸንፎ ተንሰራፍቶአል፤ ስለዚህ ማንም ሰው ልቡን ወደ አለም ካዘነበለ በዚያ መንፈስ መያዙ አይቀርም፤ በዚያ ምክኒያት አለምን እንዳንወድ ተመክረናል።
እግዚአብሄር በአለም ለተሸነፍነው የሰው ልጆች የምስራች አለው፣ እንዲህ ሲል፦
‘’ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።’’ (ቲቶ. 2:14-15)
ሰይጣን ሰው የሚወድቅበትን ማባበል/ሽንገላ ወደ አለም ሲያስገባና የመለያየት ስራን ሲሰራ እግዚአብሄር ደግሞ ሰው ወደ እግዚአብሄር የሚመለስበትንና ከዲያቢሎስ ስራ የሚድንበትን አንድ አሰራር ወደ አለም አስገብቶአል። ሰይጣን በአይናችን ላይ መንፈሳዊ አሰራሩን ሰርቶ እንደጣለን እግዚአብሄር ደግሞ በልጁ በኩል በሰራው የመስቀል ስራና በሰጠን የጸጋ አሰራር መድህን አመጣልን፤ ከዲያቢሎስ የመነጨው የሃጢያት መንፈስ እንደገደለን ሁሉ ከእግዚአብሄር ወጥቶ ወደ ህይወታችን የፈሰሰው የጸጋ መንፈስ ሊያድነን በቃ፤ ይህ የእግዚአብሄር አሰራር ከሰው እርዳታ የሚፈልግ ሳይሆን ሰውን የሚረዳ ነው፤ ባለፉት ዘመናት ከክርስቶስ ውጪ በነበርንበት ጊዜ ሁሉ የሰይጣን መንፈስ ደግም ደጋግሞ ስላጠቃን ከርሱ በታች ባሪያ ሆነን ኖረናል፤ የእግዚአብሄር ቸርነት ሲገለጥ ግን የመጣው የርሱ ጸጋ ነጥቆ አወጣን፣ አዲስ ህይወት ሰጠን፣ ከባርነት ነጻ አደረገን፣ ከሰይጣንና ከአለም ተጽእኖ ፈታን።
የእግዚአብሄር ጸጋ በዋናነት ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ከላያችን የማራገፍ ጉልበት ሲኖረው እኛም ዳግመኛ በርሱ እንዳንያዝ ይልቅ እርሱን ክደን በነጻነት እንድንኖር የማብቃት ስራ ይሰራብናል። ከሰው ላይ የሰይጣንን ሽንገላ የጣለ ብሩክ ጌታ እለት እለት ሊፈልግ፣ በጽድቅ ህይወት ውስጥ መገለጡን መጠባበቅም ሰው እንዲችል ጸጋው ያስችላል። ጸጋ ከሌለን ግን በአለም ስርአት ማነቆ በቀላሉ እንያዛለን፣ ያን የሰይጣን አሰራር ልናመልጥ ከተመኘን ግን የሚበልጥ መንፈሳዊ ጉልበት ከጸጋው ብቻ ማግኘት ይገባናል። ዳግመኛ በሃጢያት ወጥመድ እንዳንወድቅ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንድንኖር ጸጋው ህሊናችን ላይ ይደውላል፣ ልባችን ላይ ይናገራል፣ የነፍሳችንን ስሜት፣ አሳብና ፈቃድ ወደ እግዚአብሄር አሰራር ይመራል።
እንዴት በቅድሚያ ዳንን ስንል ራሳችንን እስቲ እንጠይቅ? ለመዳን የሆነልን ሁሉ መነሻው ቃሉን በመጀመርያ የሰማን ሰአት ላይ የተገለጠ መለኮታዊ አሰራር በመኖሩ ነበር፤ የዚያ መለኮታዊ እርዳታ መገለጥ ከአለማዊ ድርጊታችን እንድንገታ አድርጎአል፤ በዚያም የገባንበትን ጥፋት እንድንመለከትና ከዚያ መንገዳችን እንድንመለስ ንሰሃም እንድንገባ ወደ ጸጋው አሰራር አስገብቶናል፤ ያ ንሰሃ ወደፊት አምጥቶን ጌታን በእምነት እንድንቀበለው በሩን የሚከፍት ነው፣ ንሰሃና እምነትም በጸጋው እርዳታ ወደ ዳግም ልደት አሰራር የሚያደርስ ታላቅ በር ሆኖልናል። የዳግም ልደት ትልቁ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፤ ከውሃና ከመንፈስ እንድንወለድና የእግዚአብሄር ልጆች እንድንሆን ያስተማረው ጌታ ኢየሱስ ራሱ ነው፤ የቀድሞው ልደት ከአዳም ስለነበረ እዚሁ ምድር ላይ በጠፋው አለም ውስጥ ያልጽድቅ የመኖር እድል ላይ ጥለውናል፤ በኢየሱስ ስም ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ስንወለድ ግን ከሰማያዊው አባት ጋር የምንኖርበትን ጸጋ አገኘን። ያን የመዳን መንገድ ማንም ቸል ሊለው አይገባም፤ ምስጢሩ ከአለም ጥፋት የሚያድን፣ ከአጋንንት እርግማን የሚያስመልጥ፣ ከጌታ ጋር የሚያኖር ጸጋ ነውና። የተገለጠው የመዳን አሰራር ይህ ነው፦
‘’ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት። ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።’’ (ሃስ. 2:38-39)
ይህ የጸጋ አሰራር ነው፤ ለሰው ልጆች በሞላ ተሰጥቶ የነበረው የተስፋ ቃል በተግባር የተገለጠበት ስለሆነም እስከ አለም መጨረሻ ሰዎችን ያድን ዘንድ በትውልድ ላይ ይሰራል፤ በዚህ መንገድ በቅርብ ላሉ እስራኤላውያን ሆነ ጌታ አምላክ ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ አህዛብ ጭምር የደህንነት አሰራር በመሆን እስከ አለም ፍጻሜ ይቀጥላል።
የተገለጠው ጸጋ እያገዘ ከአለማውያን ስብራት፣ ከጠማማ ትውልድም ልማድ የሚያድን ነው። በዚያን ዘመን የሃዋርያትን ትምህርት የታዘዙ ሁሉ ቃሉን ተቀብለው ተጠመቁ፣ በበአለ ሃምሳ በተገለጠው ጸጋም በዚያው ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ወደ እግዚአብሄር መንግስት ተጨመሩ።በሃዋርያት ዘመን የተገለጠ ጸጋ አማኞችን ከአለም የሚጠብቅና ከጌታ ጋር የሚያጣብቅ ስለነበረ የትኛውም ደቀ-መዝሙር ከአለማዊነት ስርአት በሚሰነዘር አጋንንታዊ ጥቃት አልዛለም ነበር፤ እንዲያውም መንፈሱ ሰበሰባቸው፣ቃሉ እንደሚለውም፦
‘’በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።’’
በጌታ ፊት ሃጢያትን በተሰበረ ልብ መናዘዝ ያድናል፣ የሚረዳንን ጸጋ እንድንቀበል ያስችላል፤ እግዚአብሄር ተቀብሎን እምነታችንን ይደግፋል፤ ክርስቶስም ራሱ ባነጻው ልባችን ያድራል፤ ጌታ እለት በእለት እያስተማረ፣ እየመራና በጸጋው እያዳነ ከአለም ስርአት ይታደገናል። ያመነ የተጠመቀም ስለሚድን በዚያ በኩል የተቀበለው ጸጋ ይህን አማኝ እስከመጨረሻው ይረዳዋል፣ ይደግፈዋል። በዚህ አይቆምም እድገታችን እንዲቀጥል በመንፈስም እንድንጠነክር የጸጋው መንፈስ እለት እለት ያሳድገናል። በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እጅግ የሚፈለግና የሚናፈቅ የእግዚአብሄር አሰራር ነው፤ ምክኒያቱም የእግዚአብሄር ስጦታ የተባለ ሁሉ በመንፈሱ መውረድ በኩል ስለሚመጣ ነው። ከአለም ስርአት መለየት የምንችለውም ሆነ በቅድስና በእግዚአብሄር ፊት መመላለስ የምንችለው የእግዚአብሄር መንፈስ በሃይል ሲወርድብን ብቻ ነው።
‘’ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።’’ (ሃስ. 1:9)
ይህ መንፈስ የሚያግዝና የሚያሰራ መንፈስ ነው፣ የሚጠብቅ መንፈስ ነው፣ የሚመራ መንፈስ ነው፣ የሚያሳውቅ ነው፣ አለምንና ሰይጣንን የሚያጋልጥ መንፈስ ነው፤ ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኝ መንፈስ፣ እግዚአብሄር በህይወታችን የሰራውን ስራ በውስጣችን ጠብቆ ማቆየት የሚያስችል የሃይል መንፈስ ነው፤ ያለ እርሱ ምንም ነን።
‘’ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።’’ (ዮሃ. 14:14-16)
የእግዚአብሄር መንፈስ ለሰው የሚያስፈልገውን እውቀት በሙሉ ሊያስተምር እንደሚመጣ ጌታ ኢየሱስ ቃል ገብቶአል፤ የእኛ ሁኔታ በርሱ መንፈስ እርዳታ ብቻ የሚታገዝ ከሆነ መንፈሱ ሊኖረን ግድ ነው ማለት ነው። ጌታ ኢየሱስ ያስተማረንን የምናስታውሰው፣ የምናሰላስለውና እለት እለት የምንኖረው መንፈሱ ሲኖረን ብቻ ነው፤ አለም ሁከት በመሆንዋ ከሁከትዋ ርቀን በሰላም ተሞልተን የምንኖረው መንፈስ ቅዱስ ከተሞላን ብቻ ነው፤ መንፈሱ የሌለው አማኝ መጽናት ያዳግተዋል፣ መቅረብ ያዳግተዋል፣ ማስተዋል ያዳግተዋል፣ መታመን ያዳግተዋል፤ ብዙ ነገሮችን መተግበር ስለሚያዳግተው ለአለምና ለሰይጣን እጅ ሊሰጥ ይገደዳል።
አማኝ በሽንፈት እጅ ሲሰጥ አለም ውስጥ ተጠናቆ ገብቶ ላይሆን ይችላል፤ ባለበት ሆኖ እግዚአብሄርን እያመለክሁ ነው እያለ ተሸርሽሮ ነው፣ እያገለገልኩ ነው እያለ ተነጥሎ ነው፤ እለት በእለት ሲራመድ የሚወርደውና የሚጎድለው ግን ሙሉነት እየተሰማው ሳለ ነው፣ ምክኒያቱም የአለማዊነት ጉልበት መንፈሳዊነቱን በስውር እያሳጣው ቀጥሎአልና።
‘’እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።’’ (ሃስ. 1:7-9)
እንዲህ ነው፦ በጌታ ኢየሱስ የዘላለም እቅድ ውስጥ ስለ አለም የሚነሳ ጥያቄ አንገብጋቢው ጉዳይ ሆኖ አይቀርብም፤ ነገር ግን በጊዜ የተገደበውን የሰው ልጅ ህይወት የሚታደግ ፈጣን ስራ ደግሞ ተዘጋጅቶአል፤ ይህን ተረድቶ የሚንቀሳቀስ አስተዋይ ሰው ትክክለኛ የእርሱ አገልጋይነት ክብር ይቀበላል፤ በዚያ መንገድ ላሉ ሁሉ እርሱ አንድ ነገር ሊሰጣቸው ቃል ገብቶአል፣ እርሱም መንፈስ ቅዱስ። ከተቀበልንው የመንፈስ ቅዱስ ሃይል በዙሪያችን የተኮለኮሉ ተዋጊ ሃይላትን ክንድ ይሰብራል፣ አቅማቸውን ያመክናል፣ የዘረጉትን መንገድ ይዘጋል፣ ያጠመዱትን ሰው ይታደጋል። የአጋንንት፣ የአለምና የስጋ ሃይላት የሚሸነፉልን በሰብአዊ ጉልበት ሳይሆን በመለኮታዊ ሃይል ብቻ ነውና፤ ያም በእኛ ህይወት ውስጥ የሚሰራ የእግዚአብሄር መንፈስ ሃይል ነው። ስለ ምድራዊ መንግስት ማሰብና መጨነቅ የሚኖረው ከመንፈስ ቅዱስ በፊት በድቀት ውስጥ እስካለን ነው፤ ስለ ስጋ ህይወት ማሰብና መስጋት፣ በዚህ ምድር ላይ ስለሚኖረን ቆይታ አብዝቶ መጨነቅና መቆዘም ያለው ከመንፈስ ቅዱስ መሞላት በፊት ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ከወረደብን በሁዋላ የመንፈሱ ሃይል አሮጌውን አስተሳሰብና ድርጊት ከላያችን ስለሚጥለው አሸናፊ ህይወት መምራት እንጀምራለን፤ ከሃይል በሁዋላ የአሳብ ጥራት አብዛኛው መንፈሳዊነትን በሚያማክል እሳቤ ላይ የተቀመጠ ይሆናል፤ ማወቅ የሚገባንን እንጂ የማይመለከተንን ይዘን እንድንቆዝም አያደርግም፤ ትክክለኛው የእግዚአብሄር አላማ በመንፈሱ በኩል ስለምንረዳ በማይገቡ ነገሮች ላይ ጊዜ አናባክንም።
በሚያስደንቅ ሁኔታ ሰው ወስኖ ፊቱን ወደ እግዚአብሄር ከመለሰበት ጊዜ አንስቶ ከአለም ጋር ቅራኔ ይጀምራል፤ አለማዊነት የተቃርኖ ትግሉ ይሆናል። አለም የምታቀርበው ስጦታ ጠላት ይሆነዋል። አለማዊነትም አይቆምም፣ በተለያየ የህይወትና የማስተዋል ደረጃ ሰዎችን ይፈታተናል፤ በእያንዳንዱ የህይወት እርምጃ ውስጥ ተገልጦ ይነቀንቀናል፤ ያለነው በአለም ስለሆነ፣ ግንኙነታችን በአለም ካሉት ጋር ስለሆነ ተጽእኖው ፈጽሞ አይጠፋም፤እንዲህ ሆኖ ቢታገለንም ግን አንርሳ፣ የጌታ ኢየሱስ አሸናፊ ሃይል ሊረዳን ይችላል፣ እርሱ ራሱ ስላለ፦
‘’በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።’’ (ዮሃ.16:33)