ቸል ባይ ተዋጊ አስቀድሞ ራሱን ያስጠቃል፤ ትጥቁን ስለማይጠብቅ፣ ራሱን በአግባቡ ስለማያሰማራ፣ በንቃትና በጥንቃቄ ስለማይመላለስ እንዲሁም ቸልተኝነት ስለሚያበዛ ድንገት ጠላት ይጎዳዋል፡፡ ከራሱ አልፎም የተደገፈው ወገኑን የሚያስጠቃ ስህተት ይፈጽማል፤ ሀላፊነቱን ባለመጠበቅ፣ የተጣለበትን አደራ ባለማቆየትና ለባልንጀራው መከታ ባለመሆን ለጠላት ያጋልጣል፡፡
የምድራዊ ሀይል ከላይ እንዳለው አይነት ሽንፈት ላለማስተናገድ ሲል ቢያንስ ወደ ውጊያ የሚልከውን ወታደር ሃላፊነት/ሸክም ይሰጠዋል፤ ወታደሩ ደግሞ በተመደበበት ስፍራ እንደሚጠበቀው ሊገኝ ያ ባይሆን ግን በርሱ ምክኒያት ራሱንና ቀሪውን የጦር ክፍል ከፍተኛ ኪሳራ ላይ እንደሚጥል ጠንቅቆ ይረዳል፤ የተዋጊ ኪሳራ ቀላል ሳይሆን ከንብረት ውድመት እስከ ህይወት ማጣት የሚደርስ ነውና፡፡
ወደ እምነት መለስ ስንል በስንፍናቸው ቸል ያሉ ሰዎች በነገር ሁሉ የተጎዱትን ጉዳት የምናይ ቢሆንም ቸልተኝነትን ያራቁና በእምነት የበረቱ ቅዱሳን ተዘርግተው የእግዘአብሄርን ጦርነት በስኬት እንደተዋጉ ሲነገርላቸው የታያል፡፡ በዕብ.11:32-34 ውስጥ ቃሉ ሲናገር፡-
”እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ… ” ይላል፡፡
ብርቱዎች የበረታባቸውን አልፈውና አሸንፈው ወደፊት ሲጉዋዙ ቸልተኛ አማኞች ግን ከትኩረት ውጪ ሆነው በመደንዘዝ ለራስ ሆነ ለወገን ሳይበጁ ይወድቃሉ፡፡ ከዚህ ዞር ሲል ለከፋ ውድቀት ምክኒያትነትና የጠላት በር ሆኖ መገኘት ያጋጥማቸዋል፣ በድካማቸው በኩል አድብቶ ጠላት ስለሚመጣ ተሰውሮም ስለሚወርሳቸውና መሸሸጊያ ዋሻ ስለሚሆኑ ብርቱ ተዋጊዎችን ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ በነህሚያ ዘመን በጠላት ማባበል የተማረከ ሸማያ የሚባል ሰው የህዝቡን ጠላት ሴራ ሊያስፈጽም የሀሰት ምክር እያወራ ነህሚያን ሲያዘናጋና ህዝቡን በወሬ ሲያደክም ይታያል (ነህ.6:10-12)፡፡
አንዳንዴ መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ የሚፈጠር ስህተት ያልተገመተ ችግር ፈጥሮ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመንፈሳዊ የውጊያ አውድ ውስጥ ያለውን የጦርነት ሁኔታ ያስተዋለው ሳሙኤል ባለመጸለይና በቸልተኝነት (ለህዝቡ መንፈሳዊ ውጊያ ከመዋጋት በማፈግፈግ ) እግዚአብሄርን እንደማያሳዝን አረጋግጦአል፡፡
1ሳሙ.12:22-24 ”እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም። ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት።”
እግዚአብሔር የመረጠውን ሕዝብ ወድዶአልና ስለ ታላቅ ስሙ አይተዋቸውም። ለህዝቡ የሚያሳስብን፣ መንፈሳዊ ውጊያ የሚዋጋንና መልእክት አድራሽን ሰው በመሃከላቸው የሚያስቀምጠውም ለነርሱ ባለው ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ ከጠላት እንዲጠበቁ፣ ከእግዚአብሄር ጋር በህብረት እንዲሄዱና እንዲባረኩ በጸሎት መታጠር ስላለባቸው እንደ ሳሙኤል ያሉ መንፈሳዊ ተዋጊዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከፍተኛ መንፈሳዊ ጠላት የእግዚአብሄርን ህዝብ በሚያዋክብበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሄር ሰው ስለ ህዝቡ ቆሞ ካልተዋጋ ጥፋቱ የአካል ብቻ ሳይሆን የነፍስ፣ የመንፈስ፣ የህሊናም ጭምር ነው፣ መጨረሻውም ምርኮና ውድቀት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን የነበረው የውጊያ ዝግጅት አህዛብንና የሚያመልኩትን ጣኦት ለመዋጋት ያለመ ነበር፡፡
ነህ.4:13-15 ”ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው። አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ፡- አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው። ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፡፡”
እግዚአብሄር የእስራኤላውያን ጠላት ስለሆነው አማሌቅ ወስኖ ተናገረ፡- ሙሴ እርሱን ተዋግቶ እንዲያጠፋውና ዝክሩን ከምድረ ገጽ እንዲደመስስ አዘዘው፡፡ አማሌቅ እግዚአብሄርን የማይፈራ የእስራኤል ክፉ ጠላት ነበረ፤ ይህ የኤሳው ወገን የሆነ ህዝብ በቅርብ አድፍጦ እስራኤል በደከመና እረፍት በናፈቀበት ወቅት እንዲያርፍ ከመርዳት ይልቅ እግር ለእግር እየተከታተለ አስጨንቆታል፡፡ ዛሬ የመንፈስ አገልግሎት ባለበት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከነፍሳችን ጋር እንደ አማሌቅ ተጣብቆ በክፉ ባህሪ መንፈሳችንን የሚያስጨንቅና የሚያሳድድ ጠላት ስጋና ምኞቱ ከእኛ ጋ እንዳለ የሚታይ ነው (ገላ.5፡24-25)፡፡
ዘዳ.25:17-19 ”ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን አስብ፤ በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተስኖህ ደክመህም ሳለህ ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራም። ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንን አትርሳ።”
ጠላት በውሃና በምግብ እጥረት ተጨንቀን፣ በጸሀይ ትኩሳትም ተቃጥለን በደከምንበት ወቅት (በመንፈሳዊ ህይወት ዝለንና በአለማዊ ነገር ተጠቅተን ሳለ) ደርሶ እንዳንነሳ አድርጎ ሊፈጠፍጠን ይመጣል፡፡
የእስራኤል ልጆች ማኅበርን ጠላት ሲከታተል ቆይቶ ድንገት ደረሰበት፡፡ ህዝቡ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲና ምድረ በዳ ተነስተው ከረጅም ጉዞ በሁዋላ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ በዚያ ግን ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አላገኙም። ይህን ሲረዱ ሕዝቡ ምግብና ውሀ ሊሰጥ ወደሚችለው እግዚአብሄር መቅረብን ትተው ወደ እግዚአብሄር ባሪያ በቁጣ ተመለከቱ፣ ሙሴን በዚያ ተጣሉት። … አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር ራፊድም በሚባል ስፍራ ተዋጋ። ሙሴም ኢያሱን፡- ወጥተህ ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው።ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። … ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ ተናገር አለው። ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም ይህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፤ እርሱም፡- እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ።
በስጋ እስራኤል ለሆነው የያእቆብ ዘር አማሌቅ ሁሌም ያልተቆረጠ ጠላትነት የነበረው ሲሆን ለመንፈሳዊው እስራኤልም መንፈሳዊ ጠላት የሆነው ክፉ ሰራዊት በመንገዱ ተገዳዳሪ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ላለው ለዚህ የእግዚአብሄር ህዝብ መንፈሳዊ መሳሪያ/ የእግዚአብሄር እቃ ጦር በእምነት ይታጠቅ ዘንድ ተሰጥቶታል፡፡ የህዝቡ ውጊያ ከመናፍስት ጋር ነው፡፡ ህዝቡ ያን አስተውሎ በቀጥታ ከጠላት ከሚወረወር ፍላጻ ጋርና በተዘዋዋሪ በነገሮች መሀል ሰርጎ ከሚከሰት አጋንንታዊ አሳብ ጋር ሳያቁዋርጥ/ቸል ሳይል ሊዋጋ ይገባል፡፡
ኤፌ6:11-18 ”የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤”
የአዲስ ኪዳን የቃሉ አገልጋዮች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴና ውጊያ ውስጥ ስናልፍ ትኩረት እንድናደርግ የሚያሳዩን ዋና ነገር የሰልፍ ዝግጅት እንደነበረ ማስተዋል ይገባል፡፡ የአእምሮና የልብ ዝግጅት ያደረገ እንዲሁም የሀይል መንፈስ የተሞላ አማኝ ንቁ ሊሆን እንጂ ለቸል ባይነት ስፍራ ሊሰጥ አይገባም፡፡
2ጢሞ.4:2-4 ”ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።”
ጳወሎስ በግልጽ ጢሞቲዎስን ሲያዝ ቃሉን ስበክ አለው፤ ደግሞም ጽና (የሚያናውጥ ትምህርት ስላለ)፤ ጊዜ እየመረጥክ ሳይሆን ሁልጊዜ ለማስተማር ዝግጁም ሁን፣ ህይወት የሚገኝበትን ትምህርት መስማት የማይፈልጉ ሰዎች ሰለሚነሱ ስለነርሱ ሁልጊዜ ለመልስ ዝግጁ ሁን፤ እንዲሁም ተቃዋሚ መንፈስ ስላላቸው ያን ለመዋጋት ጠንካራ ሁን አለው፡፡
ሀሰተኞች መንፈሱ ለውጊያ ያልተነሳሳን ደካማ አማኝ በብርቱ ያጠቁታል፤ እንዲያውም በቀላል ይወርሱታል፡፡ ስለዚህ አማኞች የእግዚአብሄርን እቃ ጦር ለብሰው ለውጊያ ዝግጁ እንዲሆኑ ከጌታ ደቀመዛሙርት መማር ይገባቸዋል፡፡
በሮሜ.6:12-13 ውስጥ ሃዋርያው በምክሩ ደቀመዛሙርት ደካማ ያልተዘጋጁም ሆነው በሚሞት ሥጋቸው ኃጢአት አንዳይነገሥና ለምኞቱ እንዳይታዘዙ አስቀድመው ብልቶቻቸውን ለዓመፃ የጦር ዕቃነት ከማዋል እንዲቆጠቡ ያሳስባል፡፡ ከዚህ ይልቅ ራሳቸውንም ሆነ ብልቶቻቸውን የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርገው ለእግዚአብሔር በማቅረብ ከሙታኖች እንዲለዩ በሕይወት እንዲኖሩም ያመለክታቸዋል፡፡
በ2ቆሮ.6:7-10 ላይ ሀዋርያቶች በመንፈስ ተዋጊነት ተልኮአቸው ውስጥ ስለነበረው አካሄድ ሲመሰክሩ፡- ”በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።” ብለዋል፡፡
2ቆሮ.10:2-5 ”በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን”
ሃዋርያው ጳውሎስ ከምክሩ በተጨማሪ ለጢሞቴዎስ አንድ የሚጨነቅለት ነገር እንደነበረ በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ ገልጾለታል፡-
1ጢሞ.1:18-19 ”ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና” ሲል የሚያሳስበውን ያመለክተዋል፡፡
ቸል ባይ ተዋጊ መንፈሳዊ እቃ ጦሩን ጥሎ ራሱን እንዳያስማርክ፣ ግን የተሰጠውን ጠብቆ እንዲኖር፣ ራሱን በህሊናው እንዲመራ፣ የተጣለበትን የቃሉን አደራ እንዲጠብቅና በቸልተኝነት ተይዞ ጠላት እንዳይጎዳው ከስህተት ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ቃሉ ለዚያ አደራ ሲያኖር እንዲህ ይናገራል፡-
2ጢሞ.2:4-9 ”የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል። የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።”
ገበሬ እርፍ ይዞ ወደ ሁዋላ ቢል ኪሳራ እንዲሆንበትና ወታደር ትጥቁን ይዞ ከዘመተበት ጦር ሜዳ ቢያፈገፍግ ሞት እንዲሆንበት እንዲሁ መንፈሳዊ ሰራዊት ወደ ተጠራበት የትግል ሜዳ ገብቶ ሳለ አመንትቶ ቢያፈገፍግ በጠላት መማረክ ወይ መመታት ይሆንበታል፡፡ ተማርከንም ሆነ ተመትተን ስንደነዝዝ፣ ስንዘናጋና አሳባችንን በጠላት ስናስማርክም ማመን ሳይሆን ማልቀስ ይቀናናል፣ እንደ ያእቆብ ልጆች፡-
ዘኊ.14:1-4 ”ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ፡- በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው። እርስ በርሳቸውም፡- ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።”
ባለማመን ያስማረክነው እምነት ትቶን ከእኛ ሲጠፋ መምታታት ተሞልተን ማንን መከተል እንዳለብን ማወቅ እስኪያቅተን ግራ እንደምንጋባ ከላይ ባለው ሁኔታ ውስጥ የምንመለከተው ነው፡፡ በታጠቅነው የእግዚአብሄር ተስፋ ስንበረታ ግን ቃሉን እያነሳን በጠላት ላይ እናውጃለን፣ ያንን ነው ከነሙሴ የምንማረው፡-
ዘኊ.14:5-8 ”ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ። ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ፡- ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል።” አሉ፡፡
እግዚአብሄር አልወደደንም ወይ? እስከዚህች ቀን ድረስ አልጠበቀንም ወይ? እስከአሁን በጥበቃው ያለው እርሱ ከሆነስ ነገን ሊጠብቀን አይችልም ወይ? በማንገራገርና በማጉረምረም ጊዜን ከማባከን ራስን መፈተሽ ቢሆን ምንኛ በጠቀመ! ራስን በራስ ካስማረከ የውስጥ ጦር ነጻ መውጣት ቢቻል ምንኛ መባረክ በተቻለ!
ያዕ.4:1-3 ”በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።”
ትዋጋላችሁ አለ ፣ትጣላላችሁ አለ፣ ትገድላላችሁ አለ፡፡ ግን አይሆንላችሁም፣ እየተዋጋችሁ ያላችሁት በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚርመሰመሱት የምቾት ጥማቶች በመነሳት እንጂ ከመንፈሳዊ እቃ ጦር ትጥቅ የተነሳ በተፈጠረ መንፈሳዊ ቅንአት አይደለም፣ ስለዚህ አንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በማትንቀሳቀሱበት ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ የእርሱን ነገር አምጣ ብትሉት አታገኙም፣ ከአሳቡ ጋር አልተገናኛችሁምና አይሳካላችሁምም ነው፡፡
1ጴጥ.4:1-3 ”ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።”
ስለዚህ፡-
ቀድሞ ያደረግነው ጥፋት በአህዛባዊ ፈቃድ ተሞልተን ያደረግነው፣ ጽድቅን ቸል ያለና በአለማዊነት ላይ ያተኮረ ልማድ ስለነበር ያ ተግባርና ዘመን እንዳለፈ ይቅር፣ ዳግም አይመለስ፣ ሊመለስ ዳር ዳር የሚል ካለም የያኔው ጥፋት እንዳይደገም እንንቃበት፡፡