በእግዚአብሄር የታመንን ክርስቲያኖች ድሮ በአለም ሳለን (ወደ እምነት ሳንመጣ አስቀድሞ በአለማዊነት ህይወት ሳለን) ከነበረን ተግዳሮት ይልቅ አሁን የተለየ ምን አይነት ፈተና ገጠመን? በአለም ተጽእኖ ስር ሳለን ሲያስቸግሩን የነበሩ የስጋችን፣ የአለምና የሰይጣን ፍልሚያዎች አሁንም እንዳሉ ስላሉ በእኛ ህይወት ምን አዲስ ነገር ይኖራል? የሚል ጥያቄ ሊያመራምር ይችል ይሆናል። ምርመራውም ጥያቄውም ቢመጣ ትክክል ነው፣ ግን ተጠግተን ስንመለከት ውጊያውና ተዋጊዎቹን በተመለከተ አሁንም ምንም የተቀየረ ነገር የለም፤ ከላይ የጠቀስናቸው መንፈሳዊ ህይወታችንን የሚገዳደሩ የፈተና ምንጮች እንዳሉ ስላሉ። የተቀየረው ነገር ከእኛ ጋር ያላቸው ግኑኝነት በተለይ በውስጣችን ከተቀመጠው አዲሱ ሰው ጋር ያላቸው ዝምድና የኮመጠጠ፣ ጥሉ የበረታና ጠላትነቱ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑ ነው።
አስቀድመን የአለም ወዳጆች ነበርን፣ በአለም ያሉ የስጋ ምኞት፣ የአይን አምሮትና ስለ ገንዘብ መመካት በኛ ላይ ንጉስ ሆነው ያዝዙንና ይገዙን ነበር፤ ጠላት ዲያቢሎስም ከእምነት አስቀድሞ በነበረን ህይወት ውስጥ ጠላት ሆኖን ሲኖር ሳለ እኛ ግን ስሜት ሳይሰጠን ስለተመላለስን ልናዳምጠው ልንቃወመውም አልቻልንም ነበር፤ ማንነቱ ስላልተገለጠ ቸል ብለነዋል፣ ስለርሱ ባለን ግምትም ዝቅ አድርገነዋል። ስለዚህ እኛም ያለእውቀት ስንመላለስ፣ እርሱም እንደ ቦይ ውሃ ባሻው አቅጣጫ ሲመራን ኖሮአል፤ አሁን ግን ማስተዋል ከአምላካችን መጥቶ በእያንዳንዱ የጠላት አሰራር ላይ ጥንቃቄ ስናደርግና ውጊያ ስንጀምር ከርሱ ዘንድ ብርቱ መቋቋም ተፈጥሮአል።
ስለ እኛ ጠላቶች ያሉ እውነታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የስጋ ፈቃድ፦
‘’እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።’’ (ሮሜ.8:5-8)
የስጋ ፈቃድ ውስጥ ነፍስን የሚያጠምድ፣ የሚያስርና ቆይቶም የሚያጠፋ የሃጢያት ሃይል ካለ እንዴት ያለውን የራስ ጠላት በህይወታችን ውስጥ እንደምንጋፈጥ መመልከት ይቻላል። አዳምና ሄዋን ውስጥ የነበረው የስጋ ፈቃድ በእግዚአብሄር ትእዛዝ ላይ እንዲያምጹ እንዳደረገ በቃሉ ተመልክቶአል፤ ውሳኔያቸው ከእግዚአብሄር ጋር ጠላትነት ውስጥ ነው የከተታቸው፤ እግዚአብሄር ስለአመጻቸው የተናገረው እርግማንም ፍርድ ውስጥ አስገብቶአቸዋል።
የስጋ ፈቃድ ሃጢያት ያለበት ሰዋዊ ዝንባሌ ነው፣ በምንም መንገድም ከሰው ማንነት ውስጥ ሊወጣ ወይም ሊላቀቅ አይችልም፣ በእርግማን ታትሞአልና፤ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ህይወትም ታላቅ ተግዳሮት ሆኖ እስከ ጌታ ቤዛነት ጊዜ ድረስ በአለም ነግሶ ነበር።
ሮሜ.3:23-34 ‘’ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።’’
ሰው ከፈጠረው አምላክ ጋር ህብረት ቢያደርግ ምንኛ በደስታና በደህንነት በኖረ፣ ሆኖም ያ እንዳይቻል ሆኖ የጽድቅ መንገድ በሰው መተላለፍና ሃጢያት ስለተቆረጠ መንገዱም ዳግም ወደ ህይወት ላይመራው አንዴ ወደ ጨለማ አለም ገብቶአል፤ በወደቀበት ሰአት የተደረበበት መሸፈኛም አምላክን የማወቅ ግርዶሽ ጣለበትና አቅም አሳጣው፤ መሰናክልና ተግዳሮት ሆኖበትም ከመንፈሳዊ ክልል ጎዶሎ እንዲሆን ያ የስጋ ሃጢያት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቶአል። ቃሉ እንደሚያሳየው ኃጢአት ሰዎች ሁላችንን ከእግዚአብሄር ክብር አጉድሎናል፣ ይህን መቀበል ያዳገተን እጅግ ብዙዎች (በተግባር ያልተቀበልነውና ያልታዘዝነው) የሃፍረት ማቅ ለብሰን እስከዛሬዋ ሰአት እንገኛለን፣ እንዲሁም የሃጢያት ደሞዝ በሆነ ሞት ተይዘን ያለን እያንዳንዳችን የግዴታ ምስክር ነን፤ ዛሬም ቢሆን እያንዳንዱ ትውልድ በዚህ ልምምድ እያለፈ ይገኛል፤ በምድር ገጽ ላይ በግልጽ የሚታይም ነው። እያንዳንዳችንም በፈጠረን በአባታችን እግዚአብሄር ፊት ይህን ነውር ተሸክመናል።
መቼም ልንሰውረው አንችልም ፣ ቃሉ ስለገለጠን፦ በሥጋ ፈቃድ ምሪት እስከኖርን ድረስ የሥጋ ነገር ይገዛናል፣ አሳባችን ወደርሱ ነውና ከስጋ ስራ መንጻት አንችልም፣ ይህን ህይወት ይዘን ጻድቅ ልንባልም አይገባም። ለእግዚአብሔር ሕግ አልገዛም የሚል ፈቃድ የእግዚአብሄር ፈቃድ አይገዛውም፤ በዚህ የሥጋ ፈቃድ ውስጥ ያሉትም በምንም መልኩ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም፤ ስለአምላክና ስለ አምላክ ህግ ማሰብ ተስኖአቸው ከእግዚአብሄር ጋር እንደምን ይወዳጃሉ?
በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁን?
ሥጋዬን የነፍሴ መመከቻ ማድረግ አልችልም፤ ምክኒያቱም በጎ ነገር፣ ጠቃሚ ነገር፣ ሞገስ ያለውም ነገር በዚህ በኩል አልቀበልም፣ ከዚያ ይልቅ በእግዚአብሄር ፊት ሞገስ ያለው ነገር በሥጋዊ ህይወት ምክኒያት ፈጽሞ ላገኝ አልችልም። ያለጥርጥር በዚህ እውቀት እጦት ትልቅ የጽድቅ ተግዳሮት ይሆናል፤ ከፍ ብሎ ሲታይም ያለክርስቶስ የሆኑ ሁሉ ዛሬም ድረስ ነጻ ስላልወጡ የችግር አዙሪቱ እያደቀቃቸው ይገኛል።
አዎ የሚገዳደር እስካለ ድረስ በነፍስ መድከምና መበርታት፣ መውጣትና መውረድ አለ፣ መሸነፍ ማሸንፍም አለ፣ መውደቅ መነሳት፣ መቀበል የተቀበሉትን ማጣትም እንዲሁ።
ገላ.5:16-17 ‘’ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።’’
የሰውን ውድቀትና መነሳት የሚወስኑ ሁለት ምኞቶች በሰው ማንነት ውስጥ ያድራሉ፤ አንደኛው በጽድቅ ምክኒያት ስለጽድቅ ለነፍሳችን በጎነት የሚሞግት፣ በስጋ ምኞት ላይ ሊሰለጥን ስጋን የሚታገል መንፈሳዊ ምኞት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በተቃራኒው መንገድ የሚታገል የስጋ ምኞት ነው።
በብዙ መልኩ የእኛ መንፈሳዊ ተግዳሮት የሚመነጨው የእኛ ከምንለው ስጋዊ ነገር በመሆኑና የነገሮች አካሄድ ለመንፈስ አሰራር መገድ ስለማይሰጡ የህይወት መንገድ እንቅፋት የሚበዛበት ሆኖአል (የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም ስለሚል)፤ ከእኛ ጋር የሚውል፣ ከእኛ ጋር የሚያድር፣ ከእኛ ጋር የሚወጣ፣ ከእኛ ጋር የሚገባ፣ ስንደክም ቀድሞ የሚወድቅ፣ ስናስብ ቀድሞ የሚናገር፣ ስንፈልግ ፈጥኖ የሚመኝ በብዙ መልኩ የሚያስቸግረን አብልጠን ልንጠነቀቀው ደግሞ የሚያስፈልግ ተግዳሮታችን የስጋ ፈቃድ ነውና። የስጋ ፈቃዳችን ነፍሳችንን ወደፈቀደው መንዳትና በመተላለፍ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ በቀላሉ የሚችል ነው፤ ልባችንን ማሸነፍ ስለሚችል ለመንፈሳዊ ጠላት ያጋልጣል፤ በእርግማን ውስጥ ታስረን እንድንቀመጥም ትልቅ አስተዋጾ ያደርጋል። ስለዚህ የሰው ልጆች የስጋ ፈቃዳችንን የምናስገዛበትን መንፈሳዊ ብልሃት ከቃሉ ላይ መቅሰም ይገባናል።
ሮሜ.7:15-24 ‘’የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ። እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?’’
የስጋ ፈቃድ ለመንፈሳዊ ሰው ምን ያህል ሰቀቅን እንደሆነ ከላይ መመልከት እንችላለን፦ በብዙ መልኩ የሚጎዳ፣ የሚያጎድል፣ የሚያስነክስ ሆኖ ከእኛ ጋር ይዘልቃልና፤ መንፈሳዊ ሆኖ ሁለንተናችን እንዲገዛ ስንታገል አንዱ ብልት አምልጦ የስጋ ፈቃድ ሲመራው ይገኛል፣ ሲገዛና በእኛ ያልተመረጠ ድርጊት ውስጥም ይሰጥማል፤ ይህ የሰው ልጅ ድካም ነው፤ ተስፋ ያለውና የሚያስደስተው ነገር ግን አዲሱ ሰው በጸጋው አሸናፊነትን እንዲቀዳጅ ተድርጎ ዳግም በጌታ መፈጠሩ ነው። ስለዚህ በእኛነታችን ውስጥ ምርጫ ስላለ በመንፈሱ ለመገዛትና በስጋ ላይ አርነት ለማወጅ ከፈቀድን ነጻነትን ለነፍሳችን ልናውጅ እንችላለን።
እንደ ሥጋ ፈቃድ እየኖርንና የሥጋን ነገር በማሰብ እየተመላለስን ከሆነ ግን ያን መንገድ ማስተዋል አንችልምና በጣም ችግር ውስጥ እንገባለን፤ ሆኖም ለእኛ የተፈቀደ ህይወት እርሱም እንደ መንፈስ ፈቃድ መኖር ላይ ካተኮርን ወደ አሳቡና ወደ ፈቃዱ እንገባለን፤ ቃሉ፦
‘’ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው።’’ ይላልና። (ሮሜ.8:5-10)
አሁን ምርጫ አለን፦ እግዚአብሄር ያደረገልንን አስበንና አሰተውለን ከሆነ በእኛ የሰራውን ታላቅ የማዳንና የማብቃት ስራ አጥብቀን በመያዝ የስጋን ስራ መግደል (ፈቃድ መከልከል፣ ስፍራ ማሳጣት እንዲሁም ስለርሱ ከማሰብ መታቀብ)፣ ያልያም የተሰጠንን ቸል ብለን ክብር የሌለው ህይወት መኖር፦ እግዚአብሄር ግን ለለመኑት አብልጦ አስቻይ ጸጋውን ሊሰጥ ይችላልና በእምነት መጠየቅና ለመሰራት መፍቀድ ያዋጣል።
በሮሜ.7 የተገለጸው የስጋ ፈቃድ ግራ የሚያጋባ/ የሚያጨልም አሰራር በልቤ ሞልቶ እውነት ከእኔ እንዳይታጠፍ እንዲሁም በዚያ ህይወት ውስጥ እንዳልዘረጋ የእግዚአብሄር አንቂ እገዛ ከመጣ ትልቅ ድል ሆነልኝ ማለት ነው፤ የጸጋው መንፈስ ያኔ ስለሚቆጣጠረኝ የማደርገውን እያዳንዱን ነገር ካለማስተዋል ወደ ማስተዋል፣ የምጠላውን ከማድረግ ራሴን ወደ መግዛት፣ እንዲሁም የምወደውን የርሱን ፈቃድ እርሱንም አደርግ ዘንድ ዘወትር መሻትና ትጋትን ብቀበል ለእኔ መንፈሳዊ ድል ነው። የማልወደውን እንዳደርግ የተቆጣጠረኝ ፈቃዴ ከገዛኝ የስጋ ነኝ፤ በእግዚአብሄር የጸጋ ጉልበት ከተገዛሁ ግን ነጻ ወጣለሁኝ። ደግሞ በእኔ የሚያድር ኃጢአት በደሙ ጉልበት ሲወገድ ለእግዚአብሄር ቅዱስ መስዋእት መሆን እችላለሁ። የማልወደውን ክፉ ነገር እስካደረግኩና የምወደውን በጎውን ነገር እስካላደረግኩ ድረስ ህሊናዬ ነጻ እንዳልሆነና ለተቆጣጠረኝ ተገዢ እንደምሆን በመረዳት ባለ ጸጋውን አምላክ ከመቼውም ዘመን ይልቅ እየተማጸንኩ ነጻነቴን መቀበል አለብኝ፤ አሁን በመጣልኝ የእውቀት መረዳትም ታግዤ በእምነት ወደ እርሱ መቅረብ አለብኝ።
የስጋ ፈቃድ ጉልበትን ማስተዋል
የስጋ ፈቃድ ጉልበትን ማስተዋል ቃሉ ስለ ስጋ የሚሰጠውን ምክርም ሆነ ግሳጼ ከልብ እንድናስብበት፣ አስተውለን እንድንጠነቀቅና በርሱ ምክኒያት የሚመጣውን ውጤት ከልብ እንድንረዳው የሚያደርግ ነው።
አዳም ከእግዚአብሄር ፈቃድ ይልቅ (አትብላ ከሚለው ትእዛዝ ይልቅ ) የስጋ ፈቃድ ስለበለጠበት (ሚስቱን መስማት፣ የቀረበለትን ፍሬ የመብላት መሻት የመሳሰለው ስላሸነፈው) የሚጸጽት ውሳኔ ውስጥ ገባ። በአዳም ውስጥ የበቀለው መሻት ከህይወቱ በንሰሃ የተነቀለ ሳይሆን በእርግማን የጸና ስለሆነ የስጋን ፈቃድ የተኮነነ አድርጎታል፤ ማንም ትውልድ ከአባታችን ከወረስነው ፈቃድ ገሸሽ ሊል አይችልም፤ የትኛውም አዋቂ ከእውቀቱ ብዛት ያን ፈቃድ ከውስጡ ሊሽር ከቶ አይችልም፤ የትኛውም መንፈሳዊ ሰው ራሱን በጸሎት ቢያተጋ፣ ስጋውን በጾም ቢያደክም ያን የስጋ ፍቃድ ሊሽር አይችልም። የስጋ ፈቃድ የሚሻረው በመንፈስ ፈቃድ ብቻ ነውና የእግዚአብሄር መንፈስ እንዲያግዘን የተመቻቸ ህይወት (ለመንፈስ ቅዱስ አሰራር የተመቸ ህይወት) እንዲኖረን እንፍቀድ፤ በእርግት ከዚህ ሌላ መፍትሄ የለም።
‘’ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።’’ (ሮሜ.8:10-14)