በአለም ውስጥ ለመልካም ስራና አገልግሎት የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዚያው ልክ ለአመጽ ውለው ይታያሉ።ቴክኖሎጂና ፈጠራ ብዙ ተደክሞበት ለውጤት የሚበቃ ስራ ሲሆን ዋና አላማውም ኑሮን ማቅለልና ምቹ ማድረግ ነው። ነገር ግን እነርሱ ከተፈጠሩለት አላማ ውጪ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉ።ኑሮን ለማቀላጠፍና ለማቃለል ተፈጥረው ሳለ የሰው ልጅን መከራ ያብሳሉ።በጎ አእምሮ ያመነጨው መልካም ቴክኖሎጂ ክፉ አእምሮ ቀይሮት የክፋት መሳርያና የመርገም መሳቢያ ያደርገዋል።
ቴክኖሎጂ ጥቅሙ፣ስልጣኔው፣ህይወትን ማቅለሉ፣ተደራሽ መሆኑ፣ግንኙነትን ማቀላጠፉ፣ህይወትን ማዘመኑ ጠቃሚ ጎኑ ሲሆን የማህበረሰብ እሴትን መሸርሸሩ፣የባእዳን አመልና ባህል ማራቢያና አመጽ መፈልፈያ ማእከል ሆኖ ማገልገሉ፣ማህበራዊ ግንኙነትን ዝቅ ማድረጉ ፣ወንጀልን በቀላሉ ማስፋፍያ መሆኑና ክፉዎች የዋሆችን በቀላሉ የሚያጠቁበት መሳርያ መሆኑ፣ በአጥፊ ጎኑ የሚገለጥ ጉዳቱ ነው።
ቴክኖሎጂና ዘመናዊነት በአንድነት የሚገለጡ ናቸው።ዘመናዊነት በተለይ በዚህ ዘመን ከፍታው የጨመረው በቴክኖሎጂ መራቀቅ ምክኒያት ነው።ሆኖም ከቀን ቀን ኑሮ እየቀለለ ነገሮች በምቾት እየታጀቡ ሲሄዱ የሰው ልጅ ጥንካሬ በተለይ አዳጋች ሁኔታዎችን የመጋፈጥ ድፍረቱ እየቀነሰ መሄዱ አልቀረም።ምቾት መጨመሩ ትንሽ የሚሻክር ነገር ቢፈጠር እንኩዋን መታገስ ያለመቻል ሁኔታን አምጥⶆል።ነገሮች በራስ ዙርያ ብቻ እንዲያጠነጥኑ የሚገፋፋ ሁኔታም በመፈጠሩ ሰው ከጎረቤቱ ወይም አብሮት ከሚሰራው ጋር ያለው ቅርርብ እለት እለት እየወረደ ነው።ሰው በማህበር የሚኖር ፍጥረት እንጂ መነጠል ባህሪው ባለመሆኑ ለአብሮነት የተፈጠረው አመለካከቱና አስተሳሰቡ እየተሸረሸረ ለብዙ ነገር ግድየለሽ የመሆን አዝማሚያ የሚታይበት ሆኖአል።ይህ ክስተት ባደጉ ሃገሮች ጥልቅ ችግር ነው።እንደዚህ ያሉ ነገሮች ደግሞ መንፈሳዊነት ላይ አደጋ ይጋርጣሉ።እግዚአብሄር የወንድማማች ህብረትን አጥብቀን እንድንዪዝ ይመክረናል።ያን ካልሰማን ለጠላት አሰራር መጋለጣችን የማይቀር ነው።
ወደ እግዚአብሄር ፊት በጾምና ጸሎት ለመቅረብ መስዋእትነት አስፈላጊ ቢሆንም በዘመናዊነት ተጽእኖ ስር ወድቀን ከሆነ እነዚህን መንፈሳዊ ስራዎች መሞከር ያዳግተናል፣እንዲያውም በረሃብ የምንሞት እስኪመስለን ልንፈራ እንችላለን።
ብዙ ጊዜ በራስ ሙሉ የመሆን ስሜት ወዳጅነትን ገፍቶ ያራርቃል፣ምክኒያቱም ወዳጅነት መቀራረብ የሚፈልግ ልምምድ በመሆኑ ተራርቆ መወዳጀት የሚባል ጉዳይ አይሳካም። መራራቅም ባለበት አይቆምም ይልቅ ይገፋና ይነጥላል፣ ነጣጥሎም ያዘናጋል፣ እግረ-መንገዱን ፍቅርን ያቀዘቅዛል፣ያረሳሳልም።ሰው ብቻውን ሲወጣና ሲገባ፣ ያለ አማካሪ በክፉም ሆነ በደጉ ብቻውን ተነጥሎ ሲቆይ ለድብርት፣ለቁዘማና ለትካዜ ይጋለጣል።ፈረንጆች በዚህ ዘመን ያለቅጥ እየተጎሳቆሉ ያሉበት ችግር የሄ ነው። ለብቸኝነት ስፍራ ሰጥተው ትዳርን አላልተው ያዙ፣ከቤተሰብ ህብረት ይልቅ ራስ ላይ ማተኮራቸው የሚያገኛቸውን ችግር በተለይ ስነልቦናዊ የሆኑትን መጋፈጥ ተስኖአቸው ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርሱበት አጋጣሚ እንደበረከተ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አለምን የገዛው የቴክኖሎጂ ምጥቀት በተለይ መንፈሳዊነትን ለመደለዝና ለመሰረዝ ቀላልና ፈጣን መሳርያ ነው።፣መንፈሳዊነት የሚጠይቃቸውን ማህበራዊ ህይወቶች የሚገዳደር ስለሆነም ትኩረትን በማጥፋት በኩል አስተዋጸኦ አለው።የተሳሳቱ የሃሰት አስተምህሮዎችን በቀላሉ ማስፋፊያ መንገድ መሆኑ፣ ቀልብን መማረክና ጊዜን መስረቅ መቻሉ እንዲሁም ሰዎች ከመጠጋጋት ይልቅ መራራቅን እንዲመርጡ ማስገደዱ የጎንዮሽ ችግሮቹ ሆነው ይጠቀሳሉ።የዘመናዊ ሚዲያ ትኩረቶች ወደ ግለሰቦች ህይወት ስለሚያመዝን ማህበራዊነት እየሳሳ ሄዶአል።በዘመናችን የሚቀርቡ ዜናዎች ወንጀልን የሚሰብኩ፣ሞትን የሚያውጁ፣የሰውን መልካም ጎን የማያሳዩ እንዲያውም ሞትን፣ ጉዳትንና የማህበረሰብ መላሸቅን የሚያለማምዱ ናቸው።ዜናዎች ከማስደሰት ይልቅ የሚያሳዝኑ፣ ከእድገት ይልቅ ውድቀትና ጥፋትን የሚለፍፉ ናቸው።አብዛኛው አድማጭ ዝንባሌው ወደዚያው ስለሆነ የዜና ማእከሎች ያንን የጥፋት ዜና ያውጃሉ። አብዛኛው የአለም ህዝብ በዜና እወጃ ውስጥ አተኩሮ የሚጠብቀው ልማትን ሳይሆን የጥፋት ዜናን፣የሰው ልጅ ሃዘንና ፍጅትን ነው።የዜና አውታሮች የሰውን ልጅ ጭካኔ ከማለማመዳቸው የተነሳ ግድያን፣ጥፋትን፣መቅሰፍትን፣ጦርነትንና የረሃብ እልቂትን ያለ መሰቅጠጥ በትኩረት እንዲከታተል ያለጭንቀት እንዲታዘብና ያለ ህሊና ወቀሳ እንደ ቀላል ነገር እንዲያወራው አስችሎታል።
በሌላ በኩል ግለሰባዊ ጉዳዮች የሚጎሉበት፣የሚወደሱበትና የሚበረታቱበት ማህበረሰብ ደካማ ህብረት ያለውና ራሱን የሚወድ ነው።ለሌላው ብዙም የማይጨነቅ የፈለገውን እንጂ ሰው ከርሱ የሚፈልገውን የማይመለከት ነው።ስለዚህ ተላምዶ ሳይሆን ተጠባብቆ በፍርሃት መኖር እንዲህ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ይበረታል።
በዚህ ዘመን የፌስቡክ ወይም የመሳሰለው ማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚነት መስፋፋቱን ተከትሎ መጥፎ ተጽኖው እያሻቀበ ሄዶ መንፈሳዊ አካል ለሆነችው ቤተክርስቲያን ይቅርና የአለም መንግስታቶችም ሳይቀሩ እየተጨነቁበት ያለ ጉዳይ ሆኖአል።ማንም ግለሰብ ለልማትም ሆነ ለጥፋት በተና|ጠል የሚመሽግበት የጊዜው ስውር ስፍራ ይህ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ሆⶈል።ስሜትን በመኮርኮር ረገድ የተሳካላቸውና ብዙዎችን ከሁዋላቸው ሊያስከትሉ የቻሉ ተዋናዮች ብዙዎች ወዳጆቻቸውን በበጎ ሳይሆን በክፉ ጎን ይጫኑአቸዋል።ሰዎችም ሱሰኞች ሆነው ከስክሪን ላይ ተተክለው ይውላሉ።በዚህም የስራ ጊዜ ባክⶈል፣የትምህርት ሰአት ተጎድⶆል፣ብዙ ወጣቶች የዝሙት ሱሰኛ ሆነዋል፣የማይኖሩትን አለም በምናብ እንዲኖሩና እንዲጉዋጉ በማድረግ ራሳቸውንና ማህበረሰባቸውን የሚንቁ ያልያም የሚጠሉ ትወልዶች እንዲሆኑ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል።
ቤተክርስቲያን በወሬ የተጠመደ ትውልድ እንዳይበዛባት በእግዚአብሄር ቃል ብርታት የትውልዱን ልብ መደገፍ ይገባታል።የኢንተርኔት ተጽኖ ያሰጋቸው ወገኖች ቤተክርስቲያን ለትውልዱ ከዘመናዊነት ጋር የሚጠጋጋ የትምህርት ዘይቤ እንድትቀርጽ ይመክራሉ።በእውኑ የቤተክርስቲያን ባለቤት ተዘነጋ ወይ? ባለቤቱ እግዚያብሄር ስለመሆኑ እርግጠኛ የሆነ ሁሉ ታዲያ ለምን ባለቤቱ ትውልዱን እንዲመክርና እንዲናገር አልወደደም።
ዮሐ.6:63-65 “ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።“
እግዚአብሄር የማይለወጥ ከሆነ የኛ ትውልድ እንዲቀይረው ለምን እንመኛለን? ትውልዱን የሚመጥን ቃል ቤተ ክርስቲያን እንድታዘጋጅ የምንመክር ደግሞ አልጠፋንም። ነገር ግን የትውልዱ ምጥቀት ቤተ ክርስቲያንን ልቆ ስለተገኘ ይሆን እንዲያ እያልን ያለነው? በዚህ እውቀታችን ሰይጣንን ወደ ቤተክርስቲያን እየሳብን አይደለምን? ብናስተውል ግን ኢየሱስ ሁልጊዜ ከትውልድና ከዘመን ፊት የላቀና ቀዳሚ እንጂ ከሁዋላ የሚከተል ጣኦት ወይም ሰው አይደለም። ቃሉም አስረግጦ የሚናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬም እስከ ለዘላለምም ያው ስለመሆኑ ነው።
ሉቃ8:11-15 “ … ምሳሌው ይህ ነው:- ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።“
ስለዚህ ቃሉ መቼም ቢሆን ህያው ነው።የማይጠፋና የማያረጅ በትውልድ መሃልም እየተገለጠ ትውልድን የሚያድስ ነው። ይህ ቃል የእግዚአብሄር እውነትና ለትውልዱ የሚያስፈልገው የሃያሉ እግዚአብሄር ድምጽ ነው፣ግን የተከፈተ ልብ ይሻል።
ትውልድ ምንም በአእምሮ ቢልቅ፣ በቴክኖሎጂም ቢመጥቅ ያው ፍጡር ነው፣መቼም ቢሆን ከአምላኩ እጅ በታች ነው።ችግሩ እንደው ያለው የሰው ልብ ጋ ነው፣ፍላጎቱና ፍቃዱ ላይ ነው።አለምን ካስበለጠ ምቾቱንም ከአምላኩ ካስቀደመ ደግሞ ምን ማድረግ ይቻላል?
1ቆሮ.1:18- 19“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።“
ሰው የራሱን መደገፍ ትቶ ቢፈልገው ያገኘዋል፣እንዲያውም አለም ከምትሰጠው ቁሳዊ ምቾት የላቀ ደስታ ይሰጠዋል። መንፈሱም ልብን መቀየር የሚችል ሃይል ስላለው ሰው የተጠማው ሊሞላና የላቀውን ደስታ ሊያገኝ ይችላል።
የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ላይ ሲበረታ በቅድሚያ የበረታብንን የአለም መንፈስ ይመታል።እኛም ነጻ ከወጣን በሁዋላ በአዲስ መንፈስ የተስተካከለ ማንነት ላይ እንደርሳለን።የትኛውም ሰው ያለ እግዚአብሄር መንፈስ እርዳታ እንኩዋን የአለምን መንፈስ ሊረታ የድር-ገጽን ተጽኖ እንኩዋን ማሸነፍ አይችልም።በዚህ ጉዳይ ማንም ራሱን አያታል።