የነጻነት ትርጉም
የነጻነት ህይወት ትክክለኛ ትርጉም በኢየሱስ የሚገኝ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጆች በነጻነት ከአምላካቸው ጋር እንዲኖሩ የነጻነት መንገድ ሆነ። ሰዎች በህሊና እየተመሩ ከሚኖሩበት ነጻ ህይወት ተገፍተው ወጥተው በዲያቢሎስ ጫና የእርሱን ፈቃድ ይከተሉና ይፈጽሙበት የነበረው ብዙ ሺ ዘመን ያበቃው በነጻነት የሚኖሩበትን መንገድ ጌታ ኢየሱስ ስለገለጠው ነበር፤ ያን የነጻነት ህይወት ሰዎች ሁላችን ልንኖር ክርስቶስ ሃጢያት ከሚባል የሰይጣን የባርነት አገዛዝ ሊያወጣን ራሱን ለሞተ አሳልፎ ሰጥቶአል፤ ሃጢያት በጌታ ኢየሱስ ደም ብቻ የሚወገድ በመሆኑ ይህን ስራ ለመስራትና የዲያቢሎስን ማስደንገጫ፣ ማሸማቀቂያና ማሰሪያ ሃይል ሊያስወግድ በመስቀል መሞት ነበረበት፦
ገላ.5:1-4 “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።”
የእግዚአብሄር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የተወለዱ ከባርነት እስራት ነጻ የወጡ ናቸው፤ በአለም ያሉ ሰዎች ግን በዲያቢሎስ አገዛዝ ስር በመሆናቸው በሕይወታቸው ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት የታሰሩ ናቸው፤ ጌታ ኢየሱስ በሥጋና በደም መጥቶ የዲያቢሎስን ስራ (ሃጢያትን) አፈረሰው፤ በእርሱ የሚታመኑ ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነጻ በመጣታቸው የርሱ ዛቻ (ስለሃጢያት በሚሆን ማስፈራራትና ክስ በኩል) አያስፈራቸውም።
ጌታ ኢየሱስ እኔ መንገድ ነኝ ባለው መሰረት ከእግዚአብሄር ጋር በአባትነትና በልጅነት ቅርበት መገናኘት እንድንችል አድርጎአል። ይህ ነጻነት ቀድሞ በእኛ ህይወት አልነበረም። በእግዚአብሄር ቁጣ ስር ሆነን ፍርድ ስንጠባበቅ ከዚያ አስመለጠን፤ ከዚያ አልፎ የእግዚአብሄር ወዳጅ እስከመባል አደረሰን። ይህ ነጻነት በጦር ውጊያ አይገኝም፤ በሰዋዊ ጉልበት፣ ብልሃት፣ እውቀት፣ ምርምር፣ ፍልስፍናና የመሳሰለው መንገድ አይገኝም። ለዚያ ነው የሰው ልጅ በራሱ መንገድ መፈታትና ከአምላኩ ጋር መገናኘት የማይችለው።
ዕብ.2:14-15 “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።”
ሰው የተባለ በሙሉ በሞት ፍርሃት ባርነት ስር ነው፤ የሞት ፍርሃትን ያመጣውም ከዲያቢሎስ ወጥቶ ወደ አዳምና ሄዋን የገባው የሃጢያት መንፈስ ነው። ይህ የሃጢያት መንፈስ የሰውን ልጅ በሙሉ በሕይወቱ ዘመን ነፍሱን እያስበረገገ ድንጉጥና ፈሪ አደረገው። ነፍሱን አንቆ ስለያዘ ማምለጭ የለውም፣ በእግዚአብሄር ፊት እርጉም አድርጎ ያቆመው ይህ የሃጢያት መንፈስ ህሊናው ላይ፣ ነፍሱና መንፈሱ ላይ ስለተጣበቀ ማምለጫ የለውም።
የጌታ ኢየሱስ ሥጋና ደም እንደ ሰዎች ያለ ስላልሆነ በሞት ፍርሃት ባርነት ሊገዛ አልቻለም፤ በእስራት ስር ሊወድቅም አይችልም፤ ነገር ግን ስጋው በመቆረሱ በምድር ላሉ የሰው ልጆች የእርቅ መንገድ ሆኖ ከእግዚአብሄር ጋር መገናኛ መካከለኛ ሆነ፣ የፈሰሰው ደሙ የሰውን ሃጢያት በማስወገዱ ያለ ነቀፋና ያለ ፍርሃት የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣንን ሰጠ፤ የእግዚአብሄር ልጆች የዲያቢሎስ አገዛዝ አይገዛቸውም፣ አይመራቸውም፣ አይሰለጥንባቸው፣ ነፍሳቸው ከዘላለም ሞት በማምለጥዋ በርሱ ማስፈራሪያ የምትደነግጥበት መንገድ ተዘግቶአል፤ የጌታ ኢየሱስ ዋስትና ለዳኑት ማረጋገጫና ትምክህት ነው፦
ዮሐ.3:14-15-21 “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።”
በእርሱ በሚያምን ለምን አይፈረድበትም? ምክኒያቱም አድነሀኛል ብሎ ተቀብሎታልና፤ ነገር ግን የጠፋውንና በዲያቢሎስ የሞት ወጥመድ ውስጥ የተገኘውን የሰው ልጅ ሊያድን ክርስቶስ በመሰቀል መሞቱን ያላመነ ያንን የሞት ወጥመድና ፍርሃት ማምለጫ የሆነ የመስቀል ስራ ባለመቀበል እምቢታው ቢጸና ፍርዱ (የሞት እስራቱ) እንደሚጸና እርግጥ ሆኖበታል።
በጌታ ነጻነት የስጋ አርነት ማለት አይደለም፤ ስጋ አርነት ሲያገኝ የስጋ ስራ የተባሉ ከእርሱ የሚመነጩ ሃጢያትና መተላለፎችን ይወልዳል። የስጋ ስራ የሚባሉት ልምምዶች ከውስጣችን የሚመነጩ ልዩ ልዩ ሃጢያቶች ናቸው። የስጋ ስራዎቻችን የነፍሳችን ማሰሪያዎች የህሊናችንም መተብተቢያዎች ናቸው፤ በነርሱ ታስረን የአምልኮ ነጻነት ሳይሆን ክስ ነው ያለው፣ በግድ ብናመልክ ጠብ የሚል መንፈሳዊ በረከት ግን የለም፣ የእግዚአብሄር መንፈስ አይወርድልንምና።
የስጋ ስራ የነፍስ ስጋት ነው፤ ከህሊና ጋር የሚያታግል ነው፤ በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ሲመጣም ያጎሰቁላል፤ ሰው ተፈትቶ እግዚአብሄርን እንዳይጠራ፣ ወደ እርሱ በተፈታ መንፈስ እንዳይቀርብም ያደርጋል። በሰው መንፈስ ላይም በጠላትነት ይነሳል። የመርጨት ደም ግን መንፈስን፣ ነፍስን ህሊናንና አእምሮን የማንጻት ሃይል አለው።
1ዮሐ.1:7-8 “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።”
በብርሃን ካለን እኮ ነጻ ነን፣ ነጻ ሆነን እያንዳንዳችን ከእርሱ ከአምላካችን ጋር ኅብረት አለን፤ በኃጢአት ታስረን ግን እንደተፈታን ብናስመስል ራሳችንን እናስታለን፣ እናታልላለን፤ ይልቅ በኃጢአት ውስጥ መሆናችንን ተቀብለን አምላካችንና አባታችን ፊት በንሰሃ ብንቀርብ ያለጥርጥር በደሙ ያነጻናል (ነጻ ያወጣናል)፣ ዳግም ወደ ህብረቱም እንመለሳለን።
የእኛ እስራት (በሌሎች ላይ)
ሌሎችን ያሰሩ ሰዎች ራሳቸው ከእስራት ነጻ መሆን እንደማይችሉ ቃሉ ይናገራል፤ በኢሳ.58:6 ላይ በነጻነት እግዚአብሄር ፊት እንቀርብ ዘንድ የባልንጀሮቻችንን እስራት ልንፈታ የግድ እንደሆነ ይናገራል፦
“እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?” የላል።
እግዚአብሄር ነቢዩ ኢሳያስን ጠርቶ በኃይልህ ጩኽ አለው፤ ዝም አትበል ድምጽህን አትቈጥብ አለው፤ በተሳሳተ አካሄድ ውስጥ ላለ ህዝቤ ትናገር ዘንድ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ (ከፍ አድርገህ ጩህ) አለው፤ ለምን? እግዚአብሄር ሕዝቤ ያላቸው ወገኖች በመተላለፋቸው ላይ ተቀምጠዋልና፣ ያላስተዋለው ኃጢአት በያዕቆብ ቤት ነግሶም ነበር። ህዝቡ ነጻ እደሆኑ ሁሉ ዕለት ዕለት ይሹት ነበርና እግዚአብሄር አዝኖአል፤ እስራታቸውን አላወቁም፣ ያሰሩትንም ወንድማቸውን አላስተዋሉም ግን ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይሹ ነበርና እግዚአብሄር አዝኖባቸው ነበር፤ መንቀሳቀስ አይችሉም ግን ከእስራት ነጻ የነበሩ ስለመሰላቸው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ወደዱ። እንዲያውም በመንገዳቸው ላይ እርሱ ያለመገኘቱ ደርሶ አሳስቦአቸዋል፣ በአምልኮአቸው መሃልም እርሱ አለመመላለሱ ጥያቄ እንዲጣይቁት አድርጎአቸዋል
“ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ።”
እግዚአብሄርም ተሳስራችሁዋል ነበር መልሱ።
ኢሳ.58:4-7 “እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?” ሲል በጥያቄ ይመልስላቸዋል።
ዳግመኛ ባርነት?
እየደጋገመ የሚያጠቃ ጠላት የከፋ ጠላት ነው፤ በእርሱ ምክኒያት ነጻነት ፈጽሞ ሊገኝ ስለማይቻል አሳሳቢ ነው። አርነታችንን የማይሻ ጠላት አለን፣ ሁልጊዜ ድካማችንን እያመሃኘ ይመጣል፣ ድንኩዋናችን ይገባል፣ ማስቀመጥ የፈለገውንም በዚያ ትቶ ይሄዳል፤ እኛም በዚያ ምክኒያት እንደተጣላንና እንደጠላን፣ እንዳለቀስን፣ እንደነፈረቅን፣ እንደቆዘምንና እንዳነከስን እንቆያለን፤ ቸሩ አምላክ እንዴት ደግ ነው፣ የርሱ ደም መጥቶ የማያነጻን ቢሆን ኖሮ እስከምን ያህል ርዝመት በዚያ ህይወት መቆየት እንችል ኖሮአል?
የእስራኤል ንጉስን ግን እንመልከት፦ ይህ ንጉስ ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ ባለመቻሉ ጠላት ደጋግሞ ያጠቃው ያዘ፤ እርሱ ግን የንሰሃ መንገድን ሊከተል አልቻለም፣ እንዲያውም በሃጢያቱ ገፋበት፣ ከእግዚአብሄር ጋር እልህ ተጋባ፣ ግን ህይወቱ፣ ንግስናው፣ ህዝቡም ጭምር እስከመጨረሻው ሊሰምርላቸው አልቻለም፣ መንገዱን አላወቀምና፦
2ዜና.28:16-25 “በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። ደግሞም ፍልስጥኤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። የይሁዳም ንጉሥ አካዝ እግዚአብሔርን ክዷልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቆአልና እግዚአብሔር ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው። የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኵሌታውን ገፈፈ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን አንዳች አልተጠቀመበትም። ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ እግዚአብሔርን መበደል አበዛ። ለመቱትም ለደማስቆ አማልክት፦ የሶርያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን ይረዱ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ። አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ። በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ፤ የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።”
በእግዚአብሄር የዳነ ህዝብ የተቀበለውን የሚያጸናበትን መንገድ ከመከተል ውጪ አዲስ ነገር እንዲሻ ቃሉ አይመክረውም፤ የእግዚአብሄር ቃል ፋሽን አይከተልም፣ ስለዚህ በዘመናት መለዋወጥና በትውልዶች መቀያየር ምክኒያት ቃሉ አሳቡን አይለዋውጥም፤ መለወጥ ካለባቸው እንደ ዘመኑ የሚቀያየሩት የሰው አሳቦች ናቸው። አማኞች ግን በቃሉ ላይ እርግት እንዲሉና ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ በእግዚአብሄር ዘንድ የተጠበቁትን የርሱ ስጦታዎች እንዲሹ ይጠበቅባቸዋል።
እግዚአብሄር የእስራኤልን ባርነት በሰበረ ጊዜ ዳግመኛ ወደ ወደቁበት አገዛዝ እንደማይጋዙ በእርሱም በነጻነት እንደሚኖሩ ተስፋ ሲገባላቸው እነርሱም በተመለሰ ልብ በምድራቸው ላይ ሊኖሩ ያስፈልግ ነበር፦
ዘካ.8:13-15 “የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ።”
የአዲስ ኪዳን ወገኖችም የዘላለምን ርስት ከተቀበሉ በሁዋላ በእርሱ ሆነው በእምነት እንዴት በመጽናት መኖር እንዲገባቸው ቃሉ በስፋት ያስተምራል።
ገላ.4:7-13 “ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም።”
ክርስቲያን ዳግም ከእግዚአብሄር ተወልደሃልና ከሃጢያት እስራት ነጻ ነህ፣ ልጅም ነህ እንጂ በሃጢያት እስራት ስር እንዳሉት አህዛብ ባሪያ አትባልም፤ አህዛብ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆነው የሚገዙ ናቸው፣ እነርሱ አማልክትን ይፈራሉ፣ ለፈቃዳቸውም ባሪያ ናቸው፤ አማኞች ግን በእግዚአብሄር በልጅነት ደረጃ ስለታወቅን የርስቱ ተካፋይ ተደርገናልና ከጣኦታት ጋር የሚጋጠም የጋራ ነገር የለንም፣ በዚያም አርነት ምክኒያት የጌታ ነጻ ሆነናል፤ ከዚህ ከፍታ ሲያወርድስ? ዳግም ወደ ደካማ፣ ወደሚናቅ ስርአት ውስጥ ስለምንወርድ ዳግመኛ በባርነት ለመገዛት እንገደዳለን፤ እነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ውድቀት የሚያሳዩ ናቸውና ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻሉ።
ለመፈታታችን ምስጋና ይድረሰው
እግዚአብሄር ከምንም በላይ በአምላክነቱ ምስጋና ይግባዋል፦ ፈጣሪ ነው፣ ህይወት ሰጪ ነው፣ አዳኝ ነው፣ መድሃኒት ነው፣ መከታ ነው፣ መጠለያ ነው..፤ ሌሎች ገዢዎች አምላክ ሳይሆኑ ያመለክናቸው አገዛዛቸውን ጭነውንብን ስለነበር ነው፤ ጌታ ኢየሱስ ግን ደሙን አፍስሶ ካገዛዛቸው ነጻ አወጣን፣ በገዙን ላይም ገዢ አደረገን፦
– ስለዚህ ምህረትን አድርጎልናልና እናመሰግነዋለን
– ቀንበራችን በእርሱ ስለተሰበረ እናመሰግነዋለን
– ወጥመዱ በእርሱ ስለተሰበረለት እናመሰግነዋለን
– ቀስት በእርሱ ስለተቆረጠለት እናመሰግነዋለን
– ስለባረከን እናመሰግነዋለን
– ምህረቱን ስላገነነልንም እናመሰግነዋለን።
“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል፦እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥ቍጣቸውን በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፤ በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር። ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ። ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን። ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።” (መዝ 124:18)