ነጻ የወጣ ህዝብ[1…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የባርነት ሸክሞች ነበሩ…
እነዚህ ሰውን የሚያጎብጡ፣ የሚያስሩ፣ የሚያስጭንቁ፣ የሚያውኩ ነበሩ። የተሸከማቸውን አያነቃንቁ፣ አያራምዱ፣ አያዘረጉ እረፍትም አይሰጡ። ጌታ ኢየሱስ ግን ከእኛ ላይ አወረዳቸው። ከሸክም በሁዋላ ጎብጦ መቅረትም አለ፣ የእስራት ጠባሳ ፈሪ አድርጎም ያስቀራል፣ የሚያስጨንቁም ለቀው ቢሄዱም በሩቅ ቢያስፈራሩ ዋስትናችን ጌታ ኢየሱስ ካለን ብቻ መፍትሄ ይሰጣል፤ እምነት በእርሱ ላይ ባለን መደገፍ፣ እርሱን በህይወታችን በማንገስ፣ ይሄ ልምምድ ብቻ ከቀጠለ ነው እነዚያ የቀድሞ ገዢዎችን ፈጽሞ መጥረግ የሚቻለው።
ሸክም ባሪያ ያደርጋል። የተገዙበት ነገር ምክኒያት ሆኖ ጫናው ያስጎነብሳል። እንዳሰብነው የማንሆነው በመያዛችን ነው፣ ለመናገር የማንችለው አንድ ነገር ውስጣችን አድሮ እያነቀን ነው፣ ነጻነታችንን ከቀማን እንዴት ባለ አእምሮ ልንሆን እንችላለን?
ሸክም የስጋ ከብደት ነው፣ የስሜት ክብደት ነው፣ የአሳብ ክብደት፣ የነፍስ ክብደት የመንፈስ ክብደትም ነው። በከበደን ነገር ምክኒያት ህሊናችን ሊጎዳ ይችላል፣ ስነልቦናችን ይላሽቃል፣ መንፈሳችን አቅም ያጣል (ለአምልኮ፣ ለጸሎት፣ ለጽድቅ ህይወት…)
ሸክም የከበደባቸው እስራኤላውያን ታሪክ ቀጥሎ ባለው ቃል ውስጥ ይገኛል፦
“ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም፦ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። ሮብዓም፦ ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። እነርሱም፦ ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት። እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም፦ አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች፦ አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ፦ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።” (1ነገ.12:3-11)
እስራኤል ቀንበር ከበደው እና ነጻነት ፍለጋ ወደሚመለከትው አካል ስሞታውን አቀረበ፦ በኢዮርብዓም በኩል ህዝቡ ወደ ንጉሱ ቀረቡና የአባትህን ቀንበር ከላያችን ብቻ አንሳ በቀረው እንገዛልሃለን አሉት፤ እርግጥ ነው እስራኤል በአምላኩ ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጣ ህዝብ ነው እንጂ በባርነት ቀንበር ሊጨቆን የሚገባው አይደለም፤ ነገር ግን ንጉስ ሰለሞን የእግዚአብሄርን ድምጽ ትቶ፣ህጉን ትቶ፣ ስለአባቱ የሚነገረውን የአስተዳደር ታሪክም ዘንግቶ ወደ ጣኦት ሰፈር ውስጠኛው ክፍል ስለገባ ህዝቡ ላይ የሚያደርገውን እስኪዘነጋ አስጨናቂ ቀንበር አሳረፈበት፤ ያንን በመቃወም እስራኤል ተሰብስቦ ነጻነቱን ጠየቀ።
እባክህ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ለሰለሞን ልጅ ተናገሩት። እርሱ ግን በክፉዎች ምክር ተነድቶ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ አላቸው። ይሄ ድምጽ የባርነትን ቀንበር፣ የግብጻውያንን አገዛዝና ጭካኔ ዳግም የሚመልስ እንዲያውም የሚያባብስ ሆኖ ስላገኙት ተቃወሙት፣ ተዋጉትም፤ በመጨረሻም ከግዛቱ ተለዩት፣ ዳግመኛም አይኑን ላያዩት ሸሹት።
የእግዚአብሄር ቃል መንፈሳዊ በሚመስል በሰብአዊ ተጽእኖ ስር እንዳንወድቅ ይመክራል፣ እኛን የሚገዛን ቃሉ፣ ለመገዛትና ሙሉ በሙሉ ፈቃዳችንን መተው ካለብን ለእርሱ ብቻ ሊሆን አስፈላጊ መሆኑን መመልከት እንችላለን፦
ማቴ.23:2-4 “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።”
ጻፎችና ፈሪሳውያን የሙሴን ህግ እንዲያስተምሩ ስልጣን የነበራቸው ቢሆኑም ራሳቸው ለህጉ ተገዝተው ህዝቡን መንገድ የሚያሳዩ አልነበሩም፤ ይልቅ ምላሳቸው ህጉን የሚናገር እጃቸው የልባቸውን ፈቃድ የሚፈጽም ነበረ፤ ይህም በእግዚአብሄር ፊት ጸያፍ ነበረ።
በጌታ ነጻ የሆኑ ሃዋርያት ደግሞ ህዝቡን ከህግ እስራት የሚያወጡበትን ትምህርት አስተምረዋል፤ ሸክም ከሆነ የስጋ አምልኮ ይልቅ በመንፈስ ለሆነው አምልኮ ብቻ ትኩረት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል፣መንፈስን ከሚያረክሰው ግን እንዲጠበቁ በማስገንዘብ ጭምር።
ሐዋ.15:28-29 “ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።”
ከአጋንንት ነጻ የወጣ ህዝብ እንደምን ባለ መንገድ ሸክም ይጫነዋል? በመልሱ ያን የሚያሳየን በዕብ.12:1-2 ውስጥ ያለ መልእክት ሲሆን እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦
“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”
የባርነት መንገድ
አንድ ተላላ ሰው በአንዲት አጥማጅ ሴት እጅ ወደቀ፣ ሲከተላት ምን ታደርግበታለች?
“… በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች። እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ። ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ።ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል በጎዳናዋ አትሳት። ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው።ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።” (ምሳ.7:21-27)
በቃሉ ላይ የተጠቀሰችው አሳች ሴት በአለማዊነት የሰለጠነች ሰው መሆንዋ ብቻ ሳይሆን አለም በቀጥታ የተገለጠችባት ሴት ናት። ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ አለም ለእስራት፣ ለወጥመድ፣ ለፍላጻና ለነፍስ ጥፋት አሳልፋ ትሰጠን ዘንድ በውበትዋ በማባበል ታስታለች፣ በሰጠችው ነገር ልዝብነት ወደ ጥፋት ትጎትታለች።ብዙው የአለም የሽንገላና የማባበል ጨዋታ የህይወት መስመር የሚያስትና የህሊና ሚዛንን የሚያዛባ ነው፤ ድምጽዋም የሚያባብልና በልዝብነት አለሳልሶ ልብን የሚያሸፍት ሃይል አለው። በርስዋ መንፈስ የተያዘ እንዲጠፋ ስቶ ይከተላታል፥ ይህም ለሚከተላት ለርሱ ነፍስ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻዋ ላይ ይወድቃል፤ አለም ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፣ አለምን የወደዱ ከእግዚአብሄር ጋር የተጣሉ ብቻ ናቸውና፤ እርስዋም ያን አስታክካ የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው፣ ከእግዚአብሄር የለየቻቸው ከግምት ይልቃሉ። ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው ሲልም ማንም አለምንና አለማዊን ተከትሎ ወደ ጽድቅ እንደማይደርስ እርግጠኛውን ውጤት ሲናገር ነው።
ኤር.2:19-20 “ክፋትሽ ይገሥጽሻል ክዳትሽም ይዘልፍሻል፤ አምላክሽንም እግዚአብሔርን የተውሽ እኔንም መፍራት የሌለብሽ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቂ፥ ተመልከቺ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም፦ አላገለግልም አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ።”
እስራት
በእግዚአብሄር ምክር ላይ ቸል ማለትና ትእዛዙ ላይ ማፌዝ የማይፈታ እስራት ያመጣል።
ኢሳ.28:22 “አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸንባችሁ አታፊዙ።”
እግዚአብሄር ከሌለ እስራት ነው፣ እርሱ ሲመጣ ግን ያሰሩንን ሃይላት ያስወግዳል፣ እስራታቸውንም ይፈታል፦
ኢዮ.12:18 “የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።”
እስራት እየተንቀሳቀስን እንዳለን እንዲመስለን ለዘብ አድርጎ የያዘ ነገር ነው። እንደ ወጥመድ አንቆ ስለማይይዝ የታሰረ ሰው ስለሚሄድ ብቻ ነጻ የሆነ እንዲመስለው ይሆናል፣ መስማቱ ፈጽሞ ስላልተቁዋረጠ አጥርቶ መስማት የሚችል ይመስለዋል፣ በሌላውም እንዲሁ። ከታሰርን የሆንን ይመስለናል እንጂ አይደለንም፣ የቻልን ይመስለናል እንጂ አንችልም። ለምሳሌ ለመጸለይ እንሞክራለን እንጂ ጠልቀን ወደ አምላክ መገኛ አንደርስም፣ በጽድቅ ለመኖር እንሞክራለን እንጂ ብዙ መራመድ አንችልም። ይሄንን አደጋ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ያየዋል፣ እስራታችንን ከላያችን ይበጥሳል።
ከእስራት ነጻ የሆነ ህዝብ
ቀንበርና እስራት የሰውን ልጅ የሚያስጎነብሱ የባርነት መሳርያ ናቸው፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሄር የተፈታን ህዝቦች ነን ማለት ያስጎነበሱንን ሁሉ ከላያችን አራግፎልናል ማለት ነው።
ኤር.30:8-9 “በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም፤ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሎች አሕዛብ እንደ ገና አይገዙአቸውም።”
ጌታ ኤፍታህ ብሎ የሚፈታው ህዝብ በቅድሚያ በስጋው ላይ ካለ እስራት የተፈታ ሲሆን ከዚያ በላይ ግን የመንፈሱ እስራት የወደቀለት ነው፤ ጌታ ኢየሱስ መንፈስን ሲፈታ የልብ አይኖች ይከፈታሉ፦
ማር.7:31-35 “ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ።
ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና፦ ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ።”
የጌታ መፍትሄ ሙሉ መፍትሄ በመሆኑ በእርሱ ማንነት እምነት ያላቸው ከነችግራችውም ሆነው ቢሆን ወደ እርሱ ቢቀርቡ ያዩትም፣ ያላዩትም፣ የሚያውቁትም፣ የማያውቁትም ቢሆን ሁሉም ነገር ይፈታል፣ ከነርሱ ይልቅ ስለነርሱ ይበልጥ የሚያውቅ እርሱ ነውና።
አንዲት ሴት ነበረች፤ በሰዎች ፊት ጐባጣ ሆና ትታይ የነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ የማትችልና ከአስራ ስምንት አመት ጀምራ ታስራ እንደልቧ መንቀሳቀስ የማትችል ሆና ስትሰቃይ ነበር። በሰው ዘንድ በህይወትዋ የሆነው(ያጎበጣት ምክኒያት) ግልጽ ሳይሆን የሃዘን ኑሮ ኖራለች፤ ከዚያ የድካም እስራት ማን ነጻ ሊያወጣት ኖሮአል? የመጎብኛ ጊዜዋ ሲመጣ ግን ከጌታ ኢየሱስ ጋር ተገናኘች፤ ጌታ ኢየሱስ ሲያገኛት እሱዋን አየ፣ ድካምና ሃዘንዋን አየ፣ ያደከማትን ሰይጣንም አየ፤ ሰው ውጪን ያያል እግዚአብሄር ግን ሁሉን ያያል፣ ሰው ውጤቱ ላይ እግዚአብሄር ምንጩ ላይ! ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፦ አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት (ያደከመሽን ፈታሁት አሁን ቃና በይ፣ ያጎበጠሽ ለቅቆ ሄዱዋል በሚል)፦
ሉቃ13:1017 “በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፦ አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን፦ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ። ጌታም መልሶ፦ እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው።”
በምድር ላይ የነበረው የጌታ ስራ በመንፈሱ በነብያት አንደበት አስቀድሞ ተናግሮ የነበረው ሁሉ ፍጻሜ ነው፣ በእርሱ መንፈስ ነብያት የተናገሩት ሁሉ እንደተፈጸመ ቃሉ ይመሰክርልናል፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ እንደተጻፈ በሰይጣን የታሰሩትን ፈትቶአል፣ አጋንንት አቅም ያሳጣቸውን ነጻ አውጥቶአል፤ የታሰሩ ሲፈቱ ለምስጋና፣ እውሮች የእግዚአብሄርን ማዳን አይተው ስራውን ያወሩም ዘንድ አድርጎአል።
ሉቃ4:16-21 “ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር።”
ሰንሰለቱ ስለተበጠሰለት
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሃጢያት ሊያነጻን የተሰጠን የደህንነት ጸጋ ነው፣ ይህ የሰው ደም አይደለም። እግዚአብሄር የሃጢያት ስርየት ይሆን ዘንድ ካዘጋጀው ልጁ በሞቱ የፈሰሰልን ህይወት ነው። ደሙ ከሃጢያት ሃይል ሲያነጻን ከሚታየው ስራ ጀርባ ስውር የሆነ የመንፈስ አሰራር በህይወታችን ይከናወናል፦
“እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም።ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።” (እብ.2:14-17)
እኛን ሊሆን (በስጋና በደም ሊዋሃደን) ሳይሆን እኛን ሊመስል(ቃል ስጋ በመሆን) እና መሰበር ያለበትን ከላያችን ሊሰብር፣ መበጠስ የሚገባውን ከላያችን ሊበጣጥሰው፣ በላያችን የተጣበቀውን በደሙ ሃይል አጥቦ ሊያስወግደው በመሃከላችን ተገኝቶአል። … የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።