ተግዳሮት ተሸንፎአል(2..)

ተግዳሮት ተሸንፎአል የሚለውን ትልቅ ርእስ ከማየት በፊት ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች ለምሳሌ ተግዳሮት ምንድነው? ተግዳሮትስ ከማንና ለማን(ማን ላይ) የሚሆን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በአጭር ትርጉዋሜ ለማየት መሞከር ተገቢ ነው። ተግዳሮት በህይወት መንገድ ላይ የምናገኘው ፈታኝና አሰናካይ ነገር ሁሉ ነው፤ እርሱ፦ የሚገዳደር ነገር፣ የሚከለክል ነገር፣ ወደ ሁዋላ የሚስብ ነገር፣ የሚያደናቅፍ ነገር፣ የሚይዝ ነገር፣ የሚያፍን ነገር፣ ከመንገድ የሚያስቀር ነገር፣ እንቅፋት የሚሆን ነገር፣ ስኬት የሚከለክል ነገር፣ ከድል የሚመልስ ነገር፣ ከህይወት መንገድ የሚያስቀርም ነገር ነው። እንዲህ ያሉ ገጠመኞች የመንፈሳውያን ሰዎች ፈተና ቢሆኑም የእግዚአብሄርን ፈቃድ አጥብቀው ለሚይዙቱ የማደጊያ መንገድ የሚሆኑበትም አጋጣሚ አለ። ያም አንድ ሰው በሚገዳደረው ፈተና ፊት በማስተዋልና በጥበብ ማለፍን የሚያገኘው የተግዳሮቱን ባህሪይ ሲረዳ ነው። ተግዳሮትን ማለፍ ድል ነውና፤ ተግዳሮትን መሻገር አሸናፊነትም ነውና። ነገር ግን ተግዳሮትን እንወቀው፣ በተለይ በእግዚአብሄር የምህረት መንገድ በኩል።
በዚሁ አጋጣሚም ተግዳሮት ተሸንፎአል ብለን እርግጠኛውን እንድንናገር ምን እንዳስቻለን ማወቅም ይገባል። እርግጥ ነው አንድ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ተግዳሮት (እርሱም ሃጢያት) ተሸንፎአል፣ አሸናፊውም ጌታ ኢየሱስ ነው። ሌላው ምድራዊ ተግዳሮት እንደ እንቅፋት፣ ችግርም ጭምር ሲታይ የግለሰብ ገጠመኝ ብቻ እንዳልሆነ ይልቁን የእግዚአብሄር ህዝብ በጠቅላላው በየጊዜው ሊያልፈው የተገባ የህይወት መሰናክል እንደሆነ መረዳት ይገባል፤ ለምሳሌ ይህን ሁኔታ ያጤነና ችግሩ ያሳሰበው አንድ ብላቴና (ኋላም ንጉስ የተደረገው) በሆነ ወቅት ለተግዳሮት መፍትሄ ይጠይቃል፦
‘’ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።’’ (1ሳሙ.17:26)
ፍልስጤማዊው (ወይም ጣኦትን ትምክህቱ ያደረገ ወገን) በእግዚአብሄር ለተጠራው እስራኤል የበጎነቱ፣ የድሉ፣ የበረከቱ እንዲሁም የሰላሙ ተግዳሮት ሆኖ ነበርና ያን እንቅፋት ከመንገዳቸው የሚያስወግድ እጅጉን ይፈለግ በነበረ ወቅት አንድ ብላቴና በጦር ሜዳ ታየ። ይህ ብላቴና ያነሳው ዋና ነጥብ ይታይ የነበረውን ግኡዝ ተግዳሮት (ጎልያድ) ሳይሆን አጽኖት ሰጥቶ ያነሳው መንፈሱ ላይ ያለውን የመሰናክል ምንጭ ነበር። ይህም የተግዳሮት መነሻ ከወዴት እንደሆነ እንድንመለከት ይረዳል።
በመንፈሳዊ አለም ያለ ተግዳሮት በግኡዝ አለም ካለው ይልቅ ጥልቅና የተወሳሰበ ነው። ለምሳሌ በአንድ አጋጣሚ የሰው ልጆችን ከእግዚአብሄር ክብር የጣለና ያዋረደ ሰይጣን በሌላ አጋጣሚ ጌታ ኢየሱስን ተገዳድሮ ሊያሸንፍ ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ያ እቅዱ ሳይሳካ ቀርቶ በጌታ ኢየሱስ ተሸነፈ፤ አሁን ደግሞ በጌታ የሆኑ እርሱን በህይወታቸው ያነገሱም ከክርስቶስ ብርታት የተነሳ በሙሉ ሊያሸንፉት ችለዋል፤ ይህ ድል አሁንም ሆነ ወደፊት ብችኛ የሰው ልጅ ትምክህት ነው።
ሮሜ.5:14-18 “ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ።”
እንግዲህ በአንዱ አዳም ወገብ ውስጥ የነበሩ የአዳም ልጆች በሙሉ ሃጢያተኛ የሆኑት አባታቸው በዲያቢሎስ ወጥመድ ተይዞ ሃጢያት ላይ በመውደቁ ነበር። ነገር ግን በዳግም ልደት በስሙ ተጠምቀው ክርስቶስን የለበሱ ሁሉ ከአዳም እርግማን ነጽተው በክርስቶስ ውስጥ ተጠቅልለዋልና የኢየሱስን ጽድቅ ወርሰዋል፤ የዲያቢሎስ የነፍስ ተግዳሮት እንዲህ ተሸንፎአል።
ዲያቢሎስ ግን ለአፍታም ሊከስና ሊያዋርድ በቀር ለሌላ ከቶ እንደማይመጣ በሰው የጽድቅ ህይወት ውስጥም ደጋግሞ እንቅፋትን ከማኖር እንደማይመለስ ቀጥሎ ባለው ቃል ውስጥ እናያለን፦
ኢዮ.1:6-11 ’’ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን:- ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም:- ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን:- በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት። በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።’’
ትግል ከተግዳሮት ጋር
አማኞች ሁሌም እደምንለው ከሚገዳደረን ጋር በአምላካችን ሃይል ታምነን ትግሉን እናሸንፋለን እንላለን፣ ነገሩ ቀላል ባለመሆኑ። ለኛ መንፈሳዊ ትግልና ድል የሚያልፈው በዚህ መንገድ ነው፤ ነገር ግን እውነቱ ይህ ቢሆንም ማሸነፍ ቅጽበታዊ ሆኖ ሳለ ትግሉና ሂደቱ ግን እንዲያ አይደለም፤ ማለት የእግዚአብሄር እጅ ባረፈበት ተግዳሮት ላይ ሁሉ ፍርዱ ቅጽበታዊ ሲሆን በእኛ ህይወት ሲሰራ ግን አንዴ ተገልጦ የሚጠናቀቅ ላይሆን የሚችል ነው፤ ምክኒያቱም ድሉን ተቀብሎ ማፍራት በሰኮንድ የተወሰነ አይደለምና። በደቂቃ፣ በሰአት፣ በቀን፣ በሳምንት፣ በወር ተብሎ አይገደብምም። ጠላት እነዚህን ጊዜአት በሙሉ ያለማባራት/ሳያቆም እየሰራ ስለሆነ፣ ተግዳሮቱ በዚያው ልክ የማያቆም እንዲያውም ያገኘነው ድል እንዳይጸና ተከታታይ ሊሆን በሚችል ትግል የሚጠምድ ስለሆነ ነው፤ ድሉ ይጸና ዘንድ ግን ሰው በነዚህ ጊዜያት ሁሉ በጌታ ሃይል በእምነት መዝለቅ አለበት። አይደክምም አይባልም ይደክማል፤ ተስፋ አይቆርጥም አይባልም በጣምና ብዙ ጊዜ ይቆርጣል፤ ግን ተስፋው በእግዚአብሄር መንፈስና ቃል ሲጎበኝ ዳግም ያንሰራራል፤ እንዲሁም አይመታም አይባልም ልቡ እስኪሰበር ጠላት ክው ያደርገዋል፣ ግን የእግዚአብሄር የእርዳታ እጅ ስትዘረጋ እንደገና እምነቱን ተደግፎ ይነሳል፦ ስለዚህ እንዲህ እንዲህ እያለ እስከተግዳሮት ቀብር ድረስ ሳይታክት ይጓዛል።
እምነት የድል አምላክ ከፊታችን ወጥቶ እንዲሰራና እንቅፋትን ከመንገዳችን እንዲያስወግድ ያደርጋል፤ እግዚአብሄርም ያን ሊያደርግ ጊዜ አይወስድበትም። በኛ ህይወት ተገልጦ ስራው የመታየቱ ሂደት ግን በእምነታችን የሚወሰን በመሆኑ ጊዜ ይጠይቃል። ኢዮብ የትግስት ምሳሌ ነው፤ እግዚአሄር እስኪመልስለት ድረስ ስጋውን በጥርሱ ይዞ ዘልቆአል፣ እስከ ድል ቀን ረጅምና አስጨናቂ ትግስት ታግሶአል። እግዚአብሄር በጎ ነገርና ድል የወሰነለት ገና ጠላት ብቅ እንዳለ ቢሆንም ተግዳሮቱ በእዮብ ህይወት ውስጥ አልፎ እዮብ በድል እስኪወጣ አስጨናቂ ጉዞ አድርጎአል።
የክፋት መናፍስት እንቅስቃሴን የሚያስተውል አንድ ነገር ልብ ይላል፤ ሁሌም ጠላት ካላቆመ፣ ተግዳሮት ማቆምያ የለውም። በዚህ ምክኒያት ወደ እኛ ለሚሰነዘር ተግዳሮት ንቁ ክትትል ከሌለ በኛ በኩል ግብግቡን መገዳደር አንችልም። በጎው ነገር ከአሸናፊው ጋር መሆናችን ሲሆን ጠላት ተሸንፎአል በምንልበት ሰአት ጌታ ኢየሱስ በውስጣችን መንገሱን እያረጋገጥን ነው ማለት ነው። የርሱም በኛ የመኖር ብቸኛ መለኪያ በውስጣችን የሚሰራው የእግዚአብሄር መንፈስ በሃይል ከመራን፣ ከተቆጣጠረንና የህይወት ሚዛናችንን እንዲጠብቅልን ከፈቀድን ብቻ ነው። መንፈሳዊውን ውጊያ የሚዋጉ ባሪያዎቹ ተግዳሮታቸውን ምን ይሉታል?
2ቆሮ.4:8-10 ‘’በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።’’
ጠላት በምን መንገድ ተሸነፈ?
ጠላት በእምነት ምክኒያት ተሸንፎአል፤ የጠላትን መሸነፍ የምናውጀውም እኛ ተሸንፈን ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሆን ስላለበት ጭንቅ ውስጥም ሆነን ሳለ የሚዋጋንን አስበን ከእምነታችን እንዳንነቀል መጠንቀቅ እንዲሁም ከፍ ያደረግነው የእምነት አዋጃችን ዋጋ እንዳያጣ መጠበቅ አለብን። ምክኒያቱም አስቀድሞም ቢሆን አሸናፊው የሰው ጉልበት ስላይደለ፤ የጠላት የመሽነፉ ድምዳሜም በእምነት በመረጋገጡ ነው (አሸናፊውንም በልባችን ይዘናል)። በዚህም ዘመን ባመንንበት ሰአት ያው ጠላት ይሸነፋል፣ ምክኒያቱም ድል አድራጊው ኢየሱስ እንጂ ተዋጊዎቹ እኛ ስላልሆንን ነው። ማንም በጌታ ቢሆን ባለድል ነውና።
ቃሉ በ1ዮሐ.5:4-5 ‘’ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?’’ ይላል።
ይህ የሚያሳየው አሸናፊ ህይወት ሙሉ በሙሉ በጌታ ኢየሱስ ፈቃድ ስር ያለ ህይወት እንደሆነና ከአሸናፊው ክንድ ስር ያለች ነፍስ ባለድል በመሆንዋ ነው (ኢየሱስ ስላላት)፤ ሌላ ትምክህት በዚህ ደረጃ ሊኖረን አይችልም።
ሮሜ.8:10-11 ‘’ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።’’
ተግዳሮት በማን ተሸነፈ?
ያለጥርጥር በጌታ ተሸንፎአል፤ ጌታ ኢየሱስ ዲያቢሎስና ጭፍሮቹን እንዲሁም የክፋት ስራቸው የሆነው ሃጢያትን ድል ነስቶአል፣ በዚህ ምክኒያት በሰው ልጅ ላይ የሚደቅኑት እንቅፋትም ሆነ ማንኛውም ተግዳሮት ለአንዴና ለዘላለም ተሸንፎአል፦
‘’እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።’’ (ቆላ.2:13-15)
በዚህ የምስራች ቃል የተበሰረልን፦
-ጠላት በጌታ ኢየሱስ ስለተሸነፈ የርሱ ተግዳሮት ከራሱ ጋር ተሸንፎአል
-ተግዳሮት በጌታ ምሪት ዛሬም ይሸነፋል
-ጌታ የሰጠን ድል በሰራው የቀራኒዮ ስራ ነው
-የቀራንዮ ስራው የፋሲካ ጉልበትን በኛ ህይወት ይገልጣል
-በትንሳኤው ሃይል ህይወታችን በድል ይጓዛል
-በመንፈስ-ቅዱስ ስራ የተጠመደብን መንፈሳዊ ወጥመድ ይሰበራል
-በኛ ውስጥ የጌታ መንፈስ ሲሰራ ተግዳሮት ይሸነፋል
-የጽድቅ ልብሳችን ሆኖ በጥምቀት አሰራር እርሱን ስለለበስን አሸናፊ ሆነናል
-እለት እለት ከእርሱ ጋር በመጓዋዝ፣ ከርሱ መገኘት ሳንለይ ከተጓዝን ደግሞ አሸናፊነታችን ይጸናል። የተሰጠንን መዳን የማይመጥን ህይወት የምንኖር እንደሆነ ግን እጅግ አስቸጋሪ የሰይጣን ጥልፍልፍ ውስጥ እንወድቃለን፣ ህይወታችንንም አደጋ ላይ እንጥላለን፦
‘’ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።’’ (1ቆሮ.6:9-11)
ባህሪያችንን የሚበክልና ጨርሶ የሚያጠፋ ተግዳሮት እንዲህ በህይወታችን የሚጥለቀለቀው የምንሄድበት የተሳሳተ መንገድ ለስጋ፣ ለአለምና ለሰይጣን አሳልፎ ስለሰጠን ነው፤ በአጠቃላይ ተግዳሮትን የሚያሸንፍ ቢኖር ተግዳሮቱ ምን እንደሆነ የተረዳ፣ ለእግዚአብሄር ምህረት ዝግጁ የሆነና በቃሉ በእምነት የቆመ ሊሆን ይገባል። ተግዳሮት ለኛ የህይወት እንቅፋት ነው ካልን በዋናነት እንቅፋትነቱ መንፈሳዊነትን በማሰናከል፣ በመክበብና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነው፤ የሚቋቋመን በመንፈሳዊ ነገር ላይ ባለ እንቅስቃሴያችን ነገር ሁሉም ነው።
የተግዳሮት ባህሪይ ምንድ ነው?
የምናልፋቸውን አስቸጋሪ ወቅቶች በጌታ ቅባት በመታገዝ ይሆኑ ዘንድ ተግዳሮት የምንለው ነገር ምን እንደሚመስል ማወቅ ይኖርብናል። ተግዳሮት በተለይ መንፈሳዊ የሆነው ሲመጣ ምን ይመስላል? ስንል ከባህሪው ጥቆቶቹ፦
-እንደ አየር የማይዳሰስ፣ የተሰወረና መኖሩ በብዙ መልኩ የተደበቀ ግን ለመንፈሳዊ ህይወት ጠላታችን ሆኖ ይገለጣል
-እንደ በረከት የመሰለ በመሆኑ ልባችንን ወርሶ ወደ ስህተት እንድናዘነብልና የጌታን ምክር እንድንጥል ያደርጋል
-እንደ እውቀት የመሰለ በመሆኑ ጭራሽ ለርሱ እስከመሟገትና ሰዎችን በስህተት ልናሳጣ ሁሉ እንደምንችል የተረጋገጠ ነው
-እንደ ውሃ ፈሳሽ የሚያጥለቀልቅ በመሆኑ በአንዳንድ ገጠመኞች ወቅት ከፍጥነቱ የተነሳ ማገናዘብ ሳንችል ራሳችንን በከባድ ፈተና ውስጥ እንድናገኘው ይሆናል
-እንደ ሃሩር የሚለበልብ የሚሆንብን ከፈተናው ጭካኔ የተነሳ የሚራራ ነገር ስለሌለው ነው
-እንደ ግንብ የተገተረ፣ የማይታለፍም ደንቃራ በመሆኑ ትግስታችንን ሙልጭ አድርጎ በመብላት እምነታችንን ጥያቄ ውስጥ እስከመክተት ይደርሳል
-እንደ እሳት የሚበላ የሚጨርስም ነው፣ የተግዳሮቱ ታላቅነት የኛን ጉልበት በልቶ እስከሞት የሚያሳድድም ሊሆን የሚችል ነው።