አንድ አገር እየሰለጠነች ስትሄድ በዚያው ልክ ለማህበራዊ እሴትዋ ካልተጠነቀቀች እጅግ ስር በሰደደ ማህበራዊ ቀውስ ትመታለች። ቴክኖሎጂና ስልጣኔ የእውቀት ሽግግር ብቻ ሳይሆን የመጥፎ ባህል ተስቦ መተላለፊያ መንገድም ነው። ባእድ አምልኮና ያልተለመደ ወግ አንድን ሃገር እንደ በረሃ አንበጣ በጥቂት ወቅት ሊያጥለቀልቅና ሃገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል።
ዋጋ መሰጣጣት፣ መከባበርና መተሳሰብ የሚቀዘቅዘው ማህበረሰቡ ያካበተውን ማህበራዊና መንፈሳዊ ሀብቶች በስልጣኔ አመካኝቶ ሲጥለው ነው። ቤተሰብ መውደድ፣ ወላጅ ማክበር፣ ለጎረቤት ስፍራ መስጠት፣ ለአረጁና ለደከሙ ሰዎች ቅድሚያና ርህራሄ ማሳየት የሚባሉ ልማዶች እንዲሁም ከራስ አስቀድሞ ለሌላው የሚሰጡ ስፍራዎች በባህል ወረርሽኝ በተወረሰ ማህበረሰብ ውስጥ እየጠፉ የሚሄዱ ናቸው። በዚህ ዘመን በአውሮፓ ውስጥ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ክርስትና ሽታው እንኩዋን እስካይገኝ ሊጠፋ የተቃረበው በስልጣኔ ስም መንፈሳዊነት እየሞተ በመሄዱ ነው። ስልጣኔ ሚዛን ሲስት በቁሳዊነት ያስወርሳል። ያኔ ጥያቄያችን ሁሉ ከማየትና ከመጨበጥ ጋር ይያያዛል፣ መንፈሳዊነትም በስሜታዊነት ይተካል። መንፈሳዊነት የሚሰበክለት ሰው የማይታይና የማይዳሰስ ሁሉ ሞኝነት ይሆንበታል፣ ቁሳዊነት ይነግስበታልና።
በጠንካራ ማህበረሰባዊና ባህላዊ ህይወታቸው የሚታወቁ የኢስያ ሃገሮች (እንደ ቻይና፣ ጃፓንና ህንድ የመሳሰሉ ሃገሮች) በስልጣኔ ሰበብ መልካም እሴታቸው እንዳይሸረሸር አብልጠው ይጠነቀቃሉ፣ በዚህ ምክኒያት የውጪ ሃገራት ሰዎችን እንደባእዳን ቢቆጥሩ ወደው አይደለም ያሰኛል። ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን ጉዳዩ ተቃራኒ ሆኖ እናየዋለን፣ የኛም ሃገር ችግር ከዚያ መሃል ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ያየነውንና የሰማነውን ያለማጣሪያ ወደ ውስጣችን ስለምናስገባ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየገባን እንገኛለን። ትውልዱ በዚህ በኩል ምን እየሆነ ነው? ወጣቶች በቸልተኝነት ገፍተው በመሄድ አመጽ ባለበት ተግባር ላይ ሲሳተፉ እናያለን። በዚህ ዘመን ቀድሞ ያልተለመዱ ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው። ወሰን የታጣለት ክፍተት በቴክኖሎጂ ሰበብ ሾልኮ በሚገባ ክፉ ባህል እየተዋጠ በመሆኑ የምናየውና የምንሰማው እየወረደብን ነው፡፡ የእነዚህን ቀጣይ ተጽእኖ ለመረዳትና ለመቆጣጠር ካስፈለገ ግን የችግሮቹን ስረ-መሰረት ከመነሻ አንስቶ ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው።
አንድ አገር ሰለጠንኩና ሃብታም ሆንኩ ስትልና የህዝቡዋ የበጎነት ውበት ችላ እየተባለ ሲሄድ የጥቂቶች አመለካከት፣ ፍልስፍና፣ ቁስ፣ ሃብትና ውሳኔ ገዢ እየሆነ ይሄዳል። ጥቂቶች በቴክኖሎጂ በሚቆጣጠሩዋት ሃገር ላይ የሰፊውን ህዝብ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ሀብት ማስጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክኒያቱም ህዝቡን ባላቸው ተጽእኖ በመጫን የአመለካከት ባርያ አድርገው እንደልባቸው ምኞት ሊነዱት ይችላሉና። ትምህርት በጥቂቶች ፍላጎት መሰረት ሲቀረጽ፣ ፖለቲካውና ኢኮኖሚውም ጭምር በነዚያው ሰዎች አስተሳሰብ ሲዘወር አብዛኛው ማህበረሰብ በእነሱ መንፈስ ሊነዳ ይገደዳል።
ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ውጤታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ አድናቂና ተከታይ ያላቸው ሰዎች የሚፈጥሩት ተጽእኖ ተመሳሳይ ችግር በማህበረሰቡ ላይ ይደቅናል። ይሄን ሁሉ አስተውለን ከሆነ ስለ ውጤቱ ጭንቀት ውስጥ መውደቃችን የማይቀር ነው፡፡
የክፉ አመል ተጽእኖን የሚያሸንፍ ትወልድ ለመፍጠር ብዙ መድከም ቢያስፈልገንም (ያውም ከተሳካ) ወሳኝ መፍትሄ የሚሆን ግን እንደ እግዚአብሄር ቃል ያለ አናገኝም፡፡የእግዚአብሄር ቃል የሰውን ልብና አእምሮ መመርመር፣ ማቅናትና መምራት ስለሚችል የተያዘውንም ሆነ ተስፋ የቆረጠውን ትውልድ ነጻ ለማውጣት መፍትሄ ነው፡፡ የወራሪን ተጽእኖ የሚቁዋቁዋምና ራሱን የሚቀበል ትውልድ መፍጠር ከታለመ ወደ ህያው እግዚአብሄር እንዲያዞር ማመላከት ይበጃል።
በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ የተማረከ አእምሮ እምነትን እንደሚገዳደር ማየት እንችላለን። እምነት እግዚአብሄርን የሚከተል ሁሉ አምላኩን መጠበቅ እንዲማር ያስተምራል። ተስፋ ማድረግንና መታገስን ይፈልጋል፡፡ አእምሮ በቴክኖሎጂ ትንግርት ከተጠበበ ግን እምነት ነክ ጉዳዮችን ማስተናገድ ይከብደዋል። ትንግርት ማየት የሚናፍቅ ይህ አእምሮ ”እመን እግዚአብሄርንም ተጠባበቅ” የሚለው መንፈሳዊ ቐንቐ ላይገባው ይችላል፡፡
አንዳንዴ ቴክኖሎጂ ሰውና ሰው በመነጣጠል ለሰይጣን ያመቻቻል። ብዙ ”ስልጡን” ሰዎች በራሳቸው የቆሙ ይመስላቸዋል፡፡ እውቀታቸው፣ ክህሎታቸው ወይ በእጃቸው ያለው ቁሳቁስ ሁሉን የሚያደርግላቸው ይመስላቸዋል፡፡ አለምን በተለይ አተያይ እንዲመለከቱም ያደርጋቸዋል፣ ስለዚህ የማህበረሰብ ”ሁዋላ ቀርነት” ከሌላው ጋር እንዳይቀራረቡ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ ለትዳር ብዙም ግድ የላቸውም፡፡ ለማህበረሰብ ጥልቅ ስፍራ አይሰጡም፡፡ ሰው ሲፈጠር አብሮት የተፈጠረውን የህይወት ሂደት አያከብሩም፡፡ ስለዚህ ጥብቅ ማህበራዊነትን አያምኑበትም፡፡ ”ትዳር ለስጋዊ እርካታ ብቻ ያስፈልጋል” የሚሉ አንዳንዶች የሆነ ስፍራ ስሜታቸውን ከማንም ጋር ተጋርተው ያለሀፍረት ቀናቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ብዙ እንደዚህ ያሉ የተዛቡ ነገሮች በእንደዚህ አይነት ሰዎች ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ሳያውቁት ለግብረሰዶማዊነት (ወንድ ከወንድ ጋርና ሴት ከሴት ጋር ለሚፈጽሙት ግንኙነቶች) እና ለሌሎች የተጠሉ ልምምዶች ተላልፈው ይሰጣሉ፡፡ ምክኒያቱ ብቸኛ ሆነዋልና፣ የቅርብ አማካሪ ርቆአቸዋልና፡፡ የሚገርመው በድብርት ተጠቅተው ሲገለሉ በሁዋላም በራስ ጥፋት ሲሞቱ ብዙም ትኩረት ሳያገኙ የሚረሱ ናቸው፡፡
ብዙ ዘመናውያን በእግዚአብሄር እምነት ለመደገፍ ያዳግታቸዋል። ውስጣቸው (መንፈሳቸው) በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትንግርት ስለሚደርቅ። ዘመናዊነትና ቴክኖሎጂ የተቆራኙ ናቸው፣ በአለም ላይ ላለ ኑሮ። ጠቃሚነታቸው ለስጋዊ ኑሮ መሆኑ ባይዘነጋ ግን አደጋው እጅግ ይቀንሳል፡፡ ያለበለዚያ የአለም ስልጣኔ የመንፈሳዊነት መጥፊያ እንዳይሆን ያሰጋል፣ በአግባቡ ካልተያዘ ልብን ይሰርቃልና። አልፎም በእግዚአብሄር መታመንን ስለሚያዘገይ ለነገሮቻችን እግዚአብሄርን ከማስቀደም ይልቅ መጠበብና ምክንያቶችን መተንተን፣ ሁኔታዎችን ማመካኘት፣ ሰው ሰራሽ መፍትሄዎችን መመካትና የመሳሰለው ላይ ይጥለናል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ ልብ ከማመን ይሸፍታል፦
1ቆሮ.1:18-27 ”የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ…”